የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለቱርክ ግዙፍ ጨርቃ ጨርቅ አምራች አይካ አዲስ ጨርቃ ጨርቅና ኢንቨስትመንት ግሩፕ ያበደረውን ገንዘብ ለማስመለስ ኩባንያውንና ንብረቶቹን ወርሶ ቢቆይም፣ በሐምሌ ወር ሁለት ቢሊዮን ብር በሚጠጋ የመነሻ ዋጋ በሐራጅ እንደሚሸጠው ይፋ አደረገ፡፡
አይካ አዲስ በአለም ገና ከተማ በ205 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ለገነባው የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ማምረቻ ፋብሪካ፣ በጠቅላላው ከ2.8 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ተሰጥቶት ነበር፡፡ ይሁንና ልማት ባንክ ባወጣው የሐራጅ ማስታወቂያ መሠረት ፋብሪካው ብቻውን ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ዋጋ ለጨረታ ሲቀርብ፣ በሦስት ዙር የሚሸጡ የተከማቹ ልዩ ልዩ አልባሳት በጠቅላላው በ130 ሚሊዮን ብር ለጨረታ መቅረባቸውን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ድርድር ሲደረግ ቆይቶ ባለፈው ዓመት ፋብሪካውን ሙሉ በሙሉ የተረከበው ልማት ባንክ፣ የሐራጅ ጨረታውን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ይፋ እንዳደረገና በዚሁ አቋሙ እንደሚቀጥል ሪፖርተር ከባንኩ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ያገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ የቱርክ ኩባንያ ሥራ ከጀመረ ከሦስተኛ ዓመቱ ጀምሮ ችግር ውስጥ መግባት እንደጀመረ ሲታወቅ፣ ለአራት ዓመታትም ኪሳራ ሲያስታውቅ መቆየቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ባንኩም በተደጋጋሚ ለማስታመም እንደሞከረና ባለፈው ዓመት ኩባንያውን ከመውረሱ በፊት፣ የመጨረሻውን የማገገሚያ ድጋፍ በማድረግ ወደ ውጭ ለሚልከው ምርቶች ተጨማሪ ብድሮች ሲሰጠው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይህም ሆኖ ኩባንያው ከኪሳራ ለመውጣትም ሆነ የብድር ዕዳውንም ማቃለል ባለመቻሉ በልማት ባንክ ከመወረስ አልዳነም፡፡ ላለፉት ዓመታት ሲፍገመገም የቆየው አይካ አዲስ፣ በአገሪቱ በተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ሳቢያ ጉዳት የደረሰበት ከመሆኑም በላይ፣ ወደ ውጭ ሊላኩ የተዘጋጁ አልባሳት ሳይላኩ በመቅረታቸው ኪሳራ እንደደረሰበት አስታውቆ ነበር፡፡ በጠቅላላው ከ1.9 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ማስተናገዱን ኩባንያው ገልጾም ነበር፡፡ የሥራ ማስኬጃ እጥረት፣ የጥሬ ዕቃ ዕጦት በተለይም የጥጥ ምርት ዕጦት በተደጋጋሚ በኩባንያው ጥያቄ ሲያቀርብባቸው የቆዩ ችግሮች ናቸው፡፡
ችግሮች እየተባባሱ የመጡበት የአይካ አዲስ በተለያዩ ጊዜያት ከገጠመው የፋይናንስ ቀውስ የሚወጣባቸውን ድጋፎች ከውጭ ኩባያዎች ማግኘቱን ሲገልጽ ቢቆይም፣ ኩባንያውን በፕሬዚዳንት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲያስተዳድሩ የቆዩት ሚስተር ዩሱፍ አይዴኒዝ ለባንኩም ሆነ ለመንግሥት ኃላፊዎች ሳያስታውቁ ከአገር መውጣታቸው ተሰምቷል፡፡
በዚህም ምክንያት ከ7,000 ያላነሱ ሠራተኞቹ ግራ መጋባት ውስጥ መውደቃቸው በመዘገቡ፣ ልማት ባንክ ሠራተኞቹ እንደማይበተኑና ኩባንያውን በመውረስ ኢትዮ ካፒታል ኢንቨስትመንት አክሲዮን ማኅበር በተሰኘው የባንኩ እህት ኩባንያ በኩል እንደሚተዳደር አስታውቆ ነበር፡፡ በዚሁ ተቋም በኩል ተይዞ የቆየው አይካ አዲስ፣ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በጨረታ ወደ ሌሎች እንዲተላለፍና ዕዳውም እንዲመለስ ለማድረግ ባንኩ በመወሰኑ፣ የጨረታ ማስታወቂያ እንደወጣበት ለማወቅ ተችሏል፡፡
በመሆኑም ባንኩ በሦስት ዙር ለጨረታ ካቀረባቸው ከ50 በላይ የአልባሳት ዓይነት የመጀመሪያዎቹ 16 ዝርዝሮች፣ ሐምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ከ25.2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ መነሻ ዋጋ ለሽያጭ ይቀርባሉ፡፡ ሁለተኛው ጨረታ በማግሥቱ ሐምሌ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. 18.6 ሚሊዮን ብር ገደማ ዋጋ ያላቸው ዝርዝር ምርቶች ለጨረታ ይቀርባሉ፡፡ ሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ከ88 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው አልባሳት ለጨረታ የሚቀርቡ ሲሆን፣ ዋናው የማምረቻ ፋብሪካው ግን ከ1.8 ቢሊዮን ብር በሆነ መነሻ ዋጋ ለሐምሌ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. የጨረታ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል፡፡
ይህ የሐራጅ ጨረታ ሒደት ለመጀመሪያ ጊዜ ቢወጣም፣ ልማት ባንክ ለዓመታት ለፕሮጀክት ግንባታና ለሥራ ማስኬጃ ሲሰጥ በቆየው ብድር ብዛት ሳቢያ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት ታውቋል፡፡ በቅርቡ የወጡ ዘገባዎች እንዳረጋገጡት ባንኩ ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ደርሶበታል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የዘጠኝ ወራት ሪፖርት፣ የልማት ባንክ የተበላሸ ወይም ተመላሽ ለማድረግ አስቸጋሪ የሆነው የብድር ክምችት መጠን 40 በመቶ መድረሱን ገልጸው ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት በፊትም የተባለሸ ብድር ክምችቱ በተመሳሳይ 40 በመቶ እንደነበር የወቅቱ የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ስንታየሁ ወልደ ሚካኤል (ዶ/ር) ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡