Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ትንንሽ ከተሞች የ50 ዓመትና ከዚያም በላይ የሚተነብይ ማስተር ፕላን ሊኖራቸው ይገባል››

አቶ አማረ ተስፋው፣ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር  

ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባዔውን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለ18ኛ ጊዜ አዘጋጅቷል፡፡ በመቻሬ ሜዳ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኮርፖሬት ማዕከል በተካሄደው በዚሁ ጉባዔ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው፣ በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጠኑ 20 ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ በቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎችም ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተካሄዷል፡፡ ከጽሑፎቹም መካከል ‹‹የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አካባቢያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖዎች ምን ይመስላሉ?›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ ይህንን ጽሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲ ዕጩና በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር አቶ አማረ ተስፋው ናቸው፡፡ በጽሑፋቸው ዙሪያ አቶ አማረን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የጥናትዎ ጭብጥ ምንድነው?

አቶ አማረ፡- በአሁኑ ሰዓት አገራችን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ላይ ትገኛለች፡፡ ይህም ትራንስፎርሜሽን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ እየተሸጋገርን ነው፡፡ በተለይም ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በአገር ውስጥና በውጭ ባለሀብቶች ወደ አገራችን እየገቡ ነው፡፡ እነዚህ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በአገራችን ላይ ምን እያመጡ ነው? የሚለው መጤን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ አንድ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ለአገር ዕድገትና ለማኅበረሰቡ ብልፅግና የጎላ ጥቅምና ሚና እንዳለው አይካድም፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም አካባቢያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖዎች ላይ ያተኮሩ ችግሮች አሉባቸው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ችግሮቹ የሚቀነሱበት የተለያዩ አካሄዶች መኖራቸውም ሊታወቅ ይገባል፡፡ ችግሮቹን ለመቀነስ ምን ዓይነት ስትራቴጂ መከተል ያስፈልጋል የሚለውን ጥናቱ ያሳያል፡፡  

ሪፖርተር፡- ጥናቱን ያደረጉት በምን አካባቢ ነው?

አቶ አማረ፡-  ጥናቱ ያተኮረው በአዲስ አበባ ከሚገኙ ፋብሪካዎች መካከል በናሙናነት በተመረጠው ጀሞ አካባቢ በሚገኘው አንድ የመስተዋት ፋብሪካ ላይ ነው፡፡ በዚህም ጥናት የፋብሪካው ጭስ በማኅበረሰቡ ላይ ያስከተለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ተዕኖውንም ለመለየት የተቻለው ‹‹ሔዶኒክ ፕራይሲንግ አፕሮች›› (Hedonic Pricing Approach) በተባለ ሳይንሳዊ ትንታኔ ወይም የአንድን ሀብት ገበያ ዋጋ የሚሰጥበትን ቴክኒክ በመከተል ነው፡፡ ይህንን ሳይንሳዊ ትንታኔ መሠረት አድርጎ በተካሄደው ጥናት የተለያዩ ጉዳዮችን ለማየት ተሞክሯል፡፡ ለምሳሌ በፋብሪካው አቅራቢያና ራቅ ባሉ ሥፍራዎች ለሚገኙ ማኅበረሰቦች የሚኖሩበትን ቤት ኪራይ ዋጋ በተመለከተ ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል፡፡ በሰጡት ምላሽም ፋብሪካው አጠገብ ወይም በአቅራቢው የሚገኙ ቤቶች ኪራይ አነስተኛ ቢያንስ ከፋብሪካው ከ250 ሜትር በላይ ርቀት የሚገኙ ቤቶች ኪራያቸው ውድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከፋብሪካው ከሚወጣው ጪስ ለመሸሽ ሲሉ አብዛኛዎቹም የሚኖሩት ከፋብሪካው ራቅ ባለ ሥፍራ በሚገኙ መኖሪያ ቤቶች ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ከፋብሪካው የሚወጣው ጪስ ያስከተለውን ችግር ቢያብራሩልን?  

አቶ አማረ፡- ቃለ መጠይቅ ያደረኩላቸው ማኅበረሰቦች እንደነግሩኝ ከፋብሪካው የሚወጣው ጪስ በተለይ ነፋስ ባለበት ቀን አካባቢውን የመሸፈን ባህሪ አለው፡፡ ይህም ሁኔታ በፋብሪካው ዙሪያ ወይም አቅራቢያ በሚኖሩ ማኅበረሰቦች ላይ ማሳልና የመሳሰሉ ችግሮች አስከትሏል፡፡   

ሪፖርተር፡- እነዚህ የጤና ችግሮች በክሊኒካል ላቦራቶሪ ታይተው ወይም ተመርምረው ተረጋግጠዋል?

አቶ አማረ፡-  በእርግጥ እነዚህ የጤና ችግሮች ጭሱ ባስከተለው ተፅዕኖ የመጡ ናቸው ወይ? የሚለውን የሚመለስ የላብራቶሪ ጥናት አላደረኩም፡፡ ነገር ግን ዓለም አቀፋዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ከመስተዋት ፋብሪካ የሚወጣ ጪስ ‹‹ሲሊካን ዳይኦክሳድ›› የተባለውን ጋዝ ይለቃል፡፡ ይህም ጋዝ በሰዎች ላይ የተለያዩ የጤና ችግሮች ያስከትላል፡፡ በተለያዩ ዓለም ከተሠሩ ጥናቶች ለመገንዘብ እንደተቻለው የደረት ኤክስሬይ ምርመራ የሚካሄደው ደረታችን ላይ ምን አለ? የሚለውን ለማወቅ ወይም ለመለየት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ከፍተኛ በሲሊካንዳይኦክሳይድ ጥርቅም የተበከለ ሰው ፖዚቲቭ ኤክስሬይ ደረቱ ላይ ያሳያል፡፡

ሪፖርተር፡- የመስታወት ፋብሪካ በተጠቀሰው አካባቢ የተቋቋመው አካባቢው ከማኅበረሰቦች መኖሪያ የፀዳ ወይም ማኅበረሰቦቹ የማይኖሩበት አካባቢ መሆኑን ከተረጋገጠ በኋላ ይመስለኛል፡፡ የፋብሪካው ጭስ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑ እየታወቀ አካባቢው ለመኖሪያነት እንዴት ሊፈቀድ እንደቻለ ቢያብራሩልን?

አቶ አማረ፡- የአሁኑ የልማት ዕቅድ እያንዳንዱ ፋብሪካ ኅብረተሰቡ ከሚኖርበት ቦታ ርቆ መተከል እንዳለበት ነው የሚያመላክተው፡፡ ለዚህም ነው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ያሉት የኢንዱስትሪ መንደሮች ራቅ ካለ ሥፍራ እንዲቋቋሙ የተደረጉት፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል ይህ ዓይነቱ አሠራር አልነበረም፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚቀርበው አዲስ አበባ እንደዚህ ትለጠጣለች ብሎ የገመተ አካል አልነበረም፡፡ ከዛሬ 10፣ 20 እና 30 ዓመት በፊት ለተተከሉት ፕሮጀክቶች አዲስ አበባ የቆዳ ስፋቷ እስከ ምን ይደርሳል የሚል የትምበያ ፕላን አልነበረም ማለት ነው፡፡ በዚህም ቀደም ሲል የተቋቋሙትን ፋብሪካዎች ከተማዋ እየተለጠጠች አልፋቸው ሄዳለች፡፡ ለወደፊት የምንመክረው በተለይ በየክልሉ ገና በማቆጥቆጥ ላይ ያሉ ትንንሽ ከተሞች፣ ወይም የከተማ አስተዳደሮች አጠቃላይ የሆነ የወደፊቱን 50 ዓመትና ከዚያም በላይ የሚተነብይ ማስተር ፕላን ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከተማው እስከ ምን ድረስ መሄድ አለበት? የኢንዱስትሪ ከተሞችስ የት ላይ መቋቋም አለባቸው? ወዘተ የሚሉትን መሠረታዊ ጉዳዮች የያዘ ማስተር ፕላን ካለ እንዲህ ዓይነት ችግር አይደርስም፡፡   

ሪፖርተር፡- አንድ ፋብሪካ ሲቋቋም ከማኅበረሰቡ መኖሪያ፣ ከመብራት ተሸካሚ ምሰሶዎችና ከውኃ ግድብ፣ ወዘተ ምን ያህል ርቀት መኖር እንዳለበት የሚገልጽ ስታንዳርድ አለ?

አቶ አማረ፡- በሌሎች አገሮች ኢንዱስትሪዎች ወይም ልማት፣ ወይም የኢንቨስትመንት ቦታዎች ከከተማው ምን ያህል መራቅ እንዳለባቸው በትክክል የሚያስረዳ ዲማርኬሽን ፕላን አለ፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ግን እስካሁን ባደረግነው ዳሰሳ መሠረት አንድ የኢንዱስትሪ መንደር ከሰዎች መኖሪያ ምን ያህል ይርቃል? ወይም ምን ያህል ርቀት ላይ መመሥረት አለበት የሚለውን እስካሁን አላየንም፡፡ በአንፃሩ ግን በእኛ አገር አንድ የተለየ የልማት ፕሮጀክት ከጥብቅ ቦታዎች (የሃይማኖት፣ ዘላቂ ማረፊያ ወይም የመካነ መቃብር ቦታዎች፣ ወዘተ) 500 ሜትር ርቀው እንዲቋቋሙ የሚጠይቅ አሠራር አለ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ከገደል፣ ከሚናዱና ከአስፈሪ ቦታዎች 200 ሜትርና ከመብራት ተሸካሚ ምሰሶ 50 ሜትር መራቅ አለበት፡፡ ግን አንድ የኢንዱስትሪ መንደር ከከተማው ወይም ማኅበረሰቡ ከመኖርበት መንደር ምን ያህል መራቅ አለበት የሚል በግልጽ የተቀመጠ ስታንዳርድ በአገራችን የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ጥናትዎን ሲሠሩ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትን አነጋግረዋል?

አቶ አማረ፡- ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሰነዶችን ወስጄያለሁ፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰነዶችን ለመጠቀም ሞክሬያለሁ፡፡ ግልጽ የሆነ ዲማርኬሽን የሚያሳይ ወይም የፋብሪካው ቦታዎች ከሰዎች መኖሪያ ምን ያህል መራቅ አለባቸው የሚለውን ማግኘት ግን አልቻልኩም፡፡ የቤቶችን ዋጋ በተመለከተ ግን በከተማ አስተዳደር ወይም ከሚዩኒሲፓሊቲ ምንም ዓይነት በሰነድ የተያዙ የቤቶች ዋጋ ባይኖርም የባለሙያዎቹን ሐሳብ ለመጋራት ሞክሬለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ለጥናቱ መስታወት ፋብሪካውን ለምን መረጡ?

አቶ አማረ፡- በመጀመርያ ለጥናቴ የመረጥኩት መንገድ ‹‹ሄደኒክ ፕራይሲንግ አፕሮች›› የተባለውን የኢኮኖሚክስ አናሊሲስን ነው፡፡ ይህን መሰል አፕሮች የተከተለ ጥናት ለማካሄድ ከሚቻልባቸው መንገዶች መካከል አንዱ የኒፎርም ወይም ወጥ የሆነ የቤቶች የኪራይ ዋጋ መኖር ይገኝበታል፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ሲታይ ደግሞ ወጥ የሆነና በሰነድ ተይዞ የተቀመጠ የቤቶች ኪራይ ዋጋ አይገኝም፡፡ ይህ በራሱ አንድ ችግር ነው፡፡ ሁለተኛው ችግር ደግሞ ፋብሪካዎች አንድ ቦታ ላይ አለመገኘታቸው ነው፡፡ አንዱ ፋብሪካ ቄራ አካባቢ ከተቋቋመ ሌላው ፋብሪካ ደግሞ ጀሞ አካባቢ ሊሆን ይችላል፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ግን አዲስ አበባ ውስጥ ፋብሪካዎቹ የተቋቋመት በአንድ ቦታ ሳይሆን ተራርቀው ነው፡፡ ስለሆነም ተራርቀው የተቋቋሙትን ፋብሪካዎች አንድ ዓይነት ባህሪ ስላላቸው ጀሞ አካባቢ የተቋቋመ የመስታወት ፋብሪካ ሌሎቹንም ሊወክል ይችላል ከሚል ሐሳብ በመነሳት ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...

በርካታ ሐኪሞችን የሚፈልገው የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና

በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ ባለፉት አሠርታት የተሠሩ ሥራዎች ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ሆኖም በጨቅላ ሕፃናት ሕክምና ዘርፍ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው ቢሻልም፣ የጨቅላ ሕፃናት...