Thursday, November 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሚኒስቴሩ የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያግዙትን አንድ ሚሊዮን የውኃ ማከሚያ እንክብሎች ተረከበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከውጭ የሚመጣውን ውኃ ማከሚያ እዚህ ለማምረት ታስቧል

ከአየርላንድ የውኃ ማከሚያ እንክብሎችን በማስመጣት የሚያከፋፍለው ሲትረስ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኮሌራና የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) በሽታ ለመከላከል እንዲቻል፣ አኳ ታብስ የተሰኘውን አንድ ሚሊዮን የውኃ ማከሚያ ለውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስረከበ፡፡

የሲትረስ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ምናሴ ክፍሌ እንደገለጹት፣ ኩባንያው ባለፈው ዓመትም እንዳደረገው፣ ዘንድሮ የኮሌራና የአተት በሽታ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ንፁህ የመጠጥ ውኃ ለማቅረብ የሚያስችልና 20 ሚሊዮን ሊትር ውኃ ለማከም የሚያስችል የአንድ ሚሊዮን አኳ ታብስ እንክብል ድጋፍ አድርጓል፡፡

 በአሁኑ ወቅት በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌና በአዲስ አበባ የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱን መንግሥት አስታውቋል፡፡ በመሆኑም የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ማከሚያዎቹን በሽታው ለተከሰተባቸው አካባቢዎች እንዲያከፋፍል በማሰብ ኩባንያው ድጋፍ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ውኃና ኢነርጂ ሳምንት በተካሄደበት ወቅት ሰኔ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. የውኃ ማከሚያው እንክል ርክክብ ተፈጽሟል፡፡ በችርቻሮ ዋጋው 800 ሺሕ ብር የሚገመተውን ይህንን ልገሳ፣ በሚኒስቴሩ የመጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነጋሽ ዋጌሾ እንክብሎቹን ከአቶ ምናሴ ተረክበዋል፡፡

ባለፈው ዓመትም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል ተፈናቃዮች ጋር በተያያዘ ለተከሰተው የአተት ወረርሽኝ መከላከያነት እንዲውል የ1.5 ሚሊዮን የውኃ ማከሚያ አኳ ታብስ መለገሱን አቶ ምናሴ አስታውሰዋል፡፡ ይህም 30 ሚሊዮን ሊትር ውኃ ለማከም የሚያስችል ነው፡፡ አንድ የውኃ ማከሚያ አኳ ታብስ 20 ሊትር ውኃ ለማከም ያስችላል ያሉት አቶ ምናሴ፣ እንክብሉ በምንም አኳኋን መዋጥ እንደሌለበት፣ ሕፃናት በማይደርሱበት ቦታ መቀመጥ እንዳለበት፣ የሚታከመው ውኃም አኳ ታብስ ከተጨመረበት በኋላ እስከ ሦስት ደቂቃ በመጠበቅ ከዚያም መጠቀም እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡

ላለፉት 12 ዓመታት የውኃ ማከሚያውን እንክብል ሲያቀርብ የቆየው፣ ሲትረስ ኢንተርናሽናል ከአየርላንድ የሚያስመጣውን አኳ ታብስ በአገር ውስጥ ለማምረት የሚችልበትን ዕቅድ እንደወጠነ የገለጹት አቶ ምናሴ፣ ይህም በየጊዜው በውጭ ምንዛሪ ዕጦት ሳቢያ የሚፈጠረውን የአቅርቦት ችግር ከማቃለል ባሻገር በዋጋም ጭምር ተመጣጣኝ እንደሚያደርገው አብራርተዋል፡፡ ከአሥር ዓመታት በፊት 20 ሊትር የሚያጣራው አንድ እንክብል በ30 ሳንቲም ይሸጥ የነበረው የውኃ ማከሚያ በአሁኑ ወቅት በ80 ሳንቲም በችርቻሮ እንደሚሸጥ አስታውሰዋል፡፡

የውኃ ማከሚያው እንክብል በዓለም ጤና ድርጅት ፈቃድ ያለውና ከ30 ዓመታት በላይ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ወታደሮች ሲጠቀሙበት የቆየና በኢትዮጵያም የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሚገለገሉበት ስለመሆኑ አቶ ምናሴ አብራርተው፣ በቤት ውስጥ የውኃ ማከምና በንፅህና የማስቀመጥ ልማድ በየጊዜው ለውጥ እየታየበት ቢመጣም አሁንም በርካታ የግንዛቤ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ ጠቅሰዋል፡፡ ሲተርስ ኢንተርናሽናል ከሚያቀርበው አኳ ታብስ የውኃ ማከሚያ በተጨማሪ ሌሎች ድርጅቶች የሚያስመጧቸው ውኃ አጋር የተሰኘውና ሌሎችም እንክብሎች ለተጠቃሚው እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች