በተለያዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ስለተወጠረችው ኢትዮጵያ ብዙዎች ሲያወሩ ታሪኳ በውጣ ውረድ ብቻ የተሞላ አለመሆኑን ጠቆም ሳያደርጉ አያልፉም፡፡ በአንድ ወቅት የነበራትን ገናና ሥልጣኔ በማስረጃነት በማቅረብ ዜጎችዋ ወደ ቀድሞው ማንነታቸው መመለስ እንዴት ከበዳቸው የሚሉ ጥያቄዎችንም ይሰነዝራሉ፡፡ በየአካባቢው የሚነሱ ግጭቶችን ለማብረድ የበፊቷ ኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ተቻችለው የሚኖሩባት ምድር እንደነበረች ታሪክ እየጠቀሱ ሰላም ለማውረድ ይጥራሉ፡፡ በፈተና የተወጠረችው የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ለጨነቃቸው መሸሸጊያ የነፃነት ምድር እንደነበረች ይነገርላታል፡፡
አመዛኙ የአገሪቱ ታሪክ በአግባቡ ሳይመዘገብ ቀርቷል ቢባልም የተመዘገበው ጥቂቱም የኢትዮጵያ የቀድሞ ገፅታ የሚቀናበት እንደነበር ይመሰክራል፡፡ የነበረችበትን የሥልጣኔ ደረጃ የሚያሳዩ ሐውልቶች፣ የብራና ላይ ጽሑፎች፣ ቤተ መቅደሶች፣ ደብዳቤዎች፣ ልዩ ልዩ መገልገያ ቁሳቁሶችና መሣሪያዎች ወዘተ በየቦታው ያሉ ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ እነዚህ የታሪክ አስረጂዎች ግን በአግባቡ ባለመያዛቸው ለጥፋት ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡
የአክሱም ሐውልትን፣ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የጁገል ግንብን የመሳሰሉ ድንቅ የኪነ ሕንፃ ጥበብ የሚታይባቸው ታሪካዊ ቦታዎች በአያያዝና በተለያዩ ችግሮች የቀድሞ ይዞታቸውን ሲያጡ ይታያል፡፡ የነበራቸው ወጥ ገጽታ በተለያዩ ውጫዊ ኃይሎች ሲደበዝዝ፣ አንዳንዶቹም የመሰነጣጠቅና የመበስበስ ባህሪ ሲያሳዩ፣ የሕንፃ ውቅራቸውም ከነአካቴው ወድቆ ሲፈረካከስ ተስተውሏል፡፡ ለዚህም የአክሱምን ሐውልት በምሳሌነት ማንሳት በቂ ነው፡፡ የመሰነጣጠቅና የመቦርቦር ሁኔታ የሚታይበት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያንም በውጫዊ ኃይል የህልውና ሥጋት ከተደገነበት ቆይቷል፡፡ የጁገል ግንብ በዚህ መጠን የደረሰበት የገጽታ ለውጥ ባይኖርም በእርጥበትና በፀሐይ መፈራረቅ በቅርሶች ላይ ከሚፈጥረው ተፅዕኖ ነፃ እንደማይሆን ዕሙን ነው፡፡
በውጫዊ ኃይል የቀድሞ ይዞታቸውን እያጡ ካሉ ሕንፃዎችና ሐውልቶች ባሻገር ልዩ ልዩ የጥንታዊ ሥልጣኔን የሚያሳዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ በመረጃ የታጨቁ ጽሑፎችና የመሳሰሉትም እንዲሁ በዕድሜ ብዛት ሲበላሹ ይታያል፡፡ ቀሪው ዓለም ደማቅ የታሪክ አሻራ ምድር ላይ ለማስቀረት በሚጥርበት በዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊ ቅርሶች በአቧራና በእርጥበት ኃይል ሲጠፉ፣ ሲፈረካከሱ ማየት ተለምዷል፡፡ ውድ ውድ የነገሥታት አልባሳት በብል ይተለተላሉ፣ ከወጥ እንጨት የተጠረቡ የጥንታዊ ኢትዮጵያውያንን እሴት የሚያሳዩ ቁም ሳጥኖች፣ ወንበሮችና ሌሎችም የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች ተሰንጥቀው እንዲሁም በምስጥ ተበልተው ይታያሉ፡፡
ቁሶች በዕድሜ ብዛት ለምን ይጠፋሉ ብሎ መሞገት ምክንያታዊ ባይሆንም ታሪካዊ ተብለው የተመረጡ ቅርሳች ግን ተጠብቀው ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ማድረግ ግድ ነው፡፡ በቅርስነት ሲመዘገቡም የነበራቸውን ቅርጽና ይዘት ሳይለቁ ዘመናትን እንዲሻገሩ ለማስቻል ነውና ልዩ ትኩረት ይጠይቃሉ፡፡ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የተለያዩ ቅርሶች የሚደረገው እንክብካቤና ትኩረት በሚጠበቀው መጠን ባለመሆኑ ቅርሶች በዕድሜ ብዛት ሲያረጁ፣ በአያያዝ ጉድለት ሲጠፉና ሲበላሹ ይስተዋላል፡፡
እነዚህን ቅርሶች ለመታደግም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ቅርሶችን ወደ ነባር ይዞታቸው ለመመለስ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መንግሥት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተጣምሮ ይሠራል፡፡ በምርምር ሥራዎች የሚታወቀው የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ደግሞ ቅርሶችን በነበሩበት ማቆየት የሚችል ምርምር ላይ በመሥራት የበኩሉን ሊያበረክት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ይገኛል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በውኃ የሚጎዱ ቅርሶችን ለመታደግ ምርምር ማድረግ ከጀመረ ዓመት ሆኖታል፡፡ አራት የናኖ ቴክኖሎጂ ተመራማሪዎችን ያካተተው ውኃ ጠል (Super Hydrophobic) ቴክኖሎጂ በቁሶች ላይ እንደ ቀለም የሚቀባ ኬሚካል ነው፡፡ በ‹‹ሲልከን ኦክሳይድ ናኖ ፓርቲክል›› የሚሠራው ይህን ፈሳሽ የተቀባ ቁስ ውኃ አይቀበልም፣ አይርስም፡፡ እያንዳንዱን የዝናብ ጠብታ በኳስ መልክ እያንከባለለ ወደ ታች ያራግፋል፡፡ ሱፐር ኃይድሮፎቢክ ኬሚካል የተቀባ ቁስ ራሱን በራሱ የማፅዳትም ባህሪ እንዳለው የሚናገሩት ወ/ሮ ዊንታና ካሳሁን፣ እያንዳንዱ እየተንሸራተተ የሚወርደው የዝናብ ጠብታ አቧራና ሌሎችም ጥቃቅን ነገሮችን ይዞ እንደሚወርድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ውኃ ጠል ባህሪ ያለው ሲልከን ኦክሳይድ ራሱን በራሱ ከማፅዳት ባለፈ የፀሐይ ብርሃንን የመከላከል አቅምም አለው፡፡ የዚህን ሲልከን ኦክሳይድ የተባለ ቅንጣት (ፓርቲክል) በአንድ ቁስ ላይ ተቀብቶ የሚኖረውን ዕድሜ ለማርዘም ምርምር እየተደረገ ይገኛል፡፡ እንደ ተመራማሪዋ ገለጻ፣ በምርምሩ ኬሚካሉ በእንጨት፣ በካርቶን፣ በጨርቅ ላይ ተሞክሮ አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ቴክኖሎጂው መሥራት አለመሥራቱን ለወራት ሲሞከርበት የቆየ ካርቶን፣ እንጨትና ጨርቅ በውኃ የመራስ በአቧራ የመበላሸት ምልክት አላሳዩም፡፡ ነገር ግን ቅቡ የነበረውን የመከላከል አቅም ይዞ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል የሚለው በጥናት መለየት ግድ ነው፡፡ ካለው ቅርሶችን ከጥፋት የመከላከል አቅም አንፃር ቅቡ በየዓመቱ ቢታደስም አዋጭ ነው፡፡
የመሰንጠቅ አደጋ ያጋጠማቸውን ሕንፃዎችና ግንቦችም በናኖ ፓርቲክል ከተሞሉ በኋላ ኬሚካሉን በመቀባት ወደ ነባር ይዞታቸው መመለስና ዕድሜያቸውንም ማርዘም ይቻላል፡፡ ቴክኖሎጂውን ለማምረት ዋና ግብዓት የሆነው ሶድየም ሲሊኬትን እዚሁ አገር ከሸንኮሯ አገዳ ጭማቂ ማምረት እንደሚቻል የሚናገሩት ወ/ሮ ዊንታና፣ ኬሚካሉን በስፋት አገር ውስጥ ማምረት ቀላል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ፕሮጀክቱን በስፋት ለመተግበር የታቀደ ሲሆን፣ በእርጥበትና ፀሐይ መፈራረቅ አደጋ በተደገነባቸው በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ላይ ለመተግበር መታሰቡንም ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡ ቴክኖሎጂው በርካታ ቅርሶችን ጠብቆ ከትውልድ ትውልድ የማስተላለፍ አቅም አለው፡፡ ምርምሩ በኢትዮጵያ እምብዛም የማይታወቅ ቢሆንም በቀሪው ዓለም በስፋት ሥራ ላይ ይውላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከጨርቅ የሚሠሩ ሻንጣዎች፣ መጫሚያዎችና ልዩ ልዩ አልባሳት በውኃ እንዳይርሱ ተደርገው እየተሠሩ ለገበያ ይቀርባሉ፡፡