Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየሶማሊያን ምርጫ ደኅነንት የማረጋገጥ ጅማሮ

የሶማሊያን ምርጫ ደኅነንት የማረጋገጥ ጅማሮ

ቀን:

ሶማሊያ ከዚህ ቀደም በተለየ መልኩ እ.ኤ.አ. በ2020/21 የምታደርገውን ምርጫ የተሳካ ለማድረግ ከወዲሁ ለምርጫ አስፈጻሚዎቹ ሥልጠና መስጠት ጀምራለች፡፡

ሰላሟን በእርስ በርስ ጦርነት ካጣች ሦስት አሠርታት ያስቆጠረችውና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተነፃፃሪ ሰላም ያገኘችው ሶማሊያ፣ በተለያዩ ጊዜያት በአጥፍቶ ጠፊዎች በሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎቿን ብታጣም፣ የአገሪቱን ሰላም ለማረጋጥና ምርጫ ለማካሄድ ከወሰነች  ሰንብታለች፡፡

በሶማሊያ ከዓመት በኋላ የሚካሄደው ምርጫ ሰላማዊ መሆን ለሶማሊያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ብሎም ለመላው አፍሪካ ደኅንነት ወሳኝ ነው ያለው የአፍሪካ ኅብረትም፣ የሶማሊያን ውሳኔ ይሁን ብሎ ምርጫው የተሳካ እንዲሆን ቅድመ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት አጋርነቱን መግለጽ ጀምሯል፡፡

በሶማሊያ ሙሉ ለሙሉ የተረጋገጠ ሰላም ባለመኖሩ የሚካሄደውን ምርጫ ሰላማዊና ደኅንነቱ የተጠበቀ ማድረግ ቀዳሚው ሥራ በመሆኑ፣ ምርጫውን ይመሩታል ለተባሉ ሶማሊያውያን፣ በአገሪቱ ደኅንነቱ የተረጋገጠ ምርጫ ይካሄድ ዘንድ መከተል ስለሚገቡዋቸው መርሆዎች፤ በሶማሊያ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ሚሽን (አሚሶም) የአራት ቀናት ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡

በኡጋንዳ ካምፓላ በተዘጋጀው የአራት ቀናት ሥልጠና፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የምርጫ አስፈጻሚ አካላት በምርጫ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶችን እንዴት መፍታት እንዳለባቸው፣ በምርጫ ዕቅድና አስተዳደር ዙሪያ ሥልጠናውን መውሰዳቸውን ዘስታንዳርድ ዘግቧል፡፡

አሳታፊ፣ ሰላማዊና ተዓማኒ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ስትራቴጂ መንደፍም የሥልጠናው አካል ነበር፡፡

 በርካታ  አካላት የሚሳተፉበትና ሥራቸውን በኃላፊነትና በታማኝነት እንዲወጡ የሚጠበቅበት ምርጫ፣ በተለይ ሰላማቸው ባልተረጋጋ አገሮች ውስጥ የምርጫ ውጤት የማያባራ ቀውስ እንዳያስከትል ቀድሞ መጠንቀቁ አስፈላጊ ከመሆኑ ጎን ለጎን ዜጎች፣ የመምረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙበት ማነቃቃቱ ወሳኝ ነው፡፡

የሕዝቡን ግንዛቤ ማነቃቃትና ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ጭምር ትኩረት የሰጠው ሥልጠና፣ አገሪቱ ከዚህ ቀደም ትከተል የነበረውን ምርጫን በጎሳ ሥርዓት የማካሄድ አሠራር ወደ ሁሉን አቀፍ ማለትም ዕድሜው ለምርጫ የደረሰ ሁሉ ጾታንና ጎሳን ሳይለይ እያንዳንዱ ሰው ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በምርጫ እንዲሳተፍ በሚያስችለው የምርጫ ሥርዓት ዙሪያም አጽንኦት ተሰጥቷል፡፡

አሚሶም በሶማሊያ ለሚገኙ የምርጫ አስፈጻሚ አካላትና ለሶማሊያ ገለልተኛ  ምርጫ ኮሚሽን (ኤንአይኢሲ) የአቅም ግንባታና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡

ሶማሊያ እ.ኤ.አ. ከ1969 ወዲህ ጎሳን መሠረት ያደረገ የምርጫ ሥርዓት ስትከተል የከረመች ሲሆን፣ በ2020/21 ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ምርጫ የሚከተለው ሥርዓት ‹‹ዩኒቨርሳል አዳልት ሰፈሬጅ›› ላይ አፍሪካ ኅብረት ሥልጠና ሲሰጥ ይህ አራተኛው ነው፡፡

ለምርጫው ቅድመ ዝግጅት ማድረጉ እንዳለ ሆኖ፣ በምርጫው ወቅት አገሪቱ ሰላሟ የተረጋገጠ እንዲሆን ማድረግ ሌላው ሥራና ሥጋትም ነው፡፡

ባልታሰበ ሁኔታ በተለያዩ ጊዜያት ብቅ እያሉ የባለሥልጣናትንም ሆነ ምንም የማያውቁ ንፁኃን ዜጎችን፣ ሴት፣ ወንድ፣ ሕፃንና አዛውንት ሳይሉ በጠመዱት ወይም በተጠመደባቸው ቦምብ ሕይወት ከንብረት የሚያወድሙ የሶማሊያ ልጆች፣ ምርጫውን እንዳያደናቅፉ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት እንደሚገባም የሥልጠናው ተሳታፊዎች ማውሳታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል፡፡

የኤንአይኢሲ ሰብሳቢ ሐሊማ ኢስማኤል ኢብራሂም፣ የደኅንነት ጉዳይ በሶማሊያ ሁሉን አሳታፊ የሆነውን የምርጫ ሥርዓት ለማስፈጸም ቀዳሚናው ወሳኝ ሥራ ነው ብለዋል፡፡

ሚስ ኢብራሂም እንደሚሉት፣ ኮሚሽኑ የመራጭ ምዝገባ ማዕከላትን ዓይቶ ያረጋገጠ ሲሆን፣ የአገሪቱ ደኅንነት አካላት የምርጫ ቦታዎችን ደኅንነት የማረጋገጥ ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል ብለዋል፡፡ ያለ ደኅንነት አካላት ተሳትፎ ምርጫን ማናወን እንደማይቻልም አክለዋል፡፡

በአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች ኮሚሽን ኃላፊ ጉይ ሲሪል ታፖኮ፣ የሶማሊያ ስኬት የአፍሪካ ስኬት እንደሆነ በመግለጽ፣ የሶማሊያ ሰላም መሆንና ሰላማዊ ምርጫ ማካሄድ የኅብረቱ አባል አገሮች በ2063 በአኅጉሪቱ አሳታፊ የሆነ ዕድገት ለማስመዝገብ የተቀመጠውን አጀንዳ ለመፈጸም ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የሶማሊያ ሰላም መሆንና ሰላማዊ ምርጫ ማከናወን ለአፍሪካ ቀንድ አገሮችም ሆነ ለአኅጉሪቱ አንድ ውጤት ነው፡፡ ሶማሊያ እርስ በርስ ጦርነት ከገባች ወዲህ ኬንያና ኢትዮጵያም የችግሩ ሰለባ ሆነው ነበር፡፡ በተለይ ኬንያ በሶማሊያ ሰላም ለማስፈን በነበራት አስተዋጽኦ በተለያዩ ጊዜያት የቦምብ ጥቃት ሰለባ ሆናለች፡፡

በናይሮቢ፣ ሞምባሳና ጋሪሳ ላይ ከዓመታት በፊት በተፈጸሙ የቦምብ ጥቃቶች በርካቶች ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን ያጡ ሲሆን፣ ለዚህም አልሸባብ ኃላፊነቱን ወስዶ ነበር፡፡ ከጥቃቱ ባለፈ ኬንያ የሶማሊያ ስደተኞችን ተቀብላም ታስተናግዳለች፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ኢትዮጵያ ድንበሯና ሰላሟን ለማስከበር ሶማሊያ ድረስ ዘልቃ ወታደራዊ ዕርምጃ ብትወስድም፣ የሶማሊያን ስደተኞች ተቀብላ በማስተናገድም ትታወቃለች፡፡ ከዚህ ባለፈም በሶማሊያ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ሁሉ ተለይታ አታውቅም፡፡

በተለይ ጎረቤት አገሮች ላይ አሉታዊ ጫና የፈጠረው የሶማሊያ ሰላም ዕጦት፣ በምርጫው እልባት እንዲያገኝና ሶማሊያውያን ሳይሳቀቁ በአገራቸው ሊኖሩ የሚችሉበትን ድባብ ለመፍጠር የአፍሪካ ኅብረት እንደሚሠራም አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...