በአስረስ አያሌው
በእሑድ ሰኔ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ሪፖርተር ጋዜጣ ዕትም የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሰጡት ቃለ ምልልስ በርካታ ሐሳቦችን ስለፈጠረብኝ፣ በጽሑፍ አስተያየቴን ማስፈሩ አስፈላጊ መስሎ ተሰምቶኛል። ቃለ ምልልሱ ተመሳሳይ ሐሳቦች ተደጋግመው የተገለጹበት ስለሆነ ጨመቅ ተደርጎ ቢቀርብ ጥሩ ነበር እላለሁ። (በነገራችን ላይ ደብረ ጽዮንን (ዶ/ር) ያላልኩት አክብሮት ጎድሎኝ ሳይሆን የጤና፣ የእንስሳት ወይም የሥነ ልቦና ሐኪም ላልሆነ ሰው ዶ/ር የሚለውን ማዕረግ ከስም በፊት መጠቀም አግባብ ስላልሆነ ነው። ለምሳሌ ባራክ ኦባማ በአሜሪካ ትልቅ ግምት የሚሰጠውን የሕግ (Juris Doctorate) ከሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ቢቀበሉም፣ ዶ/ር ኦባማ ተብለው ተጠርተው አያውቁም። ስለዚህ ዓብይ አህመድንም ሆነ አምባቸውን መኮንን ዶ/ር ብዬ አልጠራም። በአንፃሩ ዶ/ር አሚን የጤና ሐኪም ስለሆኑ ዶ/ር ብዬ እጠራቸዋለሁ። ዶክትሬቱ የፍልስፍና ከሆነም ግለሰቡን አንዴ ለማስተዋወቅ ከስም በኋላ በቅንፍ ይቀመጣል እንጂ በሁሉም ቦታ አይጠቀስም። ማዕረጉን ከፈረንጆቹ መውሰዳችን ካልቀረ ልክ እነሱ እንደሚገለገሉበት መገልገል ያለብን ይመስለኛል።) ለማንኛውም ወደ አስተያየቴ ልግባ።
ስለመንገድ መዝጋትና ዝርፊያ
ቃለ ምልልሱን ያካሄደው ጋዜጠኛ ሳሙኤል ጌታቸው ‹‹አማራ ክልል አካባቢ ምግብ ወደ ትግራይ እንዳይሄድ መኪና አስቁመው ሲዘርፉ የሚታዩ አሉ። . . .ችግሩንና ድህነቱን የሚገነዘበው ጥቂት ነው። አዲስ አበባ ያለ ሰው ትግራይ ኒውዮርክ ናት ብሎ ያስባል፤›› የሚል የግሉን አመለካከት የሚያንፀባርቅ ጥያቄ አቅርቧል። በመጀመርያ ደረጃ ዝርፊያ መካሄዱን በተጨባጭ ማስረጃ አላስደገፈም። በመቀጠል በዝርፊያው አማራ የሆኑ ነጋዴዎችም ጭምር ንብረታቸውን እንዳጡ የሚነገረውን ሆን ብሎ ባለመጥቀስ ተጎጂዎቹ ትግሬዎች ብቻ እንደሆኑ ለማስመሰል ሞክሯል። ለመሆኑ እሱ ‹አዲስ አበባ ያለ ሰው ትግራይ ኒውዮርክ ናት ብሎ እንደሚያስብና ድህነቱን እንደማይገነዘብ› እንዴት አፉን ሞልቶ መናገር ቻለ? ይህስ ወደ ትግራይ የሚሄድ መኪናን ከመዝረፍ ጋር ምን ያገናኘዋል? ወይስ የአዲስ አበባ ሕዝብ ከመኪና ዘራፊ ወንበዴዎች ጋር ግንኙነት አለው እያለን ነው? በእውነቱ ሚዛናዊ መሆን ነበረበት።
ደብረ ጽዮን ለዚሁ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ወደ አማራ የሚሄደውን እናስቁም አላልንም። . . .ትግራይ ክልል በር ስለሆነና አጠገባችን ስለሚገኝ መንገዱን ሄደን ማፍረስ እንችል ነበር፤›› የሚል አስገራሚ ሐሳብ ሰንዝረዋል። ከትግራይ ወደ አማራ ክልል ምን ይሄዳልና ነው የሚያስቆሙት? እንጂማ የአማራን ታሪካዊ ርስቶች በጉልበት የነጠቀ ፓርቲና መንግሥት ይህን ከማድረግ ባልተመለሰ ነበር። ‹‹መንገዱን ሄደን ማፍረስ እንችል ነበር›› የሚለው አነጋገራቸው ሰውየው የለየላቸው አምባገነን እንደሆኑ ይመሰክራል። ቀደም ሲል የመንገዱን መዘጋት ሲያወግዙ አልነበረም? ታዲያ መንገድ ለማፍረስ መመኘት ምን ይባላል? (ጋዜጠኛው እዚህ ላይ ፕሬዚዳንቱን ማፋጠጥ ነበረበት) በእውነቱ መንገድ ከማፍረስ መንገድ መዝጋት አሥር እጅ ይሻላል! መንገድ ቢዘጋ ሌላ አማራጭ መንገድ አይጠፋምና። ይህን ስል መንገድ እየዘጉ የሚዘርፉት ወንበዴዎች ጠንካራ ዕርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ አጥብቄ በማመን ነው።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ የትግራይን ተበዳይነት ለማስረዳት የኢኮኖሚ ጫናን በምሳሌነት እስከ መጥቀስ መጓዛቸው ያስገርማል። ለምሳሌ ‹‹መንገድ አያስፈልጋችሁም፣ እላፊ አላችሁ፣ ሌሎች ክልሎች ገና ናቸው የሚል የሌለ መመዘኛ እየተሰማ ነው፤›› ሲሉ አማረዋል። እግረ መንገዳቸውን ትግራይ በጦርነት ተጎድታለች ተብሎ ሲደረግላት የኖረውን ልዩ ድጋፍ ቢጠቅሱትም ጥሩ ነበር። ለነገሩ ‹‹ትግራይ በአብዛኛው ከተማነት የተስፋፋበት ክልል ነው፤›› በማለት በቀጥታም ባይሆን በገደምዳሜ (Implicitly) ልዩ ተጠቃሚ እንደነበረች አምነዋል። ደብረ ጽዮን መንገድ እናፈርሳለን የሚሉትን ይተው እንጂ ትግራይ ዳር እስከ ዳር ዘመናዊ መንገድ ቢዘረጋባት ደስታዬ ነው።
በወንጀል ስለሚፈለጉ ግለሰቦች
በመቀጠል በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ይዞ ስለማስረከብ ሲጠየቁ ከሰጡት መልስ ውስጥ ‹‹. . .ለማይፈለግ ጥቃት የተላከውን ከበን በመጨረሻው እንዲመለስ አድርገናል። ሰው ለማገዳደል ነው። ተኩስ ቢጀመር እዚህ ያለው ሰው ዝም እንደማይል ይታወቃል። እዚህ ራሱ መዓት ወታደር ነው ያለው. . .›› ያሉበት ይገኝበታል። ‹የማይፈለግ ጥቃት› ማለት ተጠርጣሪን ለመያዝ መሞከር ነው? የትግራይ ልዩ ኃይል ግዴታው የክልሉን ሰላም ማስከበር ነው? ወይስ የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎችን ማዋከብ? ‹‹መዓት ወታደር ነው ያለው›› ሲሉስ የትግራይን ሕዝብ በሙሉ አስታጥቀውታል ማለት ነው?
ለመሆኑ ደብረ ጽዮን የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሥልጣንና ተግባር የሚደነግገውን አንቀጽ 62 ያውቁታል? ንዑስ አንቀጽ 9 ምክር ቤቱ፣ ‹‹ማንኛውም ክልል ይህን ሕገ መንግሥት በመጣስ ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ›› የማዘዝ ሥልጣን እንዳለው ይገልጻል። በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠረን ግለሰብ መደበቅ ሕገ መንግሥቱን መጣስ ነው። ስለዚህ የፌዴራሉ መንግሥት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ትዕዛዝ ያለ ትግራይ ክልል ፈቃድ ተጠርጣሪውን ካለበት ይዞ ለሕግ የማቅረብ መብት አለው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሕገ መንግሥቱን እንደ መጣስ ከሚቆጠሩ ድርጊቶች መካከል በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ሳያሟሉ ለመገንጠል መሞከር፣ እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብትን ሕገ መንግሥቱ ከሚፈቅደው ውጪ ጥቅም ላይ ማዋል ይገኙበታል። ለምሳሌ ትግራይ ውስጥ ነዳጅ ቢፈልቅ በአንቀጽ 55 (2/ሀ) መሠረት የነዳጅ ሀብቱን አጠቃቀም በተመለከተ ሕግ የማውጣት ሥልጣን የተወካዮች ምክር ቤት ነው። ይህን መቃወም ሕገ መንግሥቱን መጣስ ነው። አንዳንድ የትግራይ አክቲቪስቶች ግን ነዳጅ ስላገኘን እንገነጠላለን በማለት ተጣሰ እያሉ ነጋ ጠባ የሚጮሁለትን ሕገ መንግሥት ገደል ይከቱታል።
‹‹የማይፈለግ ጥቃት›› ወደ ሚለው አባባል ስንመለስ ታዲያ ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ለመያዝ የሕወሓት ታጣቂዎች ጎንደርን የጦርነት ቀጣና ሲያደርጓት፣ ደብረ ጽዮን ለምን አልተቃወሙም? ወይስ ስለኦፕሬሽኑ አያውቁም ነበር? ኮሎኔል ደመቀስ በሰላማዊ መንገድ መብቱን ከመጠየቅ ባለፈ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ምን ጥፋት ሠርቷል? ደግሞስ እሱን ለመያዝ የአማራ ክልል ፖሊስ አይበቃም ነበር? ራሱን ለመከላከል ዕርምጃ መውሰዱስ ስሙን እስከ ዛሬ በነፍሰ ገዳይነት ሊያስጠራው ይገባል? ደብረ ጽዮን ሚዛናዊ ለመሆን ቢሞክሩ ጥሩ ነበር።
ከሁሉ የከፋው በየወህኒ ቤቱ ግፍ ሲፈጸምባቸው በነበሩት ዜጎች ላይ መሳለቃቸው ነው። በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ስለተያዙት ግለሰቦች ሲናገሩ፣ ‹‹የታሰሩት እኮ አገር እየወጉ የነበሩትን ኃይሎች ሰልላችኋል ተብለው ነው። ይህን ስለሠሩ ነው የተከሰሱት። እኔ በጣም ያሳዝነኛል። ያሳፍረኛልም፤›› በማለት በሰው ቁስል ላይ ጨው ነስንሰዋል። በበኩሌ የአገር ሰላምና ፀጥታ ቢጠበቅ ተቃውሞ የለኝም። ለዚህ ሲባል ግን ንፁኃን ዜጎች ብልታቸው ላይ ኮዳ ሊንጠለጠልባቸው፣ ወይም ጉንዳን ላይ ሊተኙ፣ ወይም ከአውሬ ጋር ሊታሰሩ ይገባል ብዬ አላምንም። ደብረ ጽዮን የደኅንነት ሰዎች ኤርትራ ድረስ እየሄዱ ይሰልሉ እንደነበር በኩራት ሲያወጉልን፣ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በየወህኒ ቤቱና የድብቅ ማሰቃያው ይፈጸም የነበረውን ዘግናኝ ድርጊት ሊያነሱት አልፈለጉም።
ስለጌታቸው አሰፋ ተጠይቀው በሰጡት መልስ አንዴ ‹‹የተደረደረው በሙሉ የውሸትና የፈጠራ ነው፤›› ሲሉ ቆይተው፣ መልሰው ‹‹በግሉ ያጠፋው ጉዳይ ካለ ግን ጌታቸውንም ሆነ ሌላውንም ሰው አንጠልጥሉት ብያለሁ፤›› ይላሉ፡፡ ከዚያ ደግሞ ‹‹አገሩን ነው ያገለገለው›› ብለው ሲያበቁ አሁንም ሐሳባቸውን በመቀየር ‹‹ያጠፋው ነገር ካለ ግን መያዝ አለበት፤›› በማለት፣ በአንድ አንቀጽ ውስጥ ብቻ በተደጋጋሚ እርስ በርሱ የሚጋጭ ነገር ሲናገሩ ይታያል። ይኼ ጠንካራ መደምደሚያ ላይ የማይደርስ የሐሳብ ሽክርክሮሽ (Circular Reasoning) የፖለቲከኞቻችን ሁሉ አባዜ እንደሆነ ይታወቃል።
ስለመገንጠል
ምክትል ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን በሕዝቡ ውስጥ የመገንጠል ስሜት አለ ወይ? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ‹‹አዎ. . . አለ። እኛ እንዴት መገንጠል መፍትሔ ይሆናል? አብረን ነው መሥራትም መልፋትም ያለብን፣ አብረን ማስተካከል ያለብንን እናስተካክል እያልን እያረጋጋን ነን፤›› የሚል መልስ ሰጥተዋል። ሲጀመር ‹የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ› ስለሆነ፣ እንኳን ዛሬ ውጥረት በነገሠበትና በሰላሙም ጊዜ ከመገንጠል የሚያግድ ነገር የለም። ደግሞም መገንጠል የፈለገን ሕዝብ ለማረጋጋት መሞከር የመብት ረገጣ ከመሆኑም ባሻገር፣ የደብረ ጽዮንን መንግሥት ኢዴሞክራሲያዊነት የሚያጋልጥ ነው። የሚያስቀው ሕወሓት የመገንጠል ዕዳን እንዳላመጣብን ሁሉ፣ ዛሬ ደርሶ ምን ጊዜም ኢትዮጵያዊ የሆነውን የትግራይ ሕዝብ አንድነት ይሻልሃል ብሎ ለመምከር መዳዳቱ ነው።
የደብረ ጽዮን ለአንድነት መቆርቆር ከልብ እንዳልሆነ እንድጠረጥር ያደረጉኝን ማስረጃዎች ከዚያው ከቃለ ምልልሱ ነቅሼ ማውጣት እችላለሁ። ለምሳሌ የሚከተለውን አባባላቸውን እንመልከት፡፡ ‹‹ሰላም ፈላጊ ሁሉ እየመጣ ነው። የትግራይ ብቻም ሳይሆን፣ የውጭ ኢንቨስተርም ጭምር እየመጣ ነው። ለምን? እዚህ ክልል ውስጥ ሰላም አለ። የሚሠራና ሥራ ላይ ያለ መንግሥት አለ። የፈራረሰ የቀበሌ መዋቅር አይደለም ያለን፤›› ብለዋል፡፡
ደብረ ጽዮን በአጭሩ ሁለት መንግሥትና ሁለት አገር እንዳለ እየነገሩን ነው። ከላይ እንዳየነው ‹‹አብረን ነው መሥራትም መልፋትም ያለብን›› ሲሉ ችግሮቻችን በሙሉ የጋራችን እንደሆኑ መናገራቸው አይደለምን? ታዲያ ሌላው የኢትዮጵያ አካል ሰላም ሳይሆን፣ ትግራይ ውስጥ ‹‹ሰላም አለ›› እንዴት ይባላል? አንዱ የአካል ክፍል ታሞ ሌላው ጤነኛ ሊሆን ይችላል? ወይስ ትግራይ የኢትዮጵያ አካል አይደለችም? ደግሞም በወልቃይትና በራያ የማንነት ጥያቄ ያነሱ ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ኢሰብዓዊ ድርጊት የተሟላ ሰላም አለመኖሩን አመላካች ነው።
ደብረ ጽዮን በቃለ ምልልሱ መግቢያ ስለትግራይ ልማት ሲናገሩ፣ ‹‹እያወራን ያለነው ስለ ትግራይ ስለሆነ ነው እንጂ ሌላውም ሕዝብ በድህነት ውስጥ መኖር የለበትም፤›› ብለው ነበር። ቆየት ብለውም ‹‹የትግራይ ብቻም ሳይሆን በሌላውም ላይ ኃላፊነት ስላለብን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን፤›› ሲሉ ተናግረዋል። እና ስለሌላው የአገራችን አካባቢ እንዲህ የሚጨነቁ ከሆነ እኛና እነሱ፣ እዚህና እዚያ ማለትን ምን አመጣው? በእርግጥም በአፋቸው እንደሸነገሉን ሳይሆን፣ በምናባቸው ትግራይ የምትባል ነፃ አገር ፈጥረው እየኖሩ እንዳሉ በግልጽ ማየት ይቻላል።
የሆነው ሆኖ ደብረ ጽዮን ምንም አሉ ምን የሚመሩት ፓርቲና መንግሥት ያኮረፈው ትግራይ ላይ የተለየ ጫና ስለደረሰ ሳይሆን፣ ሕወሓት እንደ በፊቱ ያሻውን የመዝረፍና የመግረፍ መብቱን ስላጣ እንደሆነ ሊክዱ አይችሉም። የትግራይ ሕዝብ ግን በእርግጥ የሕወሓትን የተገፊነትና የተጠቂነት ፕሮፓጋንዳ አምኖ ከወንድሞቹ ኢትዮጵያውያን መለየትን ይምረጥ አይምረጥ ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡