በገቡት ውል መሠረት መቶ በመቶ ክፍያ ፈጽመው የቤቶች ዕጣ የሚወጣበትን ቀን በመጠባበቅ ላይ እያሉ የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ከ40 በመቶ በላይ የቆጠቡትን በሙሉ ያካተተ ዕጣ እንዲወጣበት የተደረገውን ከ18 ሺሕ በላይ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ በመቃወም ክስ የተመሠረተበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሐ ብሔር ችሎት ክሱን የማየት ሥልጣን የለውም ሲል ምላሽ ሰጠ፡፡
አብሮ የተከሰሰው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ደግሞ በሰጠው ምላሽ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መመርያ ቁጥር 21/2005 እንዲሻሻል በደብዳቤ ሲጠይቀው፣ በዚህ ወቅት መመርያውን ማሻሻል ለከፍተኛ ችግር እንደሚዳረግ በመንገርና በመምከር መመርያው እንዲከበር ጥረት ማድረጉን ጠቁሞ፣ የቀረበበት ክስ ግን በማይመለከተውና ከሕግ ውጪ መሆኑን በዝርዝር በማስረዳት ምላሽ ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተከሰሰበት ጉዳይ ሊያስከስሰው እንደማይችል ጠቁሞ፣ ሊያስከስሰው ቢችል እንኳ በአዋጅ ቁጥር 25/88 ድንጋጌ መሠረት ክሱን የማየት ሥልጣን ያለው፣ ፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፍትሐ ብሔር ችሎት መሆኑን አስረድቷል፡፡
ምክንያቱ ደግሞ ከሳሾቹ የጠየቁት ዳኝነት በውል የቀረበ፣ ‹‹ዕጣው ይሰረዝልን፣ በውልና በመመርያ መሠረት የቤት ዕደላ ይደረግልን፣ ቤቶች ከየሳይቱ እንድንወስድ ዕደላ ይደረግልን›› የሚሉ ስለሆነና እነዚህን ጥያቄዎች ደግሞ በገንዘብ መተመን የሚቻል ባለመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን የማየት ሥልጣን እንደሌለው አብራርቷል፡፡ በመሆኑም በፍትሐ ብሔር ሕግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 244 (2ሀ) መሠረት ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡ ከሳሾቹ እያንዳንዳቸው ከየሳይቱ ቤት እንዲወስዱ ያቀረቡት ጥያቄ ፍርድ ቤት ሊቀርብ የማይችልና አስተዳደራዊ መሆኑንም አክሏል፡፡
ባንኩ ቀጥሎ እንዳስረዳው፣ ከከሳሾች ጋር ባደረገው የመኖሪያ ቤት ግዥ የቁጠባ ውል አንቀጽ 4 ላይ፣ ‹‹ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በስተቀር ውሉ ለአምስት ዓመት ብቻ ፀንቶ ይቆያል›› ተብሎ የተደነገገ ነው፡፡ በመሆኑም በነሐሴ ወር 2005 ዓ.ም. የተደረገው ውል መቆየት የሚችለው እስከ ነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም. ድረስ ብቻ በመሆኑና ጊዜው በማለፉ፣ ተከሳሾችም ተቃራኒ ስምምነት ስለማድረጋቸው ያቀረቡት ማስረጃ ባለመኖሩ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 33(3) ድንጋጌ መሠረት ክሱ ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡
ከሳሾች ባቀረቡት ክስ ላይ በውልና በመግባቢያ ሰነዱ መሠረት ተገንብተው የተጠናቀቁ ቤቶችን ባንኩ ተረክቦ ቅድሚያ ሙሉ ክፍያ ለከፈሉ ማስረከብ ሲገባው እንዳላስረከባቸው ቢገልጹም፣ ወይም በቤት ፈላጊዎች የምዝገባ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 21/2005 አንቀጽ 19(9) (10) እና በቁጠባ መኖሪያ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራዝና በባንኩ መካከል በተደረገው የፋይናንስ አፈጻጸም ስምምነት አንቀጽ 4 እና 5 መሠረት በሁለተኛ ዙር የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች አለመረከቡን ገልጿል፡፡ ስለመረከቡም ከሳሾች ያቀረቡት ማስረጃ እንደሌለም አክሏል፡፡ ባልተረከበበት ሁኔታ እሱም ሊያስረክብ እንደማይችል አስረድቷል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሌላው የገለጸው፣ የቤት ፈላጊዎች የምዝገባ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 21/2005 መቶ በመቶ የቆጠቡ ግለሰቦች ብቻ ወደ ዕጣው ግቡ እንደማይል ነው፡፡ በመመርያው አንቀጽ 16 (1) ላይ የመኖሪያ ቤቱን 40 በመቶና ከዚያ በላይ የቆጠቡ ብቁ እንደሚሆኑ መደንገጉን ጠቁሞ፣ የከሳሾች ክስ አግባብነት እንደሌለውም አስረድቷል፡፡ ከሳሾች ተጨማሪ መከራከሪያ ማስረጃ ማቅረብ እንደሌለባቸው፣ ከውል ውጪ ኃላፊነት እንዲባልላቸው ባቀረቡት የዳኝነት ጥያቄ የሰው፣ የምሥልና የድምፅ ማስረጃዎችን ማቅረባቸው፣ ከሕጉ አንፃር ነገሩን የበለጠ ለማብራራት እንጂ ከሳሾች ግዴታቸውን ባልተወጡ ጊዜ የሚያቀርቡት አለመሆኑን ጠቁሟል፡፡ በመሆኑም የክስ አቤቱታው ውድቅ እንዲደረግለት ባንኩ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው መልስ ጠይቋል፡፡
የቀረበበት ክስ ከመመርያ ቁጥር 21/2005 አንቀጽ 17 ውጪ በአንቀጽ 18 ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠን ተግባርና ኃላፊነት በመውሰድ መሆኑን አስታውቆ፣ የእሱ ኃላፊነት ባልሆነ ነገር ክስ ሊቀርብበት እንደማይገባ መቃወሚያውን ያቀረበው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ነው፡፡ ከሚኒስቴሩ ከውል ውጪ ኃላፊነት እንዳለበት በመግለጽ ብቻ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መቶ በመቶ ከፋዮች እንደ ከሰሱት ጠቁሞ፣ የጥፋት ሁኔታዎችን ሳያሟሉ የቀረበ ክስ በመሆኑ ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡ ውል የተፈራረሙት የፋይናንስና ቤቶች ማስተላለፍ ስምምነት ውል አካል ሆኖ ከንግድ ባንክ ጋር በውል አንቀጽ (6) ሥር ተፈራርመው እያለ፣ ኮሚኒስቴሩ ጋር ባልተመሠረተ ጥቅምና ጥፋት ከውል ውጪ ኃላፊነት ሳይኖርበት ሊጠየቅ እንደማይገባም አስረድቷል፡፡ ውል ሕግ በመሆኑና ያቀረቡት ክስ ጥፋት ሳይኖር ከፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 2030(1) ውጪ በሆነ መንገድ በማለት፣ ፍርድ ቤቱ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 244 (2መ) መሠረት ውድቅ አድርጎ እንዲያሰናብተው ጠይቋል፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በከተማ አስተዳደሩ ቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ መካከል የተደረገ ስምምነት መኖሩን፣ እንዲሁም በራሳቸው በከሳሾችና በንግድ ባንክ በኩል ቤቶችን ለማስተላለፍ የስምምነት ውል አድርገው በፊርማቸው ያረጋገጡት ስምምነት መሆኑን እያወቁ፣ ሚኒስቴሩን መክሰስ የሕግ መሠረት የሌለውና ከውል ውጪም ኃላፊነት የማያስከትል መሆኑን አብራርቷል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአዲሱ የአስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1097/2011 አንቀጽ 22 መሠረት፣ ዜጎች ከአቅማቸው ጋር የተጣጣመ መኖርያ ቤት እንዲኖራቸው እንደ አገር አጠቃላይ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ፣ ጥናቶችን ማስጠናት፣ ሲፀድቁ ተግባራዊ እንዲሆኑ መደገፍ፣ የአቅም ግንባታዎችን መሥራትና ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ሥራዎችን ማከናወን እንጂ፣ ከሳሾች እንዳሉት ከተሰጠው ኃላፊነትና ሥልጣን ውጪ ወጥቶ እንደማይሠራም አስታውቋል፡፡ እንዲያውም የወጣው መመርያ እንዲከበር ጥረት ማድረጉን ጠቁሞ፣ የተጣለበትን ኃላፊነት አልተወጣም ሊባል ስለማይችል፣ እንዲሁም የቀረበበት ክስ የሕግ መሠረት ስለሌለው ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡
ለ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መቶ በመቶ የከፈሉ 98 ከሳሾች፣ ለሚደርስበት ጉዳት ዋስትና እንዲያስይዙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ላቀረበው አቤቱታ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በጠበቃቸው አማካይነት በሰጡት ምላሽ እንዳብራሩት፣ ዕጣ በወጣባቸው የ40/60 የጋራ መኖርያ ቤቶች ላይ ፍርድ ቤቱ ዕግድ የሰጠው በከሳሾች ጥያቄ መነሻ መሠረት ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ የመጀመርያውን የከሳሾች ጥያቄ መርምሮ ሁሉንም ቤቶች ያገደ ሲሆን፣ ኢንተርፕራይዙ ይደርስብኛል ያለውን ጉዳት አስልቶ ለችሎቱ ጥያቄ በማቅረቡ ፍርድ ቤቱ ጉዳቱን በመረዳት የዕግድ ትዕዛዙን ማሻሻሉን ጠቁመዋል፡፡
በተሻሻለው የዕግድ ትዕዛዝ ላይ አመልካቾች ምንም ዓይነት ቅሬታ እንደሌላቸው ገልጸው፣ እነሱ ግን በኢንተርፕራይዙ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በማያውቁበት ሁኔታና ዕግዱን የሰጠው ፍርድ ቤትም ሊያውቅ የሚችልበት አግባብ ሳይኖር በተፈጠረ ኪሳራ፣ የሚጠየቁበት ምንም ዓይነት የሕግ አግባብ እንደማይኖር አስረድተዋል፡፡
ተከሳሹ የቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ግን፣ ዜጎች ፍትሕ ለማግኘት እንዲያዳግታቸው በሚያደርግና ወደፊትም በመንግሥት ላይ ማናቸውንም ዓይነት የፍትሕ ጥያቄ ለማቅረብ እንዳይችሉና እንዲሸማቀቁ በሚያደርግ ሁኔታ፣ እያንዳንዳቸው ከሳሾች በአማካይ 1.5 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲያስይዙ መጠየቃቸው በሞራልም ሆነ በሕግ አግባብ ተቀባይነት ያለው አካሄድ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ምንም ዓይነት የደረሰ ጉዳት የለም እንጂ፣ ቢኖር እንኳን ከሳሾች መብታቸውን ስለጠየቁ የሚጠየቁበትና የሚቀጡበት፣ ለመቶ ሺዎች ዳኝነት ሚሊዮኖች የሚያስይዙበት በቂና አሳማኝ ምክንያት ስለሌለ፣ የቀረበባቸው የዋስትና ጥያቄ ውድቅ እንዲደረግላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡