Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፀጥታና ፍትሕ ግብረ ኃይል ከ255 በላይ ተጠርጣሪዎች ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው መያዛቸውን አስታወቀ

የፀጥታና ፍትሕ ግብረ ኃይል ከ255 በላይ ተጠርጣሪዎች ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው መያዛቸውን አስታወቀ

ቀን:

በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማና በአዲስ አበባ ከተማ ከተፈጸመው ግድያዎች በተጨማሪ፣ በሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ጭምር ዕርምጃ ለመውሰድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 255 ተጠርጣሪዎች ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፀጥታና ፍትሕ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡

በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎች በአማራ ክልል 212 ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ 43 ተጠርጣሪዎች ከሁለት መትረየስ፣ 27 ክላሽኒኮቭ ጠመንጃዎች፣ በርካታ ሽጉጦች ከመሰል ጥይቶቻቸውና የጥቃት ማስፈጸሚያ ዕቅዶችና ሰነዶች ጋር መሆኑን ግብረ ኃይሉ አብራርቷል፡፡  

መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት ማንኛውም ዜጋ ሐሳቡን በነፃነት እንዲገልጽ፣ መንግሥታዊ ሥልጣን ከነፍጥ ይልቅ በሠለጠነ መንገድና በሕዝቦች ይሁንታ ብቻ እንዲሆን፣ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ቢሆንም፣ የጥፋቱ ዋና አቀነባባሪ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌና ግብረ አበሮቻቸው ግን ይቅር ባይነትን ወደ ጎን በመተውና ክህደት በመፈጸም፣ ሥልጣንን በኃይል ለመጨበጥና ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በማጋጨት አገር ለመበታተን መንቀሳቀሳቸውን አስረድቷል፡፡

መንግሥት ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት፣ ነፍጥ አንግበው በአገር ውስጥና በውጭ አገር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ አገራቸው ተመልሰው በሐሳብ ልዕልና ብቻ ለአገራቸው ዴሞክራሲ ዕድገት የበኩላቸውን ሚና የሚጫወቱበት ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል ብሏል፡፡ አብዛኛዎቹ ዕድሉን ተጠቅመው እየተንቀሳቀሱና አገራቸውን ወደ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ቢሆኑም፣ በጣት የሚቆጠሩ ኃይሎች የመንግሥትን በሐሳብ ልዕልና የመታገል ሒደት እንደ ድክመት በመቁጠር፣ በሕገወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም ገልጿል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት አባል በነበሩበት ወቅት አሁን እንደፈጸሙት በተመሳሳይ መንገድ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ በሒደት ላይ እያሉ ከእነ ግብረ አበሮቻቸው ጭምር በቁጥጥር ሥር ውለው ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸው የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው፣ በሽብር ወንጀልና በሌሎች የወንጀል ተግባራት ተጠርጥረውና ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በምሕረትና በይቅርታ ተለቀው ከሰላማዊ ነዋሪ ኅብረተሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ቢደረጉም፣ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነውና ጥቂት ግለሰቦች የዴሞክራሲ ግንባታውን ለማኮላሸት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ታውቋል ሲል ግብር ኃይሉ አስረድቷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በአማራ ክልል አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣ አቶ እዘዝ ዋሴና አቶ ምግባሩ ከበደ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ጓደኛቸው ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራን ሕይወት ማጥፋት ላይ በአንድም ይሁን በሌላ መሳተፋቸውን፣ የፀጥታና ፍትሕ የጋራ ግብረ ኃይሉ አስታውቋል፡፡ ኤታ ማዦር ሹሙንና ጓደኛቸውን በመኖሪያ ቤት የገደላቸው የቅርብ ጠባቂያቸው አሥር አለቃ መሳፍነት ጥጋቡ፣ በፌዴራል የፀጥታ ኃይል ቆስሎ በቁጥጥር ሥር መዋሉንና ወደፊት ስለአጠቃላዩ ሁኔታ ማብራሪያ እንደሚሰጥ ግብረ ኃይሉ አክሏል፡፡

መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ከአደጋ ለመጠበቅ የተሟላ ቁመና እንዳለው ጠቁሞ፣ የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውም የሽብር እንቅስቃሴዎችን እንደማይታገስ አስታውቋል፡፡ በየደረጃው ያሉ የፀጥታ ኃይሎች የሚጠበቅባቸውን ግዴታ እንዲወጡም አስገንዝቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ