በገለታ ገብረ ወልድ
በየትኛውም ዓለም ቢሆን መሬት ወሳኝ የዜግነት ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን፣ የአገር ባለቤትነት መንፈስን የያዘ ሀብት ነው፡፡ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማርሽ መቀየሪያ መሣሪያም ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ፍትጊያ ውስጥም ቢሆን መሬት ዋነኛው መዘውር ሆኖ ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡ ከፊውዳሉ ሥርዓት ማኅበር አንስቶ አሁን እስከምንገኝበት የታሪክ ምዕራፍ ሥልጣንን መንጠልጠያ በማድረግ የመሬት ዘረፋና ወረራ፣ ብሎም ሽሚያና ወከባ እየጎለበት የሚታየውም ለዚሁ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን መሬትን በፍትሐዊነት ማግኘት ለየትኛውም ዜጋ በቀላሉ የሚቻል ያለመሆኑ ሚስጥርም ይኼው ነው፡፡
እንዲያውም በዚህ በኩል ሊታማ የማይችለው የደርግ ሥርዓት ነው ቢባል ሐሰት አይደለም፡፡ ደርግ ‹‹መሬት ላራሹ››፣ ‹‹ትርፍ ቤት ለጎጆ አልባው ከተሜ›› አለ እንጂ፣ እንዲህ እንደ አሁኑ ደሃው መኖሪያ ሳይሆን መቀበሪያ እየተቸገረ መሬት ሲቸበችብና ለአመራሮቹም ሲያቀራምት አልታየም፡፡ ቢኖርም በጣም ውስንና እዚህ ግባ በማይባል ደረጃ ነው፡፡ አሁን በአንድ በኩል ጉቦ እየተቀበለና እየተደራደረ በሕገወጥ መንገድ መሬት የሚሰጥ፣ የሚሸጥና የሚሸነሽን የቢሮክራሲ አካል አለ፡፡ በሌላ በኩል ሰነባብቶ ደግሞ መሬቱ ላይ ካረፈው ሀብት ጭምር ጠራርጎ የሚያፈርስና የሚያፈናቅል ኃይል አለ፡፡ ሁሉም ቢሆን ደግሞ የመንግሥት መዋቅሩ ላይ በተንጠለጠለው ኃይል የሚፈጸም ስለሆነ፣ በአጠቃላይ ፖለቲካው ላይ ያለው ተፅዕኖ እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡
በእርግጥ ከቅርብ ጊዜው ለውጥ ወዲህ በዘርፉ የተቀየረ ነገር ስለመኖሩ የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ ኢሕዴግ ‹‹መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው›› በሚል ሥሌት ሀብቱን የመጨምደድ ዝንባሌ ውስጥ እንደተዘፈቀ ነው፡፡ በዚህ መዘዝ ግለሰቦች እንኳንስ በቀላሉ የመሬት ባለቤት ሊሆኑ ይቅርና ከሕዝብ በላይ መሬትን ለመያዝ በክልሎች መካካል ያለው መፋጠጥም እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ በየአካባቢው ‹‹ክልል ልሁን››፣ ‹‹ልዩ ዞን›› ልመሥርት የሚሉ ጡዘቶች ሁሉ መነሻቸው መሬትን የመሰሉ የጋራ ሀብቶች ላይ አዛዥና ወሳኝ ለመሆን መፈለግ ነው፡፡
የተለያየ አመለካከት ያላቸው ቢሆንም ተቃዋሚዎች በበኩላቸው በተቀራራቢ ድምፀት መሬት የግለሰብ (የከተማ ነዋሪውና የአርሶ አደሩ) መሆን አለበት የሚል ሙግት ሲያቀርቡ ነው የቆዩት፡፡ የመሸጥ፣ የመለወጥ፣ የማከራየትና የማልማት ጉዳይ የገበሬው/ወይም የከተሜው ብቻ መሆን አለበት ሲሉም ሲያስረዱ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን ሕገወጥነት ከበዛና አሁን ያለው የደመ ነፍስ መሬት ወረራ አደብ እንዲይዝ ካልተደረገ፣ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የሚቻል አይሆንም፡፡ ለገዥው ፓርቲም ሆነ ለተቃዋሚው ወገን የመሬት ፖሊሲ አቅጣጫ ፍቱን መድኃኒቱ የሚሆነው፣ የሕግ የበላይነትና ሀብቱን ጠበቅ ባለ ቁጥጥርና ክትትል ለፍትሐዊ የሀብት ሥርጭት በሚረዳ መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል ሲቻል ነው፡፡
ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በአገራችን ከተሞች ያሳለፍነው ተጨባጭ ሁኔታ ግን፣ በመሬት ወረራ ረገድ የከፋ ሙስናና ዘረፋ ሲፈጸም እንደቆየ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን እስካሁንም ያልተወገደ ሥጋትም ነው፡፡ በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ መሀል ላይ የሚገኘው የኦሮሚያ ክልል በተለይ የከተማ መሬቶቹ እንደ ጉድ የተቸበቸቡበት፣ ትልልቅ የገንዘብ ዝውውሮች በመሬት ዙሪያ የሚፈጸሙበት፣ ለዋና ከተማዋ ቅርበት ባላቸው አነስተኛና መካከለኛ ከተሞችም ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመምጣት ዜጎች በብዛት የሠፈሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህ በመሆኑ ታዲያ በአቋራጭ የበለፀጉ የየከተሞቹ አመራሮችና የመሬት ደላሎች ቢኖሩም፣ መልሶ ሕገወጥነትን ለመታገል ሲታሰብም ተጎጂ የሆነው ደሃው ሕዝብ ነበር፣ አሁንም እሱው ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ የቅርብ ጊዜው የለገጣፎ ከተማ ‹‹ሕገወጥ ቤቶችን›› የማፍረስ ዕርምጃ በበታች አመራሩ ዕውቅና በፓርክ ቦታ ላይ ሳይቀር ተሸንሽኖ እንደ መሰጠቱ ሕዝብ ተፈናቅሎ ለድህነት ተጋለጠ እንጂ፣ በዚህ ጉዳይ የትኛው ሻጭና ዕውቅና ሰጪ አመራር ተወቀሰ ተብሎ ዘመቻው ውግዘት ወርዶበታል፡፡ እስከ ‹‹ዘር ማጥራት የሄደ መጥፎ ዕርምጃ›› የሚል የከፋ ፖለቲካም ተሠርቶበታል፡፡ ክፍተቱ ግን የቆየና የተንከባለለ ጭምር እንደነበር ሊካድ አይችልም፡፡
በእርግጥ መንግሥት በፌዴራልም ሆነ በክልሎች የቁጥጥር ሥርዓቱ ቢሳካለትም ባይሳካለትም፣ መሬትን በጋራ ሀብትነት ይዞ ሲያበቃ በሊዝ ጨረታ የማከፋፈል ሥራ ላይ ነው የቆየው፡፡ ለዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍልም በጋራ ኮንዶሚኒየምና በማኅበራት እያደራጀ የቤት መሥሪያ ቦታ የመስጠት ጥረት መጀማመሩ አይዘነጋም፡፡ ከሪል ስቴት ልማትም ሆነ ከግለሰቦች የዘመናዊ ቤቶች ግንባታ ጋር በተያያዘ በጊዜ ገደብ በሊዝ ኪራይ ወደ ማከፋፋል መግባቱም መልካም ዕርምጃ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ባለፉት አሥር ዓመታት በሪል ስቴት ስም ብቻ ስድስት ቢሊዮን ብር የሚገመት የከተማ መሬት መወረሩንና በፍጥነት አለመመለሱን የከንቲባው ጽሕፈት ቤት መረጃ ያሳያል፡፡
የማይታለፈው እውነት በአገሪቱ በአንድ በኩል የሕዝቡ ብዛትና ሀብት እያፈራ መምጣት መሬት የመያዝ ፍላጎቱን ከፍ አድርጎታል፡፡ በሌላ በኩል እንደ አገር ለመሬትና ቤት ባለቤትነት ያለን አተያይ የተለየ ሆኗል፡፡ ሕጋዊነትን ተከትሎ ከመግዛት ይልቅ በዘልማድ ከግለሰብ መሬት የመግዛቱ ዝንባሌም አልተሻሻለም፡፡ በዚህ ላይ መንግሥት በፍጥነትና በስፋት መሬት ለግንባታ እያቀረበ አይደለም፡፡ የሊዝ አሠራሩም ‹‹ወለም ዘለም›› የበዛበትና ግልጽነት የጎደለው ሲሆን መታየቱ አልቀረም፡፡ ምናልባት ይህ ክፍተት ቢታረም ችግሩ ሊቀረፍ ይችል ይሆናል፡፡ ሊዝ በአብዛኛው ከ25 እስከ 99 ዓመት ድረስ የሚቆይ የኪራይ ስምምነት ያለው በመሆኑ፣ ‹ዘለዓለማዊ የግል መሬቴ›› የሚል እሳቤን በማስወገድ ለትውልድ የማሰብ ምልክትን እንደ መያዙም ሊጠናከር የሚገባው ነው፡፡ ለመንግሥትም ሀብት ለማመንጨት ይረዳዋል፡፡
በመሠረቱ መሬት በሊዝ በመስጠት የእኛ መንግሥትና አገር የመጀመርያዎቹ ወይም ብቸኞቹ አይደሉም፡፡ ድፍን ዓለም የሚሠራበት ነው፡፡ የእኛ ዋነኛ ችግር ግን በምን ያህል ፍትሐዊነት ደረጃ ነው የሊዝ ሥርዓቱ እየተተገበረ ያለው? ወጣቱንስ በምን ሁኔታ ተደራሽ እያደረገ ነው? ብለን ስንጠይቅ ነው፡፡ መንግሥትስ ቢሆን ይህን ውስንና አላቂ ሀብት በምን ያህል የቁጥጥር ሥርዓት እየጠበቀው ይገኛል? ከዘረፋና የጥቂቶች መበልፀጊያነትስ እንዴት እየታደገው ነው? የሚል ትውልዳዊ ተጠየቅ ሲነሳም ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ሕገወጥ የመሬት ማስተላለፍ አካሄድ ተንሰራፍቶ ሕዝቡ በውድ ዋጋ እየተጭበረበረና በአሳሳች ደላላ እየተወናበደ በቤት ስም መሬት ከገዛ በኋላ ወደ ማፍረስ በመግባት፣ የሀብት ብክነት የመታየቱ ዝንባሌስ መቼ ሊስተካከል ነው ብሎ ሲፈተሽ ነው፡፡
እስካሁን ግን ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት መሬት የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነው በሚል የጋራ ሀብቱን በራሱ ጥበቃ ሥር ማድረጉ የጠቀመው አንድ ነገር እንዳለ መዘንጋት የለበትም፡፡ ይኼውም እንደ ልማታዊ መንግሥት በአገሪቱ በየትኛውም አቅጣጫ ለሚከናወኑ መሠረተ ልማቶች፣ የማኅበረ ኢኮኖሚ ዝርጋታዎች፣ ብሎም ለፖለቲካ መሣሪያነት የሚያገለግሉ ቦታዎችን በትንሽ ወጪና በቀላሉ ማስለቀቅ የሚችል አቅም መስጠቱ ነው፡፡ እርግጥ እዚህ ላይ ከየትኛውም የአፍሪካ አገሮችና ታዳጊው ዓለም በተሻለ ልማትን ለማፋጠንና ለማስፋት አግዞታል፡፡ ይሁንና እዚህም ላይ በተጀመረው መንገድ ያለመቀጠል ተግዳሮት አለ፡፡ በተለይ አሁን እየተከናወኑ ባሉት በትልልቅ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ላይ ለምሳሌ የዝዋይ ሐዋሳ ከፍተኛ የፍጥነት መንገድን ወሰን የማስከበር ፈተና፣ የአንዳንድ ሕገወጦች ማንአለብኝነት እየገደበው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ትናንትም ሆነ ዛሬ በመሬት አስተዳዳሩ ላይ መንግሥት የሚነሳበት ቅሬታ ግን ቸል የሚባል አይደለም፡፡ ይኼውም መሬት ለባለሀብትም ሆነ ለልማት በመሰጠቱ ነባር የከተማ ነዋሪውና ደሃው ገበሬ ያለ ምትክና በቂ ካሳ የሚነሳበት (የሚፈናቀልበት) ሁኔታ ተደጋግሞ መታየቱ ነው፡፡ እዚህ ላይ በልማት ተነሺ መኖር የለበትም የሚል አጉል ጥብቅና ለመቆም መሞከር ባይቻልም፣ ለልማት የተነሱት ሰዎች ግን ዜጋ እንደ መሆናቸው ምትክ ቦታም ሆነ ተመጣጣኝ ካሳ እንዲያገኙ የማድረግ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ እውነታ ነው፡፡ ሰሞኑን ከመገናኛ ብዙኃን መስማት እንደቻልነው ግን የአዲስ አበባ ከተማ በልማት አስነስቶ ምትክ ካርታና ቦታ ቢሰጣቸውም፣ ቦታው ቀድመው መሬት በወረሩ ሕገወጦች መያዙን ማየትና ‹‹ተነሺዎች መግቢያ መውጫ አጡ›› የሚል ዜና መስማት እጅግ የሚያሳፍርና የሚያሳዝን ችግር ነው፡፡
በመሠረቱ ልማት እየታየ ቢሆንም ካለፉት ዓመታት አንስቶ ‹‹የከተማው ነዋሪም ሆነ ገበሬው ይፈናቀላል፣ ወደ ሌላ ቦታ ይዛወራል፣ ይሰደዳል. . . ወዘተ.፡፡ በዚህም ለኢፍትሐዊነትና ለድህነት ይጋለጣል ‹‹የሚለው ሥጋት ተጨባጭ ነው፡፡ በተለይ በከተሞችና በዙሪያቸው ለነበረውና ላለው ችግር የበርካታ ቤተሰቦችን አብነት መጥቀስ አዳጋች አይሆንም፡፡ እዚህ ላይ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባ ነጥብ ግን አለ፡፡ መሬትን በሊዝ በሚያከራዩ በአብዛኞቹ አገሮች ለባለሀብት የሚሰጠው መሬት ቀድሞ ለተነሳው ማኅበረሰብ ተጠቃሚነትም ትኩረት እንዲሰጥ ማድረግ፣ በእኛ አገር ዕውን ያለ መሆኑ እውነታ ቀዳሚው ነው፡፡ ለተነሺ የሚሰጠው ካሳም ቢያንስ ነዋሪውን ቀደም ሲል ከሚኖረው ኑሮ ባነሰ ደረጃ ሊጥለው አይገባም ነበር፡፡ መሬቱ ለባለ ሀብቶች ሲሰጥም ሆነ ለአገርና የሕዝብ ልማት ሲውል ከአካባቢው የሚነሱ ሰዎች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ መቀየስና አገራዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ያስፈልጋል ብቻ ሳይሆን፣ ተግባሩም ትልቅ ፖለቲካዊ ትርጉም ሊሰጠው ግድ ይላል፡፡ እዚህ ላይ ሕዝብም ሆነ አመራሩ ግንዛቤ መጨበጥ ግድ ይላቸዋል፡፡
በመሠረቱ ለብሔራዊ ልማት ሲታሰብ ጥቂት ሰዎችን ከቦታ ቦታ ማዘዋወር ኃጥያትም ሆነ ወንጀል ሊሆን አይገባም፡፡ ሌላ ተለዋጭ ቦታ የመስጠቱ ጉዳይ ግን ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከዚህ በፊት ግን ተነሺዎችን ማሳመንና ለምን እንደሚነሱ ስለዓላማው በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ መሥራት መቅደም አለበት፡፡ በሚካሄደው የልማት ሥራ ውስጥ ዜጎች ተቀዳሚ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ዋስትና መስጠትና ለትውልዱ ማሰብም ያስፈልጋል፡፡ ለልማት ዓላማ ሲባል ሰዎች ከኖሩበት አካባቢ የሚነሱባቸው በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ የብዙኃኑን ድጋፍና አጋርነት እንዲያገኝ ብሎም ለልማት የተነሳ ዜጋ ጉዳት እንደማይደርስበት ዋስትና መስጠት ካልተቻለ ውጤታማ ለመሆን እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡
በመሠረቱ በመርህ ደረጃ ትናንትም ሆነ ዛሬ መሬትን ለተሻለ ልማት እንዲውል የማድረግ ጉዳይ አገርን ለማልማት ሲባል ዜጎች የሚከፍሉት ዋጋ እንደሆነ ዕሙን ነው፡፡ ቀድሞ ለሕዝቡ የማንቃት ሥራ ሳይሠራ ያለ የሌለ ጥሪቱን አባክኖ ከገዛው መሬት ላይ በኃይል ለማስነሳት መሞከር ግን ፖለቲካዊ አንድምታው ጎጂ ነው፡፡ ይልቁንም ዜጎች በሠፈሩበት አኳኋን ሕጋዊነትን እንዲላበሱና አስፈላጊውን ገንዘብ እንዲከፍሉ ማድረግ ይሻላል፡፡ ማንኛውም መንግሥት የራሱን ዜጎች ለመጉዳት ሲል የሚያደርገው የማፈናቀል ሴራ እንደሌለ ቢገመትም፣ በእኛ አገር ሁኔታ ግን የተካረረው ብሔርተኝነትና ለዘመናት የተሠራበት የጥላቻ ፖለቲካ ያለውን አንድምታ እየመረመሩ ካልተፈጸመ ትርምስ መጋበዙም አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ወደፊት ሕገወጦችም ሆኑ የልማት ተነሺዎች ቦታ መልቀቃቸው ግድ ቢሆንም፣ ሥጋቶችን መመርመር የመንግሥት ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡
በመሠረቱ ሕዝብ ከልማቱ ተጠቃሚ የሚሆነው የመሬትም ሆነ የሌሎች ተፈጥሮ ሀብቶች ትክክለኛ ባለቤትነቱና ዋስትናው ሲረጋጋጥ ነው፡፡ አገራችን ከተመፅዋችነት የምትላቀቀውና ጠንካራ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት መፍጠር የሚቻለውም ለእርሻ፣ ለኢንዱስትሪም ሆነ ለከተሜነት መስፋፋት ፍትሐዊና ሕጋዊ የመሬት አስተዳዳር ሲዘረጋ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ጥገኝነትና አድሎአዊነትን፣ ብሎም የመሬት ዘረፋና ወረራን ፊት ለፊት በቁርጠኝነት የሚታገል ሥርዓት ሲገነባ ብቻ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው በብርቱ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ታግዞ ነው፡፡
ከዚህ አንፃር ቅድሚያ ሕግና ሥርዓት ይከበር፣ የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ ነው እንጂ በደፈናው በምንም መንገድ ቢሆን ሕገወጥ ቤት ሊፈርስ አይገባም መባል የለበትም፡፡ አንዳንድ ጦማሪያንና የመብት ተሟጋቾችም (በርካሽ ተወዳጅነት ሒሳብ) ቢሆኑ ለሕዝብ በመቆርቆር ስም ሕገወጥነትን ወደ ማበረታታት እንዳይገቡ ነገሮችን በሚዛናዊነት መመልከት ይኖርባቸዋል፡፡ በሁሉም መስክ ሕጋዊነትን አስጠብቆ ሥራን መሥራት ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ መንግሥት ቀጠለም ተሰናበተም ሁሉም ዜጋ በመቼውም ጊዜ በፍትሐዊነት የሚጠቀምበት ሥርዓት ማበጀት ለማንም የሚበጅ ይሆናል፡፡
አንዳንድ የዘመናችን ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋች ተብዬዎች ነገሮች ወደ ራሳችን ሲመጡ፣ ሕገወጥም ቢሆኑ መብቴ ነው ማለት ነውርና ለማንም የማይጠቅም ነው፡፡ የትኛውም ዜጋ ቢሆን ሀብት፣ ሥልጣን፣ ጉልበት፣ ብሔር፣ ሃይማኖት ወይም ሌላ መሥፈርት ሳይለያየው በእኩል ሚዛን ካልተሰፈረ መንሻፈፍና መንሸራተት ማጋጠሙ አይቀሬ ነው፡፡ ሥርዓተ መንግሥቱም ለመድልኦና ኢሕጋዊነት፣ ብሎም በዘረፋና በማፍያ ቡድን ለመጠለፍ መጋለጡ ግድ ይሆናል፡፡ ስለዚህ መሬትን ወደ ሕጋዊነት ሥርዓት የማስመለስ ተግባር እንደ ቀላል ሊታይ የማይገባው ወሳኝ ተግባር መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ የሕዝብ ሥልጣን የተረከበ ኃይል ከባድ ኃላፊነትም ነው፡፡
አሁን እየተጀማመረ እንዳለው በአዲስ አበባም ሆነ በመላው አገሪቱ ማንም ይገንባቸው ማን፣ ሕገወጥ ቤቶችን አለማፍረስም ሆነ በማናለብኝነት በሕገወጥነት ማፍረስ ተገቢ አይሆንም፡፡ ጉዳዩን እንደ ዜጋ በዝምታ ማለፍም ነገ አገር ምድሩን በሕገወጥነት እንዲሞላ ማበረታታት ነው፡፡ የትም ሆነ መቼ መፍረስ ያለበት መፍረስና መነሳት እንዳለበት ጥርጥር የለውም፡፡ ትልቁ ጉዳይ ግን እነዚህን ሕገወጥ የመሬት ወረራዎችና ካርታ ሳይኖር ግንባታ የተካሄደባቸው ቤቶች እንዲህ እስኪሆኑ (አንዳንዶቹ ራሳቸውን የቻሉ ከተማ መስለዋልና! ያበረታታው፣ የፈቀደውና ዓይቶ ዝም ያለው የበላይም ሆነ የበታች አመራር ሁሉ ተጠያቂ እንዲሆን የማድረጉ ሥራ ቀድሞ መከናወን አለበት፡፡ ቁርጠኛ የፖለቲካ ውሳኔ የሚያስፈልገውም ሕገወጥነትን ከምንጩ ለማድረቅ የሚረዳ ሥርዓት መዘርጋት፣ የጋራ ትግልና ብልኃትን የተሞላበት ጥረት ማድረጉ ላይ ሊሆን ይገባል፡፡
አሁን በአገሪቱ ‹‹ለውጥ መጣ›› በተባለ ማግሥት እንኳን በበታች አመራሩ ዕውቅና ‹‹ምን ያህል የአዲስ አበባ መሬት በሕገወጦች ኪስ ተጠቅልሎ ገብቷል?›› ብሎ መፈተሸ ተገቢ ይሆናል፡፡ እንዲያው የተወሰኑ አብነቶችን ብንጠቃቅስ በከተማዋ የማስፋፊያ ክፍላተ ከተሞች (ቦሌ፣ ንፋስ ስልክ፣ ኮልፌና በተለይ የካ) ሰፋፊ የጋራ የአረንጎዴ ቦታዎችና መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ ሊያገኝ የሚገባባቸው የዋና መንገድ ዳርቻ መንገዶች፣ ለከፍተኛ ወረራና ለሕገወጥነት አደጋ መጋለጣቸውን ሕዝቡ በይፋም በጭምጭምታም እየተናገረ ነው፡፡ ይህን ደግሞ ባለተራ ነኝ የሚለው ጥገኛና የዘረፋው ተባባሪ አመራር በግልጽ የሚያውቁት ነው፡፡ ይህማ ባይሆን ካርታ ሳይዝና የግንባታ ፈቃድ ሳይኖር ሕንፃ እስከ መገንባት የሚደፍር አልነበረም፡፡ ሲኤምሲ፣ ባድመ ሠፈር፣ ጥቁር ዓባይ፣ ሀያትና ቦሌ ቡልቡላ የመሳሰሉትን የቦሌና የካ መንደሮች ያስተውሏል፡፡
በተለይ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 አነስተኛና የጭቃ ቤቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ ካርታ ሳይኖር በርካታ ቪላና ፎቅ ቤቶች እንዳሉ ይነገራል፡፡ በተመሳሳይ ቦሌ ክፍለ ከተማ ላይ በዶዘር እንኳን ለማፍረስ አስቸጋሪ የሆነ የኮንክሪት ግንባታ ተካሂዷል፡፡ የካ ወረዳ 12 ተመሳሳይ ችግር የሞላበት ነው፡፡ በተለይ ውሉ ያለየለት የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ልዩ ዞን ወሰን ጉዳይ ግልጽ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ፍፃሜ ሳይሰጠው ከጎሮ እስከ አዳማ የፍጥነት መንገድ መጀመርያ ድረስ ባለው 25 ኪሎ ሜትር ገደማ መሬት አጨናፍሮ መሬት ለመያዝ ከዚያም ከዚህም የመራኮቱ ነገር የሚያመጣው ጣጣ መክፋቱ አይቀሬ ነው፡፡ ያለያለት ዘረፋም እያንፀባረቀ ይገኛል፡፡
በአንዳንዱ አካባቢማ በሕገወጥ አመራሮችና ግለሰቦች ስም የተሰየሙ መንደሮች ሁሉ መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ለአብነት ያህል በየካ ወረዳ 13 እና የካ አባዶ ኮንዶሚኒየም ጀርባ በቀጣናው አመራር እስከ መሰየም የደረሰውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ ከአሥር ዓመታት በፊትም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በቀጣና አመራር ብቻ ሳይሆን፣ በወረዳና በክፍለ ከተማ አመራሮች እጅ አዙር አጋርነት በአሥር ሺዎች የተካሄደ ወረራ ስንቶችን በአቋራጭ አበልፅጎ ብዙዎችንም ለችግር አጋልጦ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ አሁን አዳዲስ ውስኪ አንቆርቋሪዎችና ጮማ ቆራጮች ብቻ ሳይሆኑ በቅንጦት የዜጋውን የኑሮ ውድነት የሚያባብሱ ጥገኞች የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ፣ የሕዝብ ቁጣ የሚያስነሱና ሥርዓቱን እንዲፈራርስ ሰበብ ሊሆኑ የሚችሉ እንደሆኑ መዘንጋት ተላላነት ነው፡፡
ትናንትም ሆነ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ሕገወጥና የጨረቃ ቤቶች ከሕጋዊና መደበኛ ቤቶች በላይ በሚባል ስፋትና ፍጥነት እንደሚገነቡ የሚታወቅ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በዋናነት የወረዳና የክፍለ ከተማ የመሬትና መሬት ነክ ዘርፍ ላይ ያለው አመራር በአንድም ሆነ በሌላ እጁ እንዳለበት የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ ሕገወጥ ግንባታን ማንሳትም ሆነ ወደ ሕጋዊነት ማስገባት ቀዳሚው ሥራም ቢሆን፣ አጥፊዎችን መጠየቅና ሥርዓት አልበኝነትን ማረም እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለለውጥ ኃይሉ የሚነገር ካለመሆኑም በላይ፣ የኢሕአዴግን ውድቀት ደጋግሞ ሲያስከትል የቆየና ማንም ሊዘነጋው የማይገባ እውነታ ነው፡፡
በአጠቃላይ ውድ የሆነውን የከተማ መሬት ከወረራና ከዘረፋ ለማትረፍም ሆነ ‹‹ባለተራ ነኝ›› ብሎ በማናለብኝነት ከሚጋፋው ሕገወጥ ለመታደግ፣ መንግሥት ታሪካዊ ኃላፊነት ወድቆበታል፡፡ ይህን ከባድ ሥራ ለመወጣት ደግሞ ሕዝቡ ከጎኑ ሆኖ ከመታገል ባሻገር፣ ከዚህ ቀደም በተፈጸመ ሕገወጥ ተግባር የተወረረን መሬት ለማስነሳትም ሆነ ወደ ሕጋዊነት እንዲገባ ለማድረግ የሚደረገውንም ጥረት ከግል ጥቅም ባለፈ ተባባሪ መሆን ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል፡፡ ሕገወጥነት የሞላበት ምድር ለማንም የማይበጅና እረፍት የሚነሳ ነውና፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡