አምባራይሌ አጠቃላይ ቁመናው ከቀንዱ ጥምዝ ጋር የአጋዘን ይመስላል፡፡ በመጠኑ ግን አነሰ ያለ ነው፡፡ የወንዱ ክብደት ከ92 እስከ 108 ኪሎ ግራም፤ የሴቶቹ ደግሞ ከ56 እስከ 70 ኪሎ ግራም ይሆናል፡፡ ሴቶቹና ወጣቶቹ የቀይ ቡኒ ሲሆኑ፣ ወንዶቹ ደግሞ ሰማያዊ የመሰለ ግራጫ ናቸው፡፡ ይህም ቀለማቸው ዕድሜአቸው እየገፋ ሲሄድ እየጠቆረ ይሄዳል፡፡ ጐላ ብለው የሚታዩ ነጫጭ መስመሮች ከጀርባቸው ወደ ደረትና ሆዳቸው ይዘልቃሉ፡፡ ጫፉ ቁር የሆነ ጐፈሬም ጭራ አላቸው፡፡ ቀንድ ያላቸው ወንዶቹ ብቻ ናቸው፡፡ ሁለት ተኩል ጥምዝ ያለው ቀንድ አላቸው፡፡ ደረትና ሆዳቸው ነጣ ያለ ነው፡፡ በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ፣ በኬኒያና በታንዛኒያ ብቻ ይገኛሉ፡፡ የሚኖሩት ከባሕር ወለል በላይ፣ ከ1,200 ሜትር ከፍታ በታች በሆኑ ቦታዎች ነው፡፡ እንዲህ ያለውም አካባቢ የግራርና የቆላ አባሎ (Commiphora) ዛፎች ያሉበት ነው፡፡
- ሰለሞን ይርጋ (ዶ/ር) ‹‹አጥቢዎች›› (2000)