Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትለሕገ መንግሥቱ መለወጥም ሆነ መዝለቅ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መከናወን የጋራ አደራ መሆን...

ለሕገ መንግሥቱ መለወጥም ሆነ መዝለቅ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መከናወን የጋራ አደራ መሆን አለበት

ቀን:

በገነት ዓለሙ

በአፍሪካ ኅብረት መሠረታዊ መቋቋሚያ ሰነድ መሠረት በአፍሪካ አገሮች ውስጥ ኢሕገ መንግሥታዊ የሆነ የመንግሥት ለውጥ ውግዝ ነው፣ ውድቅም ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ ሥልጣን ላይ የሚወጡ መንግሥታት በኅብረቱ ተግባራት ውስጥ መሳተፍ አይፈቀድላቸውም የሚል ከአባልነት የማገጃ ድንጋጌም አለው፡፡ ሱዳን የታገደችው በዚህ መሠረት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ እውነት መሆን ያለበት አገራችን የአፍሪካ ኅብረት አባል አገር፣ ለዚያውም መቀመጫ አገር በመሆኗ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህም በላይ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት በራሱ መሠረት፣ በሕገ መንግሥቱ ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኋን የመንግሥትን ሥልጣን መያዝ የተከለከለ (አንቀጽ 9/2/ በመሆኑ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሚከለከለው ከሕገ መንግሥቱ ውጪ የመንግሥትን ሥልጣን መያዝ ብቻ ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥቱ ከሚደነግገው ውጪ ሥልጣን ላይ መቆየትንም፣ ከሕገ መንግሥታዊው ሥነ ሥርዓት ውጪ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻልና መቀየርንም ጭምር ነው፡፡

እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት በኃይል የማፍረስ/የመናድ ክስ ማለት ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲና መንግሥት አንድ አካል፣ አንድ አምሳል ሆኖ ተቃዋሚዎችን፣ የተለየ ሐሳብ ያላቸው ሰዎችን የሚያሳድዱበት፣ የሚያሸማቅቁበት፣ እስር ቤት የሚወረውሩበት ሥልት የነበረ መሆኑ መንግሥት ራሱ በአደባባይ አምኖ የተቀበለውና ይቅርታም የጠየቀበት፣ ይቅርታና ምሕረትም ያደረገበት እውነታ ነው፡፡ ጨርሶ ውሸት ነው የሚሉ ለውጥ ተጠናዋቾች በራሱ በፓርቲ/በግንባሩ ውስጥ ቢኖሩም፡፡

ሕገ መንግሥቱ የሚለውን፣ አዲሱና የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የተካው የአፍሪካ ኅብረት የማቋቋሚያ ሰነድም (Constitutive Act) የሚሻውን ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል የከለከለው ደግሞ፣ ‹‹ሳትዋጋ ንገሥ ቢሉት ግድ ተዋግቼ›› ካለው ተቃዋሚ ይልቅ ራሱ መንግሥት ነበር፡፡ መንግሥት ከሕገወጡ ይበልጥ ሕጋዊውን መንገድ ተመራጭና ቀላል የሚያደርግ ፖለቲካና ባህል ማልማት ባለመቻሉ፣ ይልቁንም ይህ እንዳይሆን በመከልከሉና በመወንጀሉ፣ በሕጋዊነት መቀጠል፣ ወይም ወደ ሕጋዊነት መዞር እያለ የጫካን መንገድ በሚያመለክት ፕሮፓጋንዳና ድቆሳ እየቀሰቀሰና እያስገደደ፣ ተቃዋሚዎች ተማርረው ወደ ስደትና ወደ ጫካ ቢሄዱ እንደ ተገላገሏቸው መቁጠር የመንግሥት ‹‹ፖሊሲ›› መሆኑ፣ ወዘተ ነው፡፡

መንግሥትን በኃይል የመጣልና የመተካት ታሪክ መቆም አለበት መባሉ ትክክል ነው፣ ተገቢም ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በደንቡ፣ ኢትዮጵያም በሕገ መንግሥቷ ይህን ማለታቸው ጥሩ ጅምር ነው፡፡ ኢሕአዴም ሁሉም ነገር ከሆነ በኋላ 1983 ዓ.ም. ላይና በኋላም የነበረው ዕድል ካመለጠና ከባከነ በኋላም፣ እንኳን እኔ በገነባሁት ሥርዓት ውስጥ በምርጫ እንጂ በጉልበት ልትጥሉኝ አትሞክሩ፣ ያለውን ሕገ መንግሥትና የምርጫ ሥርዓት ሁሉም የእኔ ብሎ ይቀበለው ማለቱ በመሠረቱ መጥፎ መነሻ አልነበረም፡፡ ክፋት ያለው መንደርደሪያ አልነበረም፡፡

ኢሕአዴግ ይህን በሚልበት በደህናው ጊዜም ቢሆን የነበረው ችግር ግን፣ ሕገ መንግሥቱን የመቀበልና ያለ መቀበል ጉዳይ አልነበረም፡፡ ሕገ መንግሥቱን የተቀበለም ሆነ መለወጡን የሚፈልግ ሁሉ ፍላጎቱን ይዞ ለመታገልና ለመወዳደር ያስችለኛል ብሎ የሚያምንበት ዴሞክራሲዊ ሁኔታ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነበር፡፡ በተቃዋሚዎች በኩል ሊነገርና ሲባል የቆየውም ነፃ ምርጫ እየተካሄደ አይደለም፡፡ ምርጫ ቦርድ በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር በኢሕአዴግ ቁጥጥር ሥር ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲ ወገንተኛነት ነፃ ሆኖ እንደገና መደራጀት አለበት፣ የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም በገዥው ፓርቲ የተዋጠ ነው፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ዕጩ ተወዳዳሪዎች በደኅንነት ኃይሉ ጭምር እንግልት ይደርስባቸዋል፣ በአጠቃላይ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ተፈጻሚነትና ተግባራዊነት (ማለትም በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በተደነገገው መሠረት የመንግሥት ሥልጣን መያዝ) በጭራሽ የተዘጋ ነው የሚል ነበር፡፡

መውሰድ የነበረበትም ቀዳሚውና መሠረታዊው የመጀመርያ ዕርምጃ ከተቃዋሚዎች ጋር ተባብሮ ለስሞታው፣ ለቅሬታውና ለተቃውሞው ምንጭ የሆነውን ሁኔታ ማስተካከል ነበር፡፡ ይህ ከተሳካ ወደ ሕገወጥነት የሚዞር የለም፣ ጥይት ለመተኮስ ወደ ጫካ፣ ወደ በረሃ፣ ወደ ጎረቤት አገር የሚሄድ አይኖርም፣ ጥይት የሚተኩሱትም ወደ ሰላማዊው መድረክ ይሳባሉ፣ ወይም ይከስማሉ ማለት ለኢሕአዴግ የሚገባው ፖሊሲ አልሆን አለ፡፡ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥቱን የማክበር፣ በእንዲህ ዓይነት ማሻሻያ አማካይነት ተቃዋሚዎችንና ተቃውሞን የማመናመን ወይም ተባባሪዎቹ የማድረግ አስተዋይነት አልፈጥርብህ ብሎት፣ ለዚያውም አንዲት መቀመጫ እንኳን ለሌላ ፓርቲ/ግለሰብ አላስቀምስ ብሎ ሁሉንም 547 መቀመጫዎች ለብቻው ባግበሰበሰበት የ2007 ዓ.ም. ምርጫ ማግሥት (መስከረም 2008 አዲሱ ፓርላማ ተመርቆ ኅዳር ወር ላይ) የጫረውና ያቀጣጠለው እሳት ሊበላው ተነሳ፡፡

ዛሬም ውስብስብ የመንግሥት ግርሰሳ ውስጥ ሳንገባ የለውጥ ብርሃን በፈነጠቀበትና ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ጉዞ መልካም አያያዝ የሚያስጀምር ሁኔታ ውስጥ በምንገኝበት ወቅት፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ ‹‹የጋራ መግባባት›› የለንም፡፡ የጋራ መግባባት ማለት አሁንም፣ ዛሬም በደረስንበት የዕድገት ደረጃ ሕገ መንግሥቱን የመቀበልና ያለመቀበል ጉዳይ ሳይሆን ሕገ መንግሥቱን የተቀበለውም፣ ተቀብሎም አንዲት ነገር አይለወጥብኝ የሚለውም፣ የለም ሕገ መንግሥቱ መለወጥ አለበት ብሎ የሚያምነውም ፍላጎቱን የአገርና የሕዝብ ውሳኔ ማድረግ የሚያስችል የጨዋታ ሕግና የመጫወቻ ሜዳ መኖሩን ከሚያረጋግጥ ቅድመ ሁኔታ ብቻ በመነሳት ነው፡፡ የጋራ መግባቢያ መሆን ያለበት በዚህ ሕገ መንግሥት ውስጥ ሕዝብ (በፖለቲካ ፓርቲዎች አማካይነት) ፍላጎቱንና ምርጫውን፣ ብሶቱንና አማራጩን በይፋ ለመናገር፣ መብቱን ለማስከበር በደልን ለመጋተር የማይፈራበት፣ የእኔ የሚለው የነፃነት አየር ለመፍጠር፣ የአቋሞች ልዩ ልዩነትና ብዙነት፣ እንዲሁም ጥል የለሽ ነፃ ውድድር የሚኖርበት ድባብ ለማበጀት የዴሞክራሲ ሁኔታዎችን መገንባት ላይ መረባረብ ነው፡፡

አሁን በዚህ የለውጥ ወቅት ያለው ከአስቸጋሪ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ ያለ በፍጥጫ ዋልታ ላይ የቆመ የማይለወጥ አቋምና ድርቅና ነው፡፡ በአንድ በኩል ‹‹ለውጥ ማለት የኢሕአዴግ መፍረስ፣ የሕገ መንግሥቱ መለወጥ፣ የዘረኛ ፖሊሲ መጥፋትና ሕዝብ የተነጋገረበትና ባፀደቀው ሕገ መንግሥት ምርጫ ማካሄድ ነው›› የሚል ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ሙጥኝ ብለው የሚያራምዱት፣ ሲናገሩት፣ ሲያሰሙት፣ ከንግግርና ከውይይት በላይ ያደረጉት የሚመስል አቋም አለ፡፡ ይህ አቋም ወይም የአሁኑ ሕገ መንግሥት እያለ ምንም ዓይነት ለውጥ መጀመር አይቻልም ማለት፣ በአገር ውስጥም በቅንነት፣ በአባይነት፣ ዝም ብለው ሲሉ ሰምተውም የሚያነሱትና የሚወቅጡትም አሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ደሴ ውስጥ ባለፈው ሳምንት መልስ ከሰጡበት ጉዳዮች መካከል አንዱ ይህንኑ የሚመለከት ነው፡፡

በሌላ በኩል ሕገ መንግሥቱ መነካት የለበትም፣ ሕገ መንግሥቱ ተነካ ማለት የህልውና ጉዳይ ነው ብለው የሚከራከሩና ይህን መከራከሪያ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 105 (ሕገ መንግሥቱን ስለማሻሻል) እስከ መካድና መከልከል ድረስ የሚያከርሩ ተጠናዋቾችም አሉ፡፡ የእነዚህ አቋምና መከራከሪያ ሕገ መንግሥቱ እየተጣሰ ነው፣ እየተረገጠ ነው በሚል ክስና ፖለቲካም ይታጀባል፡፡

በአንድ የሆነ ቡድን፣ የፓርቲ መድረክና በአቋሙ፣ በመስመሩ፣ በፖሊሲው፣ በውሳኔው የመመራት ጉዳይ ከሌሎች ሐሳቦች ጋር በነፃ አደባባይ ወጥቶ፣ ተብላልቶ፣ ተሰልቆ፣ ውድድር ገጥሞ፣ ሐሳብን በሐሳብ አቋምን በአቋም የመርታትና ይህንንም በሕዝብ ነፃ ድምፅ የማረጋገጥ ነገር ከሆነ፣ ሕገ መንግሥቱን የመቀበልና ያለ መቀበል ውሳኔንም በዚሁ ሕገ መንግሥት ውስጥ ማሰናዳት ይቻላል፡፡ ከገዥው ፓርቲ ተፈልቅቆ የወጣው የዓብይ አህመድ የለውጥ ቡድንም እንረባረብ የሚለው ይህንን ማድረግ የሚያስችለውን ዴሞክራሲያዊ ሁኔታዎችን ማሰናዳትና ማደላደል ነው፡፡ ዛሬም እንደ ትናንትናው፣ አሁንም ልክ እንደ 1997 ዓ.ም. (በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት የመንግሥት ሥልጣን የመያዝ ድንጋጌ ከምር የተፈተነው በ1997 ምርጫ ነው) ያለውና መፈታት ያለበት ችግር ሕገ መንግሥቱን የመቀበልና ያለመቀበል ጉዳይ ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥቱን የተቀበለውም ሆነ መለወጡን የሚፈልገው ሁሉ ፍላጎቱን ይዞ ለመታገልና ለመወዳደር የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ የመኖርና ያለ መኖር፣ ይህን ለማደላደል የመፈለግና ለዚህ አለመተባበር ጉዳይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጮችን ፈትሾና አመዛዝኖ መወሰኑን ከተቀበልነውና ከወደድን፣ በውሳኔውም ለመገዛት ከፈለግንና ዝግጁ ከሆንን፣ በአንድ በኩል እንከን የለሽ ተብሎ፣ ይህን ጉዳይ ማንሳትማ ቅልበሳ ነው፣ ሕገ መንግሥቱን ማፍረስ ነው የሚል ‹‹አስፈራሪ›› ማገጃ እያቀረቡ፣ በሌላ በኩል ደግሞ መነሻችን ሁሉ የጥበብ መጀመርያችን ኢሕአዴግንና ሕገ መንግሥቱን ማፍረስ ነው እየተባለ ከውይይት ውጪ የሚደረግ ነገር መኖር የለበትም፡፡

በአገራችን ሁኔታ በተለይም በአሁኑ በለውጥ ዘመን በሕገ መንግሥቱ መተማመኛ የተሰጣቸው መብቶችና ነፃነቶች አይረገጡ፣ የተለመደው ዓይነት መንግሥታዊ ሕገወጥነትና አጥፊነት መከላከያና መቃኛ ይኑረው፣ ሲከሰትም ተጠያቂ ይሁን ከማለት የሚቀድምና የሚያዋጣ የትግል ዓይነት የለም፡፡       

የሕገ መንግሥቱ አስኳል ማለት ፌዴራላዊ ሪፐብሊካዊ የሕዝብ ሥልጣን ነው፡፡ ይህ በነፃ ዴሞክራሲያዊ ሒደት አንዴም ዕውን ሆኖ አያውቅም፡፡ የኖርንበት የሩብ ምዕት ዓመት አገዛዝ በፌዴራላዊነትና በዴሞክራሲያዊነት ቅርፅ የሚነግድ የሕወሓት/ኢሕአዴግ አምባገነንነት ነበር፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል ምክር ቤት ደረጃ ሕዝብን ይወክላሉ ተብለው ሲመረጡ የኖሩት ሰዎች የዚሁ አምባገነንነት አገልጋዮች ነበሩ፡፡ ሕገ መንግሥቱ፣ ፓርቲና መንግሥት ይቀላቀሉ፣ ፓርቲ የመንግሥት ሥራዎችን ከላይ እስከ ታች ይዋጥ አይልም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከፖለቲካዊ ወገናዊነት ገለልተኛ መሆን የሚገባቸውን ሁነኛ አውታራትና ገዥ ፓርቲ ያቦትልካቸው አይልም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ገዥነታችሁን የሚዳፈር ቅዋሜ ሲከሰት ረሽኑ፣ 20/30 ሺሕ ሰው እስር ቤት አጉሩ የሚል ሥልጣን ለገዥዎች አልሰጠም፡፡ ሕገ መንግሥቱ በተከሳሾች ላይ መንግሥት የሚዲያ ዘመቻ ያካሂድ፣ ግርፊያና ልዩ ልዩ ሥቃይ ያካሂድ አይልም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ገዥ ፓርቲ በመንግሥት ሀብት እንዳሻው ይጠቀም፣ ታላቅ መሪ ለሚለው ሰው በሕዝብ ሀብት ላይ መዋጮ/ዕርዳታ ብጤ አከል አድርጎ ፋውንዴሽን ያቋቁም አይልም፡፡ ስንቱ ይቆጠራል!! ኢሕገ መንግሥታዊ የሆነ ብዙ ነገር በኢትዮጵያ ምድር ኑሮ ሆኖ ኖሯል፡፡

ዛሬ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሆነን ለውጥ እናካሂድ ስንል ምስቅልቅል ውስጥ እንዳንዘፈቅ በ‹ሆድ ሲያውቅ…› ሕገ መንግሥታዊ ወግ ውስጥ ስለመኖራችን ራሳችንን እየሸነገልን፣ ወደ ሕገ መንግሥታዊ/ዴሞክራሲያዊ ኑሮ እናምራ ማለታችን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢሕአዴግንና ሕገ መንግሥቱን አስፈላጊ የሚያደርግ ዕዳ ስላለብንም ነው፡፡  ያልቦተለኩ አውታራት (መከላከያ፣ ፖሊስ፣ ደኅንነት፣ ፍትሕ፣ ምርጫ አስፈጻሚ፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ፣ ወዘተ) እንዲኖሩ ዛሬ የማሻሻያ ሥራዎች የሚካሄዱትም፣ ያለፈውን ሕገ መንግሥት የደፈጠጡ ብልሽቶችን ለማረምና የሕዝብ ልዕልናን የተቀዳጀ ፌዴራላዊነትን ለመቆናጠጥ ተብሎ ነው፡፡ ያለንበትን ምዕራፍ የሽግግር ጊዜ የምንለውም ሕገ መንግሥትን ካሰነካከለ አፈና ወደ ሕገ መንግሥታዊነትና ወደ ዴሞክራሲ የማለፍ ጉዞ ውስጥ ስለሆንን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ይህ የሽግግር ጊዜ ዴሞክራሲያዊነትና ኢዴሞክራሲያዊነት፣ ሕገ መንግሥታዊነትና ኢሕገ መንግሥታዊነት አንድ ላይ የሚገኙበት፣ አንድ ላይ ሊሠሩም የሚችሉበት ወቅት ነው፡፡ ወደ ዴሞክራሲና ወደ ሕገ መንግሥታዊ አኗኗር ለመሸጋገር ሲሞከር፣ ከሕገ መንግሥት አንቀጾች ይልቅ ፖለቲካዊ መፍትሔዎችን የሚሹ ብዙ ጣጣዎች የሚገጥሙንም ለዚሁ ነው፡፡ 

የወሰንና የማንነት ኮሚሽን መቋቋምም መታየት ያለበት ዛሬ የገጠሙንን ጣጣዎች ለመፍታት ባለው ጠቀሜታ እንጂ፣ ሳይሠራ የኖረ ሕገ መንግሥትን በማክበርና ባለማክበሩ መሆን የለበትም፡፡ ሕገ መንግሥታዊ አንቀጾች ላይ ድርቅ እንበል ቢባልማ ኖሮ ከክልል ክልል የሰው ልጆች (የትኛውንም ብሔረሰብ ባዳረሰ ደረጃ) የእንስሳትን ያህል ክብር አጥተው የጭካኔ ዓይነት ሲወርድባቸው፣ የክልል አስተዳደሮች ራሳቸው ግፍ አዳይ ሲሆኑ አንቀጽ 55(16)ን ተግባራዊ ወደ ማድረግ በተገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ከሽግግር ጋር የመጣው ቀውስ በብዙ ሥፍራ የተሳደደ ስለሆነና ባልተገነባና ባልተሠራበት መዋቅር ሁሉም ዘንድ ገብቶ ዕርማት ማካሄድ ስለማይቻል፣ አንጀት እያረረም ቢሆን ከሕጋዊ መፍትሔ ይልቅ ወደ ፖለቲካዊ መፍትሔ ማድላት ግድ ሆኗል፡፡ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የእስር ማዘዣ የቆረጠባቸው ግለሰቦች እንዳይያዙ የትግራይ ክልል መንግሥት በእብሪት ጋሬጣ ሲሆን፣ ሕገ መንግሥታዊ ትድድርን አደጋ ላይ በሚጥል አፈንጋጭነት የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 62(9)ን ተግባራዊ በማድረግ በኃይል መንገድ ያልተሄደውም፣ ያለንበት ሁኔታ ከሕገ መንግሥታዊ ዕርምጃ ይልቅ ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚሻ ስለሆነ ነው፡፡

ኢሕአዴግ በድኅረ ደርግ ኢትዮጵያ የማኅበራዊ አዕምሮ ሙሽት ላይ ርዕዮተ ዓለማዊ አሻራውን አሳርፏል፡፡ የአገሪቱን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መልክዓ ምድር ቀይሯል፡፡ የብሔረሰብ መብትን አነሰም በዛ የተመረኮዘ የአስተዳደር ይዞታ አሸናሽንን፣ የፓርቲ አደረጃጀትንና የሥልጣን አያያዝን ያመጣ ሕገ መንግሥት ተክሏል፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአገሪቱ የልማት ግስጋሴ ጀማሪም ሆኗል፡፡ ኢሕአዴግ በሥልጣን ዘመኑ ውስጥ ተቃውሞና ድጋፍ እንዳፈራ ሁሉ ሕገ መግሥቱም ደጋፊና ተቃዋሚ አፍርቷል፡፡ እንዲያውም የሕገ መንግሥቱን መዝለቅ የህልውናቸው ዋስትና አድርገው የሚያዩትንና ‹‹ሕገ መንግሥቱ ሊያሠራ ይችላል፣ ተግባራዊ የሚያደርገው ታጣ እንጂ›› የሚሉትን የኢሕአዴግ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች አንድ ላይ ወስደን፣ ‹‹ለሰላማችን ጠንቅ የሆነው ሕገ መንግሥቱ ነው›› ከሚሉት የተቃዋሚ ክንፎች ጋር ስናነፃፅር እነዚህኞቹ በቁጥር የሚያንሱ ናቸው፡፡ ወይም የሚያንሱ ይመስላሉ፡፡

ይህ ሁኔታ በራሱ ኢሕአዴግንና ሕገ መንግሥቱን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግንባታ ውስጥ ወደ ጎን የማይባሉ አስፈላጊ ሰበዞች ያደርጋቸዋል፡፡ በተጨማሪም የኢሕአዴግና የተቃዋሚዎቹ ዴሞክራሲን ተጋግዞ የመገንባት ዕድል ዕውን የመሆን ተስፋ የሚኖረው፣ ‹‹የሽግግር መንግሥት ይቋቋም›› በሚል ጥያቄ በኩል ሳይሆን፣ ያለውን ሕገ መንግሥት የጋራ መገናኛ በማድረግ በኩል እንደሆነም የሚያሳይ ነው፡፡ እናም በሽግግር መንግሥት ጥያቄ አማካይነት ካለው ሕገ መንግሥት ለማምለጥ መሞከር ለተከፋፈለ የፖለቲካ ንጠት በር መክፈት ነው፡፡ ለውጥ ማለት ዝም ብሎ የኢሕአዴግ መፍረስ፣ የሕገ መንግሥቱ ተሽቀንጥሮ መጣል የማይሆነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ኢሕዴግንና ሕገ መንግሥቱን አስፈላጊ የሚያደርጋቸው ሌላም ሰበዝ አለ፡፡  ኢሕአዴግ በሥልጣን አወጣጡና “በአዲስ” አገዛዝ ግንባታው የራሱን ሠራዊትና የፀጥታ ኃይል ከእነ ርዕዮተ ዓለሙ በዋናነት የተጠቀመ መሆኑ፣ አውታረ አገዛዙን ገለልተኛና ነፃነት የጎደለው መንታ ተፈጥሮ (ከውስጥ ባሻ/በጨነቀ ጊዜ አድራጊ ፈጣሪ ለመሆን የሚያስችል ኢሕአዴጋዊ ቡጥ፣ ከውጪ ደግሞ ‹‹የዴሞክራሲ›› ቅርፊት) እንዲኖረው አድርጓል፡፡ የዴሞክራሲ መብቶችን ተግባራዊ ሕይወት ከሲታ እንዲሆን ያደረገው፣ የኢሕአዴግንም በሥልጣን ላይ መቆየት በሕዝብ ድምፅ ብቻ የማይወሰን እንዲሆን ያደረገው፣ ይኸው የቡጥና የቅርፊት አለመጣጣም (የቡጡ ቅርፊቱን ለመጫን መቻሉ) ነው፡፡ ኢሕአዴግ በምርጫ ድምፅ ቢሸነፍና ሽንፈቱን ተቀብሎ ከሥልጣን ለመውረድ የተስማማበት ሁኔታ ቢከሰት እንኳ፣ ከአገዛዙ የሥልጣን ኃይል ውስጥ ዘራፍ ብሎ ወታደራዊ ግልበጣ የማድረግ ምናልባት ሁሉ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ማለትም እስከ ዓብይ ድረስ በዓብይም የለውጥ ዕርምጃዎች ውስጥ ሲያስፈራ፣ ሲያስደነግጥ የቆየ የአሁንም ገና መተማመኛ ያላገኘ ሥጋት ነው፡፡ በአገሪቱ የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ የኢሕዴግ ሰበዝ (ፋክተር) ለበጎም ለክፉም ውጤት መዋል ይችላል፣ እንዳያያዛችን፡፡

ሰላማዊ ዕድል እስካለ ድረስ የሚፈለገው ቡጡ ቅርፊቱን እየመሰለ እንዲመጣ፣ መልካዊውን “ዴሞክራሲ” ወደ ሥጋነት የሚቀይር ግንባታ እንዲካሄድ ነው፡፡ ለዚህ ተግባር የዴሞክራት ተቃዋሚዎቹን ያህል የኢሕአዴግ ዴሞክራቶች ሚና አስፈላጊ ነው፡፡ በምርጫ ጨዋታ ዴሞክራሲን የማደላደል ቀዳዳ ኢሕአዴግ አይሰጥም የሚል መከራከሪያ እንኳን ድሮም አይረታም፡፡ ከዚህ በፊት በ1997 ዓ.ም. ቀዳዳው ተገኝቶ ገና ምርጫ ከመካሄዱ በፊት፣ በተቃዋሚ በኩል የታየው ጅልና ጀብደኛ አቅራሪነት ሳይጀመር አበላሽቶታል፡፡

ዛሬ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሆነን መረማመድንና ለተሻለ ሥርዓት መታገልን ምርጫችን የምናደርገው፣ ያጋጠመንን የዴሞክራሲን ዕድል ላለማስቀጨትና ደም አፋሳሽ የእሳት መንገድን ለማምለጥ የሚያስፈልገን ግዴታ ክፍያ በመሆኑ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...