Wednesday, December 6, 2023

‹‹የኢትዮጵያን ሽግግር ለመደገፍ የያዝነውን ዕቅድ በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን›› ኒኮላስ ባርኔት፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ የፕሬስ ኦፊሰር የነበሩ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኒኮላስ ባርኔት በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በፕሬስ ኦፊሰርነት ለሦስት ዓመታት አገልግለው የኢትዮጵያ ቆይታቸውን ሰሞኑን አጠናቀዋል፡፡ ባርኔት በኢትዮጵያ ቆይታቸው በርካታ ሰዎችን እያገኙ ያነጋግሩ ነበር፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎችም በመዘዋወር ስለኢትዮጵያ የሚችሉትን ሁሉ ለማወቅ ሞክረዋል፡፡ ቆይታቸውን አጠናቀው አሸኛኘት ከተደረገላቸው በኋላ ወደ አገራቸው የተመለሱት ባርኔት ከብሩክ አብዱ ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢትዮጵያ ስለነበራቸው ጊዜ፣ እየተካሄደ ስላለው ለውጥ፣ ስለሚዲያ ነፃነት፣ ስለመጪው ምርጫ፣ ብሎም የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ስለሚያከናውናቸው የልማት ተግባራት ያወሳሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣትዎ በፊት ስለነበረዎት ግምትና ምልከታ በማንሳት እንጀምር፡፡ ኢትዮጵያ ስደርስ ምን አገኛለሁ ብለው አስበው ነበር? የገመቱትንስ አግኝተዋል? ወይስ የተለየ ነገር ነው የገጠመዎት?

ባርኔት፡- በአፍሪካ መሥራት አለብኝ ብዬ የወሰንኩት በቀድሞዋ የሶቭየት ኅብረት ሦስት አገሮች ተዘዋውሬ ከሠራሁ በኋላ ነበር፡፡ እናም ከኢትዮጵያ አስቀድሜ በታጂኪስታን፣ በሩሲያና በአዘርባይጃን ሠርቻለሁ፡፡ እነዚህ አገሮች በራሳቸው የተለዩ ቢሆኑም፣ ፍጹም ልዩ የሆነ ሥፍራ እፈልግ ነበር፡፡ ይኼንን ስወስን ስለኢትዮጵያ እምብዛም አላውቅም ነበር፡፡ በልጅነቴ አባታችን በዋሽንግተን የሚገኝ የኢትዮጵያ ምግብ ቤት ወስዶን ከእህቴ ጋር ለየት ባለው አመጋገብ ዘይቤ በእጃችን እንድንመገብ አድርጎን ነበር፡፡ ያኔም የመጀመርያው የኢትዮጵያ የሆነ ነገር ያየሁበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ወደዚህ ስመጣ መጀመርያ የተረዳሁት ጉዳይ የኢትዮጵያን ብዝኃነት ነበር፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሬ ለማየት በመቻሌም እጅግ ዕድለኛ ነኝ እላለሁ፡፡ ሁሉንም ክልሎች ጐብኝቻለሁ፡፡ አንዳንዶቹን እንዲያውም በተደጋጋሚ፡፡ በርካታ ሰዎችን አግኝቻለሁ፡፡ በርካታ ባህሎችንም ማወቅ ችያለሁ፡፡ ይኼ በእጅጉ የሚያስደስት ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ ባህላዊ ቅርሶች፣ ታሪክ፣ እንዲሁም ተፈጥሯዊ ብዙኃነቱ አስደናቂ ነው፡፡ ቀደም ብሎ እንዳልኩትም በእጅጉ ዕድለኛ ነኝ፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ብቻ ምን ማለት እንደሆነ መረዳት የሚቻለውን የኢትዮጵያን ታሪክ ማወቅ መቻል በእጅጉ አስደሳች ነው፡፡ ይኼም ከቅድመ ክርስትና የአክሱም ሥልጣኔ እስከ ቀደምት ክርስቲያናዊ ሥልጣኔ፣ ብሎም ከመካከለኛው ምሥራቅ ሸሽተው የመጡት ሙስሊሞች ታሪክ፣ እንዲሁም በጅማ የሚገኘው የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት ድረስ የህንድና የፓስፊክ አካባቢዎች ተፅዕኖዎች ምልክት የሚታይበት ነው፡፡ ምንም እንኳን ከውቅያኖስ አጠገብ ያለች አገር ባትሆንም የእነዚያ ዓይነት ምልክቶች ግን በሰፊው ይታያሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከጥንታዊ ታሪክ ጋር ያላትን ቁርኝት፣ ከወደ ሰሜን አካባቢ የነበረው የንግድ ግንኙነት፣ እንዲሁም ከጥንታዊ ሥልጣኔዎች ጋር ያላት ቁርኝት ሲታይ ምንም እንኳን አገሪቱ በበርካታ ምክንያቶች ተራራ ላይ ያለች ብትሆንም ከዓለም ጋር ግን በእጅጉ የተሳሰረች ነች፡፡ አልማዝ የምትባል አትሌት ስሟ ምን ማለት እንደሆነ አንዴ ጠይቄ በእንግሊዝኛ ዳይመንድ እንደሆነ ሲነግሩኝ አስደንቆኝ ነበር፡፡ በአዛርባይጃንም ተመሳሳይ አጋጣሚዎች ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ በዚህኛው የዓለም ጥግ፣ አዘርባይጃን ደግሞ በካስፒያን ባህር ዳርቻ ከማዶ ብትገኝም ተመሳሳይ ስሞችን መጋራታቸው ንግድ ያመጣውን  ተፅዕኖ ያመላክታል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያን በአብዛኛው ከግምቴ በላይ ሆና አግኝቻታለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት ወቅት ለኢትዮጵያም ፈታኝ ነበረ፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር ስለመቀጠሏ እንኳን ጥርጣሬን የሚያንፀባርቁ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰነዘሩ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሳለች በመምጣትዎ ምን ዓይነት ዕሳቤ እንዲይዙ አደረገዎት?

ባርኔት፡- እዚህ ስደርስ ነገሮች እጅግ ከባድ ነበሩ፡፡ እኔ በደረስኩ በሁለት ወራት ውስጥ የመጀመርያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ነበር፡፡ በእርግጥም ኤምባሲው ሁሉንም ክስተት ሲከታተል ነበር፡፡ ሆኖም እንዴት ወደኋላ መለስ ብሎ መመልከት ይቻላል? ያለፈውን ጊዜ በማየት እንዴት መተንተን ይቻላል? እውነታው ኢትዮጵያውያን ድምፃቸውን አሰምተዋል፣ የተለየ ነገርም እንዲመጣ ጠይቀዋል፡፡ ይኼ መልዕክታቸውም ከበርካታ ዓመታት በኋላ ግቡን መትቷል፡፡ አሁን የት እንደምንገኝ ማየት ነው እንግዲህ፡፡

ይኼ ማለት ግን አሁን ፈተናዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ከሦስት ዓመታት በፊት ልናየው ከምንችለው በላይ አሁን በርካታ የስኬት ዕድሎች አሉ፡፡ ይኼ ነው በእጅጉ የሚያስደስተው፡፡ ለማመን የሚከብድም ነው፡፡ እነዚህ ዕድሎችን ማየት ተጀመረ እንጂ አላለቀም፡፡ ባለፉት 14 ወራት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ አመራር አማካይነት አስደናቂ ለውጦችን ዓይተናል፡፡ እነዚህ ለውጦች ስንፈልጋቸው የነበሩ ናቸው፡፡ ግፊት ስናደርግም ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ ፍጥነት ይሆናሉ ብለን አልጠበቅንም፡፡ ስለዚህም  በእጅጉ አስገርሞናል፡፡

እኛ እንደ አሜሪካ መንግሥት አገሮች ምን ዓይነት ፖሊሲ መከተል እንዳለባቸውና በየት አቅጣጫ መጓዝ እንዳለባቸው መናገር አንፈልግም፡፡ በእርግጥ እንደ ዴሞክራሲና የገበያ መር ኢኮኖሚ የመሳሰሉት እሴቶቻችን መልካም እንደሆኑ እናምናለን፡፡ ነገር ግን አሁን እያደረግን ያለነው ታሪካችንንና ልምዳችንን ማጋራት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን እንዲረዱት የምፈልገው  አንድ ጉዳይ ግን፣ ፈተናዎች አሉ ማለት ውድቀት ማለት አይደለም፡፡ ፈተናዎች የተለመዱ ናቸው፡፡ በአሜሪካ ሕገ መንግሥታችን 240 ዓመታት የቆየ ቢሆንም ፈተናዎች ሁሌም ሊያጋጥሙን ይችላሉ፡፡ የዴሞክራሲ ቁልፉ ግን ሰዎች በነፃነት ይኼንን አይደለም የምንፈልገው፣ ይኼ ልክ አይደለም ማለት እንዲችሉና ለፈተናዎቹ ምላሽ መስጠት የሚችሉበትን አቅም መገንባት ነው፡፡ ይኼም ሕዝቡ የተለየ ነገር እንፈልጋለን ሲል ምላሽ መስጠት የሚችል መንግሥታዊ መዋቅር እንዲኖር ማስቻል ነው፡፡ እናም የባርያ ንግድን የተሻገርነው በዚህ ዓይነት ሒደት ነው፡፡ እርግጥ ነው የእርስ በርስ ጦርነት ማድረግ ነበረብን፡፡ ግን ከጅምሩ ይኼ ልክ አይደለም፣ ከአሁን በኋላ ይኼንን ማድረግ የለብንም ባሉ ሰዎች ነው፡፡ ሴቶች የመምረጥ መብትን የተጎናፀፉት በዚህ መንገድ ነው፡፡ ሴቶች እኛ ለምንድነው የማንደመጠው አሉ፡፡ እስከሚፈጸምም ድረስ ታገሉና ለውጡን አመጡ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ የነበሩ የሲቪል መብቶችን እንቅስቃሴ የተሻገርነው እንዲሁ ባለ ሒደት ሲሆን፣ ሰዎች ጉዳዮቻቸውን የመናገርና የመግለጽ መብት ነበራቸው፡፡ ተቋማቶቻችንም የሕዝብ ተጠያቂነት ስላለባቸው የሕዝብ ጥያቄዎችን ተግባራዊ ምላሽ ለማሰማት ያስችላሉ፡፡ ለኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋትና ጠቃሚው ይኼ ነው፡፡ ፈተናዎች ሊኖሩ አይገባም ሳይሆን፣ እነዚህን ፈተናዎች ለመመለስ የሚያስችሉ ተቋማት መገንባት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በድጋሚ እርስዎ ወደ ኢትዮጵያ ወደመጡበት ወቅት ልመልስዎትና ወቅቱ በአሜሪካ የአስተዳደር ለውጥ የተደረገበት ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን የመጡበት ጊዜ ነበር፡፡ የፕሬዚዳንት ትራምፕ አዲሱ አስተዳደር አፍሪካን በተመለከተ ያለውን ፖሊሲ በግልጽ ባለማስቀመጡ፣ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ዘንድ ግራ መጋባት ፈጥሮ ነበር፡፡ ይኼ በኢትዮጵያ በምታደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ አሳድሮበታል?

ባርኔት፡- በእርግጥ በአሜሪካ ያለው አስተዳደር ማንም ይሁን ማን ቅድሚያ ለምንሰጣቸው ጉዳዮች ትኩረት እናደርጋለን፡፡ ይኼም የሽግግር ሒደቶቻችን አንዱ አካል ነው፡፡ ነገር ግን ላስተዋለው ሰው የእኛ ፖሊሲዎች ባለፉት ሁለት አስተዳደሮች ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያ ቀድሞ በነበሩት ጊዜያትም ጭምር ቋሚና ተገማች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የነበረው የአሜሪካ ፖሊሲ ዴሞክራሲያዊ ዕድገት፣ ኢኮኖሚያዊ ብልፅግናና አካባቢያዊ ደኅንነት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ እነዚህ አሁንም ድረስ አልተለወጡም፡፡ እኔ እዚህ ከመጣሁ ወዲህ የተቀየረ ነገር ቢኖር፣ እኛ ልንሳተፍበት የምንችልበትን ዘርፍ ተሳትፎ ሊያሰፋ የሚችል ዕድል ነው፡፡ በሪፎርሙ አማካይነት በርካታ የተሳትፎ ዕድሎችን አግኝተናል፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት ማግኘት የማይቻሉ በርካታ ዕድሎች ተፈጥረዋል፡፡ በኢትዮጵያ አቅም ግንባታ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ የሚያስችለን አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡

አሜሪካ ለኢትዮጵያ በምታደርገው ድጋፍ ለረዥም ጊዜያት ትልቋ የሁለትዮሽ ድጋፍ ሰጪ ነች፡፡ ድጋፍ በማለት የምናገረው እኛ እውነተኛ ድጋፍ የምንለውን የአቅም ግንባታ ሥራን ይመለከታል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ በኢትዮጵያ ያፈሰስን ሲሆን፣ ገንዘቡም ለተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ የዋለ ነው፡፡ በትምህርት ዘርፍ የምናደርገው ድጋፍ ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ነው፡፡ አሁን በአገሪቱ በቀደምትነት የሚጠቀሱትን የሃሮማያና የጅማ ዩኒቨርሲቲዎችን ለማቋቋም አሜሪካ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጋለች፡፡ የምግብ ዋስትናን ለማስፈንም እየረዳን እንገኛለን፡፡ አስቸጋሪና የእኛ ድጋፍ በእጅጉ በሚፈለግበት የሞትና የሽረት ጊዜ ሳይቀር ከኢትዮጵያ ጎን የምትቆመው አሜሪካ ናት፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን አርብቶ አደሮች እንደ ድርቅ ያሉ ችግሮችን መቋቋም እንዲችሉ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረግን እንገኛለን፡፡ አርሶ አደሮች ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ድጋፍ እያደረግን እንገኛለን፡፡ በቅርቡ ዓለም አቀፋዊ የምግብ ዋስትና ስትራቴጂ ይፋ ያደረግን ሲሆን፣ ከዚህ ጎን ለጎን አርብቶ አደሮች እንደ ድርቅ ያሉ ችግሮችን መቋቋም እንዲችሉ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረግን ነው፡፡ አርሶ አደሮች ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ድጋፍ እያደረግንም ነው፡፡ በቅርቡ ዓለም አቀፋዊ የምግብ ዋስትና ስትራቴጂ ይፋ ያደረግን ሲሆን፣ ከዚህ ተጠቃሚ ከሚሆኑ ጥቂት አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡

በእነዚህ ሁሉ ዘርፎች ድጋፍ እያደረግን ብንገኝም፣ ምርጫ ለማካሄድ አቅምን ለማሳደግ ድጋፍ የምናደርግባቸውን ሁኔታዎች እያጤንን እንገኛለን፡፡ ኢትዮጵያ እንዴት ተዓማኒና ፉክክር የሚታይበት ምርጫ አከናውና ኢትዮጵያውያን ከምርጫው በኋላ ድምፃቸው እንደተሰማ አምነው እንዲቀበሉት ልናደርግ እንችላለን? ምርጫ በውጤቱ ደስተኛ መሆን ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ሒደቱ የሚጠበቅበትን ደረጃ መከተሉንና በዚህ ሒደት ምርጫው መካሄዱን ማመንና መቀበል ነው፡፡ አሁን ደግሞ ለሚዲያው የበለጠ ድጋፍ ማድረግ የምንችልበት ዕድል አለ፡፡ እኔ እዚህ በቆየሁባቸው ዓመታት ከ500 በላይ ለሚሆኑ ጋዜጠኞች ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ አሁን ሰፊ ምኅዳር ስላለንም ይኼንን በሰፊው ማድረግ የምንችልበትን መንገድ እያየን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ በኢትዮጵያ ሁለት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በእጅጉ ሲጠበቅ የነበረው ለውጥ መጣ፡፡ ይኼ ለውጥ በኢትዮጵያና በአሜሪካ መንግሥታት ግንኙነት ላይ ምን አመጣ?

ባርኔት፡- እዚህ ላይ ጥቂት ወደኋላ መለስ ብለን መመልከት የሚያስችለን ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ለዚህ ሁሉ ሁነት መሠረቱ የተጣለው ቀደም ብሎ ነበርና፡፡ ኢትዮጵያውያን በነበረው ሁኔታ ደስተኞች እንዳልነበሩ በአደባባይ ወጥተው ሊያሰሙ እስካሁን ድረስ ትልቁና ዋነኛ ብለን የምናስበውን ውሳኔ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አሳለፉ፡፡ ይኼም እኔ ከሥልጣን ለቅቄ ለሪፎርሙ የተመቻቸ መደላድል መፍጠር አለብኝ በሚል የሆነ ነው፡፡ ይኼ እጅግ የሚደነቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክም እንዲህ ያለ ተምሳሌታዊ አጋጣሚ ሊጠቀስ የሚችል የነበረ አይመስለኝም፡፡ በወቅቱም እኛ ኢትዮጵያ የትኛውን አቅጣጫ እንደምትከተል ለመረዳት በጥሞና ስንከታተል ነበር፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ከዚህ ቀደሙ ጭቆናን በማጠናከርና በማስፋት ለማፈን ትመርጣለች? ወይስ መንግሥት በቃኝ ጊዜው አሁን ነው ብሎ ወደ ተቀባይ   ለውጥ ይሄዳል ወይ? የሚለው ጥያቄ ነበር፡፡ እናም በወቅቱ ሁለተኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ ጠንከር ያለ መግለጫ አውጥተን ነበር፡፡ ምክንያቱም ያ ትክክለኛው መንገድ አይደለምና፡፡ የአሜሪካ አቋም ምን እንደሆነ በግልጽ ማሳወቅ ያለብን ጊዜ እንደነበር አምነን ነበር፡፡ ስለዚህም በእጅጉ እንደማንስማማ አስታወቅን፡፡ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው የበዛ ነፃነት እንጂ ያነሰ ነፃነት አልነበረም፡፡ አቋማችን ያ ነበር፡፡ በወቅቱም ገና ውሳኔዎች እየተሰጡ ስለነበር መግለጽ ነበረብን፡፡ በሁለተኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት መንግሥት በማን ሊመራ እንደሚገባው ስምምነት ላይ አልተደረሰም ነበር፡፡ እኛም ኢትዮጵያ ይኼ ዕድልሽ ነው ማለት እንደነበረብን አመንን፡፡ የተለየ ነገር ለማድረግ ዕድል  አለ ስንል ይኼንኑ ተቀብለው አደረጉ፡፡ ከመጀመርያው ቀን አንስቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የተለዩ ምርጫ እንደነበሩ ግልጽ ነበር፡፡ እኛም ኢሕአዴግ ጊዜው አሁን ነው ብሎ ለለውጥ መዘጋጀቱን ያየንበት ነበር፡፡

ይኼንን ተከትሎ የመጣው ፈጣን  ለውጥ እጅግ ግሩም ነበር፡፡ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ ጋዜጠኞችን መፍታት፣ ብሎም በውጭ አገር ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ማድረግ እጅግ የሚደነቁና ትልቅ ለውጥ ያመጡ ነበሩ፡፡ የግል ባለሀብቶችን ለማበረታታትና የመንግሥት ተቋማትን ወደ ግል ለማዛወር የተላለፈው ውሳኔ፣ ከኤርትራ ጋር ከተደረገው ዕርቅ ጋር ተደምሮ መጪውን ጊዜ የሚቀይሩ ውሳኔዎች ነበሩ፡፡ አሁን ከአንድ ዓመት በኋላ የወደፊቱን መንገድ ቀና ብለን ስንመለከት፣ እስካሁን የተከናወኑ ሥራዎች ምን እንደሆኑ ማስታወስ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ይኼ ይበልጥ  ጠቃሚ የሚሆነው የተፈጠረው የመጀመርያው ነገር ኢትዮጵያ በየት አቅጣጫ መጓዝ እንዳለባት መነጋገር የሚቻልበትን ምኅዳር መፍጠርና መወያየት መቻል በመሆኑ ነው፡፡ እነዚህ የመጀመርያ ዕርምጃዎች ናቸው እነዚህን ሁሉ ዕድሎች የፈጠሩት፡፡ በአሜሪካም ቢሆን ያለው ይኼ ዕድል ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለንን ተሳትፎና መዋዕለ ንዋይ በድጋሚ ለማጤን ያስቻለን ለውጥ ነው፡፡ በተመሳሳይ ግን የትኛውም ሽግግር የራሱ የሆኑ ፈተናዎች ይኖሩታል፡፡ በርካታ ሥጋቶችም ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ በአሜሪካም ይኼ ያለ ነው፡፡ ልዩነቱ አሁን ኢትዮጵያ ዕድሉ አላት፡፡ ነገሮችን በልዩ መንገድ የማስኬድ ዕድል አለ፡፡ እነዚህ ፈተናዎች በመጡ ቁጥር ግን ምኅዳሩ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ይኼንን መድረክ በመጠቀም ገንቢ በሆነ ውይይት ተሳትፈው፣ የአገሪቱን የወደፊት አቅጣጫ መቀየስ መቻል አለባቸው፡፡ ሙሉ በሙሉ ስምምነት መኖር ግድ አይልም፡፡ ሁሉም እኩል ምልከታና አስተሳሰብ ሊኖራቸው ይገባል ማለት አይደለም፡፡ የጋራ መድረክ መኖሩና የሚፈለገውን ለማሳካት መወያየት መቻሉ ነው ዋናው፡፡ አሜሪካ ፍፁም አይደለችም፡፡ ፍፁም ነች የሚል ሐሳብም አንፀባርቀን አናውቅም፡፡ ሆኖም ልናድግና ስኬታማ ልንሆን የቻልነው ስለፈተናዎቻችን መነጋገርና የጋራ መፍትሔ መስጠት ስለቻልን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሁለተኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ ስላወጣችሁት መግለጫ ጠቅሰውልኛል፡፡ ሆኖም አቋማችሁ በኢትዮጵያ መንግሥት በበጎ የታየ አልነበረም፡፡ በወቅቱ ምን ነበር የተፈጠረው?

ባርኔት፡- እኔ መቼስ ስለኢትዮጵያ መንግሥትና በወቅቱ ስለተሰማቸው ነገር መናገር አልችልም፡፡ ማለት የምችለው እኛ ያደረግነው ማድረግ ያለብንን ነው፡፡ በዚህም አቋማችን ፀንተን ነበር፡፡ የምታስታውስ ከሆነ እንዲያውም የአሜሪካ የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርጉ ያንኑ ነው የደገሙት፡፡ ይኼ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ነበርና በዚያው ፀናን፡፡ ተመልሼ ሳየውም ትክክለኛ ዕርምጃ ነበር፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ለውጡ እንዲመጣ ባደረጉት ጥረት መሞገስ አንፈልግም፡፡ ሆኖም የእኛ አቋም ምን እንደነበር በግልጽ መልዕክት ማስተላለፍ አስፈላጊ ነበር፡፡ ምልከታችንን በግልጽ አስቀመጥን፡፡ ኢትዮጵያም ለዘላቂ ለውጥ ዕድሎችን በሚያመቻች መንገድ ላይ በመሆኗም እጅግ ደስተኞች ነን፡፡

ሪፖርተር፡- ከአንድ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ለመጣው ለውጥና ሽግግር አሜሪካ ድጋፍ ታደርግ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሆኖም የአሜሪካ መንግሥት እጅ ረዥም እንደነበር፣ እንዲያውም በለውጡ ከፍተኛ ሚና ከመጫወት አንስቶ ለውጡን በራሱ መንገድ እንዲሄድ የማድረግ ተፅዕኖ ነበረው ይባላል፡፡ አሜሪካ የወቅቱ በኢትዮጵያ የነበራት ተሳትፎ እስከ ምን ድረስ ነበር?

ባርኔት፡- ይኼ አስቂኝ ነው፡፡ እዚህ ላይ ቀጥተኛና ያልተድበሰበሰ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ይኼ የተሻለ መልስ ስለሚሆን፡፡ እኛ ያደረግነው በግልጽ ያያችሁትን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ለውጦች እንዲመጡ በግልም ይሁን ሕዝባዊ በሆኑ ቦታዎች ድጋፋችንን ስንገልጽ ቆይተናል፡፡ ይኼንንም ስናደርግ እንዴት ከኢትዮጵያ ፍላጎት ጋር እንደሚጣጣምና አገሪቱ የተሻለ አካታች ፖለቲካና ሰፊ መሠረት ያለው ብልፅግና ብቻ ሳይሆን፣ ድርጊቶች ምን ያህል ለዘላቂ መረጋጋት ወሳኝ እንደሆኑም ጭምር ስንናገር ነበር፡፡ ይኼ ያልኩህ ሁሉ ምኑም አዲስ አይደለም፡፡ እውነት ለመናገር ግን እነዚህ ሁሌም የእኛ ፖሊሲዎች ሆነው ሳሉ፣ ውሳኔ ማስተላለፍ የሚያስችለን ሥልጣን ቢኖረን ኖሮ እስካሁን ለምን ቆየን? እውነታው ግን አይደለም እንዲህ አይደለም የሚሠራው፡፡ ይኼንን ያህል ቀላል አይደለም፡፡ ማወቅ የሚገባን ነገር ቢኖር ግን፣ ይኼ ለውጥ የመጣው ኢትዮጵያውያን ስለፈለጉት ነው፡፡ ነጥቡ ይኼ ነው፡፡ መደገፍ በምንችለው ሁሉ ደግፈናል፣ ልምዳችንንና እሴቶቻችንን አካፍለናል፣ ለመንግሥትም ሆነ ለሕዝቡ፡፡ አሁን ባለው ዕድል እጅግ ደስተኞች ነን፡፡ ከዚህ የዘለለ ጉዳይ አለ ብሎ ማሰብ ግን የሚያስቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ሐሳብ ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ በወቅቱ የነበረው እርስዎ የጠቀሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲለርስንን ጉዞ ጨምሮ፣ ባልተለመደ ሁኔታ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ወደ ኢትዮጵያ እግር ማብዛታቸው ነው፡፡ ይኼ ምንም የሚያመላክተው ነገር የለም ይላሉ?

ባርኔት፡- በጭራሽ፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚያደርገው የውጭ አገር ጉዞ እጅግ ቀደም ብሎ ነው የሚታቀደው፡፡ እናም ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ማቆራኘቱ ትክክል አይደለም፡፡ እርግጥ ኢትዮጵያ እጅግ ጠቃሚ አጋራችን ናት፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰንም በወቅቱ ለሥራ አዲስ እንደነበሩም ማስታወስ ይገባል፡፡ የአፍሪካ የመጀመርያ ጉዟቸውን እያደረጉ ስለነበርም፣ ኢትዮጵያ በእርግጠኝነት ከሚመረጡ አገሮች ዝርዝር ውስጥ መኖሯ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ክስተት ውስጥ ሌላ ታሪክ መምዘዝ አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲለርሰንም ቢሆኑ በኢትዮጵያ የበለጠ ነፃነት እንጂ አፈና እንደማያስፈልግ የአሜሪካን አቋም በአደባባይ በግልጽ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን እንደሚባለው አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ሌላ ጉዳይ ስንሸጋገር በኢትዮጵያ የተደረገውን የአስተዳደር ለውጥ ተከትሎ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የተፈጠረው አንድ ትልቅ ክስተት፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት ዕርቅና የሰላም ጅማሮ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ዕርቁን በእጅጉ የጓጓችለትና ያፈጠነችው ቢሆንም፣ አሜሪካ ግን በተለይ በኤርትራ ላይ ተጥሎ የቆየውን ማዕቀብ ማንሳት በተመለከተ በእጅጉ ጠንቃቃ ነበረች፡፡ አሜሪካ ለምን ነበር የማዕቀቡን መነሳት በተመለከተ መቆጠብን የመረጠችው?

ባርኔት፡- በወቅቱ ዕርቁ ስለሚያመጣው ዕድል ብሎም በሒደቱ ደስተኛ መሆናችንን አሳውቀናል፡፡ አሁንም እንደዚያው ነው የሚሰማን፡፡ ዋናው ጉዳይ የነበረው ኤርትራን በተመለከተ ሌላ ሥጋቶች በመኖራቸው ይመስለኛል፡፡ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ቃል አቀባይ ሆኜ ግን ከዚህ በላይ መናገር አልችልም፡፡ ነገር ግን ሐሳቡ የነበረው ሙሉውን ሥዕል መመልከት አለብን የሚል ነው፡፡ ስለዚህም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ጥረት በማድነቅ ዕርቁን በመቀበል፣ ለሰፊው ቀጣና የሚሰጠውን ጠቀሜታ አድንቀን ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ይኼ ዕርቅ ለሁለቱ አገሮችም ሆነ ለሰፊው ቀጣና ቀጣይነት ያላቸውን ጥቅሞች ያስገኛል የሚል ተስፋ አለን፡፡ ሆኖም እውነት ነው አሁንም ድረስ ሥጋቶች አሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- መለስ ብለን እስቲ የአሜሪካ መንግሥት ስላሉት እንቅስቃሴዎች እናንሳ፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ፕሮግራሞች በትምህርት፣ በግብርና፣ በመልካም አስተዳደር፣ በሴቶች አቅም ግንባታና በበርካታ ዘርፎች  ድጋፍ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ሆኖም በማዕከል የማይመሩና የተበታተኑ፣ ትኩረትና የገንዘብ ድጋፎች የማያገኙ እንደሆኑ ይተቻሉ፡፡ ስለዚህ ትችት ምን ይላሉ?

ባርኔት፡- በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ ማውጣት ስትችል፣ በአንድ ጊዜ በርካታ ሥራዎችን ማከናወንና በእኩል ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን ይቻላል፡፡ በእርግጥ እንደ ትምህርት ባሉና ለሰባት ማሊዮን ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የንባብ መጻሕፍትን በምናቀርብባቸው ዘርፎች ያለንን ውጤት ስናይ ይኼንን ትኩረት የሌለው ማለት አያስችሉም፡፡ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶቻችንም ምን ያህል ለውጥ እያስመዘገብን እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር እየቻሉ ካሉ አገሮች አንዷ  ለመሆን ከጫፍ ደርሳለች፡፡ ይኼ ድንቅ ነው፡፡ ይኼ የሆነው በከፊል ከኢትዮጵያ ጋር ባለን የላቀ ትብብር ቢሆንም፣ ያሉ ፈተናዎችን ለመጋፈጥና ለመወጣት በምናደርገው እንቅስቃሴ ትኩረት የምንሰጥና ግብ ተኮር በመሆናችንም ነው፡፡ ወደ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ስንመጣ እነዚህ አዳዲስ ያገኘናቸውን ዕድሎች ናቸው፡፡ ነገር ግን በተለይ ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ሊኖር የሚባውን ተቋማዊ ጥንካሬ ለማምጣት የተቋማት ግንባታን በትኩረት እንደግፋለን፡፡ እዚህ ላይ ፍላጎታችን መራጩ ድምፁን ሰጥቶ ሲወጣ ድምፁ  እንደተቆጠረ በመተማመን ውጤቱን መጠበቅ እንዲችል ነው፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ያለን ትልቅ የተሳትፎ አድማስ መመልከትና መረዳት ከባድ ነው፡፡ ማንም ከምንሠራው ጋር የሚስተካከል እየሠራ አይደለም፡፡ የምንሠራው አስደናቂ ለውጦችን እያመጣ ነው፡፡ በዚህ አገር ሕይወት እየቀየርን እንገኛለን፣ እጅግ ጠቃሚና አሸጋጋሪ በሆነ መንገድ፡፡

ሪፖርተር፡- እንደጠቀሱልኝ አንዱ የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ ቀጣዩን የምርጫ ሒደት ይመለከታል፡፡ አሜሪካ ቀጣዩን ምርጫ እንዴት ነው የምትደግፈው? ምርጫውን ለማካሄድ ምን ዓይነት ፈተናዎች ሊኖሩ ይችላሉ ይላሉ?

ባርኔት፡- ወደፊት ሩቅ ሄጄ  መናገር ባልፈልግም፣ የኢትዮጵያን ሽግግር ለመደገፍ የያዝነውን ዕቅድ  በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን፡፡ ምርጫ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጋር አንድ ላይ ለመሥራት ፍላጎታቸውን እየለየን እንገኛለን፡፡ ይኼም ቀጣይ ድጋፋችን ምን መሆን እንዳለበት ለማወቅ የሚረዳን ይሆናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -