Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየሰሞኑ የገበያዎቻችን ውጥንቅጥና የልጠት ጽንሰ ሐሳብ

የሰሞኑ የገበያዎቻችን ውጥንቅጥና የልጠት ጽንሰ ሐሳብ

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

ሰሞኑን በገበያዎቻችን ውስጥ ባጋጠሙ የዋጋ ውድነቶች ያልተገረመ ሰው የለም፡፡ ፓርላማው የፕላን ኮሚሽኑን መንስዔውን አጥንቶ እንዲያቀርብ አዟል፡፡ ብዙ ሰዎች የዋጋዎች መወደድ ምክንያት የፍላጎት መጨመርና የአቅርቦት ማነስ ነው ይላሉ፡፡ ይህን የሚሉ ሰዎች ግን ፍላጎትም አቅርቦትም ምን እንደሆኑ አያውቁም፡፡ ጥቅል ፍላጎትና ጥቅል አቅርቦት እኩል መሆናቸውን የብሔራዊ ኢኮኖሚ ሒሳብ፣ የግብርናና የኢንዱስትሪ የአገልግሎት በድምሩ ጥቅል  አቅርቦትና የግል ፍጆታ ወጪ፣ የመንግሥት ፍጆታ ወጪ፣ የግልና የመንግሥት መዋዕለ ንዋይ ወጪ፣ የተጣራ የኤክስፖርት ወጪ፣ በድምሩ ጥቅል ፍላጎት ከጥቂት የሥሌት ልዩነት በቀር እኩል መሆናቸውን እናያለን፡፡ ታዲያ ማን ከምን ተነስቶ ነው ፍላጎትና አቅርቦት አልተጣጣሙም የሚለው?

ሕዝቡም በሁኔታው አሁን ግራ ይጋባ ፓርላማውም አሁን ጉዳዩ ይጠና ይበል፣ ለማያነብ ሰው ቢጻፍም ዋጋ ስለሌለው እንጂ፣ ምክንያቶቹን እኔ በ1987 ዓ.ም. እና በ2007 ዓ.ም. ባሳተምኳቸው ሁለት መጻሕፍት ምክንያቶቹን ገልጬአለሁ፡፡ በ2007 ዓ.ም. ባሳተምኩት መጽሐፍም ገቢያችን ከምርታማነታችን መብለጡ፣ ወደፊት በኢኮኖሚያችን ውስጥ ቀውስ እንደሚፈጥር አበክሬ ገልጬአለሁ፡፡ በ1987 ዓ.ም. የኢትዮጵያን ትኩረት የሚሹ ሦስት የኢኮኖሚ ጥያቄዎች በሚል ባሳተምኩት መጽሐፍ እና በ2007 ዓ.ም. ግላዊና ብሔራዊ ኢኮኖሚያችን በሚል ርዕስ በጻፍኩት መጽሐፍ ውስጥ ደግሜ የገለጽኳቸው፣ የፍላጎትና የአቅርቦት ትርጉሞችና የፍላጎትና የአቅርቦት ልጠት (Demand and Supply Elasticities) ጽንሰ ሐሳቦች ሰሞኑን በገበያችን ውስጥ የተከሰቱትን የዋጋ ውድነቶች ምክንያቶች እንደሆኑ ለመግለጽ ምንም ነገር ሳልቀይር ከእነ ምሳሌዎቹ አቀርባለሁ፡፡ አሁን ካሉኝ መረጃዎች ተነስቼ አንዳንድ ሁኔታዎችን ልለውጥ ብችልም እንዲሁ እንደነበረ ማቅረቡን መርጬአለሁ፡፡

1. ፍላጎትና አቅርቦት

በኢኮኖሚ ጥናት ፍላጎት በተጠየቀ ዋጋ ሸቀጥን ለመግዛት በመስማማት ገንዘብ ከማውጣት ተነጥሎ አይታይም፡፡ አቅርቦትም በተሰጠ ዋጋ ሸቀጥን ለመሸጥ ከመፍቀድ ተለይቶ አይታይም፡፡ የመግዛት አቅም ሳይኖር ሸቀጥን መሻት ከመጓጓት አልፎ ፍላጎት እንደማይሆን ሁሉ፣ በአምራች ወይም በሻጭ መጋዘን ውስጥ ያለ የሸቀጥ ክምችት ሁሉ አቅርቦት አይደለም፡፡ አንድ ሰው አንድ ወይም ሁለት ጥንድ ጫማ እፈልጋለሁ ቢል፣ ፍላጎቱ በኢኮኖሚ ጥናት ምንም ትርጉም የለውም፡፡ አንድና ሁለት ጫማ የሚፈልገው የጫማው ዋጋ ስንት ቢሆን እንደሆነ አልተገለጸም፡፡ የጫማው ዋጋ 50 ብር ቢሆን፣ ሁለት ጥንድ ጫማ ለመግዛት እፈልጋለሁ፡፡ የጫማው ዋጋ 80 ብር ቢሆን አንድ ጥንድ ጫማ ብቻ ለመግዛት እፈልጋሉ ቢል ግን ንግግሩ የተሟላ ይሆናል፡፡ ይህን በተለያዩ ዋጋዎች የሚፈለግን የሸቀጥ ፍላጎት መጠን ነው ኢኮኖሚስቶች ፍላጎት ብለው የሚጠሩት፡፡

አምራቾችም እንደ ሸማቾች በተለያየ የሸቀጥ ዋጋ የተለያየ መጠን ሸቀጥ ለሽያጭ የሚያቀርቡ ሲሆን፣ ከሸማቾች የሚለዩት አምራቾች ዋጋ ሲጨምር ብዙ ሸቀጥና ዋጋ ሲቀንስ፣ ጥቂት ሸቀጥ ለሽያጭ በማቅረባቸው ነው፡፡ በጠራ ገበያ (Perfect Market) ሥርዓት የሸቀጥ ዋጋ የሚወሰነው ፍላጎትና አቅርቦት እኩል በሚሆኑበት የሸቀጥ መጠን ላይ በሚወሰን የግብይይት ዋጋ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የሸቀጦች ዋጋ የሚወደደው ፍላጎትና አቅርቦት ስላልተጣጣሙ ነው እንላለን፡፡ ይህን አባባል በትክክለኛነቱ ለመቀበል ብንፈልግ ማን ነው ለክቶ ያረጋገጠልን፡፡ በምን ያህል ዋጋ ነው ፍላጎትና አቅርቦት ያልተጣጣሙት፡፡ ስለፍላጎትና ስለአቅርቦት በሾላ በድፍን ብዙ ጊዜ ብዙ ያልን ቢሆንም፣ ፍላጎትንም ሆነ አቅርቦትን የለካንበት ጊዜ የለም፡፡ ፍላጎትና አቅርቦትን እኩል የሚያደርጋቸው ዋጋም ምን ያህል እንደሆነ አናውቅም፡፡ ከሃያ ዓመት በፊትም ሆነ ዛሬ የሸቀጦቹ ፍላጎት ምን ያህል እንደሆነ ፈላጊዎቹ እነማን እንደሆኑ፣ እያንዳንዳቸው ምንህል እንደሚፈልጉ፣ ለምን ያን ያህል እንደሚፈልጉ፣ አቅርቦት ምን ያህል እንደሆነ፣ አቅራቢዎች እነማን እንደሆኑ፣ ለምን ያን ያህል እንደሚያቀርቡ፣ ፍላጎት ለምን ከአቅርቦት እንደሚበልጥ፣ በምን ያህል የሸቀጡ መጠንና የሸቀጡ ዋጋ ፍላጎትና አቅርቦት እኩል እንደሚሆኑ በጥናት ያረጋገጥነው ነገር የለም፡፡

 የፍላጎትናአቅርቦት ለውጦች ጥንካሬ

ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ የአንዳንዶቹ ሸቀጦች ዋጋዎች ሦስት እጥፍ ሲያድጉ፣ የሌሎች ሸቀጦች ዋጋዎች አምስት እጥፍና የተቀሩትም አሥር እጥፍ አድገዋል፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ለምን የሁሉም ሸቀጦች ዋጋዎች በእኩል መጠን አላደጉም? መልሱ ለዋጋ ለውጥ የፍላጎትና የአቅርቦት አፀፋዊ ምላሽ ለውጦች ጥንካሬ ወይም መላላት ነው፡፡ ለኑሮ እጅግ አስፈላጊ በሆኑ ሸቀጦች በዋጋ ለውጥ ምክንያት ፍላጎት በጣም አይለወጥም፡፡ በሌሎች መሠረታዊ ባልሆኑ ሸቀጦች በዋጋ ለውጥ ምክንያት ፍላጎት በጣም ይለወጣል፡፡ ፍላጎት በጣም በማይለወጥባቸው ሸቀጦች የዋጋው ለውጥ ፈጣን ይሆናል፡፡ ፍላጎት በጣም በሚለወጥባቸው ሸቀጦች የዋጋው ለውጥ አዝጋሚ ይሆናል፡፡ በገቢ ለውጥ ምክንያትም እንደዚሁ ፍላጎት ከፍተኛ የመጠን ለውጥ የሚያሳይባቸውና ከፍተኛ ለውጥ የማያሳይባቸው የሸቀጥ ዓይነቶች አሉ፡፡

በዋጋ ለውጥ የአቅርቦት መጠን ከፍተኛና ዝቅተኛ የሚሆንባቸውን ለማምረት አጭርና ረጅም ጊዜ የሚጠይቁ የምርት ዓይነቶች ሲኖሩ፣ ዋጋ ሲጨምርና ሲቀንስ አቅርቦትም በመጨመርና በመቀነስ ከዋጋ ጋር በአንድ አቅጣጫ ጎን ለጎን ይጓዛል፡፡ በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃና በሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በእንግሊዝ የኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚስት አልፍሬድ ማርሻልና ሌሎች ተሃድሶ ጥንታውያን (Neo-Classical) ኢኮኖሚስቶች የፍላጎትና የአቅርቦት ለውጦች ጥንካሬና መላላትን በልጠት ጽንሰ ሐሳብ ገልጸዋል፡፡ የዋጋ ዕድገትና ዋጋ መዋዠቅ ኑሯችንን ያመሰቃቀሉብን እኛ ኢትዮጵያውያን  ገበያዎቻችን ውስጥ የአንዱ ሸቀጥ ዋጋ በፍጥነት የሚያድግበትንና የሌላው ሸቀጥ ዋጋ ባለበት የሚቆይበትን የልጠት ጽንሰ ሐሳብን ተረድተን፣ ለምን የሸቀጦች ዋጋ ዕድገት እንደሚለያይ ማወቅ እንደ ሸማችም እንደ አምራችም እኩል ይጠቅመናል፡፡

የፍላጎት ልጠት

በየጊዜው በተለያዩ ምክንያቶች ፍላጎቶች ይለዋወጣሉ፡፡ አሮጌ ሸቀጦች ከገበያ ይወጣሉ፣ አዳዲስ ሸቀጦች ወደ ገበያ ይገባሉ፡፡ ቀድሞ ሸቀጦቹን ይፈልጉ የነበሩ ሰዎች ወደ ሌሎች ሸቀጦች ሲቀይሩ አዳዲስ ሸቀጦቹን ፈላጊዎች ይፈጠራሉ፡፡ በርካታ የፍላጎት ለውጦች ምክንያቶች ሲኖሩ፣ እያንዳንዳቸው በተናጠል ከሚያሳድሩት ተፅዕኖ ባሻገርም በአንድነት ሆነው የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ ኢኮኖሚስቶች በኢኮኖሚ ልኬት (Econometrics) አስልተው፣ ውጤቱን የሚያውቁበት ዘዴ አላቸው፡፡ የፍላጎት ልጠት ዋና ምክንያቶች የዋጋ ለውጥና የገቢ መጠን ለውጥ ሲሆኑ፣ በእነኝህ ለውጦች ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ሁኔታዎችም አሉ፡፡ እነርሱም የጣዕም ለውጥ፣ የሕዝብ ብዛት ለውጥ፣ የሸቀጡ በሸማቹ እጅ መኖር አለመኖር፣ ሸቀጡን የሚተካ ሌላ ሸቀጥ መኖር አለመኖር የሸቀጦች ደባልነት ወይም አብሮ መወሰድ፣ ወዘተ. ናቸው፡፡  

 በዋጋ ለውጥ የፍላጎት ልጠት

በዋጋ ለውጥ የፍላጎት ልጠት ማለት ለዋጋ ለውጥ መጨመርና መቀነስ አፀፋዊ ምላሽ፣ የሸቀጥ ፍላጎት ለውጥ የመለጠጥ ደረጃ ማለት ነው፡፡ ቀደም ባለ የፍላጎት ትርጉም ምሳሌያችን የጫማ ዋጋ ከሃምሳ ብር ወደ ሰማኒያ ብር ቢያድግ፣ የዋጋ ጭማሪው ስልሳ በመቶ ነው ፍላጎትም ከሁለት ወደ አንድ ሲቀንስ ቅነሳው መቶ በመቶ ነው፡፡ የፍላጎት ለውጥ መቶኛ ከዋጋ ለውጥ መቶኛ ስለበለጠ በልጠት ቋንቋ ፍላጎት ተለጣጭ ነው፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስ መጓጓዣ ዋጋ ከአሥራ አምስት ሳንቲም ወደ ሃያ አምስት ሳንቲምወይም ስልሳ ሰባት በመቶ ጨምሯል፡፡ በአውቶቡስ ለመጓጓዝ የሚፈልግ ሰው ቁጥር ግን የዋጋ ጭማሪ መቶኛውን ያህል አልቀነሰም፡፡ ስለዚህም በአሥራ አምስት ሳንቲም ዋጋ ደረጃ ላይ የከተማ አውቶቡስ መጓጓዣ ፍላጎት ለውጥ ዝቅተኛ ስለሆነ፣ በልጠት ቋንቋ  ፍላጎት ኢተለጣጭ ነው፡፡ እንደ ሽንኩርት፣ ጨው፣ ዘይትና ሌሎች የምግብ ምርቶች የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የልጆች ትምህርት ቤት፣ የንፅህና መጠቀሚያዎችና የመሳሰሉ መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ዋጋ ሲለወጥ ፍላጎት ኢተለጣጭ ነው፡፡ በአንፃሩ የቅንጦት ሸቀጦች ዋጋ ሲለወጥ ፍላጎት ተለጣጭ ነው፡፡

በገቢ ለውጥ የፍላጎት ልጠት

የሰዎች ገቢ ሲጨምርና ሲቀንስም የሸቀጥ ፍላጎታቸው ይለወጣል፡፡ እነኚህ ለውጦችም በተለያዩ መልኮች ይከሰታሉ፡፡ ገቢ ሲጨምር ቀድሞ ተፈላጊ የነበሩ እንደ ጎመን፣ ሽሮ፣ ዘይት፣ ርካሽ ልብሶች፣ ላስቲክና ሸራ ጫማዎች፣ የዘንጋዳና የበቆሎ እህሎችየመሳሰሉ ርካሽ የፍጆታ ሸቀጦች ፍላጎት ቀንሶ በምትኩ እንደ ቅቤሥጋ፣ ውድ ልብሶችና ቆዳ ጫማዎች የመሳሰሉ ሸቀጦች ፍላጎት ይጨምራል፡፡ ከሸማቹ ገቢ መጠን አንፃር የሸቀጡ ዋጋ ዝቅተኛ ከሆነም የሸቀጡ ፍላጎት ኢተለጣጭ ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ ጨው፣ ክብሪት፣ እርሳስ፣ ወረቀት፣ የልብስ መስፊያ መርፌ፣ ምላጭ፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ሸቀጦች ዋጋቸው በእጥፍ ቢጨምርም እንዃ መካከለኛ ገቢ ላለው ሰው የሸቀጦቹ ፍላጎት ኢተለጣጭ ነው፡፡ በጥቅሉ ሲታይ በዝቅተኛና በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖር ኢትዮጵያዊ በገቢ ለውጥ ከምግብ ከልብስና ከመጠለያ በስተቀር፣ የሌሎች ሸቀጦች ፍላጎት ተለጣጭ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከፍተኛ ገቢ ለሚያገኙና ከፍተኛ ሀብት ላከማቹ ጥቂት ሰዎች በገቢ ለውጥ ውድ የሆኑ የውጭ አገር ምርቶችና ጌጣ ጌጦችም ሳይቀር ፍላጎት ኢተለጣጭ ነው፡፡ 

በፍላጎት ልጠት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ሁኔታዎች፣ የሸቀጡ በሸማቹ እጅ መኖር አለመኖር 

ሸቀጡ በብቃት በሸማቹ እጅ ያለ ከሆነ የሸቀጡ ፍላጎት ተለጣጭ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የልብስ ዋጋ ሲጨምር አምስትና ስድስት ቅያሪ ልብስ ላለው ሰው ፍላጎት፣ ተለጣጭ ስለሆነ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት ፍላጎት በጣም ይቀንሳል፡፡ ቅያሪ ልብስ ለሌለው ሰው ግን የልብሱ ዋጋ መጨመር ከፍተኛ የፍላጎት ቅነሳን አይፈጥርም፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የብዙ ሸቀጦች ፍላጎቶቻቸው ገና አልተሟሉም፡፡ ከዓለም አቀፍ የኑሮ ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር አልተሟሉም ብቻ ሳይሆን፣ ባዶ ናቸው ማለትም ይቻላል፡፡ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለው እጅግ መሠረታዊ የሆኑ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን ማሟላት ቀርቶ ምግቡን፣ መላበሻውንና መጠለያውንም ማግኘት አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ከሸቀጦች ይዞታ ክምችት አንፃር ሲታይ በዋጋ ለውጥ የብዙ ሸቀጦች ፍላጎት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ኢተለጣጭ ስለሆነ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሸቀጦች ዋጋ የመጨመር እንጂ፣ የመቀነስ አዝማሚያ እንደማያሳይ ያመለክታል፡፡ 

የጣዕም ለውጥ

የአንድ ሸቀጥ ፍላጎት በሰዎች ሸቀጡን የማወቅ ለማግኘት የመሻትና ለመግዛት አቅም መኖር ላይ ይመሠረታል፡፡ ትምህርት፣ ሥልጣኔ፣ ከተሜነት፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ዘመናዊነቶች የሸቀጦችን ጣዕምና መሻት ይለውጡታል፡፡ ሰዎች አሮጌና ነባሩን እንዲንቁና አዲሱን የተሻለውን ዘመናዊውን እንዲሹ፣ የመግዛት አቅም ካላቸውም እንዲገዙ ያደርጋሉ፡፡ አዳዲስ ሸቀጦች አሮጌዎችን በመተካት ብዙ ሸቀጦች በየወቅቱ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ይሆናሉ፡፡ ሌሎች ብዙ ዕቃዎችም የጊዜው ፋሽን በመሆን የሰዎችን የዕቃ ጣዕምና ፍላጎት ይስባሉ፡፡ ኩራዝ በፋኖስ፣ ፋኖስ በአምፖል፣ መደብ በደረቅ ወንበር፣ ደረቅ ወንበር በሶፋ መቀመጫ፣ አቡጀዲ በካኪ፣ ካኪ በሱፍ ጨርቅ፣ የጠፍር ጫማ በላስቲክ ጫማ፣ ላስቲክ ጫማ በሸራ ጫማ፣ ሸራ ጫማ በቆዳ ጫማ፣ ኦፔል በቶዮታ፣ ቶዮታ በመርሰዲስ መኪና ይተካሉ፡፡ የአንዱ ፍላጎት ሲቀንስ የሌላው ፍላጎት ይጨምራል፡፡ የማያቋርጥ ሰንሰለታዊ የለውጥ ሒደት ነው፡፡

1966 ዓ.ም. እስከ 1985 ዓ.ም. በነበሩት ሃያ ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ የሸቀጦች ጣዕም በእጅጉ ተለውጧል፡፡ ለውጡም በከተማ የሚኖሩ ጥቂት የኅብረተሰብ ክፍሎችን ብቻ ሳይሆን፣ ጠቅላላውን ሕዝብ ያካለለ ነው፡፡ እንደ ስኳር፣ ሳሙና፣ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ ልብሶች፣ ጫማዎች፣ ቴአትር ቤቶች፣ የባንክ አገልግሎቶች፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ከሃያ ዓመታት በፊት በገጠሩ ሕዝብ ዘንድ የማይታወቁና የማይዘወተሩ ሸቀጦች የገጠሩም ሕዝብ  አውቋቸዋል፡፡ እንደ የትምህርት አገልግሎት፣ የጤና አገልግሎትና የመኪና ትራንስፖርት አገልግሎትን መጠቀምም ጀምሯል፡፡

በከተሞች ብዙ ሀብት የነበራቸው ሰዎች የቴሌቪዥን፣ የሬዲዮ፣ የመኪና፣ ወዘተ. ጣዕም አልነበራቸውም፡፡ የሆቴሎችና የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ የቴአትርናሲኒማ ቤቶች ተጠቃሚዎች አልነበሩም፡፡ ሕዝብ ከገጠር ወደ ከተማ ስለፈለሰና ከተሞች ስላደጉም የብዙ ሕዝብ የሸቀጦች ጣዕም እጥፍ ድርብ አድጓል፣ ተለውጧልም፡፡ ሥልጣኔ በኋላ ቀር ቴክኖሎጂ በአገር ውስጥ የሚመረቱ የዘመኑን ፋሽን ያልተከተሉ ሸቀጦችን ጣዕም ቀንሶ፣ በበለፀጉት አገሮች በአዳዲስ ቴክኖሎጂ የሚመረቱ ዘመናዊ ሸቀጦችን ተክቷል፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች ታዳጊ አገሮች የባዕድ አገር ሸቀጦች ጣዕም ምርኮኛ ሆነዋል፡፡ ቀናት፣ ወራትና ዓመታት በተተኩ ቁጥር የጣዕም ለውጡ እየባሰበትም ሄዷል፡፡ ስለዚህም በጣዕም ለውጥ ምክንያት የአንዳንድ ሸቀጦች በዋጋ ለውጥ ፍላጎት ኢተለጣጭ ሲሆን፣ በሌሎች ሸቀጦች በዋጋ ለውጥ ፍላጎት ተለጣጭ ሆኗል፡፡

የሕዝብ ብዛት ለውጥ

የጠቅላላው ሕዝብ ቁጥር በማደጉ በጥቅሉ የሁሉም ሸቀጦች ፍላጎት ጨምሯል፡፡ በሕዝብ ብዛት ለውጥ ምክንያት የሕዝቡ ዕድሜ ቅንብር ተለውጦ የሕፃናትና የወጣቶች ቁጥር በመጨመሩም፣ ለሕፃናትና ለወጣቶች የሚሆኑ ዕቃዎች ፍላጎት ጨምሯል፡፡ በፆታም እንዲሁ ለወንዶች የሚያገለግሉና ለሴቶች የሚያገለግሉ ዕቃዎች ፍላጎት ይለያያል፡፡ ሴቶች የራሳቸው የሆነ የሥራ ገቢ የሌላቸውና በቤት እመቤትነት ተወስነው በወንዶች ገቢ ላይ ጥገኛ ሆነው የመኖር ባህላዊ አኗኗር ልምዳችን፣ በሥልጣኔና በመሻሻል በመቅረቱና ሴቶች በገቢያቸው የሚያምራቸውን ዕቃ መግዛት በመቻላቸውም የዕቃዎች ፍላጎት መጠን ዓይነትና ጥራት ተለውጧል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በየዓመቱ በሦስት በመቶ እያደገ ቢሆንም፣ ከዕድገቱ ጋር አብሮ የልጆችናወጣቶች ቁጥር ዕድገት ፈጣን ቢሆንም፣ አገሪቱ ባላት አቅም ፍላጎቱን ለማርካት የሚችል ማምረቻ ድርጅቶችን ስላለመሟላታቸው ሕዝቡ በሸቀጥ ፍላጎት እንደተራበ ነው፡፡ የሕዝብ ብዛት መጨመሩ በዋጋ ለውጥ የሸቀጦች ፍላጎትንም ኢተለጣጭ አድርጎታል፡፡

የአቅርቦት ልጠት በዋጋ ለውጥ 

በዋጋ ለውጥ ምክንያት የሚፈጠር የአቅርቦት መጠን ለውጥ ጥንካሬና መላላት የአቅርቦት ልጠት ይባላል፡፡ ከዋጋ ለውጥ መቶኛ በላይ የአቅርቦት ለውጥ መቶኛ ከተፈጠረ አቅርቦት ተለጣጭ ነው ሲባል፣ ከዋጋ ለውጥ መቶኛ በታች የአቅርቦት ለውጥ መቶኛ ከተፈጠረ አቀርቦት ኢተለጣጭ ነው ይባላል፡፡ አቅርቦት ከማምረት ሒደት ጋር የተያያዘ ስለሆነ እንደ ፍላጎት ለዋጋ ለውጥ ፈጣን ምላሽ አይሰጥም፡፡ ዋጋ ሲጨምር አቅርቦትን ለመጨመር አምራች ድርጅቶች የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ፣ ወይም ሌሎች አዳዲስ ድርጅቶች ለመክፈት ጊዜ ይወስድባቸዋል፡፡ ዋጋ ሲቀንስም አቅርቦት ለመቀነስ ለወደፊት በምርት መጠን ላይ የሚሰጥ ውሳኔ እንጂ፣ የተመረተ ምርት መጠንን መቀነስ አይቻልም፡፡ በዚህም ምክንያት በዋጋ ለውጥ የአቅርቦት ለውጥ መጠን አዝጋሚ ነው፡፡

በአቅርቦት ልጠት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ሁኔታዎች

በዋጋ ለውጥ የአቅርቦት ለውጥ ላይ ተፅዕኖ ከሚያሳድሩ ሁኔታዎች የማምረቻ መሣሪያዎች ዋጋ ለውጥ፣ የመንግሥት ግብር ለውጥና የአየር ንብረት ለውጥ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ በዓለም ገበያ በተለይ የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው መጨመር ምክንያት የማምረቻ ዋጋ ጨምሯል፡፡ ሆኖም የደርግ መንግሥት የሕዝቡን በኑሮ መማረር ለማርገብ በወሰዳቸው የፖሊሲ ዕርምጃዎች፣ የምርቶች ዋጋ የጨመረው ከሚታሰበው በታች ነው፡፡ ይህም አምራች ድርጅቶችን አትራፊ ሊያደርጋቸው ስላልቻለ፣ ብዙ የሕዝብ ፍላጎቶች ሳይረኩ ለወደፊት በመተላለፍ ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዋጋዎች ሁኔታ ከዓለም አቀፍ ዋጋዎች ጋር ሲነፃፀር 

እንደየ አገሩ ተጨባጭ ሁኔታና የዋጋ ዕድገት ታሪክ በተለያዩ አገሮች የሸቀጦች ዋጋዎች ከፍተኛ ልዩነት ያሳያሉ፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም ተደብቃ ስለኖረች፣ የሸቀጦቿ ዋጋዎች ከሌሎች አገሮች ሸቀጦች ጋር ሊነፃፅሩ የሚችሉ አይደሉም፡፡ በብዙ ምዕራባውያን አገሮች ውስጥ ከቦሌ እስከ ፒያሳ ድረስ ለሚርቅ መንገድ የታክሲ መጓጓዣ ዋጋከአሥር ዶላር አሥራ አምስት ዶላር ይደርሳል፡፡ ትንሹን አሥር ዶላሩን እንውሰድ፡፡ አሥር ዶላር የአውሮፓና የአሜሪካ ከተሞች ከበረንዳ መደብር፣ አንድ ጥንድ የሴት ጫማ መግዛት ይቻላል፡፡ ይህ ጫማ ኢትዮጵያ ውስጥ መርካቶ ወይም ፒያሳ ከሦስት መቶ እስከ አራት መቶ የኢትዮጵያ ብር ይሸጣል፡፡ ዝቅተኛውን ሦስት መቶ ብር እንውሰድ፡፡ በኢትዮጵያ በሦስት መቶ ብር ከቦሌ ፒያሳ በሚኒባስ ታክሲ ሰማኒያ ጊዜ መጓጓዝ ይቻላል፡፡ ምቾቱ የተለያዩ ቢሆንም፣ በታክሲ አገልግሎት የእኛንና የምዕራባውያንን ገበያዎች ስናወዳድር በኢትዮጵያ የታክሲ አገልግሎት ዋጋ ከጫማው ዋጋና ከሌሎችም ሸቀጦች ዋጋ ጋር ሲነፃፀር ርካሽ ነው፡፡

ይህም ሆኖ አንድ ሚኒባስ በወር ከሾፌሩ ደመወዝ ሌላ እስከ ሦስት ሺሕ ብር ገቢ ያስገኛል፡፡ ይህን ሦስት ሺሕ ብር በኢትዮጵያ ከባለሙያዎች ወርኃዊ ገቢ ወይም ደመወዝ ጋር ብናነፃፅርየሦስት የኢትዮጵያ መንግሥት ሚኒስትሮች የተጣራ ወርኃዊ ደመወዝ፣ የአራት ሐኪሞች የተጣራ ወርኃዊ ደመወዝ፣ የአምስት ኢኮኖሚስቶች ወይም ጋዜጠኞች የተጣራ ወርኃዊ ደመወዝ፣ የአሥራ አምስት መምህራን የተጣራ ወርኃዊ ደመወዝ፣ የሰላሳ ወዛደሮች የተጣራ ወርኃዊ ደመወዝ ያክላል፡፡ በአውሮፓ በአሥር ዶላር ጫማ የሸጠው ነጋዴ በአሥሩ ዶላር በአንድ ተራ ሻይ ቤት፣ በአንድ ዶላር የአንድ ሲኒ ሻይ ዋጋ አሥር ሲኒ ሻይ ሊጠጣ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ያንኑ ጫማ በሦስት መቶ ብር የሸጠ ነጋዴ በሦስት መቶው ብር በአሥራ አምስት ሳንቲም የአንድ ሲኒ ሻይ ዋጋ ሒሳብ ሁለት ሺሕ ሲኒ ሻይ ሊጠጣ ይችላል፡፡

የምርት ጠቀሜታ ስሜታዊ ግምት፣ የምርታማነት ደረጃና የማምረቻ ወጪዎች ትንተና፣ የፍላጎትና የአቅርቦት የዋጋ አወሳሰን ሥርዓቶች፣ ወዘተ. የተለያዩ ምርቶች ለምን የተለያየ ዋጋ እንደሚኖራቸው ሲያመለክቱን በምሳሌዎቹ እንደ ተመለከትነው፣ በተለያዩ አገሮች የተለያዩ ምርቶች ዋጋዎች ከሌሎች ምርቶች ጋር ሲነፃፀሩ የተለያየ ነው፡፡ ለተመላላሽ ነገዴዎች መበልፀግ ምክንያት ይህ የገበያዎቻችን ሁኔታ ከሌሎች አገሮች ገበያዎች ጋር አለመናበብ ምክንያት ነው፡፡

በኢትዮጵያ የዋጋዎች አወሳሰን ሥርዓት ስለሚሻሻልበት ሁኔታ 

ሶሻሊዝምን ለመገንባት በተደረገው የሀብት መውረስ ግለሰቦች ከሀብት የሚያገኙትን የገቢ መጠን መገደብ፣ የሥራ ገቢ ወይም ደመወዝ ከሞላ ጎደል ተቀራራቢ እንዲሆን ማድረግና የመሳሰሉት የመንግሥት ፖሊሲዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ የኑሮ ደረጃ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድረዋል፡፡ የአብዛኛው ሕዝብ የገቢ መጠን እጅግ ከመቀራረብም አልፎ ቁልቁል ስለወረደ፣ የአብዛኛው ሕዝብ ሸመታ ወደ ዝቅተኛ ጥራት ደረጃ የሚመደቡ ሸቀጦች አዘቅዝቋል፡፡ ከዚህም ጋር በጠቅላላው ሕዝብ የሚፈለጉ የሸቀጥ ዓይነቶችን ተመሳሳይ ስላደረገና የሚፈለገውን መጠን ያህል ማምረት ስላልተቻለ፣ በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል መራራቅ ተከስቶ ዋጋ ተወዷል፣ የኑሮ ደረጃም ቁልቁል ሄዷል፡፡

የፍላጎትና የአቅርቦት ልጠት ጽንሰ ሐሳቦች የብዙ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችንና የዋጋዎችን ለውጦች ጥንካሬዎችና አዝማሚያዎችን ለመገመት ስለሚረዱ፣ የሸቀጦቻችንን የፍላጎትና የአቅርቦት ልጠቶች ብንለካ የገበያውን ውዝግብ እናረግባለን፡፡ በኢትዮጵያ በየጊዜው የሸቀጦች ዋጋ የሚንረው በአንድ በኩል አብዛኞቹ ሸቀጦች በአብዛኛው ሕዝብ በጣም ተፈላጊና መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ስለሆኑ፣ በዋጋ ለውጥ ፍላጎት ኢ ተለጣጭ በመሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩልም ከመረጃ ማነስ የተነሳ የመዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች የአትራፊነት ወይም የትርፍ ተስፋዊ ግምት ደብዛዛ በመሆኑ፣ ምንና እንዴት ማምረት እንደሚገባቸው ማወቅ ስለተሳናቸው በዚህ ምክንያት በዋጋ ለውጥ አቅርቦትም ኢተለጣጭ ነው፡፡

አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ መሠረታዊ የሆኑ ብዙ ሸቀጦች በእጁ የሌሉና የኑሮ ደረጃውም እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ ገቢው ሲጨምር የሸቀጦች ፍላጎቱ መጠን ይጨምራል፡፡ የፍላጎቱን መጠን ልናውቅ የምንችለው የፍጆታና የቁጠባ ዝንባሌውን በማጥናት ነው፡፡ ከቀጣይ ገቢው ውስጥ ቀጣይ የፍጆታ ዝንባሌው ከፍተኛ ከሆነ ፍላጎት ከፍተኛ ጭማሪ ይኖረዋል፡፡ ከቀጣይ ገቢው ውስጥ ቀጣይ የፍጆታ ዝንባሌው ዝቅተኛ ከሆነ ቁጠባው ያድጋል፡፡ ለአቅርቦት ማነስ ዋናው ምክንያትም በሥራ ላይ ያሉ አምራች ድርጅቶች ምርታቸውን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉበትን የማምረቻ አደረጃጀት ዘዴ፣ ካለማወቅና በየትኛው የሥራ መስክ ቢሠማሩ የቅርብ ጊዜና የሩቅ ጊዜ ጥቅም ወይም አስተማማኝ ትርፍ እንደሚያገኙ ለመወሰን የሚያስችላቸው በቂ የኢኮኖሚውን ሁኔታ የሚገልጽ መረጃ ለማግኘት አለመቻል ናቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...