Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉዝግመተ ለውጥና የኢትዮጵያ ውድቀት

ዝግመተ ለውጥና የኢትዮጵያ ውድቀት

ቀን:

በሽፈራው ሉሉና በእንግዳሸት ቡናሬ

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከ1953 ዓ.ም. የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አካባቢ ጀምሮ የወጣቶች የለውጥ እንቅስቀሴ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ በወጣቶች በአብዛኛው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ መሠረተ ሐሳቡ፣ ኢትዮጵያ የነበረችበት የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ዕድገት ካደጉት አገሮች ጋር ያለው ልዩነት በወጣቱ ዘንድ ቁጭት በመፍጠሩ፣ ኢትዮጵያን ከኋላቀርነት ለማላቀቅና ሌሎች ወደ ደረሱበት የዕድገት ጎዳና ለማስገባት የታሰበ ነበር፡፡ ሆኖም ይህንን ለማሳካት እንደ መፍትሔ የተወሰደው የካርል ማርክስና ፍሪድሪክ ኤንግልስ (Karl Marx and Fridrich Engels) የኮሙዩኒዝም ፍልስፍና ነበር፡፡ በወቅቱ የወጣቶች አዕምሮ በዚህ ፍልስፍና በመጠለፉ፣ ሌሎች አማራጮችን እንኳን ለመመርመርና ለመፈተሽ ፈቃደኝነቱ አልነበረም፡፡ ይህ ፍልስፍና መሠረቱና ከበስተጀርባው የያዘው ክፉ ሐሳብ መኖሩን ለመመርመርም ሆነ ለማሰብ አልተሞከረም፡፡ ችግር እንደሚያመጣና ከበስተጀርባው የክፋት ሐሳብ እንዳለ የተረዱ ጥቂቶች ባይታጡም፣ የፀረ አብዮተኛ ስም ተለጥፎባቸው ከመስመር ተወግደዋል፡፡ እንዲያው በደፈናው የእነ ማርክስ የኮሙዩኒዝም ፍልስፍና መፍትሔ ተደርጎ ተወሰደ፡፡ የብዙው ወጣት አዕምሮ ደነደነ፡፡ ከዚህ ውጪ የሚያስብ የአገር ጠላት ተደርጎ ተወሰደ፡፡ ምክንያቱም አገሪቱን እንደ ሚሳኤል አምዘግዝጎ ወደ ብልፅግና፣ ሁሉም እኩል የሆነበት ገነት የሚያደርስ መንገድ ተደርጎ ስለተወሰደ፡፡

የሚያማልለውን የእነ ማርክስ የኮሙዩኒዝም ፍልስፍና መፍትሔ አድርጎ የወሰደው የኢትዮጵያ ወጣት አገሪቱን ወደ ብልፅግና፣ ሁሉም እኩል የሆነበት ገነት የሚያደርስ መንገድ ያገኘ መሰለው፡፡ ሁሉም ማርክሲዝምን ዘመረ፣ ሰበከ፣ አስተማረ፣ ለመሞትም ተዘጋጀ፡፡ ‹‹ማን ይፈራል ሞት?›› ብሎ ዘመረ፡፡ የላብ አደሩን/ወዝ አደሩን አምባገነናዊ ሥርዓት ለመመሥረት ተዘጋጀ፡፡ ይህንን የላብ አደሩን/ወዝ አደሩን አምባገነናዊ ሥርዓት ለመመሥረት ሁሉም በየበኩሉ የላብ አደሩ/ወዝ አደሩ ወኪል ለመሆን ተነሳ፡፡ በመሆኑም ከኢድኅ (የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት) በስተቀር  ላብ አደሩን/ወዝ አደሩን እንወክላለን የሚሉ ብዙ ፓርቲዎችና በማርክስና በስታሊን የብሔር ሐሳብ ላይ የተመሠረቱ ተገንጣዮች ተፈለፈሉ፡፡

እነሱም የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ መላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)፣ የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል (ኢጭአት)፣ አብዮታዊ ሰደድ (ሰደድ)፣ ማርክሲሰት ሌኒኒስት ሪቮሉሽነሪ ድርጅት (ማሌሪድ)፣ አብዮታዊ ደርግ፣ የወዝ አደር ሊግ (ወዝ ሊግ)፣ የኢትየጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ኅብረት (ኢማሌድኅ)፣ የኢትየጵያ ሠራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሠፓአኮ)፣ የኢትየጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ)፣ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አወጪ ግንባር (ትነአግ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ ተጋድሎ ሐርነት ኤርትራ (ተሐኤ)፣ ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)፣ የምዕራብ ሶማሊያ ነፃ አውጪ ግንባር (ምሶነአግ)::

ሁሉም በየበኩሉ የላብ አደሩ/ወዝ አደሩ ተወካይ ነኝ፣ ከእኔ በቀር አብዮታዊና ማርክሲስት ላሳር ነው የሚሉ ነበሩ፡፡ ምክንያቱም በማርክሲዝም ፍልስፍና ኮሙዩኒዝም የሚመሠረተው በላብ አደሩ/ወዝ አደሩ አብዮትና አምባገነን መሪነት ነው፡፡ ላብ አደር/ወዝ አደር አንድ መደብ ነው፣ የሚመራውም የላብ አደር/ወዝ አደሩ ፓርቲ ብቻ ነው፡፡ ይህ የላብ አደሩ/ወዝ አዳር ፓርቲ ደግሞ አንድ ነው ብዙ ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ከላይ የዘረዘርናቸው ፓርቲዎች እያንዳንዳቸው የላብ አደሩ/ወዝ አደሩ ወኪል ነን በሚለው የእርስ በርስ የሥልጣን ትግል ውስጥ በመግባት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዘግናኝ የሆነ ዕልቂትና ሰቆቃ ተፈጸመ፣ ቁጥሩ በትክክል ባይታወቅም፡፡ የእርስ በርስ የሥልጣን ፍትጊያና እንዲሁም ማርክሲዝም/ሶሻል ዳርዊኒዝም ያመጣውን የብሔር  ፍልስፍና ይዘው በተነሱ መካካል በተደረገው መጨፋጨፍ፣ ብዙ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሰቃቂ ሁኔታ ለማለቅ ችሏል፣ አሁንም አላበቃም፡፡

የዲያቢሎስን ሐሳብ ይዘው የሚነሱ መጨረሻቸው ነፍሰ ገዳይነትና አጥፊነት ነው፡፡ ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ‹‹እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፡፡ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመርያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፡፡ እውነትም በእርሱ ስለሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፡፡ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና›› (የዮሐንስ ወንጌል ም. 8፣ ቁ፡ 44) የሚለው፡፡

ከዚህ የተነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ መስዋዕትነት በሕይወት መጥፋት ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚም በከፍተኛ ደረጃ አሽቆለቆለ፡፡ ኢትዮጵያ በሚያሳዝን ሁኔታ የድህነትና የረሃብ ምሳሌ አገር ልትሆን ቻለች፡፡

ይህ ብቻ አይደለም ማርክሲዝምና ዳርዊኒዝም ያደረሰው ውድቀት፡፡ ትልቁ ውድቀት በትወልዱ ላይ ከፍተኛ የግብረ ገብነትና የአስተሳሰብ ውድቀት አስከትሏል፡፡ በጥቂቱ ለመዘርዘር፣

ያለፈውን አባቶቹን የሚያወግዝ ትውልድ መበራከት፣ የአገሩን ታሪክ የሚጠላ ትውልድ መበራከት፣ ታሪክ እውነታ (Fact) መሆኑ ቀርቶ፣ ታሪክን የሚፈለስፉ ምሁራን መፈጠር፣ ለአባቶችና እናቶች በዕድሜ አንጋፋ ለሆኑ ክብር የሌለው ትውልድ መበራከት፣ አባቶችና እናቶች በዕድሜና በልምድ ያበረከቱትን ዕወቀት ለመስማትም ሆነ ምክር የማይፈልግ ትውልድ መበራከት፣ የአገር ፍቅር እየመነመነ መምጣት፣ የብሔር/ጎሳ አስተሳሳብ በሽታ እየጎለበተ መምጣት፣ የሰው አስተሳሳብ በሰውነቱ ሳይሆን በጎሳ አባልነቱ ብቻ በግል የማሰብና የማገናዘብ ነፃነቱ መጠለፍ፣ ብሔርተኝነት የግል ጥቅም ማግኛ ዓይነተኛ መሣሪያ መሆኑ ግንዛቤ በማግኘቱ፣ ለአገር ደንታ የሌላቸው፣ ኃላፊነት የጎደላቸው የብሔር ፖለቲከኞች መበራከት፣ የብሔር ፖለቲካ ተሟጋቾች (Activist) መበራከት፣ አንድ ጎሳ ሌላውን በጥላቻና በጥርጣሬ መመልከት፣ ሌብነት (ሙስና) አስነዋሪና አስፀያፊ ድርጊት መሆኑ ቀርቶ ቢዝነስ/ሥራ ተብሎ የተጠራበት ሁኔታ መፈጠር፣ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች የዕውቀት፣ የምርምርና የፈጠራ ማፍሪያ ቦታ መሆናቸው ቀርቶ የብሔርተኞች መፈልፈያ መሆናቸው፣  ሥልጣን በችሎታ፣ በዕውቀትና በብቃት መመዘን ቀርቶ በፖለቲካ/በጎሳ/በዘር የሚለካበት ሁኔታ መፈጠር፣ ዲግሪና ዲፕሎማ በገንዘብ የሚገዛበትና የፖለቲካ ስጦታ የሆነበት ክስተት መፈጠር፣ የሰውን ክቡር ሕይወት ከበሽታ ከመታደግ ይልቅ፣ ገንዘብን የሚያመልኩ የሕክምና ባለሙያዎች መበራከት፣ የማኅረሰብን ደኅንነት ከመጠበቅ ይልቅ፣ የሙያ ሥነ ምግባር የጎደላቸው/ያጡና ገንዘብን የሚያመልኩ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዎችና ባለሙያዎች መበራከት፣ ገንዘብ ከሰው ሕይወት በላይ ክብር ያገኘበት ሁኔታ መበራከት፣ የፍትሕ አካላት በፍርደ ገምድልነታቸው የሚሞገሡበት፣ ፍቅር የሌለው ጨካኝ በመግደልና በማሰቃየት የሚረካ ሰው መከሰት፣ ወዘተ ናቸው፡፡

ማርክሲዝም ለኢትዮጵያ ይጠቅማል? ወይስ ጉዳት ይኖረዋል? በማለት ማንም ሳያመዛዝን እንዲሁ በስሜት ወጣቱ ነጎደ፡፡ ይህም አስተሳሳብ በቀላሉ የማይነቀል የትውልድ ነቀርሳ ተክሎብናል፡፡ በደርግ ዘመን በአንድ ወቅት የተነገረ ቀልድ፣ ትውልዱ እንዴት በማርክሲዝም አስተሳሰብ ታውሮ እንደነበረ ሊያስረዳ ይችላል፡፡ ቀልዱ እንደሚከተለው ነው፡፡

በአንድ የአብዮት/የቀበሌ ስብሰባ ላይ ሐሳብና አስተያየት ይሰጣል፡፡ ታዲያ ሐሳብ ሰጪዎቹ በየተራ እየተነሱ፣ ‹‹ማርክስ እንዳለው …፣ ኤንግልስ እንዳለው…፣ ሌኒን እንዳለው …፣ ማኦ እንዳለው …፣ ቼጉቬራ እንዳለው…፣ ሆቺሚኒ እንዳለው…፣ እስታሊን እንዳለው…፣›› ወዘተ እያሉ አስተያየታቸውን፣ ሐሳባቸውንና ትንታኔ ይሰጣሉ፡፡ ታዲያ አንድ አዛውንት በተመስጦ ሲያዳምጡ ቆይተው፣ እኔም ሐሳብ አለኝ ብለው እጃቸውን አወጡና ተፈቀደላቸው፡፡ ከዚያም አዛውንቱ፣ ‹‹እንዲያው አቶ እንዳለው የተባሉት ሰውዬ ምንኛ የተባረኩ ናቸው፣ እነዚህን ሁሉ ልጆች መውለዳቸውና ለእኛ በመስጠታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፤›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተው ቁጭ ይላሉ፡፡ ታዲያ በአዳራሹ የነበረው ሰው ነገሩ ሳይገባው ይቀርና የአቶ እንዳለው ልጆች እነማን ናቸው ብሎ መጠያየቅ ይጀምራል፡፡ እያንዳንዱ ይኼ ሽማግሌ እስካሁን ስለአብዮቱና ስለእነዚህ ሰዎች ሳይገባው ቀርቶ ነው ብለው ይነጋገራሉ፡፡ አንዲት ወይዘሮ ነገሩ ገብቷቸው ኖሮ እጃቸውን አውጥተው ሐሳብ አለኝ አሉና ተፈቀደላቸው፡፡

‹‹እኔ ያለኝ ሐሳብ አሁን አዛውንቱ ባቀረቡት የምሥጋና ሐሳብ ላይ ነው፡፡ ብዙ ሰው የአቶ እንዳለው ልጆች እነማን ናቸው እያለ ግራ ገብቶታል፣ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ የአቶ እንዳለው ልጆች እኛ ነን፣ የራሳችን አስተሳሳብ የሌለን፣ የራሳችን ባህል የሌለን፣ የራሳችን የፈጠራ ችሎታ የሌለን፣ በራሳችን መቆም የማንችል፣ እከሌ እንዳለው እያልን በሰው አምሮ ወይም በሰው አስተሳሰብ ለመኖር የምንታትረው እኛ ነን የአቶ እንዳለው ልጆች፤›› በማለት አብራርተው ተቀመጡ ይባላል፡፡

ይህ ቀልድ ጥልቅ ሐሳብ የያዘ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ታሪክ፣ ዕውቀት፣ ችሎታ፣ አስተሳሰብ በመጣል አሁንም በእነ እከሌ አስተሳሰብ የምንመራ መሆናችንን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ፖለቲከኛው ማንም ሳይወክለው የአቶ እንዳለው ልጅ ለመሆን የእከሌ ጎሳ/ሕዝብ፣ ላብ አደር/ወዝ አደር ተወካይ ሆኖ ይቀርባል፡፡ ወክለኝ ያለው ሕዝብም ሆነ ጎሳ የለም፡፡ ሲጠየቅ የሚያቀርበው ኢትዮጵያዊ/አገራዊ የሆነ አስተሳሰብ የለውም፡፡ የሚያቀርበው መከራከሪያ እነ እከሌ እንዳሉት የሚል ነው፡፡ የአገሩን ታሪክ እነ እከሌ ባሉት መሠረት ለመተርጎምና ለመናገር/ለመጻፍ ይሞክራል፡፡ ለእሱ እነ እከሌ ያሉት ሁሉ ትክክል ነው፡፡ ምክንያቱም የማሰብ የመመርመርና የማገናዘብ ተሰጥኦውን ለእነ እከሌ አሳልፎ ስለሰጠው ነው፡፡ የዳርዊንና የማርክሳዊ አስተሳሰብን መመርያችን አድርገን ለመኖር ባደረግነው ጥረት የሰው ልጅ መሠረታዊ የሆኑ የግንዛቤ ማዳበሪያና መመራመሪያ መሣሪያ የሆኑ ጥያቄዎች ከትውልዱ ተነጠቁ፡፡ እነሱም ምን? ማን? መቼ? የት? ለምን? እንዴት? የመሳሰሉት ትውልድን ጠያቂና ተመራማሪ ሊያደርጉ የሚችሉ ከትምህርት ቤት ጠፉ፡፡ ሁሉም እንደ እነ አቶ እንዳለው ልጆች እንዲያስብ ተገደደ፡፡ አሁንም በትውልዱ የምንመለከተው ይኼንኑ ነው፡፡ አንድ ሰው ተነስቶ ከተናገረ ወይም ሐሳብ ካቀረበ የምንመዝነው ከየትኛው ቡድን (እከሌ) ውስጥ ነው በሚል ነው እንጂ ሐሳቡን በመመርመር፣ ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም በሚለው መመዘኛ አይደለም፡፡ የምንመራው በእነ እከሌ አዕምሮ እንጂ እግዚአብሔር በሰጠን የማሰብና የመመርመር ዘዴ አይደለም፡፡

አንድን አገር የሚገለው የገንዘብ ዕጦት አይደለም፣ ገንዘብና ንብረት በሥራና በፈጠራ የሚገኙ ናቸው፡፡ አንድን አገር የሚገለው የኮሌጆች ማነስ አይደለም፣ ኮሌጆችን ማብዛት ስለሚቻል፡፡ አንድን አገር የሚገለው የትምህርት ቤቶች ማነስ አይደለም፣ ትምህርት ቤቶችን ማብዛት ስለሚቻል፡፡ አንድን አገር የሚገለው የኢንዱስትሪ ወይም የእርሻ ማነስ አይደለም፣ ሁለቱንም ማብዛት ስለሚቻል፡፡ አንድን አገር የሚገለው የአዕምሮ ዝቅጠት ነው፡፡ አዕምሮ የላቀ ነገር ለመፍጠርና ለመመርመር የተሰጠ ነው፡፡ ይህንን አዕምሮ ለሌሎች አስተሳሰብ እስረኛ ካደረግነው ግን ሞታችንን መደገስ መጀመራችንን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ አንድ አገር የሚያስብና የሚመራመር ትውልድ ካጣች ሞቷን እያፋጠነች መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ዳርዊኒዝምና ማርክሲዝም ያበረከቱልን ትልቁ ነገር ውዱን አዕምሯችንን ለእነሱ ክፉ አስተሳሰብ እስረኛ እንዲሆን ማድረጋቸው ነው፡፡ እዚህ ላይ እነሱ አላስገደዱንም፣ እንዴት ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ትክክለኛ ጥያቄ ነው፣ እነሱ በአካል አላስገደዱንም፡፡ ነገር ግን የእነሱን ሐሳብ የማይፈጽም የድገት ፀር፣ የእኩልነት ፀር፣ ወይም የላብ አደሩ/ወዝ አደሩ ፀር መሆኑን አስረድተውናል፡፡ ስለዚህ የላብ አደሩ/የወዝ አደሩ ተወካይ ነኝ የሚል ሁሉ ሌሎችን ማስወገድ የግድ ነው፡፡ ካላስወገደ የላብ አደሩ/ወዝ አደሩ ተወካይ ሊሆን አይችልም፡፡

በዚህ ምክንያት ለአገር የሚያስቡ ሰዎች የተለያየ ቅፅል ስም እየተሰጣቸው ለአገሪቱ በዕውቀታቸውና በገንዘባቸው ማበርከት አልቻሉም፡፡ ከተሰጣቸው ቅፅል ስሞች በጥቂቱ ብንመለከት፡፡

አድኃሪ፣ ፊውዳል፣ ኢምፔሪያሊስት፣ ቀኝ መንገደኛ፣ ሐሳባዊ፣ በራዥ/ከላሽ፣ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ፣ ጠባብ፣ ትምክህተኛ፣ ፀረ አብዮት፣ ፀረ ሕዝብ፣ ትሮተስካይት፣ ማኦይስት፣ ወዘተ ናቸው፡፡

የሚገርመው በአገራችን የላብ አደሩ/ወዝ አደሩ ተወካይ ፓርቲ ነኝ በሚሉ መካካል በቃላት ልዩነት እንኳን ሰዎች ተጋድለዋል፡፡ ለምሳሌ ላብ አደሩ/ወዝ አደር እናቸንፋለን/እናሸንፋለን በሚሉ ቃላት፡፡ አሁን ላይ ሆኖ ለሚሰማ ተረት ሊመስል ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በትክክል የተፈጸመ ታሪክ ነው፡፡ እንግዲህ ሰው እግዚአብሔር ባርኮ በሰጠው አዕምሮ ማስብ ሲያቆምና እግዚአብሔርን በመካድ አዕምሮውን ለሌሎች  አስተሳሰብ አሳልፎ ሲሰጥ፣ ምን ዓይነት ክፉ ነገር ሊፈጽም እንደሚችል ለመገመት አያዳግትም፡፡

(ይቀጥላል)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዎቹን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ወይም [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...