Friday, December 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ከሰላምና ከዕድገት ውጪ አቋራጭም ሆነ አማራጭ የለም!

ወቅታዊውን የኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በይፋ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ያለውን ለውጥ በተመለከተ፣ የሚደመጡ አስተያየቶች ፈርጀ ብዙ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል ከሥልጣነ መንበረ የተገፉ ወገኖች ቅሬታና የመገፋት ስሜት ያሰማሉ፣ በሌላ በኩል ለውጡ በመምጣቱ ደስተኛ ሆነው የሚኮፈሱ አሉ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ያኮረፉና ግራ የተጋቡ በየፈርጁ ይስተዋላሉ፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ በቅንነት በጎ የሚመኙ አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የተለያዩ ስሜቶች መኖራቸው ያን ያህል ባያስከፋም፣ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ በማምራት የግጭት መቀስቀሻ እንዳይሆኑ ግን ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የአገር  ህልውና ጉዳይ ሲነሳ ከግልና ከቡድን ጥቅም በላይ ማሰብ የግድ ነው፡፡ የተከፋው ያጣውን ሥልጣንና ጥቅም ብቻ እያሰላሰለ የአገር ውድቀትን የሚመኝ ከሆነ ተስፋ ቢስ ነው፡፡ በለውጡ ደስተኛ የሆነው ሁሉን አሳታፊና አቃፊ የሆነ ሥርዓት እንዲፈጠር ካልታገለ መቅኖ ቢስ ነው፡፡ ኩርፊያ ውስጥ ያለው በዚያ ልቀጥል ካለ ፈላጊ የለውም፡፡ ግራ የተጋባው ከደመነፍሳዊ እንቅስቃሴው ካልተገታ ጊዜ ጥሎት ይሮጣል፡፡ የአሁኗ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የተከፋፈለ ልብ  ሳይሆን፣ በአንድነት የቆመ ጠንካራ ትብብር ነው፡፡ ይህ ትብብር ልዩነትን የሚያከብር፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚገዛ፣ የጋራ አገራዊ እሴቶችን የሚያከብርና ሥልጡን የሆነ መስተጋብርን የሚያንፀባርቅ መሆን አለበት፡፡ በዚህ መንፈስ መንቀሳቀስ ሲቻል ሰላምና ዕድገት የኢትዮጵያ ሀብት ይሆናሉ፡፡

በተደጋጋሚ እንደምንለው ኢትዮጵያ ለዓመታት የተከማቹ በርካታ ውስብስብ ችግሮች እግር ከወርች ያሰሯት አገር ናት፡፡ እነዚህ የዘመናት ችግሮች የሚፈቱት ደግሞ፣ እንደ ሥልጡንና ጨዋ ሕዝብ መነጋገርና የጋራ አቋም መያዝ ሲቻል ነው፡፡ የሃይማኖት ተቋማት የውስጣቸውን ችግር መፍታት ተስኗቸው ምዕመናንን ሲያወዛግቡና ትዝብት ውስጥ ሲገቡ ይታያሉ፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ በመንግሥት ሸምጋይነት ሲደራደሩና ለዕርቅ ሲግደረደሩ ያስተዛዝባል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ችግር ለምን ተፈጠረ የሚለው አይደለም፡፡ ችግሩን ለመፍታት የሚኬድበት መንገድና የሚወስደው ጊዜ፣ እንዲሁም በራስ ጥረት መፍታት ሲገባ ሌላውን አካል ሥራ ማስፈታትና መጠቋቆሚያ መሆን አንዱ አንጓ ነው፡፡ በሌላ በኩል ምዕመናንን ማስታረቅ፣ መገሰፅና መስመር ማስያዝ የሚገባቸው የሃይማኖት ተቋማት የአገር ችግር ሲሆኑም ያሳዝናል፡፡ ስማቸው ከነዋይና ከንብረት ሻሞ ጋር ሲነሳም ግራ ያጋባል፡፡ ይህ አንዱ ልብ ሊባል የሚገባው የጋራ ችግር ነው፡፡ የትምህርት ተቋማት የዕውቀት መገብያ መሆንና ችግር ፈቺ ትውልድ ለአገር ማበርከት ሲገባቸው፣ የግጭትና የሞት አውድማ ሲሆኑ ያሳዝናል፡፡ ተማሪዎች ከመጻሕፍትና ከብዕር ውጪ ዱላና የስለት መሣሪያዎች ታጣቂ ሲሆኑ ያንገበግባል፡፡ ይህም አንዱ የጋራ መከራ ስለሆነ በጋራ የመፍትሔ ያለህ መባል አለበት፡፡ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች አዲሶቹ የብሔር ፖለቲካ ሽኩቻ ማስተናገጃ ሆነው ሽብር ሲነዛ እንደ አገር ያሳዝናልም፣ ያሳፍራልም፡፡ የግጭት ነጋዴዎች ከስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች በጊዜ ገለል እንዲሉ ካልተደረገ የአገር ህልውና ለአደጋ መዳረጉ የማይቀር ስለሆነ፣ በጋራ መረባረብ ግድ የሚሆንበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ከረፈደ በኋላ መተራመስ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ይህም ልብ ይባል፡፡

ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን አክብረው በሠለጠነ መንገድ መነጋገር ከቻሉ፣ ለማመን የሚያዳግት ተዓምር መሥራት ይቻላል፡፡ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምኅዳር የተቆጣጠሩት ቂም በቀል፣ ቁርሾ፣ ጥላቻና ሴረኝነት መወገድ አለባቸው፡፡ የፀጉር ስንጠቃ ፖለቲካ ትርፉ የዜሮ ድምር ውጤት ስለሆነ ማንንም የትም አላደረሰም፡፡ አሁን ሌላው ቢቀር በአንፃራዊ ሁኔታ የፖለቲካ ምኅዳሩ ተከፍቶ፣ አላሠራ የሚሉ የሕግ ማዕቀፎች እየተሻሻሉና እየተለወጡ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተከብሮ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስንፍና ካልያዛቸው በስተቀር በተሻለ ሁኔታ መሥራት የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቶና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚረዱ ተግባራት እየተከናወኑ ሴራ ውስጥ መገኘት አይገባም፡፡ አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ችግሮች ቢኖሩም፣ በጊዜ ሒደት እንደሚቀረፉ ታሳቢ መደረግ አለበት፡፡ ይህ ሁሉ የሚያግባባ ጥረት እየተደረገ በረባ ባልረባው ማኩረፍና ቅራኔ መፈልፈል ጤነኝነት አይደለም፡፡ በለውጡ ምክንያት ተበድያለሁ የሚል አካል ካለ፣ በቅንነትና በጨዋነት ጥያቄ ማንሳት መብቱ ነው፡፡ ‹እኔ  ዋነኛ ሆኜ ከሌለሁበት ይደፈርሳል› ማለት ግን ትክክል አይሆንም፡፡ የለውጡ ባለቤት እኔ ብቻ ነኝ ብሎ መኮፈስም ለለውጡ ጥቅም የሌለው ከመሆኑም በላይ፣ የግድ ጠላት ፍለጋ መባዘን ነው የሚሆነው፡፡ ኩርፊያና ግራ መጋባትም ራስን ከማስገመት የዘለለ ሚና የላቸውም፡፡ ይልቁንም በሀቅና በድፍረት እውነታን ተጋፍጦ ለአገር ሰላምና ዕድገት መነሳት ነው የሚጠቅመው፡፡

ኢትዮጵያ ድህነት ውስጥ ሆና መዝናናት አይቻልም፡፡ ሚሊዮኖች ዕርዳታ እየተለመነላቸው ሥራ ፈቶ ማስፈታት ነውር ነው፡፡ ባሉ ችግሮች ላይ ተጨማሪ መደረብ አሳፋሪ ነው፡፡ ከአገር ህልውናና ከሕዝብ ጥቅም በላይ የራስንና የቡድንን ብቻ  ለማስጠበቅ መረባረብ ኋላቀርነት ነው፡፡ ግጭት እየቀሰቀሱ በዕርዳታ ገንዘብ ኪስን መሙላት፣ የገዛ ወገን ማንገላታት፣ አገርን የሥጋት ቀጣና ማድረግ፣ ግብር ማጭበርበርና መሰወር፣ በሰው ሠራሽ እጥረት የዋጋ ግሽበት መፍጠር፣ የሕዝብን ጤና አደጋ ውስጥ የሚከቱ ምግቦችንና መድኃኒቶችን መሸጥ፣ በብሔራዊ ደኅንነት ላይ ማሴርና የአገር ጠላት መሆን የሚወገዙና የሚያስጠይቁ ወንጀሎች መሆን አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በድህነት እየማቀቀ በጎስቋላ ኑሮ አሳሩን ሲበላ፣ በላዩ ላይ ለማትረፍ የሚማስኑ ኃይሎች የሕዝብ ጠላት መባል አለባቸው፡፡ ሀቀኛ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ዓይነቶቹን የማጋለጥ ኃላፊነትም ግዴታም አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ደስተኛ የሚሆኑባት አገር ታስፈልጋቸዋለች፡፡ ይህች አገር ደግሞ ሕግ፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ያስፈልጋታል፡፡ በአምባገነኖችና በከፋፋዮች ደባ ሕዝብ መሰቃየት የለበትም፡፡ በዚህ ጊዜ የሀቀኛ ኢትዮጵያውያን ጥረት ከምንም ነገር በላይ ተፈላጊ ነው፡፡

ለኢትዮጵያ ከሰላምና ከዕድገት ውጪ አቋራጭም ሆነ አማራጭ የለበትም መባል አለበት፡፡ ምክንያቱም በአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥላ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ አገር የሆነችው ኢትዮጵያ ሰላም፣ ዕድገትና ብልፅግና ያስፈልጓታል፡፡ ከአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች በተጨማሪ በርካታ የውጭ ኢንቨስተሮች መምጣት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቅ ገበያ ስለሆነች በርካታ የልማት አጋሮች ያስፈልጓታል፡፡ ሰፊ ለም መሬቷ መታረስ አለበት፡፡ በርካታ ማዕድናቷ ወጥተው ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው፡፡ የኃይድሮ፣ የፀሐይ፣ የንፋስና የጂኦተርማል ሀብቷ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስገኘት አለበት፡፡ የውኃ ሀብቷ ጥቅም ላይ ውሎ ሲሳይ ማስገኘት ይጠበቅበታል፡፡ የቱሪዝም ሀብቷ በአፍሪካ ቀዳሚ ሆኖ በረከት ማምጣት ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያውያን በእነዚህ ሀብቶች ባለፀጋ የመሆን መብት አላቸው፡፡ ጥራቱ የተጠበቀ የመኖሪያ አካባቢ፣ ምግብ፣ ጤና፣ ትምህርትና የመሳሰሉት አገልግሎቶች ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከተመፅዋችነት ተላቀው በምቾት መኖር አለባቸው፡፡ ግጭት፣ ሞት፣ ውድመትና መፈናቀል በፍጥነት ተወግደው በክብር መኖር የኢትዮጵያውያን አዲሱ ገጽታ እንዲሆን፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት መነሳት አለባቸው፡፡ በሕግ የበላይነት የሚመራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ መገንባት አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ አቋራጭም ሆነ አማራጭ የለም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...