Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ የዕዳ ጫና እያየለ ቢመጣም ድጋፉን እንደማያቋርጥ አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዓለም ባንክና የልማት ብድር አቅራቢ ቅርንጫፍ የሆነው ዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር (አይዳ) ሰሞኑን በአዲስ አበባ ሲያካሂድ የቆየውን ጉባዔ ባጠናቀቀበት ወቅት፣ ማኅበሩ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ላለው ሪፎርም የሚሰጠውን ድጋፍ እንደማያቋርጥና ኢትዮጵያን ጨምሮ የአይዳን ድጋፍ የሚያገኙ አገሮች ያለባቸውን የውጭ ዕዳ ጫና በማያባብስ መንገድ ድጋፉን እንደሚያቀርብ ገለጸ፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2021 እስከ 2023 ላሉት የበጀት ዓመታት፣ ለአይዳ-19 የብድር ድጋፍ ማድረግ እንዲቻል ከማኅበሩ ደጓሚ አገሮች ሀብት ለማሰባሰብና በቀጣዩ የአይዳ-19 የብድር ፖሊሲ ዙሪያ ለመወያየት አዲስ አበባ የሰነበቱ ሲሆን፣ ደጓሚ አገሮቹ የአይዳ ተበዳሪ አገሮች የዕዳ ጫና እየበዛ በመምጣቱና ችግሩን በማያባብስ ሁኔታ እንዴት ብድር ሊቀርብላቸው እንደሚገባ ለሦስት ቀናት በሸራተን አዲስ ተወያይተዋል፡፡  

የዓለም ባንክ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክሪስታሊና ጂዎርጂዬቫ ከ200 በላይ ሀብታም ለጋሽ አገሮችን ወክለው በጉባዔው ከታደሙ ተሳታፊዎች ጋር መደራደራቸው ታውቋል፡፡ ይኼውም ባንኩ እ.ኤ.አ. ከ2021 እስከ 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ ለብድርና ለዕርዳታ ድጋፎች የሚያውለው የ80 ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ ሀብት ከለጋሾቹ አገሮች ለማግኘት በመወጠን የተደራደሩ ሲሆን፣ በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥም በብድር አሰጣጥ ፖሊሲው ላይ ስለሚከተሏቸው አሠራሮች ከሰኞ ሰኔ 17 ቀን እስከ ሰኔ 20 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተካሄደው ጉባዔ ወቅት እንደተወያዩ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ጉባዔው በሚካሄድበት ወቅት አባታቸውን በሞት ያጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ረቡዕ ሰኔ 19 ቀን በተፈጸመው የአባታቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ በተገኙ በማግሥቱ ከገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ዋና የንግድ ተደራዳሪና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ ጉዳዮች አማካሪ ከአቶ ማሞ ምኅረቱ ጋር በመሆን በጉባዔው መዝጊያ ዕለት ንግግር አድርገዋል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ለተመዘገበው ልማት የዓለም ልማት ማኅበር ዕገዛ ወሳኝ እንደሆነ አስታውሰው፣ የተቋሙ ድጋፍ በአገሪቱ ለሚታየው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ፋይዳው የጎላ እንደሆነም አውስተዋል፡፡ የልማት ማኅበሩ ድጋፍ ባይታከልበት ኖሮ ይህ ዓይነቱ ለውጥ ዕውን እንደማይሆን አስታውቀዋል፡፡

የልማት ማኅበሩ ለአገሮች መለወጥ የሚጫወተውን ሚና ኢትዮጵያን ዋቢ በማድረግ ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከዓለም ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋር በነበራቸው ውይይት ወቅትም በኢትዮጵያ ስለሚታዩት የብድር ጫናና የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ውስጥ እያደገ የመጣውን የብድር ዕዳ ጫና የመቆጣጠር ኃላፊነት በተበዳሪ አገሮች ላይ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ቢሉም፣ በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚታየውን ሰፊ የልማት ፋይናንስ ጉድለት ለመሸፈን እንደ ዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር ያሉ አስተማማኝና ተመጣጣኝ የልማት ገንዘብ ከለጋሾች ማግኘቱ የግድ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ‹‹አሁንም ተስፋችን በእናንተ ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ለተሳታፊዎቹ እንዳስታወቁት፣ በኢኮኖሚው መስክ እንደ ቴሌኮም፣ ኢነርጂ፣ ሎጂስቲክስና መሰል ወሳኝ ዘርፎች ለግሉ ዘርፍ ክፍት እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ በመንግሥት ይመራ የነበረውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ወደ ግሉ ዘርፍ ያዘመመና በርካታ የሥራ ዕድል ወደሚፈጥርበት አቅጣጫ ኢኮኖሚው እንዲያመራ የሚያደርግ የዕድገት ምዕራፍ መከተል እንዳስፈለገ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዝግ የነበሩ ዘርፎችን ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ክፍት የማድረጉ ሥራ ቅድሚያ የሚሰጠው የፖሊሲ ዕርምጃ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

‹‹የሪፎርም ዕርምጃዎቹ ሰፊና ጊዜ የሚጠይቁ እንደሆኑ እንገነዘባለን፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹ከፖለቲካ አኳያም ውስብስብና ትልቅ ዋጋ የሚያስከፍሉ ናቸው፤›› በማለት የተደቀኑባቸው ችግሮች ግዙፍ ስለመሆናቸው  አምነዋል፡፡ ይሁን እንጂ ‹‹ዛሬ ባያዋጡም ለነገ ይከፍላሉ፤›› በማለት አክለዋል፡፡

የዓለም ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጂዎርጂዬቭ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ የሚካሄዱት የሪፎርም እንቅስቃሴዎች ለኢኮኖሚው ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው፣ የታሰቡት የሪፎርም ዕርምጃዎች ስፋት አስገራሚ እንደሆኑም በተለይ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ወቅት ገልጸዋል፡፡ የቴሌኮም፣ የኢነርጂና የሎጀስቲክስ ዘርፎች ወደ ግል እንዲዛወሩ መደረጋቸው፣ የአገልግሎት ዋጋቸው እንዲቀንስና ጥራታቸው እንዲሻሻል በማገዝ ሕዝቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉት አስታውቀዋል፡፡

የዓለም አቀፉ የመልሶ ግንባታና የልማት ባንክ እየተባለ የሚጠራው ሌላኛው የዓለም ባንክ አበዳሪ ተቋም መካከለኛ ገቢ ላላቸው፣ ብድር ቢሰጣቸው በብቃት እንደሚመልሱ ለሚታመንባቸው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ከገበያ ዋጋ ባነሰ ተመን ያቀርባል፡፡ በአንፃሩ የዓለም የልማት ማኅበር ግን ያለ ምንም ወለድ አሊያም እጅግ ዝቅተኛ በሚባል የወለድ ተመን ለደሃ አገሮች የሚያቀርበው ብድር በየጊዜው በለጋሽ አገሮች እንዲተካ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ለደሃ አገሮች የሚሰጠውን ብድር ከመተካት ባሻገር፣ በሚያበድርበት የፖሊሲ ማዕቀፍ ላይም ክርክር የሚደረግ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከ68 ተበዳሪ አገሮች ውስጥ 34ቱ እያደገ በሚገኝ የውጭ ብድር ጫና ውስጥ መገኘታቸውም ክርክር ከሚደረግባቸው አጀንዳዎች መካከል ይመደባል፡፡ ይሁን እንጂ ተበዳሪ አገሮች ከፍተኛ ወለድ ወደሚታሰብባቸው የአጭር ጊዜ ብድሮች መሄዳቸውም ሌላው መነጋገሪያ እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አስታውሰዋል፡፡

ከልማት ማኅበሩ የሚበደሩ አገሮች የዕዳ ጫና እያደገ መምጣት የአጭር ጊዜ ብድሮችን እንዲቆሙ እያስገደዳቸው መምጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ቢናገሩም፣ በአንፃሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ግን ኢትዮጵያ እንዲህ ያለውን ብድር መገደቧ ትክክለኛ ዕርምጃ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

የዓለም ባንክ የዚህ ዓመት ዓለም አቀፍ የብድር ስታቲስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው፣ እ.ኤ.አ. ከ2017 ወዲህ የኢትዮጵያ ውዝፍ የብድር ዕዳ 26.56 ቢሊዮን ዶላር አስመዝግቧል፡፡ ከዚህ ውስጥ የዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር ድርሻ 7.039 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎም እ.ኤ.አ. በ2017 ብቻ ኢትዮጵያ ለዕዳ ክፍያ ያዋለችው 1.38 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ሲገለጽ፣ ከዚህ ውስጥ ዋናው ብድር 946.1 ሚሊዮን ዶላር እንደነበርና ተከፋይ ወለዱም 442 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ መረጃው ያሳያል፡፡

ኢትዮጵያ ያለባት የውጭ ብድር ዕዳ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድርባት ደረጃ ላይ ከመድረሱም ባሻገር፣ ከወጪ ንግድ አንፃር ሲታይም የ397.6 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ ይህም ሆኖ 81 በመቶው ብድር የረጅም ጊዜና ዝቅተኛ ወለድ የሚታሰበብ መሆኑ አወንታዊ ጎኑ ሲሆን፣ አይዳ የሚሰጠው ብድር በአማካይ የ23.9 ዓመታት ቆይታና የ2.2 በመቶ ወለድ የሚታሰብበት መሆኑ የተቋሙ የብድር አቅርት ተፈላጊነቱን ያመላክታሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች