የአማራ ክልል ልዩ የፖሊስ ኃይል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞን ጨምሮ፣ አራት የክልሉ አመራሮች መታሰራቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ አበረ አዳሙ ለአማራ ክልል መገናኛ ብዙኃን ድርጅት እንደገለጹት፣ የልዩ ኃይሉ ዋና አዛዥ ጨምሮ ሌሎች በስም ያልተገለጹ ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች ታስረው በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ እየተደረገባቸው ነው፡፡
አመራሮቹ በክልሉ ፕሬዚዳንት አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) እና በሕዝብ አደረጃጀት አማካሪያቸው እዘዝ ዋሴ፣ እንዲሁም በክልሉ ዋና ዓቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ ላይ ከተፈጸመው ግድያ ጋር ግንኙነት ይኑራቸው ወይም አይኑራቸው የሚለውን ለማጣራት መታሰራቸውን ኮሚሽነር አበረ አስታውቀዋል፡፡
ኮሚሽነሩ እንዳሉት በግድያና በተቀነባበረው ሴራ በመሳተፍ ከተጠረጠሩ 190 የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት መካከል፣ ከ170 በላይ የሚሆኑት በፈቃደኝነት እጃቸውን ሰጥተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ በሰጡት ማሳሰቢያ በቅርቡ የተመለመሉ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላትም ሆኑ ነባሮቹ፣ ዋና ኃላፊነታቸው የክልሉን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ እንደሆነና ከግለሰቦች አምላኪነት መውጣት አለባቸው ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ሕዝብም የልዩ ኃይሉ የፖሊስ አባላትን በእኩል ዓይን እንዲመለከት አሳስበዋል፡፡
ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ በባህር ዳር ከተማ በርዕሰ መስተዳድሩ ቢሮ ላይ በተሰነዘረ ጥቃት አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) እና የአደረጃጀት አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴ ሲገደሉ፣ የክልሉ ዓቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ በደረሰባቸው ከፍተኛ ጉዳት ሕክምና ሲከታተሉ ቆይተው ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡
የሦስቱም የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሥርዓተ ቀብር በባህር ዳር ከተማ ዓባይ ማዶ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ረቡዕ ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደሚፈጸም፣ የክልሉ መንግሥት አስታውቋል፡፡