Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአዲሱ የጥናት መዘክር

አዲሱ የጥናት መዘክር

ቀን:

‹‹ቅዱሱ መንበር (ቫቲካን) ዋናውን ወራሪ አላስጠነቀቁም (አልመከሩም) ወይም አላወገዙትም ወይም ተጠቂውን አካል አላጽናኑም፡፡ የዓለም አቀፍ ሕግንና የተደረገውንም የማስታረቅ ጥረት አልደገፉም፡፡ ፖፕ ፒዮስ 11ኛ ከእርሳቸው በፊት እንደነበሩት እንደ ፖፕ በኔዳክት 15ኛ የሥነ ምግባሩና የሕግ መሠረቱ ከክርስቲያን ሃይማኖት ጋር ተመሳሳይ የሆነውን የመንግሥታቱን ማኅበር ጥረት ፈጽሞ አልደገፉም ወይም አላበረታቱም፡፡››

 እ.ኤ.አ. በ1967 ባየር የተባለው ሊቅ ነበር የቫቲካንን አቋም በመተቸት ይህን ሐረገ ሐሳብ የጻፈው፡፡ ፋሺስት ጣሊያን በ1928 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላይ ወረራ አካሄዳ ለአምስት ዓመት የዘለቀ ጦርነትን ተከትሎ ባየር ያንፀባረቀውን ሐሳብ የገለጹት ቀሲስ ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል (ዶ/ር) ‹‹በኢትዮጵያ ላይ የፋሺስት ጣሊያን ወረራና የፖፕ ፒዮስ 11ኛ አቋም›› በሚል ባቀረቡት ጥናት ነው፡፡

ይህንና ስድስት በአማርኛና እንግሊዝኛ የተጻፉ ጥናቶች የተካተቱበት መድበል በቅርቡ የኅትመት ብርሃን አይቷል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት መጽሔት “Journal of Ethiopian Church Studies” በሚል መጠርያ የሚታወቀው መድበል በቅፅ አምስት ያሳተመው የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል ነው፡፡

 ቀሲስ ምክረ ሥላሴ በጥናታቸው እንዳመለከቱት የጣሊያን ጦር በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመውን ወረራ ርዕሰ ጉዳያቸው ያደረጉ በርካታ ጥናቶች፣ ወዘተ ተደርገዋል፡፡ ጥናቶቹ በጊዜው የነበረውን የኃይል አሠላለፍ የኢትዮጵያውያን አርበኞችን ተጋድሎ፣ የጣሊያን ቅኝ ገዥ ጦር በኢትጵያውያን ላይ የፈጸመውን ግፍ፣ ወዘተ ዘግበዋል፡፡ ይሁን እንጂ የጣሊያን ወራሪ ጦር በኢትዮጵያ ላይ በከፈተው ጥቃት የሮሙ ፖፕ ፒዮስ 11ኛ አቋምን በተመለከተ የተዘገበው ትክክለኛውን የታሪክ ሁኔታ አያስረዳም፡፡ ከሁሉም በላይ አጥኚው ‹‹የመንበረ ቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን መሪ ፒዮስ 11ኛ ኢትዮጵያ በፋሺስት መንግሥት በተጠቃችበት ዘመን የሙሶሎኒ ተባባሪ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ቅዱስ ፓፓው ለኢትዮጵያ አዛኝና የተለየ አስተያየት የነበራቸው መንፈሳዊ አባት ነበሩ፤›› በማለት የተዘገበው የመረጃ ክፍተትና የመረጃ አተረጓጎም ክፍተት እንዳለበት እንገነዘባለን፡፡ ክፍተቱም ይህን ጥናት ለማቅረብ ምክንያት ሆኗል ይላሉ፡፡

የአጥኚው ዓብይ ዓላማ ከ1928 ዓ.ም. እስከ 1933 ዓ.ም. ጣሊያን ኢትዮጵያን ወርራ በቆየችበት ጊዜ ስለፈጸማቸው የግፍ ተግባሮች የፓፕ ፒዮስ 11ኛ አቋም ምን እንደነበር መመርመር ነው ይላል፡፡

በማሳያነት ከተዘረዘሩት የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡፡ አንደኛ ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በግፍ ስትወር ቫቲካን በፓፑ አማካይነት ሚስጥራዊ የሆነ የሞራል ድጋፍ ለጣሊያን መስጠቷን፣ ሁለተኛ የጣሊያን ወታደሮች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በተለይ በየካቲት 12 እና 13 ቀናት፣ 1929 ዓ.ም. እጅግ የሚያሰቅቅ የጭካኔ ጭፍጨፋ በማድረጋቸው ዓለም ሁሉ ሲጮህ ቫቲካን ምንም ድምፅ አለማሰማቷን፣ ሦስተኛ የፋሺስቱ ጣሊያን ወታደሮች የመርዝ ጋዝ እየረጩ ድልን ባገኙ ጊዜ ፖፑ ይህን ድል የሚያስደስት ድል ብለው ማወደሳቸውን፣ አራተኛ የፋሺስቱ ጭፍሮች ከ200 የሚበልጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማትን ሲያቃጥሉ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ መነኮሳትንና ካህናትን፣ እንዲሁም ጳጳሳትን በግፍ ሲገድሉ ቫቲካን ዝም ብላ መመልከቷ ያስረዳሉ፡፡

በጥናቱም፣ የፋሺስቱ ጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት የሮሙ ፖፕ ፒየስ 11ኛ ትክክለኛ አቋም ምን እንደነበር በማስረዳት በዚህ በኩል የነበረውን የታሪክ ክፍተት ይሞላል፡፡ በተጨማሪም በወረራ ወቅት ስለተፈጸመው የግፍ ተግባርና ስለተዘረፈው በርካታ የአገር ቅርስ ዛሬ ምን ማድረግ እንደሚገባ ለሚመለከታቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ ያሳስባል፡፡

በአማርኛ ከተዘጋጁት አራት የጥናት ወረቀቶች ውስጥ ሁለተኛው በደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ከቃል ኪዳን፣ ፈውስ፣ ስያሜና ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር በተያያዘ የሚነገሩ ታሪኮችን መፈክር፣ እንዲሁም የተረኮቹን ፋይዳ የሚተነትን ነው፡፡ ሦስተኛው የጥናት ጽሑፍ በተመረጡ አብያተ ክርስቲያናትና፣ ገደማት መዘክሮች (ሙዚየሞች) ተግዳሮቶችን በመግለጽና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም ሊወሰድ የሚገባውን የመፍትሔ ሐሳቦች ይዘረዝራል፡፡ አራተኛው ደግሞ ከፍልፍል ድንጋይ ከተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱና አዲስ ከሆነው የመቄት ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊና ሥነ ኪናዊ ሁኔታን በመረጃ በማስደገፍ ትንታኔ ይሰጣል፡፡

በዚሁ አምስተኛ ቅፅ በእንግሊዝኛ ከተዘጋጁት ሁለት የጥናት ጽሑፎች መካከል አንደኛው ጥልቅ ትዕምርታዊ ትንተና ምርምር ዘዴን በመጠቀም ከ200 በላይ የሚሆኑ የድኅነት ማግኛና የልመና ማቅረቢያ ትዕምርቶች ተጣምረው የሚገኙባቸውን የኢትዮጵያ ልዩ ልዩ መስቀሎች ሁናቴ በስፋት ይመረምራል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ትምህርት ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው የዜማ ትምህርቶች መካከል አንዱ ስለሆነው መጽሐፈ መዋስዕት ይዘት ትንታኔ ከመስጠት ጀምሮ ሊቃውንቱ መዋስዕትን እንዴት እንደሚማሩትና እንደሚያስተምሩት ከጀማሪ ደቀ መዝሙር እስከ አድራሽ (ዕጩ መምህር) የትምህርት አሰጣጥ ሥልቱን ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም መጽሐፈ መዋስዕትና ሌሎች የዜማ ድርሰቶችን ስለደረሰው ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፣ ጻድቁ አባ አረጋዊና ንጉሥ ገብረ መስቀል፣ እንዲሁም ስለታላቋ ገዳም ዙር አምባ አረጋዊ ጽርሐ ዓርያም በስፋት እንደተተረከ አዲሱ የጥናት መድበል ኅትመት ያሳያል፡፡         

ማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማዕከል አቋቁሞ የቀደምት ሊቃውን የቤተ ክርስቲያናትን አስተዋጽኦ ቀጣይ እንዲሆን ለማስቻል ለዘመኑ ትውልድ የጥበብ አሻራቸውን ለማስተዋወቅ፣ እንዲሁም ዘመናዊ ምሁራን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በጥናትና ምርምር በመታገዝ የበለጠ እንዲጠናከር በማድረግ ረገድ ባደረገው ያላሳለሰ ጥረት ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ አራት ደረጃቸውን የጠበቁ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ለኅትመት እንዲበቁ ማድረጉን የጥናት መጽሔቱ ተወስቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...