Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየበጋ መቀበያ በዓል በስቶክሆልም

የበጋ መቀበያ በዓል በስቶክሆልም

ቀን:

በስዊድን መዲና ስቶክሆልም ብሩኬት ወደሚባለው የጎርቮንስ ጥብቅ የተፈጥሮ ቦታ ውስጥ ዓርብ ሰኔ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀትር ላይ የአገሬው ሰው ይተማል፡፡ በአቅራቢያው ከሚገኝ ኮረብታ ግርጌና ከወንዙ ወዲህ በሚገኘው መስክ ላይም ተሰባስቧል፡፡ ከመስኩ ማዕከላዊ ሥፍራ በተተከለና በዕፀዋትና በአበቦች በተጌጠ ምሰሶ ዙርያ የተወሰኑ ሰዎች ከልሒቅ እስከ ደቂቅ፣ ከሕፃን እስከ አዋቂ፣ ጾታ ሳይለዩ እጅ ለእጅ ተያይዘው እየዞሩ ይዘምራሉ፣ ይደንሳሉ፣ እንደ እንቁራሪት እንጣጥ እንጣጥ እያሉ እጆቻቸውን እያፈራረቁ  ጭንቅላታቸው ላይና ከኋላ እንደ ጭራ እያደረጉ ይዘፍናሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሚናፍቁት ሰመር የሚሉት የበጋ ወቅት ደርሶላቸዋልና፡፡

ስዊድንን ጨምሮ የስካንዲኒቪያን አገሮች የሚባሉት እነ ፊንላንድ፣ ዴንማርክ፣ ኖርዌይ ወዘተ ከረዥሙና የጨለማው ሰዓት ከሚበዛበት ክረምትና ተከታዩ ወቅት ገጽታ ዕፎይታ የሚያገኙት በጋ ሲገባ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ምድሪቱ በፈገግታ ትሞላለች፡፡ የበጋ ኮቴ ሲሰማ ያዘኑ ይደሰታሉ፣ ፀሐይን የተራቡ ይጠግባሉ፡፡

የበጋው በዓል ሲገለጽ

በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ፀሐይ ከምድር ወገብ በጣም ከምትርቅበት ሁለት ቀናት አንዱ ጁን 21 ቀን 2019 (ሰኔ 14) ሲውል የዓመቱ ፀሐይ ረዥም ሰዓት የታየችበት ቀን ሆኗል፡፡ ይህም በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ባሉ አገሮች የበጋ ወቅት መጀመርያ ነው፡፡

ስዊድን ስቶክሆልም በተገኘንበት የሰኔ የመጀመርያ ሳምንት የቀኑ ብርሃን ከ18 ሰዓታት በላይ ዘልቋል፡፡ ይህን የፀሐይ ክስተት ‹‹ሰመር ሶልስቲስ›› (ፀሐይ ከምድር ወገብ የምትርቅበት በጋ) በሚሉት በስዊድንም ሆነ በተለያዩ አገሮች እንደየባህላቸው ያከብሩታል፡፡

በስዊድን ከገና በዓል ቀጥሎ በከፍተኛ ደረጃ የሚከበረው ይኸው የበጋ መቀበያ ሲሆን ሚድሰመር ይሉታል፡፡ ወቅቱ ምድሪቱ በአበባ የምትጌጥበት፣ ዛፎች ለምልመው የሚታዩበት በመሆኑ ኅብረተሰቡ በልዩ ስሜት በተለያዩ ሥፍራዎች ያከብረዋል፡፡ ሕፃናትም ሆኑ ሴቶች፣ አልፎ አልፎ ወንዶች ጭንቅላታቸው ላይ የጉንጉን አበባ አክሊል ያደርጋሉ፡፡  በኢትዮጵያ ክረምት አልፎ መፀው ሲመጣ    “ተቀፀል ጽጌ”- አበባን ተቀዳጅ- እንደሚባለው ያሬዳዊ ብሒል  እነርሱም አበባን ይቀዳጃሉ፡፡

የበጋ መቀበያ በዓል በስቶክሆልም

ለክብረ በዓሉ ተብሎ ከሚዘጋጀው ምግብም ጎልቶ የሚታየው ድንችና ዓሳ ነው፡፡ በተለያዩ ቅመሞች ተቀምሞ በማዘጋጀት ይቋደሱታል፡፡ ቮድካ መጠጣቸውንም ይጎነጫሉ፡፡ እንኳን አደረሰን፣ አሸጋገረን በማለትም ጽዋቸውን ያነሳሉ፡፡ ይዘምራሉ፣ ይዘፍናሉ፣ ይደንሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ለመስቀል ደመራ እንደሚደመረው ለሚድሰመር በዓላቸው መለያ በዕፀዋትና አበባ የተጌጠ ምሰሶ ይተክላሉ፡፡ ሜይፖልስ (Maypoles) ይሉታል፡፡ በምሰሶው ዙሪያ ሕፃን አዋቂ ሴት ወንድ ሁሉም እየተሽከረከሩ ልዩ ልዩ ትርዒት ያሳያሉ፤ ልዩ ትኩረት የሚስበው አንደኛ የዳንስ ዓይነት እንደ እንቁራሪት እየዘለሉ እሷን መስለው የሚዘፍኑት ‹ዘ ሊትል ፍሮግስ›› (The Little Frogs) – ትንሿ እንቁራሪት- የተሰኘው ነው፡፡

በስዊድን ብሔራዊ በዓል ሆኖ መሥሪያ ቤቶች ብቻ ሳይሆኑ የገበያ መደብሮች ሁሉ ይዘጋሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1952 የስዊድን ፓርላማ በዓሉ በሳምንቱ መገባደጃ እንዲከበር በመወሰኑ በዓሉ በጁን 20 እና 26 መካከል ይከበራል፡፡

በበርካታ አገሮች በዓል ችቦ ለመለኮስ ይከበራል፡፡ ይህም በስዊድን አንዱ አካል የነበረ ቢሆንም ወደ አፕሪል 30 ምሽት ሲያዛውሩት በምትኩ በአረንጓዴ ዕፀዋትና አበባዎች የተጌጠ ምሰሶን በመትከል ማክበርን ተያይዘውታል፡፡ ይህ ሜይፖል (Maypole) ‹‹የግንቦት ምሰሶ›› እያሉ የሚጠሩት ተክል አዲስ ትውፊታቸው ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በመካከለኛው ዘመን ከጀርመን የመጣና በሜይ መባቻ (ሜይደይ) ይደረግ የነበረ ሥርዓት ነው፡፡

በሜይ ወር ምሰሶውን ለማስጌጥ የሚያስፈልጉ አረንጓዴ ተክሎች ማግኘት አዳጋች በመሆኑ ሥርዓቱን ወደ ሚድሰመር እንዳመጡት ይወሳል፡፡ ሜይፖል በስዊድሽ ማጅስቶንግ ሲባል ማጃ የሚለው ቃል ባረንጓዴ ቅጠሎች ማስጌጥ የሚል ፍች አለው ይላሉ፡፡

ምዕት ዓመታትን ከተሻገረው በአረንጓዴው ምሰሶ ዙሪያ ከሚደረገው ዳንኪራና ጭፈራ ባሻገር፣ ባህላዊ ዳንስና በባህላዊ አልባሳት ጋር የተያያዘ ዐውደ ርዕይ እጅ ለእጅ ተያይዞ የሚደረግ ዳንስ በተለያዩ የዕድሜ ዕርከን የሚጫወቷቸው ጨዋታዎች ይጠቀሳሉ፡፡

በምሰሶው ፊትና ዙሪያ ተያይዘው ልዩ ልዩ ውዝዋዜ በማድረግ በዓሉን ሲያከብሩ የራሳቸውንም ሆነ የውጭ አገር ተመልካቾች ልቡና መማረኩ አልቀረም በያመቱ ፀሓያውያን ረዥም ቀን ለ18 ሰዓታት ለማየት ወደ ስቶክሆልም የሚዘልቁ ጎብኚዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

በ”ሰመር ሶልሰቲስ” ፀሐይ ከምድር ወገብ በጣም ርቃ በሰማይ የምትታይበት፣ በዚህም ምክንያት የቀኑ ብርሃን በዝቶ ረዝሞ የሚገኘው በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ (ጁን 20 ወይም 21) ሲሆን፣ በደቡብ ንፍቀ ክበብ ደግሞ የሚያጋጥመው በክረምት (ዲሴምበር 21 ወይም 22) ነው፡፡

ዕለተ በዓሉ ረዥም ፀሐያዊ ቀን የሚውልበት የበጋ ወቅት መባቻ ብቻ ሳይሆን፣ መከር የሚሰበሰብበትም በመሆኑም ይህ ወቅት ከልምላሜና ከመራባት ጋር መያያዙ አያስደንቅም ይላሉ፡፡

‹‹ከስዊድን ከሚድሰመር ዘጠኝ ወር በኋላ የሚወለዱ ሕፃናት በርካታ ናቸው፡፡›› የሚሉት የስዊዲሽ ኢትኖሎጂስትና በርዕሰ ጉዳዩ ላይ በርካታ መጻሕፍትን የጻፉት ጃን-ኦጂቪንድ ስዋሃን ናቸው፡፡

በስዊድን ትውፊት መሠረት በአረንጓዴው ምሰሶ (ሜይፖል) ዙሪያ እየተጨፈረ የመከበሩ ተምሳሌት ከልምላሜ ጋር ይያያዛል፡፡ እንደ ስዋሃን አገላለጽ፣ ያላገቡ ልጃገረዶች ጨው የበዛበት ምግብ በሚድሰመር ጊዜ ከበሉ ወይም በርካታ የተለያዩ አበቦችን ሰብስበው ከትራሳቸው ሥር አድርገው ከተኙ የወደፊት ባላቸውን ያልማሉ፡፡ በግሪክም ተመሳሳይ ስለወደፊት ባላቸው የሚነገር አፈታሪክ አለ፡፡

ይኸው በዓል በጎረቤት አገሯ ኖርዌይም ሲከበር ከስዊድን የሚለየው ለፀሐይ ክብር ሲሉ ደመራ ደምረው እሳት ማቀጣጠላቸው ነው፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት በኦሌሱንድ (Alesund) ከተማ ለበዓሉ የተከሉት ደመራ ርዝመቱ 47.39 ሜትር በመሆኑ በጊነስ የዓለም ክብር መዝገብ ውስጥ በረዥምነት ተመዝግቧል፡፡ ደመራውን ለማዘጋጀት ሦስት ወር እንደፈጀና እሳቱም ለሁለት ቀናት እየተቀጣጠለ መቆየቱም ተዘግቧል፡፡ እንደ ኖርዊጅያን እምነት ችቦውን ማቀጣጠላቸው የመሬታቸው ምርታማነት ይጨምራል፡፡ ቤተሰቦችና ጓደኛሞችን በተለይ በአንድነት ተሰብስበው ምሽታቸውን ለተፈጥሮ ቅርብ ከወንዝ ዳርቻ ከኮረብታና በተመሳሳይ ቦታ በመሆን ያሳልፉታል፡፡

የሚድሰመር ክብረ በዓል ከጁን 21 ይልቅ ጁን 23 እና 24 የሚያከብሩት ስፔኖች ናቸው፡፡ በትውፊት እንደቆየው ቅድመ ክርስትና የነበረው ሚድሰመር የሚከበረው ጁን 24 የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ልደት የሚውልበት ነው፡፡ ሁለተኛው ፀሐይ ከምድር ወገብ የምትርቅበት የክረምት ዲሴምበር 25 አቅራቢያ የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ቀን ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጠቀሰው፣ ቅዱስ ዮሐንስ የተወለደው ከእግዚእ ኢየሱስ ልደት ስድስት ወር በፊት ነው፡፡

በጎርጎርዮስዊው የዘመን ቀመር መሠረት በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ የበጋ (ሐጋይ) ወቅት ጁን 21 (ሰኔ 14) ሲገባ ከምድር ወገብ በሚገኙ አገሮች ይፋዊ ባይሆንም የክረምት ወቅት ይጀምርበታል፡፡ በኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ መሠረት ግን ክረምት በይፋ የሚገባው ወቅቱን ከፀደይ የሚረከበው ሰኔ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ነው፡፡

ሶልስቲስ የሚከሰተው መሬት በፀሐይ ዙሪያ በ23.4 ዲግሪ ስታዘነብል/ስታጋድል በመሆኑ የሰሜንና የደቡብ ንፍቀ ክበቦች በዓመት የሚያገኙት የፀሐይ ብርሃን እኩል አይሆንም፡፡

በሰሜን ንፍቀ ክበብ ከመጋቢት እስከ መስከረም የፀሐይ ብርሃን የሚያዘነብል ሲሆን መፀውና በጋ ይውሉበታል፡፡ ከመስከረም እስከ መጋቢት ደግሞ ፀሐይ ትርቅባቸውና ፀደይና ክረምት ይውሉበታል፤ በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ የሚውሉት ወቅቶች በተቃራኒው ይሆናል፡፡ በባሕረ ሐሳባችን እንደተጻፈው ‹‹በኛ ክረምት ሲሆን በእነሱ በጋ፤ በኛ መፀው ሲሆን በእነሱ ፀደይ፤›› እንዲል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ የበጋ ወቅትን ለመቀበል የሚሰባሰቡበት በዓለም በከፍተኛ ደረጃ ከሚከበርባቸው ቦታዎች አንዱ በሆነው የእንግሊዝ ስቶንሄንጅ ነው፡፡ በዓለም ቅርስነት የተመሰገበውና ትክል ድንጋዮችና የቅድመ ታሪክ ሐውልቶች በብዛት ያሉበት ስቶንሄንጅ የ5,000 ዓመት ታሪክ አለው፡፡

ዘገባዎች እንዳመለከቱት፣ የዘንድሮው ፀሐያዊ በዓልን የሃርቫርድ የሳይንስና ባህል ሙዚየም በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ከጎብኚዎቹ ጋር አክብሯል፡፡ የከተማው አራት ታላላቅ ሙዚየሞች – ሃርቫርድ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም፣ ፒቦዲ የአርኪዮሎጂና ኢትኖሎጂ ሙዚየም፣ የሃርቫርድ ሴሜቲክ ሙዚየምና የታሪካዊ ሳይንሳዊ መሣሪያዎች ስብስብን ከ3,100 በላይ ጎብኚዎች በነፃ እንዲጎበኙ ተደርጓል፡፡

የበጋ መቀበያ በዓል በስቶክሆልም

 

የኢትዮጵያ ክረምት ሲወጣ የነበረው በዓል የት ደረሰ

አውሮፓዎች በጋን ሲቀበሉ የምድርን ልምላሜ የአበቦችን ኅብር (ሥነ ጽጌያት) ይዘው ነው፡፡ ስዊድኖች በዓላቸውን ሲያከብሩ ባጋጣሚ ስንገኝ የኢትዮጵያ ክረምት ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25 ዘልቆ የአበባና የነፋስ ወቀት ‹‹መፀው›› ሲገባ የነበረው፣ የሚኖረው አከባበር ታውሶናል፡፡ ኢትዮጵያ በዘመነ ደአማት ቀጥሎም ከዘመነ አክሱም ጀምሮ ‹‹ክረምት ወጣ መፀው ገባ›› ብላ በያመቱ መስከረም 25ን ‹‹ተቀጸል ጽጌ›› (አበባን ተቀዳጅ) እያለች ስታከበር ኖራለች፡፡ በሰነድ ደረጀ ተመዝግቦ የሚገኘው በስድስተኛው ምዕት ዓመት በአፄ ገብረ መስቀል ዘመን የተነሳው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጻፈው መጽሐፈ ድጓ ውስጥ ነው፡፡

ክረምት ሰኔ 26 ሲገባ ‹‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናም›› – የዝናብ ኮቴ ተሰማ- ብሎ ክረምቱ መስከረም 25 ወጥቶ በማግሥቱ መፀው ሲገባ ‹‹ኀለፈ ክረምቱ ጸገዩ ጽጌያት›› – ክረምቱ አለፈ አበቦች ፈኩ- ብሎ የመዘገበው ርሱ ነው፡፡ ቀንና ሌሊቱ እኩል 12፣ 12 ሰዓት በሚሆንበት መስከረም 25 ቀን ይከበር የነበረው ‹‹ተቀጸል ጽጌ›› (አበባን ተቀዳጅ) ከ15ኛው ምዕት ዓመት ጀምሮ ወደ መስከረም 10 ቀን ተሸጋግሯል፡፡ ይህም የሆነው እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ክፋዩ (ግማደ መስቀል) ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ ነው፡፡ ‹‹ተቀጸል ጽጌ – አፄ መስቀል›› እየተባለ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት (1923-1967) ድረስ ሲከበር ቆይቷል፡፡ በዓሉ ተቋርጦ ከቆየ በኋላ ከ1980ዎቹ አጋማሽ ወዲህ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዐውደ ምሕረት (አደባባይ) አበባ እየታደለ እየተከበረ ይገኛል፡፡

የመፀው መግቢያ በዓል ወደ ቀደመ ክብሩ ወደ መስከረም 25 የሚመለስበትና ሁሉ አቀፍ ዝግጅት የሚቀርብበት ጊዜ መቼ ይመጣ ይሆን?

በሔኖክ ያሬድ፣ ስዊድን፣ ስቶክሆልም

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...