አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አራት ተከሳሾች በጋዜጣ እንዲጠሩ ትዕዛዝ ተሰጠ
በቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ኃላፊዎች በእነ አቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ ተካተው በተከሰሱ 26 ተጠርጣሪዎች ላይ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ከቆጠራቸው በርካታ ምስክሮች መካከል፣ ለተወሰኑት ጥበቃ እንዲደረግለት ያቀረበውን አቤቱታ አሻሽሎ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
ትዕዛዙን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ አዋጅ ቁጥር 699/2003 ድንጋጌን መሠረት አድርጎ፣ በተከሳሾች ላይ ከቆጠራቸው ምስክሮች መካከል ለተወሰኑት ምስክሮች ጥበቃ እንዲደረግላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ የጥበቃ አዋጁን በሚመለከት እንዳብራራው፣ በአዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 6(2) ድንጋጌ መሠረት፣ የጥበቃ ተጠቃሚነት ለማግኘት ጥበቃ የሚደረግለት ሰው ማንነትንና አድራሻ የሚገልጹ ማስረጃዎችን ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ጥበቃ ለማድረግ ምክንያት ከሆነው ጥቆማ፣ ምስክርነት ወይም ምርመራ ጋር የተያያዘውን ድርጊት ወይም ጥበቃ እንዲደረግለት የተጠየቀው ሰው ላይ የተጋረጠበትን አደጋ፣ የጥበቃ ተጠቃሚ ለመሆን ከማመልክቱ በፊት የቀረበበት የወንጀል ወይም የፍትሐ ብሔር ክስ፣ ወይም ሌላ ነገር ካለ ማስረጃ መቅረብ እንደሚያስፈልግ በዝርዝር ገልጿል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ማስረጃዎች ለችሎቱ ዳኞች ብቻ ዘርዝሮ መስጠት እንዳለበት በመንገር፣ ቀደም ብሎ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው አቤቱታ ከላይ ፍርድ ቤቱ በገለጸው መንገድ ባለመቅረቡ በሕጉ በተጠቀሰው አግባብ አሻሽሎ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ሌላው የሰጠው ትዕዛዝ ዓቃቤ ሕግ በምርመራ ወቅትም ሆነ ክስ ሲመሠረት፣ ትክክለኛ አድራሻቸውን ማወቅ እንደተሳነው በመግለጽ በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በአራት ተከሳሾች ላይ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ባቀረበው አቤቱታ ላይ ነው፡፡
በመሆኑም ተከሳሾቹ የተከሰሱበት ወንጀልና የተጠቀሰባቸው የወንጀል ድንጋጌ ከ12 ዓመታት በላይ ሊያስቀጣቸው የሚችል መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በማመልከቻው መጥቀሱን አስታውሶ፣ አራቱም ተከሳሾች በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥሪ ደርሷቸው እንዲቀርቡ ሲል፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 161 (2(ሀ) እና 162 (ሀ) ድንጋጌ መሠረት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ከተከሳሾቹ መካከል የቀረበባቸውን ክስ በመቃወም፣ የክስ መቃወሚያ ባቀረቡት 21ኛ ተከሳሽ አቶ ሰይፈ በላይ ላይ ብይን ሰጥቷል፡፡
አቶ ሰይፈ በዓቃቤ ሕግ የቀረበባቸው የመጀመርያ ክስ ሥልጣንን አላግባብ በመገልገል ሙስና ስለመፈጸማቸው ቢሆንም፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 407 (1) እና 407 (2) ድንጋጌን እንደማያሟላ በመግለጽ ተቃውመዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 404 ድንጋጌን አለማመሏቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሌላው ተከሳሹ የተቃወሙት የተጠቀሰባቸውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 407 (2) ድንጋጌን ነው፡፡ የተጠቀሰባቸው አንቀጽ መሆን ያለበት 407 (1) በመሆኑ፣ ክሱ መሻሻል እንዳለበት በመቃወሚያቸው ጠቅሰው ማቅረባቸውን ፍርድ ቤቱ በብይኑ ገልጿል፡፡
ተከሳሹ ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ እንደገለጸው፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 407 (1) (ሀ፣ ሐ) እና 407 (2) ሥር የተደነገገውን ተላልፈዋል ያለው፣ ተከሳሹ በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ለማድረግ በማሰብ በሌሎች ሰዎች መብት ላይ ጉዳት በማድረሳቸው ነው፡፡ ወንጀሉ የተፈጸመው ጥቅም ለማግኘት ሳይሆን በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል በመሆኑ የተጠቀሰው የሕግ አንቀጽ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ድርጊቱ መፈጸም አለመፈጸሙ የሚረጋገጠው በማስረጃ በመሆኑና የሙስና ወንጀል የሚያቋቁም የሕግ አንቀጽ አልተጠቀሰም ማለት ስለማይቻል፣ ፍርድ ቤቱ የቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ እንዲያደርግለት ዓቃቤ ሕግ መቃወሚያ ማቅረቡን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን መከራከሪያ አቤቱታዎች ከመረመረ በኋላ፣ በተከሳሹ ላይ የተጠቀሰው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 407 (1) እና 407 (2) የሚያቋቁሙት ፍሬ ነገሮች በተከሳሹ ተፈጽሟል በሚል ከቀረቡት ግዙፍ ተግባራት ጋር ተጣጥሞ የቀረበና ከአገላለጽ አንፃር የተለያዩ በመሆናቸው፣ እንዲሁም በሥልጣን አላግባብ መገልገል ወንጀል የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ብቻ ሳይሆን፣ በሌላ ሰው መብት ላይም ጉዳት ማድረስን የሚያካትት በመሆኑና መብት ደግሞ ሰብዓዊ መብትን የሚያካትት ነው፡፡ እንዲሁም የተከሳሹ ድርጊት በማስረጃ ከተረጋገጠ በኋላ ድርጊቱ የሚያቋቁመው የወንጀል ሕግ ድንጋጌ የትኛው ነው የሚለውን ወደፊት በመደበኛ ብይን ሊመዘን የሚችል በመሆኑ ተከሳሹ ያቀረቡን መቃወሚያ እንዳልተቀበላቸው አስረድቷል፡፡
ሌላው፣ ‹‹ተከሳሹ መከሰስ ያለባቸው በወንጀል ሕግ አንቀጽ 407 (1) ነው ወይስ 407 (2) ሥር በተደነገገው?›› የሚለውን ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ፍርድ ቤቱ የሚወስነው በመሆኑ እሱንም እንዳልተቀበለው በመንገር፣ ተከሳሹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም ተከሳሹ ድርጊቱን እንዳልፈጸሙና ጥፋተኛም እንዳልሆኑ በመናገር የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም ዓቃቤ ሕግ አሻሽሎ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ የተሰጠበትን የምስክሮች ጥበቃና አቶ ጌታቸውን ጨምሮ አራት ተከሳሾች በጋዜጣ እንዲጠሩ የተሰጠውን ትዕዛዝ ለመጠባበቅ፣ ለሐምሌ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ዓቃቤ ሕግ ጥበቃ እንዲደረግላቸው የጠየቀውን ምስክሮች በሚመለከት እንዲያሻሽል የታዘዘውን አሻሽሎ የሚያቀርብ ከሆነ ተከሳሾች አስተያየት እንዲሰጡበት ከተደረገበት በኋላ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት ጠቁሞ፣ ቀሪዎቹን የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ለመስማት ለሐምሌ 18፣ 23፣ 24፣ 25፣ እና 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡