ከዚህ በፊት ቀደም ብዬ ከምሠራበት መሥሪያ ቤት ለቅቄ የግል ሥራ ለመሥራት በመወሰኔ፣ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ በተማርኩበት የአካውንቲንግ ሙያ የተለያዩ የግል ድርጅቶችን የሒሳብ ሥራዎች መሥራት ጀምሬያለሁ፡፡ ለነገሩ ለመግቢያ ያህል ስለሥራዬ አወራሁ እንጂ ዛሬ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ጉዳይ ግን ሌላ ነው፡፡
ቀኑ ረቡዕ ነው፡፡ ቦታው ሲኤምሲ አካባቢ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት፡፡ ወደዚህ ቦታ የመጣሁት አንድ ወዳጄ የሚያስተዋውቀኝን የድርጅት ባለቤት ተዋውቄ፣ ከዚያም ከጥቂት ቀናት በኋላ የሒሳብ ሥራ እንድሠራላቸው ቀጠሮ ይዤ ነው፡፡ ቀጠሮውን በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቄ 11፡00 ሰዓት ላይ ደግሞ ቃሊቲ አካባቢ እንዲሁ በተመሳሳይ የምሠራበት አንድ የግል ድርጅት መሄድ ስላለብኝ ታክሲ ይዤ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ ትንሽ ጉዞ ካደረግን በኋላ ግን ታክሲው በመንገድ መዘጋጋት ምክንያት ቆመ፡፡ …5 ደቂቃ፣…10 ደቂቃ….፣ እያለ ጊዜው ነጎደ፡፡ ከመቸኮሌ የተነሳ አንገቴን በመስኮት አስግጌ ወደ መንገዱ ተመለከትኩ፡፡ በግምት ከ500 ሜትር በላይ መኪኖች ተጨናንቀው ቆመዋል፡፡ አንገቴን ወደ ውስጥ መልሼ በተቀመጥኩበት መቁነጥነጥ ጀመርኩ፡፡ በውስጤ ለምን ይሆን መንገዱ የተዘጋጋው ቁፋሮ እንደሌለ ስመጣ በደንብ አስተውያለሁ፡፡ ያለው አንድ አነስተኛ ሥራ ነው፡፡ እሱም በመንገዶቹ አካፋይ ላይ ስለሆነ ለመጨናነቅ አይዳርግም፡፡ እንዲያው ምን ይሆን?
ሰዓቱ 9፡45 ቢሆንም ታክሲው እንደ ኤሊ እየተጓዘ መልሶ ደግሞ ይቆማል… አሁንም እንደገና ፎቀቅ… በአካባቢው ያሉት የጭነት፣ የሕዝብ፣ የሠራተኛ ሰርቪሶች፣ ታክሲዎችና የቤት መኪናዎች ጡሩንባቸውን አንዳንዴ በየተራ፣ አንዳንዴ ደግሞ በጅምላ ያስጮሁታል፡፡ መዘጋጋቱ ግን ወይ ፍንክች ምንም እንቅስቃሴ የለም፡፡ ታክሲ ውስጥ ያለን ተሳፋሪዎች ግጭት ይሆን? እንደዚያ መሆን አለበት፡፡ መኪና ለመኪና ይሆን ወይስ ሰው? ትራፊክ ደግሞ የለም ብቻ ሁላችንም በአዕምሯችን የመጣውን ከግምት ያላለፈ ሐሳብ እንሰነዝራለን፡፡ ይኼንን ሁሉ ውይይታችንን ሲከታተል የነበረው የታሲው ረዳት ድንገት፣ ‹‹ምን እዚህ? ተማሪዎች ናቸው . . .›› ሲል ደነገጥኩ፡፡ ‹‹ምን…..ተማሪዎች ተገጩ? ወይስ ተጣሉ? ምን ሆኑ ነው የምትለው?›› ብዬ ጠየቅኩት፡፡ ‹‹እንደሱ አይደለም እዚህ ነዳጅ ማደያው ጋ አንድ ትምህርት ቤት አለ፡፡ በቃ እነሱ ሲወጡ መንገዱ ለረዥም ሰዓታት ይዘጋል፤›› ሲል አልገባኝም፡፡
ተማሪዎቹ ቢወጡ በመኪና መንገድ ላይ አይሄዱ፡፡ ከተማችን ውስጥ ከተሠሩ መንገዶች በስፋቱም በጥራቱም ምርጥ የሆነው የመኪና መንገድ የእግረኛን አማክሎ የተሠራ ነው፡፡ የእግረኛው ስፋቱ መኪና ያስኬዳል….ታድያ ምንድነው አልኩ….? ‹‹አይ ብዛት ያላቸው ወላጆች መኪና ይዘው ስለሚመጡና ከትምህርት ቤቱ ፊት ለፊት መንገድ ላይ ስለሚቆሙ ነው፤›› ሲለኝ፣ ‹‹እንዴ ቢቆሙስ በዚህ ሰፊ መንገድ ላይ ሌላ ማሳለፍ ያቅታል እንዴ?›› አልኩት፡፡ ‹‹ኦ….ኦ… በቃ ስትደርስ ታየዋለህ መንገዱን ዘግተው ነው የሚቆሙት፤›› ብሎን እርፍ፡፡ ታክሲ ውስጥ ከነበሩት ተሳፋሪዎች መካከል አንዳንዶቹ የረዳቱን ሐሳብ የሚያጠናክሩ አስተያየቶች ሰነዘሩ፡፡ እኔም አሁን መኪናው ከኤሊ ፍጥነት በተሻለ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ስለሆነ ትምህርት ቤቱ በር ላይ ደርሼ ሁኔታውን ለመረዳት ፈለግኩ፡፡
ሰዓቱ 10፡00 ሆኗል፡፡ አሁን መኪናዎቹ እየተንቀሳቀሱ ነው….በውስጤ ይኼኔ ከዚህ መሀል በሽተኞች የጫነ አምቡላንስ፣ ታካሚ የሚጠብቀው የሕክምና ባለሙያ፣ ተማሪ፣ አስተማሪ፣ ሌላም ብዙ… በዚህ መንገድ መዘግየት የተጎዱ ይኖራሉ ብዬ አሰብኩ፡፡ ኧረ አያድርገውና የእሳት አደጋ ቢፈጠር መኪናው እንዴት ያልፋል…ብቻ አያድርስ…፡፡
አሁን ወደ ትምህርት ቤቱ አካባቢ ደረስን፡፡ በመስኮት ወደ ውጪ መመልከት ቀጠልኩ፡፡ ያየሁትን ማመን አቃተኝ፡፡ የትምህርት ቤቱ አጥር ለመድረስ 100 ሜትር አካባቢ ጀምሮ የትምህርት ቤቱን በር አልፎ ከጎኑ ያለውን የነዳጅ ማደያ ይዞ ማዶ ድረስ መኪኖቹ አንዳንድ ቦታ እስከ ሁለት፣ ሌላው ሥፍራ ሦስት፣ ከፍ ሲል ደግሞ በተለይ ትምህርት ቤቱ በር ላይ ያለው አስፋልት ላይ እስከ አራት መኪና ደርበው ቆመዋል፡፡ እንዴ ምንድነው እየሆነ ያለው ሕግ የለም እንዴ? እዚህ አካባቢ ትራፊክ ፖሊስ የለም እንዴ? አልኩኝ፡፡ ታክሲ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ሾፌሩንና ረዳቱን ጨምሮ ብስጭታቸውን በተለያየ ሁኔታ ይገልጻሉ፡፡ እኔም ብስጭቴ ወደ ሐዘን ተቀይሮብኝ ራሴን አወዛውዛለሁ፡፡
እንደ ምንም በመከራ አልፈን ሄድን፡፡ አሁን መኪኖች በተሻለ ሁኔታ ፈጠን ፈጠን እያሉ መሄድ ጀመሩ፣ እኛም እንደዚያው፡፡ መንገዱ ጥግ ላይ ብዛት ያላቸው ሰዎች ቆመዋል፡፡ ያው መንገዱ ዝግ ስለነበር በትራንስፖርት እጥረት ተሰባስበው ታክሲ የሚጠብቁ እንደሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የተሳፈርንበት ታክሲ ተጨማሪ ሰው ሊጭን ከተሰበሰቡት ሰዎች አጠገብ ቆሞ ግፊያ ሆኖ የቻለው ገባና ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ ‹‹ምን ዕዳ ነው የገባነው እባካችሁ?›› እንደ ምንም ታግሎ ታክሲ ውስጥ የገባው ሰው እየተናገረ ስለነበር የምሬቱ ትንፋሽ ጆሮ ጥላዬን አጋለው፡፡ ሰውዬው ቀጠለ፣ ‹‹ሁሌ በቃ በዚህ ሰዓት እንደዚህ መሰቃየት አለብን?›› አለ…..ሆ…ሆ…ከእኔም የባሰ አለ እንዴ አልኩኝ በውስጤ፡፡
ወሬውን ከኋላ ወንበር ላይ ያሉት ይቀባበሉት ጀመር፡፡ እኔም ዞር ብዬ፣ ‹‹ሁሌም እንዲህ ነው እንዴ?›› ብዬ ጥያቄዬን በማስቀደም ከተወያዮቹ ጋር ተቀላቀልኩ፡፡ የቅድሙ ሰው ቀደም ብሎ፣ ‹‹አዎ…አዎ…..›› አለኝ ደጋግሞ፡፡ ‹‹ታውቃላችሁ ለዚህ ሁሉ ችግር ትምህርት ቤቱ መንገድ ዳር መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ወላጆች ልጆቻቸውን ለመውሰድ መንገድ ላይ መኪና መደርደራቸው አይቀርም፤›› አለ አንድ ወጣት፡፡ ሰውዬው ግን፣ ‹‹እንደዚያስ ቢሆን መኪኖቹ በተርታ በአንድ መስመር ሥርዓት ይዘው ለምን አይቆሙም?›› እያለ ምሬት ባለው አንደበት ውይይቱ ቀጥሏል፡፡ ግን እስከ መቼ? እኔ ግን በዚህ ላብቃ፡፡
(ኤፍሬም አበራ፣ ከአዲስ አበባ)