Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሞት እንዲህ ረከሰ እንዴ?

እነሆ መንገድ። እንደ ሰሞኑ ሁኔታችን ከሆነ አያያዛችን ያስፈራል፡፡ አያያዛችንን አስተካክለን መራመድ ከተሳነን ብዙ ችግር እንደሚገጥመን ነጋሪ አያሻንም፡፡ ይሁንና የደከመው መንፈሳችን ለጊዜውም ቢሆን ሕይወት ዘርቶ በአዲስ ወኔና ጉልበት ይጓዛል። እግር ውሎ ይግባና። የመንገዱና የመንገደኛው አመል እንደሆነ ለወሬ አልመች ብሏል። ያውም የወሬ     ‹ታለንት› እኩል በተካፈለባት ምድር። ‹‹ወሬ ጠፋ ትለኛለህ?›› ሲል የምሰማው ወያላውን ነው። የዛሬ ወያላችን ሾፌራችንን በዕድሜ ይበልጠዋል። ክንዱ ሳይበቃው ገጹ በፈርጣማ ክፍልፋይ ጡንቻው ተከፋፍሎ ወጣት ባይመስል፣ አንዴ አይደለም ሁለት ጊዜ ወልዶ ያደርሰዋል ይባልለታል። ብላቴናው ሾፌራችን የታላቁን ወያላ ስላቅ እያጣጣመ፣ ‹‹የወሬ እናት ሞተች አሉ። ለጊዜው ጎረቤቷ አንደኛ ተጠርጣሪ ተብላ ተይዛለች አሉ፡፡ ወሬን ተራራ ካላሳከልነው እኮ. . . የሰማም አይደብቀውም አሉ፤›› ይለዋል። ‹‹ተው እንጂ!›› ወያላው ያዳንቃል። ተሳፋሪዎች አንድ በአንድ ወደ ታክሲያችን እየገቡ መቀመጫቸውን እየያዙ ነው። የወያላውና የሾፌሩ ነገረ ሥራ ተሳፋሪዎችን በድራማ እያማለለ የሚሸቅል እንጂ፣ የግላቸውን ፍሬፈርስኪ የያዙ አያስመስልም። ወያላው ቀጥሏል።

‹‹እና ‹አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች› ስለጉዳዩ ምን አሉ ተባለ?›› ያሽሟጥጣል ወያላው። ብላቴናው ተረበኛ ሾፌር ተቀብሎ፣ ‹‹ዌል እንግዲህ ብዙ ብለዋል። ለምሳሌ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠቀሰ የመዲናችን ነዋሪ በአንክሮ፣ የወሬን እናት ጎረቤቷ ‹መርደር› ማድረጓ በእውነቱ ‹ሪል› ከሆነ ለአገሪቱ ‹ፊውቸር› ጥቅሙ የጎላ ይሆናል ብሏል። ሌላዋ እንዲሁ ስሟም መልኳም እንዲጠቀስ ያልፈለገች ወጣት ደግሞ በእውነቱ ‹ፌር› አይመስለኝም። ማንም ገደለ ማንም ሞተ ወሬን ያህል ‹ሂውጅ የሶሳይቲ› ቤንዚን እንዲህ አቅሎ ማየት የኋላ የኋላ ‹ሂውጅ ኮስት› ያስከፍላል ብላለች. . .›› ሲል ገሚሱ ግራ ተጋብቶ ገሚሱ እየተዝናና ሲያዳምጠው ቆየ። ድንገት ወያላው፣ ‹‹ከሁሉ ከሁሉ እኔን የገረመኝ ቋንቋችን ራሱ ስደተኛ በሆነበት ዘመን ስደትን አውጋዡ ነው. . .›› ብሎ በሩን ከረቸመውና ወደ ተሳፋሪው መለስ ብሎ፣ ‹‹ሲሪየስሊ!›› አለ ሸራፋ ጥርሱን እያስቃኘ። አቤት የዘመኑ ወሬና አወራሩ። ማማሩ ወይስ መምረሩ! 

ጉዟችን ተጀምሯል። ጭቅጭቁም አብሮ ጀምሯል። መሀል መቀመጫ ላይ የተሰየሙ ተሳፋሪዎች ናቸው። አንደኛው፣ ‹‹ምን ያጋፋሃል? ድንበርህን ብትጠብቅ ይሻልሃል፤›› ማለት። ‹‹ማን ያሰመረው ድንበር ነው? ወንበር እኮ ነው፤›› ብሎ ያ ማባባስ። ‹‹ምንድነው ሽብሩ?›› ብሎ ጎልማሳው ወያላ መገላገል ያዘ። ‹‹አታየውም እንዴ እግሩን እላዬ ላይ ሰቅሎ?›› ይደነፋል ከሳሽ። ‹‹ወንበሩ ሰፊ ነው፣ ደግሞ እግሩን አልጫነብህም፤›› ብሎ ወያላው ዓይቶ ፈረደ። ‹‹ለምን ይታከከኛል?›› ከሳሽ ነገር ነገር አለው። ‹‹ታክሲ ውስጥ ነው እኮ ያለኸው ወንድም? የግልህ ሊሞዚን አደረግከው እንዴ?›› ተከሳሽ እያባሰው ሄደ። ‹‹በቃ ወደ ግዛቴ አትምጣ ማለት አትምጣ ነው፤›› ከሳሽ ደረቅ ቢጤ ይመስላል። ‹‹ፌዴራሊዝም ታክሲ ተሳፍሯል እንዴ?›› ትላለች ባለ ሻሿ። ሸሪፎ ወያላችን፣ ‹‹ተይው ሰዓቱ ደርሶ ነው እንዲህ የሚሆነው፤›› እያለ ያዛጋል። ነገር እኮ እንዲህ ነው የሚጀመረው፡፡  

‹‹ነገር ሲከር ይበጠሳል ተስማሙ እስኪ. . .›› ብለው አንድ አዛውንት መሸምገል ያዙ። ‹ፈርስት› እሱ ሥርዓት ይያዝ፤›› አለ ከሳሽ። አዛውንቱ ደግሞ፣ ‹‹‘ፈርስት’ የሚባል አማርኛ የለም። በቅድሚያ አትልም?›› ብለው እንደለመዱት ሲጦፉ፣ ‹‹አማርኛ አፍ መፍቻ ቋንቋዬ እስካልሆነ ድረስ ‹I don’t care›. . .›› ብሎ ጮኸባቸው። እሳቸው እንዳቀረቀሩ ቀሩ። ወዲያው መውረጃው ደርሶ ‹‹ወራጅ!›› ሲል አዛውንቱ ካቀረቀሩበት ቀና ብለው፣ ‹‹በላ ወንበርህን ይዘህ ውረድ፤›› አሉት ድንበር ድንበር ሲል የቆየውን። ይኼኔ አመዱ ቡን። አዛውንቱም፣ ‹‹ጊዜና ታክሲ አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር፣ አንድ ቀን ፈልገን ሳይሆን ሳንፈልግ ከተሳፈርንበት የምቾት ኮርቻ ላይ ማስወረዳቸው ነው። ስንሞት ሁሉ ቀሪ ነው። ስንኖር ግን ከተጋራነው መሬቱ፣ ሳሩ ቅጠሉ፣ እንስሳቱ ሁሉ ለእኛ ነው። እስኪ እንቻቻል፡፡ በድንበር፣ በክልል፣ በቀዬ ተቀያይመን ስለኖርን ባስከበርነው ይዞታ አፈር አንቀበር። መሬቱስ ችሎናል ምናለበት እኛ ብንስማማ?›› ሲሉ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ስቆባቸው ወረደ። አውቆ አበዱ ባሰን እኮ ዘንድሮ!

በአንድ ሁከተኛ የተነሳውን ግብግብ ለማስረሳት የተሳፈሪውን ቀልብ ለመሳብ ይመስላል ሾፌሩ ሬዲዮ ከፍቶ የሰዓቱን ዜናዎች ያስደምጠናል። ‹‹አይ አንተ ፈጣሪ ሩሲያን ከተረሳችበት አስታውሰህ እንዲህ በየአርዕስተ ዜናው ስሟን ያስናኘኸህ አምላክ፣ እባክህ እኛንም አስታውሰን እባክህ?›› ይላል ጋቢና የተቀመጠ ጎልማሳ እጆቹን ዘርግቶ። ይኼን ጊዜ አጠገቡ የተቀመጠው ወጣት፣ ‹‹ደስ አይልም?›› ብሎ ፀሎቱን አቋረጠው። ‹‹ምኑ?›› ሲለው፣ ‹‹ለጉልቤም ጉልቤ ሲያዝበት ደስ አይልም?›› አለው። ጎልማሳው፣ ‹‹ደስ ይል ነበር። ግን ጉልቤ ሲበዛ ደግሞ ጥሩ አይደለም። በዚያ ያ ጎረምሳ የሚሳይል ሙከራ እያለ ያስወነጭፋል። በዚህ በኩል ድሮን ተመታብኝ ብሎ አገር ይያዝ ይላል። ማን ለማን ነው የታዘዘው እስኪ?›› ብሎ መልሶ ሲጠይቀው፣ ‹‹ዋናው ላይ ነዋ። ምሥራቅ ምዕራብን ማስበርገግ ጀመረ። አሜሪካ እንዲህ አድርጋ፣ አሜሪካ እንዲህ ቆንጥጣ፣ አሜሪካ እንዲህ ስቃ፣ አሜሪካን ትን ብሏት. . . ከሚል ዜና ዕድሜ ይስጣቸውና እነ ፑቲን፣ እነ ኪም ጆንግ ኡን ጆግ ስሙም ልቡም አይያዝልኝም ብቻ ገላግለውናል። እሱ ያለ ቀን ደግሞ እኛም. . .›› ብሎ ሳይጨርሰው፣ ‹‹በል በል ወንድም። እኛ ከዚህ በላይ ማዕቀብ የሚችል ትከሻ የለንም። እንኳን አዲስ ለሚጣል ማዕቀብ ኑሮንም አልቻልነው. . . እንኳን የእነሱን ውርጅብኝ የእኛንም የፍጅትና የመገለማመጥ አባዜ አልቻልነውም. . .›› ብሎ ጎልማሳው አቋረጠው።

‹‹እስኪ ስላቁን ተውትና አንዴ ዜና እንስማበት?›› ሲል ከኋላ መቀመጫ፣ ‹‹ሰው በዜና ብቻ አይኖርም በስላቅና ሽሙጥ ጭምር እንጂ ብለህ ጥቅስ ለጥፍ፤›› ይላል ጎልማሳው። ‹‹አንዳንዶቻችሁ የምታስወነጭፉት ሚሳይል የት ላይ እንደሚያርፍ እያስተዋላችሁ፤›› ብሎ ወያላው ማስጠንቀቂያ ቢጤ ሲወረውር መጨረሻ ወንበር ያሉት ወጣቶች ተኮራኩረው የሳቁ እስኪመስል ድረስ በሳቅ አሽካክተው፣ ‹‹ፀረ ሚሳይል መግዛት ነዋ። ደግሞ ለዚህም ተበደሩና ግማሹን ቆርጣችሁ ኑሯችሁን አደላድሉበት አሏችሁ። ግን ሰሞኑን እንዴት ነው? ከቁጥሩ ነው ከጆሯችን? ተበጀተ ሲባል የምትሰሙት የቢሊዮን ብዛትና ዕዳችን እየተመጣጠነላችሁ ነው?›› ትላለች። ‹‹ማንን ነው? ይኼ ጆሮዬ እኮ እንቢ አለ በቃ፤›› ብለው አዛውንቱ ከጎናቸው ያለውን ቢጠይቁት፣ ‹‹እንኳን ቀረብዎ፣ እንኳንም አልሰሙ፡፡ የሰሞኑን ነገራችንን ቢሰሙት ኖሮ ያብዱ ነበር፤›› ብሏቸው ሲያበቃ፣ ‹‹ምነው ጆሮ እንደሚያከራክር ሁሉ ሆድም የሚያንገራግር ሆኖ ቢፈጠር?›› አለን ወደ እኛ ዞሮ። ወይ ታክሲና አፍ!

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ወያላው ሒሳቡን ተቀብሎ መልሳችንን አድሎ ከጎኑ ክሩን ከሚያስደግፍባት መቀመጫ ላይ ለሚተዋወቃት ቆንጆ ሰፋ ያለ ቦታ መርቶ፣ ‹‹እንዴት ነሽ እባክሽ?›› ይላታል። ‹‹እባክህ ጋብዘኝ፤›› ትለዋች ደኅንነቱን ትታ። ‹‹አንቺ በቃ ካለ ጋብዘኝ አታውቂም?›› ይላታል። ‹‹አንተስ ሰላም በጠፋበት በዚህ ጊዜ፣ አሥር ጊዜ እንደ ጀማሪ አፍቃሪ ደህና ነሽ ማለቱ አይሰለችህም?›› አለችው። ‹‹እንኳን አሥር መቼ ሁለት ጊዜ ጠየቅኩሽ?›› ሲላት፣ ‹‹ትናንት ተገናኝተን ጠይቀኸኝ መልሼልሃለሁ። አለቀ! ወር ሳይሞላህ እንዳትጠይቀኝ፤›› ብላ ተቆናጠረችበት፡፡ ‹‹ጉድ ነው እንደ ቤት ኪራይ ክፍያ ጤና ይስጥልኝም ወር በገባ ሆነ ደግሞ?›› ብሎ አጠገቧ ተጨናንቆ የተቀመጠ ወጣት አሽሟጠጠ። ‹‹አዎ። በኪራይ ኖረን በመዋጮ እየተቀበርን እስኪ አሁን በየቀኑ ጤና ይስጥልኝ ስንባባል አያቅርም?›› አለችው መለስ ብላ። ‹‹አይምሰልሽ! ደሃ ከጤናው በቀር ሀብት የለው፤›› ወያላው ስብከት ጀመረ። ‹‹እኔስ ገንዘብ ቢሰጠኝ ነበር የምመርጠው። ጤና በኪራይ ቤት በቀን አንዴ እየተበላ በራሱ ካንሰር በለው፡፡ በዚህ ላይ አስደንጋጭ ወሬ እየሰሙ መኖር ከካንሰር በላይ ነው፤›› ብሎ መሀል ረድፍ የተሰየመ ኮልታፋ ጨዋታውን አፋፋመው።

‹‹ኧረ ተመስገን ነው እናቴ። ይኼንንስ ማን አየብን?›› ብለው አጠገቡ የተቀመጡ አንዲት አዛውንት ሲናገሩ፣ ‹‹ድሮስ ማን ያይብናል እማማ? ነው ወይስ ጉዳይ ለማስፈጸም የሕይወት ጉቦ ስጡን መባል ተጀመረ?›› አላቸው። ‹‹የምን ሕይወት? እኮ ይኼ እስትንፋሴን ማለትህ ነው?›› አዛውንቷ የምራቸውን ደነገጡ። ‹‹እህ ሌላ ምን አለ?›› አላቸው ግራ ገብቶት ግራ እያጋባቸው። ‹‹ሞልቶ! እስትንፋስማ የበግ አለ፣ የበሬ አለ፣ የፍየል አለ. . .›› ሲሉ ፈገግ አስባሉን። ይኼን ጊዜ ኮልታፋው፣ ‹‹አይ እማማ! እሱማ ድሮ በደጉ ጊዜ ቀረ። አሁን ማን ይሙት ሕይወታችንን እንደ ልባችንና እንደ ለመድነው እንዳሻን የምናዝበት ቢሆን ኖሮ የገዛ ወገናችን እየበላን ይጨርሰን ነበር?›› ሲላቸው እስኪያስነጥሳቸው ከት ብለው ሳቁ። ‹‹ቆይ ግን የሰው ሕይወት በመብላት ሰላም ይኖራል እንዴ? ግራ አጋባን እኮ ሰውዬው!›› ስትል ደግሞ አንዷ፣ ‹‹ኮሌራ በወረርሽኝ መልክ ተቀስቅሶ እናንተ ድምፅ የሌለውን ሞት ታነሳላችሁ?›› አለ ጎልማሳው። ‹‹ይደንቃል እንዴ ይኼ? ሲከፋንና ሞት ደጃችን ላይ ሲንጎማለል አይደለም ኮሌራ ሌላ ነገር ጠቅልሎ ቢውጠን ይገርማል?›› ብላ ወጣቷ ስትንጣጣ የመለሰላት አልነበረም። ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› ብሏል። እኛም በድንጋጤ ግር ብለን እንደተሳፈርነው ግር ብለን ወርደናል፡፡ የዘመኑ ፖለቲከኞችም ግር ብለው ተደምረው አይደል እንዴ ግር ብለው ተቀንሰናል ሲሉ የነበሩት? የሆነስ ሆነና ሞት እንዲህ ረከሰ እንዴ? መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት