በብስራት ተክሉ
የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ከሚያስፈልጉ ነገሮች መካከል አንደኛው ፍርድ ቤቶችን በሚገባ ማጎልበት ነው፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ፍርድ ቤቶች ሕግ ሕይወት አግኝቶ የሚተረጎምባቸውና ፍትሕን የሚሹ ፍትሕን የሚያገኙባቸው ተቋማት መሆናቸው ነው፡፡ የዜጎችን የዕለት ተለት እንቅስቃሴ ተከትሎ መብታቸውን ሊነካ የሚችለውን አስፈጻሚውን አካል በዋናነት የሚቆጣጠሩትም ቢሆኑ ፍርድ ቤቶች ናቸው፡፡
ፍርድ ቤቶች የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት መብት አስጠብቀዋል ሊባል የሚችለው ነፃና ገለልተኛ ሆነው ጥራቱን የተጠበቀ ውሳኔ በአጭር ጊዜ መስጠት ሲችሉ ነው፡፡ ይህ ካልተፈጸመ ፍትሕ እንደተነፈገ ይቆጠራል፡፡ እንግሊዛዊው የመንግሥት ኃላፊ ሰር ዊልያም እንደገለጸው ‹‹የዘገየ ፍትሕ እንደተነፈገ ይቆጠራል››፡፡
ፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ ሆነው ጥራቱን የጠበቀ ውሳኔ በአጭር ጊዜ እንዲሰጡ ካስፈለገ የፍርድ ቤቶችን አቅም በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ማጎልበት የግድ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ፍርድ ቤቶችን በቴክኖሎጂ መደገፍ በምን መልኩ ሊሆን ይገባዋል? የሚለውን የሚዳስስ ይሆናል፡፡ ይኸውም በተለየ ዳኞችና የፍርድ ቤት የድጋፍ ሠራተኞች ዘመኑ በደረሰበት የአውቶሜሽን ቴክኖሎጂ በምን መልኩ ሊገዙ ይገባል? የሚለውን ይዳስሳል፡፡ ለዚህም ጽሑፉ የተዘጋጀው በተለያዩ አገሮች የተተገበሩ የፍርድ ቤት አውቶሜሽን ሥራዎች ያሳኳቸውን ግቦች መሠረት አድርጎ ነው፡፡
በእርግጥም ፍርድ ቤቶቻችንን አውቶሜት በማድረግ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በፍርድ ቤት የዕለት ተለት ሥራ ላይ ሙሉ በሙሉ ለማዋል ካስፈለገ የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጎቻችንን ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ ልናሻሽል ይገባል፡፡ ይኸውም በተለየ ከኤሌክትሮኒክ ፋይሊንግና ከተገልጋዮች ኤሌክትሮኒክ ሲግኒቸር ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችን ሊገዙ የሚችሉ የሕግ ድንጋጌዎችን በሥነ ሥርዓት ሕጎቻችን ውስጥ ስለሚያስፈልጉን ነው፡፡ አሁን በመሻሻል ላይ ያለው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ አርቃቂ ቡድን በማሻሻል ሒደቱ ለወደፊት ሊመጣ የሚችለውን አውቶሜሽን መሠረት ያደረጉ ድንጋጌዎችን በረቂቅ ሕጉ ውስጥ ሊያካትት ይገባል፡፡
በቀጣይ ይህ ጽሑፍ ‹‹አውቶሜሽን ምንድን ነው?›› ‹‹ፍርድ ቤቶችንና የፍትሕ ሥርዓቱንስ እንዴት ሊረዳ ይችላል?›› የሚሉ ጭብጦችን አንስቶ ዳሷል፡፡
የ‹‹አውቶሜሽን›› ጽንሰ ሐሳብ
አውቶሜሽን የዘመኑ ቴክኖሎጂ ካፈራቸው ዕውቀቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ በአውቶሜሽን የተዋጀ የቴክኖሎጂ መተግበሪያ የሚሰጠው ግልጋሎትም ከተራ ቴክኖሎጂዎች የራቀ“ በራሱ ውሳኔዎችንና መደምደሚያዎችን የሚሠራ የኮምፒዩተር ሥርዓት ያለው ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በአጠቃላይም አውቶሜት የተደረገ የኮምፒዩተር ሥርዓት ሦስት ዋና ዋና ነገሮችን ሊተገብር ይችላል፡፡ ይኸውም በአካባቢው ማለትም በኮምፒዩተር ሥርዓቱ ውስጥ የሚሰጡትን መረጃዎች ያቀናጃል እንዲሁም ያደራጃል፡፡ የተሰጠውን መረጃ ያብላላል (It Processes a Given Data) ያገኘውን መረጃ መሠረት አድርጎ ለሰዎች መረጃ ይሰጣል እንዲሁም የሚፈለገውን ሥራ ሠርቶ ያቀርባል፡፡ ይኸውም አውቶሜሽን ስንል ዘመኑ በሰጠን ማናቸውም ቴክኖሎጂ መጠቀም ማለት ብቻ አለመሆኑን ያስገነዝባል፡፡ አውቶሜሽን የቴክኖሎጂ ፍሬ የሆኑትን እንደ ኮምፒዩተር፣ ኔትዎርክ፣ ኢንተርኔትና ስካነር ያሉትን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በነጠላ ከመጠቀም በዘለለ የኮምፒዩተር ሥርዓታቸው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ታግዞ ሰነዶችን ማደራጀት፣ መተርጎምና አብራርቶ ሠርቶ የተለየ መደምደሚያና ውጤትን የሚሰጥ ሥርዓትን ያካትታል፡፡
የፍርድ ቤት አሠራርን አውቶሜት በማድረግ ዓቃቤ ሕጎች፣ ጠበቆች እንዲሁም ሌሎች የፍርድ ቤት ባለጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት በአካል መምጣት ሳያስፈልጋቸው መዝገብ እንዲከፍቱ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይኸውም የተለያዩ አቤቱታዎችን ማያያዝን ያጠቃልላል፡፡ የመዝገብ መከፈትን ተከትሎ የኮምፒዩተር ሥርዓቱ ከሰው ንክኪ ውጪ ተገቢውን ችሎት ይመድባል፡፡ መዝገቡ የተመደበለት ችሎትም አስፈላጊውን ማጣራት አድርጎ መዝገቡ እንዲቀጥል ያለ እንደሆነ የኮምፒዩተር ሥርዓቱ ችሎቱ ያለበትን የሥራ ጫና መሠረት አድርጎ በመዝገቡ ላይ ቀጠሮ ይሰጣል፡፡ እንዲህ እንዲህ ያለ ይኸው ሥርዓት እንደ አግባቡ አስቀድመው የሚሰጡትን መሠረታዊ መረጃዎች መሠረት በማድረግ ቀለል ያሉ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ፍርዶችን፣ ውሳኔዎችን፣ ብይኖችንና ትዕዛዞችን በራሱ ሠርቶ ያትማል፡፡
ከላይ ለመዳሰስ የሞከርኳቸውን የአውቶሜሽን ሥርዓት ፍሬዎች ዛሬ ላይ የተቋደሱ ያሉት በዕድገት ደረጃቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱት አገሮች ብቻ አይደሉም፡፡ ይልቁንስ በማደግ ላይ ያሉ የአፍሪካ አገሮች ጭምር ወደዚሁ እያመሩ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም በዋቢነት በምሥራቅ አፍሪካ በኬንያ፣ በኡጋንዳና በአንጎላ ፍርድ ቤቶች ያለውን ልምድ ማየት በቂ ነው፡፡
የሌሎች አገሮች ልምድ እንደሚያሳየው ከሆነ አውቶሜሽን የፍርድ ቤትን ሥራን በእጅጉ ያቀላል የፍርድ ቤቶችን ተደራሽነትም ያረጋግጣል፡፡ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ከማስፈን አንፃርም ቢሆን ከፍተኛ ሚናን እንደሚጫወትም የተለያዩ ጥናቶች የተረጋገጠ ነው፡፡ በዚህም ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለመዋጋትም ሁነኛ መፍትሔ ነው፡፡ በቀጣይ ክፍል አገራችን ኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶችን አውቶሜት ባደርግ እንደ አገር የፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ልናገኛቸው የምንችላቸውን ፍሬዎች እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡ በተጨማሪም መተግበሪያው ለዳኞች የተለያዩ ትዕዛዞችንና ቀለል ያሉ ውስብስብ ክርክር የሌለባቸውን ጉዳዮች በቀላሉ በሚሞሉ ፎርሞች ትዕዛዞችንና ፍርዶችን አትሞ ያወጣል፡፡ የፍርድ ቤትን አሠራር ሥርዓት ቀላል የሚያደርግ ስለሆነም ይግባኝ የመጠየቅን ሥርዓት በእጅጉ ያቀላል፡፡ ይኸውም በቀጣይ በሰፊው ይብራራል፡፡
የአውቶሜሽን ገፀ በረከቶች
ኤሌክትሮኒክ ፋይሊንግ
በአውቶሜሽን የታገዘ የፍርድ ቤት ሥርዓት ከፋይል አከፋፈት ጀምሮ ያሉ ሥራዎችን ከግለሰቦች ንክኪ ያላቅቃሉ፡፡ በዚህም የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ቢሮውና ጠበቆች በቀጥታ የኮምፒዩተር ኔትዎርክን በመጠቀም በፈለጉት ቦታ ሆነው የፍርድ ቤት ክስ ሊመሠርቱ ይችላሉ፡፡ የተከፈተው መዝገብ ተገቢውን ፎርማሊቲ ያሟላ ስለመሆኑ በሬጅስትራሩ ተረጋግጦ መዝገቡ የይለፍ ፍቃድን ሲያገኝ ኮምፒዩተሩ በቀጥታ በየምድብ ችሎቱ የሚገኙ ችሎቶችን ጫናና የጉዳዩን ዓይነት በማየት መዝገቡን ወደ አንድ ችሎት ይመራዋል፡፡ መዝገቡ የተመራለት ችሎት ዳኛም መዝገቡን አጣርቶ የይለፍ ወይም የይሻሻል የሚል ትዕዛዙን በኮምፒዩተር ሥርዓቱ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ይሰጣል፡፡ ምላሹን ተከትሎም የኮምፒዩተር ሥርዓቱ ከሰው ንክኪ ውጪ ሆኖ የችሎቱን ጫና መሠረት በማድረግ በኮምፒዩተር በተጣራው አጀንዳ መሠረት ቀጠሮ ይሰጣል፡፡
በኮምፒዩተር ሥርዓት የሚከፈት እያንዳንዱ ፋይል በተለያየ የመረጃ ቋት ውስጥ ይቀመጣል፡፡ በዚህም የተከፈቱ መዝገቦችና በውስጣቸው የተካተ~ ማስረጃዎችን ከመጥፋትና ከመሰወር ይታደጋል፡፡ በዚህ ሥርዓት ለሚከፈቱ መዝገቦች የዳኝነት ሒሳብ በኢንተርኔት ባንኪንግ፣ በክሬዲት ካርድ ወይም በሞባይል ባንኪንግ እንዲከፈልባቸው ማድረግ ይቻላል፡፡ መተግበሪያውም ቢሆን ይኸው ስለመፈጸሙ ሊያረጋግጥ የሚችል አቅም ያለው ሆኖ የሚሠራ ነው፡፡
በፍርድ ቤት የሚደረጉ ክርክሮችና የምስክር ቃል በድምፅና በጽሑፍ በቀጥታ ለዳኛው ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ
ፍርድ ቤቶችን በቴክኖሎጂ ማገዝ አንደኛው ዓላማ ዳኞች በችሎት ላይ ሰዓታቸውን በመጻፍ እንዳያሳልፉ ነው፡፡ በተለይም በክስና ምስክር መስማት ቀጠሮዎች ላይ ዳኞች ሙሉ ትኩረታቸውን ክርክር ባስነሳው ጭብጥ እንዲሁም በተከራካሪ ወገኖችና በምስክሮቻቸው ላይ አድርገው ጉዳዩን በሙሉ ትኩረት እንዲረዱ ማስቻል ነው፡፡ ይህንን ለማሳካት በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚገኙ የቀጥታ ክሶች ላይ ክስና ምስክር የሚሰማው በድምፅ መቅረጫ መሣሪያ በማገዝ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይኸውም በፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሚገኙ የንግድ ችሎቶችና አንዳንድ የወንጀል ችሎቶች ላይ ተፈጻሚ ነው፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ይኸው አሠራር ክስና ምስክር በሚሰማበት ወቅት ዳኛው ከጽሑፍ ሥራ ተላቆ ተከራካሪ ወገኖችና ምስክሮቻቸው ሊጠየቁ የሚገባቸውን ጥያቄችን አገናዝቦ እንዲያዘጋጅ ይረዳዋል፡፡ በዚህ ብቻም ሳይወሰን ዳኛው የተከራካሪ ወገኖችንና የምስክሮቻቸውን አጠቃላይ ሁኔታ በችሎት እንዲመረምር ዕድል ይሰጠዋል፡፡
ፍርድ ቤቶችን አውቶሜት ማድረግ አሁን ካለው የፍርድ ቤት የክስና ምስክር መስማት ሒደት በተጨማሪነት በችሎት የተቀረፀው ቃል በድምፅና በጽሑፍ ተገልብጦ በኮምፒዩተር ሥርዓቱ መሠረት ለዳኛው ሁሌም በአቅራቢያው እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ይኸውም ዳኛው በማናቸውም ወቅት በመዝገቡ ላይ ለሚሠራቸው ሥራዎች ተገቢው ግብዓት በአቅራቢው እንዲኖር ይረዳዋል፡፡ በዚህም የውሳኔዎችን ጥራት ለማስጠበቅ ይቻላል፡፡
የፍርድ ቤት ሰነዶችን ማዘጋጀት
የፍርድ ቤት ሥራን ለማሳለጥ የሚሠሩ መተግበሪያዎች ዋነኛ ተግባር ሊሆን የሚችለው በቀላሉ ሰነዶችን የማደራጀት እንዲሁም መሠረታዊ መረጃዎችን በመቀበል ቀለል ያሉ ሊባሉ የሚችሉ ፍርዶችን ትዕዛዞችን እንዲሁም ብይኖችን ሠርቶ ማተም ነው፡፡
በአውቶሜሽን የታገዘ የፍርድ ቤት ሥርዓት ሲኖረን የተለየ ቋሚ ፎርም ያላቸውን ሰነዶች በቀላሉ መሠረታዊ መረጃን በመስጠት ብቻ በኮምፒዩተር ሥርዓቱ ትዕዛዝ፣ ፍርድ ወይም ብይን ሠርቶ እንዲያወጣ ለማድረግ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ያህል አብዛኛውን ጊዜ መዝገቦች እንደተከፈቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጠየቁ እንደ
ዕግድ፣ ማስከበርና ጊዜያዊ ቀለብ የመሳሰሉ ትዕዛዞችን መሠረታዊ የሆኑ መረጃዎችን ለኮምፒዩተር ሥርዓቱ በመስጠት ብቻ አትመው እንዲወጡ ማድረግ ይቻላል፡፡ ለዋቢነትም የኮምፒዩተር ሥርዓቱ ለግድ የቀረቡትን ንብረቶች ዝርዝር መረጃ በመቀበል ብቻ ንብረቶች እንዲታገዱ ወይም እንዲከበሩ ለማድረግ እንዲችል ተደርጎ የሚሠራ ነው፡፡ ከጊዜያዊ ቀለብ ጋር የተያያዙ ክርክሮችንና ትዕዛዞችንም በተመሳሳይ መንገድ በቀላሉ በኮምፒዩተር ሥርዓቱ ማሠራት ይቻላል፡፡
ወደ ወንጀል ጉዳዮች ስንመጣም መተግበሪያው በተመሳሳይ የመያዣና የብርበራ ትዕዛዞችን፣ በምንነት ላይ መሠረት ያደረጉ የጥፋተኝነት ውሳኔን እንዲሁም የቅጣት ዓይነትና መጠንን በሚሰጠው መሠረታዊ መረጃ መሠረት ሠርቶ ሊያወጣ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል መተግበሪያው ተገቢውን የወንጀል ድንጋጌ የቅጣት ማቅለያና የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶችን በመቀበል በቀላሉ ቅጣትን ለመወሰን እንዲችል ሆኖ የሚሠራ ነው፡፡ እንደዚህ ያሉ ጥራታቸውን የጠበቁ መተግበሪያዎች በሥራ ላይ ሲውሉ የዳኞችን ጉልበትና ሰዓት ከመቆጠብም በተጨማሪ በፍርድ ቤቶች ለሚሰጡ ትዕዛዞችና ፍርዶች ጥራት ሁነኛ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡
ተገቢውን ሕግና ውሳኔ መጠቆም
የፍርድ ቤት ሥራን አውቶሜት ከተደረገ የመተግበሪያው አንዱ በጎ ጎን ሊሆን የሚችለው ከተያዘው ጉዳይ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያላቸውን የሕግ ድንጋጌዎችንና የፍርድ ቤት ውሳኔች ለዳኞች መጠቆም መቻሉ ነው፡፡ መተግበሪያዎቹ የተለዩ ውስን የሕግ ቃላትን ወይም ሐረጎችን መሠረት በማድረግ ከመረጃው ጋር የተያያዙ መሠረታዊ ድንጋጌዎችን ወይም የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ለዳኛው ሊጠቁሙ ይችላሉ፡፡ በዚህም ዳኞች መተግበሪያውን በመጠቀም እየሠሩት ያለውን ሰነድ የተመለከቱ ወሳኝ የሕግ ድንጋጌዎች እንዲሁም የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች ጠቋሚ መረጃ ከኮምፒዩተር ሥርዓቱ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡
ይኸው ቴክኖሎጂ ዳኞች ሕጎችንና የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን በመፈለግ ጊዜያቸውን እንዳያባክኑ ይረዳቸዋል፡፡ በተጨማሪም ወሳኝ የሆኑ የመረጃ ግብዓቶችን በመስጠት ዳኞችን ስህተት ከመሥራት ሊደግፉና የፍርድ አሰጣጥ ጥራትና ቅልጥፍና ደረጃን ያሳድጋል፡፡
የጉዳዮችን መጓተት መቅረፍና የተጠያቂነት ሥርዓትን መዘርጋት
ፍርድ ቤቶችን በቴክኖሎጂና አውቶሜሽን መደገፍ ጉዳዮችን ከመጓተት ይታደጋል፡፡ በርካታ አገሮችም ቢሆኑ የረዥም ጊዜ ውዝፍ የፍርድ ቤት ፋይሎችን በፍጥነት ለማቃለልና የፍርድ ቤት ሙግት ሥርዓታቸውን ለማሳለጥ ተጠቅመውታል፡፡ የአውቶሜሽን ሥርዓቱ ይህንን የሚያደርገው በቀጠሮ አሰጣጥና በመረጃ ረገድ ግልጽና የማይዋዥቁ መርሆዎች ተግባራዊ በማድረግ ነው፡፡
በፍርድ ቤቶች ውስጥ አውቶሜሽንን ተግባራዊ በማድረግ የቀጠሮ አሰጣጥ ሥርዓትን በኮምፒዩተር የታገዘ ለማድረግ ይቻላል፡፡ ማናቸውንም የመልስ መስጫ፣ ክስ መስማት፣ ምስክር ማሰሚያና የመሳሰሉትን ቀጠሮዎች የኮምፒዩተር ሥርዓቱ ከሰው ንክኪ ውጪ ሆኖ የችሎቱን ጫና በራሱ በማገናዘብ ቀጠሮን ይሰጣል፡፡ በዚህም የጉዳዮችን አላግባብ መጓተት ይቀርፋል፡፡ በዚህ መልኩ የተደራጀው ሥርዓት ቀጠሮ በመስጠት ብቻ ሳይወሰን እያንዳንዱ ችሎት በቀጠሮ ቀን ሊሠራ የሚገባውን ሥራ ስለመሥራቱ ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡ ዳኞችም ቢሆኑ ያለምክንያት የቀጠሮ ቀንን እንዲቀይሩ አይፈቅድም፡፡ ዳኞችና ሌሎች የፍርድ ቤት ሠራተኞች ቀጠሮ ለመቀየር ቢፈልጉ የሚቀይሩበትን ምክንያት በኮምፒዩተር ሥርዓቱ ላይ እንዲገልጹ ያስገድዳል፡፡ ቀጠሮ የሚለወጥባቸው ምክንያቶችም በሥርዓቱ ላይ ተለይተው ይወስናሉ፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቶች ያለበቂ ምክንያት የቀጠሮ ለውጥን እንዳያደርጉ ይገድባል፡፡
የአውቶሜሽን ሥርዓቱን በቀጥታ እያንዳንዱ ችሎትና ሠራተኛ የሚሠራውን ሥራ በቀጥታ በፍርድ ቤቱ ኃላፊዎች ቢሮአቸው ውስጥ ሆነው እንዲከታተሉም ይፈቅዳል፡፡ በተለይም በፍርድ ቤት በቀጠሮ ላይ አላግባብ በተደጋጋሚ እየተቀጠሩ የቆዩ መዝገቦችን የአውቶሜሽን ሥርዓቱ ለይቶ ለኃላፊዎች ሪፖርት ስለሚያደርግ አላግባብ ጉዳዮች እንዳይጓተቱ ይረዳል፡፡ ይኸውም የፍርድ ቤት ኃላፊዎች ያለአግባብ ጉዳዮች የሚጓተቱባቸውን ችሎቶችና የሥራ ክፍሎች ለይተው ተገቢውን የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወስዱ ያስችላቸዋል፡፡ ይኸውም የፍርድ ቤት ኃላፊዎቹ የፍርድ ቤት ሥራን በተዋጣ መንገድ እንዲመሩ ያግዛል፡፡ በአጠቃላይም የአውቶሜሽን ሥርዓትን በፍርድ ቤቶች ውስጥ መዘርጋት ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበትን የፍርድ ቤት ሥርዓት እንድንዘረጋ ሁነኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡
የይግባኝና የሰበር ችሎትን ሒደት ማሳለጥ
በአውቶሜሽን የገዛ የዳኝነት አካልን መገንባት ከላይ እንደተጠቀሰው መደበኛ የክርክር ሒደትን ያሳልጣል፡፡ በዚህ ብቻም ሳይወሰን የይግባኝና ሰበር ማመልከቻ ሒደቶችን ያሳልጣል፡፡ ይኸውም ማለት በመደበኛ የይግባኝና ሰበር ክርክሮች አካሄድ ላይ በመደበኛ ክርክር የሚሰጠውን ግልጋሎት መስጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የሥር ፍርድ ቤት የመዝገብ ግልባጭ በአጭር ጊዜ ለላይኛው ፍርድ ቤት ከሰው ንክኪ ውጪ እንዲደርስ ለማድረግ ያስችላል፡፡
አሁን ባለው መደበኛ አሠራር ማናቸውም ተከራካሪ ወገን ይግባኝ ለማለት ቢፈልግ የሥር ፍርድ ቤት መዝገብ ግልባጭ ኮፒ ተደርጎ እንዲሰጠው ለቀናት መጠበቅ ግዴታው ነው፡፡ በሰበር ችሎት ሒደትም የሥር ፍርድ ቤት መዝገብ እንዲቀርብ የሚያዝባቸው ጊዜያት አሉ፡፡ የሥር ፍርድ ቤት መዝገብን ዋናውን ወይም ኮፒውን ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ወይም ለሰበር ችሎት በመሸኛ የመላክ ሒደት የሰው ጊዜንና ጉልበትን የሚጠይቅ ነው፡፡
ፍርድ ቤቶችን አውቶሜት ብናደርግ አሁን የይግባኝ አከፋፈት ሥርዓቱ የሚጠይቀውን እንግልት በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ፍርድ ቤቶች አውቶሜት ከተደረጉ ሁሉም የፍርድ ቤት ሰነዶች በኮምፒዩተር ሥርዓቱ ውስጥ ይገኛሉ ማለት ነው፡፡ ማናቸውም ይግባኝ ማመልከቻ ሲቀርብም የታችኛው ፍርድ ቤት በቀጥታ ለይግባኝ ሰሚው ወይም ለሰበር ችሎቱ የሥር ፍርድ ቤት መዝገብን በኮምፒዩተር ኔትዎርክ ሥርዓት በተወሰኑ ደቂቃች ውስጥ ሊልክ ይችላል፡፡ ይኸውም ፍርድ ቤቶች ቀልጣፋና ጥራቱን የጠበቀ አሠራርን በይግባኝና ሰበር ሥርዓቶች ላይ እንዲዘረጉ ያስችላቸዋል፡፡
ማጠቃለያ
በአሁኑ ወቅት በርካታ አገሮች የፍርድ ቤት ሥራን ለማዘመን ሲሉ ፍርድ ቤቶቻቸውን አውቶሜት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደ ሞከርኩት የፍርድ ቤትን አሠራር በተወሰነ ረገድ በመቀየርና በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ በማድረግ በፍርድ ቤቶች ውስጥ ግልጽ የሆነና ተጠያቂነትን መሠረት ያደረገ ሥርዓትን ለመገንባት ችለዋል፡፡ በዚህም ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎትን ለባለጉዳዮች ለመስጠት ችለዋል፡፡
ጥናቶች እንደሚያሳዩትም የአውቶሜሽን ሥርዓቱ አንዴ ከተዘረጋ በኋላ የዚሁ ቴክኖሎጂ ሥርዓት መኖር የፍርድ ቤትን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል፡፡ የዳኞችንና የድጋፍ ሠራተኞችን የሥራ ጫና በማቅለልም ፍትሕ በአጭር ጊዜ እንዲገኝ ይረዳል፡፡ ቴክኖሎጂው ከሚያቀርባቸው በርካታ ገፀ በረከቶች በተጨማሪ ግልጽና ተጠያቂ የሚያደርግ ሥርዓት በመዘርጋት የፍርድ ቤት ሥራዎች ጥራት እንዲጠበቅና ከሙስና እንዲፀዱም ያደርጋል፡፡ ስለሆነም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ይህንን ኃላፊነት በመውሰድ ቀልጣፋና ጥራት ያለውን ፍትሕ ለማዳረስ ሲባል የአውቶሜሽን ሥራውን ሊያስጀምሩ ይገባል፡፡ መንግሥትና ሌሎች ፍርድ ቤቶችን በማገዝ ላይ ያሉ ተቋማትም ቢሆኑ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመን ሲሉ መሠረታዊ በሆነው በዚሁ የቴክኖሎጂ ማሻሻያ ላይ ተገቢውን ወጪ በማውጣት የፍትሕ ሥርዓቱን ሊደግፉ ይገባል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ አማካሪ ጠበቃ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡