Monday, March 4, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢትዮጵያ ሕዝብ ይከበር!

ታሪክ እንደሚመሰክረው ጨዋነት፣ አስተዋይነት፣ ታጋሽነት፣ አዛኝነት፣ ጀግንነት፣ አገር ወዳድነት፣ ወዘተ. የኢትዮጵያ ሕዝብ መገለጫ ናቸው፡፡ ይህ ታሪካዊ ሕዝብ ሌብነትን፣ አስመሳይነትንና ሸፍጠኝነትን ይፀየፋል፡፡ አጉል ጀብደኝነትና ከንቱ ፉከራም አይጥመውም፡፡ ታላላቆችን ማክበርና ለታናናሾች አርዓያ መሆን ዘመናትን የተሻገረ ባህል ነው፡፡ ሕዝባችን ችግሮች ሲያጋጥሙት የሚፈታው በአስደማሚዎቹ የምክክር ባህሎቹ ሲሆን፣ በግለሰቦችም ሆነ በማኅበረሰቦች ውስጥ ፀብ ሲያጋጥም አስደናቂ የሆነ የዕርቅና የሽምግልና ሥርዓቶች አሉት፡፡ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ቋንቋና የመሳሰሉ ልዩነቶችን በአኩሪ መስተጋብሮቹ እያስተናገደ አንድነቱን አጠናክሮ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት አገሩን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች በመከላከል፣ ኢትዮጵያን በዓለም ታላቋ የነፃነት ተምሳሌት አድርጓታል፡፡ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የሚመኩበትን ታላቁን የዓድዋ ድል በመስዋዕትነት በማስገኘት አንፀባራቂ ገድል አስመዝግቧል፡፡ ይህንን የመሰለ ጀግና፣ አርቆ አሳቢና ኩሩ ሕዝብ ማክበር ያስፈልጋል፡፡ የጋራ እሴቶቹን መንከባከብና ከትውልድ ወደ ትውልድ ማሸጋገር ይገባል፡፡ በአጉል ጀብደኝነት ሕዝቡን መከፋፈል፣ እርስ በርሱ ማጣላትና የሚወዳትን አገሩን ማተራመስ በታሪክ ያስጠይቃል፡፡

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ ሲመጣ መረር ብሎ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ የገዛ አገሩ ባለቤት የሆነው ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እያለ፣ ጥቂቶች የራሱንና የአገሩን መፃኢ ዕድል ሲያበላሹ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ አይገባም፡፡ ጥቂቶች በጀብደኝነት ተሞልተው አገሪቱን ወደ ቁልቁለት ሲነዷትና ሕዝቡን ለመከራ ሲያጋልጡት ዝም ማለት አይቻልም፡፡ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው አጉል ጀብደኝነት ሳይሆን፣ የዴሞክራሲና የብልፅግና ጉዞ ነው፡፡ አጉል ጀብደኝነት አሁን ላለው ትውልድም ሆነ ለአሁኗ ኢትዮጵያ እንደማይጠቅም ማረጋገጫው፣ ከሐዘንና ከፀፀት በስተቀር ፋይዳ ስለሌለው ነው፡፡ አገርን ወደ ሥልጣኔ በማሸጋገር ሕዝብን ከአሳፋሪው ድህነት ውስጥ ማውጣት እየተቻለ፣ ሕዝብን በጦርነት ለማገድ መፎከር የጤነኛ ሰዎች ተግባር አይደለም፡፡ በተለይ በአውሮፓና በአሜሪካ መሽገው በማኅበራዊ ሚዲያ ወጣቱን እየቀሰቀሱ ያሉ ግብዞች፣ ከያዙት አደገኛ ድርጊት እንዲታቀቡ የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆን አለበት፡፡ ወንድምን ከወንድሙ እያጋደሉ በየጎራው የአዞ እንባ ማፍሰስ ሕዝብን መናቅ ነው፡፡ በሕዝብ ስም እየነገዱ ማታለል ደግሞ የለየለት ወንጀል ነው፡፡

ከሃምሳ ዓመታት በላይ የዘለቀው የሴራ ፖለቲካ መቋጨት አለበት፡፡ ለሥልጣን ተብሎ ደም ማፍሰስም ሆነ፣ የሴራ ፖለቲካ እየጎነጎኑ በኢትዮጵያ ምድር መተማመን እንዳይኖር ማድረግ ሊያበቃ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሴራ ፖለቲካ አብቅቶ ለንግግርና ለድርድር አመቺ ሁኔታ መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ በሴረኞች ምክንያት ከሚፈጠር ቀውስ ማንም ማትረፍ አይችልም፡፡ አሸናፊም ተሸናፊም አይኖርም፡፡ የቀውሱ ውጤት ግን የሚታየው በሕፃናት፣ በአጥቢና በነፍሰ ጡር እናቶች፣ በአረጋውያን፣ በአቅመ ደካሞችና በቀላሉ ለችግር ተጋላጭ በሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ እንደሆነ ከመጠን በላይ ታይቷል፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለዘመናት ከሚጫወቱበት ድህነት፣ ኋላቀርነትና ጉስቁልና ማላቀቅ የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት ሆኖ ሳለ፣ በሰበብ አስባቡ ተያይዞ ለመጥፋት የሚደረገው አጓጉል ድርጊት በፍጥነት መቆም ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ዘመን የሚገባው በክብርና በደስታ መኖር እንጂ፣ ማንም ጀብደኛ እየተነሳ በሚቆሰቁሰው እሳት መሰቃየት አይደለም፡፡ ሕዝብን ለዘመናት ከሚያሰቃዩት ችግሮች ውስጥ ጎትቶ ማውጣት ሲገባ፣ በችግር ላይ ችግር እየደራረቡ መከራውን ማብዛት ኃጢያት ነው፡፡ ሕዝብን የማያከብር የሚጠብቀው ውርደት እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

በዚህ ዘመን ለሥልጣንም ሆነ ለሌላ ፍላጎት መግደልም ሆነ ማሰቃየት ከቶውንም ተገቢ አይደለም፡፡ ገድሎ መፎከርም ሆነ ማስፎከር ለዚህ ዘመን አይመጥንም፡፡ ወንድም ወንድሙን ገድሎ መፎከር ወይም የመገዳደል ትርክትን የአገር ወግ ማድረግ ነውር መሆን አለበት፡፡ የሐሳብ ልዩነትን ለመጠፋፊያ ሳይሆን ለዕውቀት መገብያና ለመረጃ መለዋወጫ ማድረግ ሲቻል፣ የተለየ ሐሳብ ያላቸውን በጠላትነት ፈርጆ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ማሰብም ሆነ መፈጸም መወገዝ ይገባዋል፡፡ በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ የሐሳብ ልውውጥን የአገር ባህል እንደማድረግ፣ አገርን ለአፈና የሚዳርግ ምህዋር ውስጥ ለመክተት መባዘን መቆም አለበት፡፡ በማናቸውም መስኮች ልዩነት መኖሩ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ ማስተናገድ ሥልጣኔ ነው፡፡ ልዩነቶችን በመደማመጥና በመከባበር ማስተናገድ ሲቻል የሕዝባችን መከራ ይወገዳል፡፡ ይህ ጨዋ ሕዝብ ጥቂቶች አገር እያመሱ ሊሳቀቅ አይገባም፡፡ የተለየ ሐሳብን በስድብ፣ በማስፈራራትና በመግደል ወይም በሌላ አሉታዊ መንገድ ለመገደብ መሞከር ከሥልጣኔና ከጨዋነት ጋር ያጣላል፡፡ የአስተዋዩንና የጨዋውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ይፃረራል፡፡ ይህ በሚገባ ግንዛቤ ማግኘት አለበት፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው ለውጥ ግቡን ይመታ ዘንድ በግልጽ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ ለውጡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ለመጣል መዳረሻ መሆኑን ማረጋገጥም እንዲሁ፡፡ ለውጡ በትክክል እየተመራ ካልሆነ በአግባቡ መስመሩን እንዲይዝ ማድረግ የኢትዮጵያውያን ኃላፊነት ነው፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ እየተፈቱና የሕዝቡም ሁለገብ ተሳትፎ እየጠነከረ እንዲሄድ የጋራ መግባባባት መኖር አለበት፡፡ የተገኘውን መልካም አጋጣሚ የጠባብ ቡድን ፍላጎት እንዳይጠልፈው፣ የመገለልና የመከፋት ስሜት እንዳይፈጠር፣ ከሕዝብ ምኞትና ተስፋ እዳያፈነግጥና የሥርዓተ አልበኝነት መፈንጫ እንዳይሆን መጠንቀቅ የግድ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው የተቃርኖ ገመድ ጉተታ ሕዝብን መናቅና አገርን ቀውስ ከመክተት የዘለለ ፈይዳ የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ነው፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር የምትተዳደር ዴሞክራሲያዊት አገር ተፈጥራ ሕዝብ የሚደሰትበት ሥርዓት የሚኖረው፣ የሴራ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ግብዓተ መሬቱ ሲፈጸም ነው፡፡ ሕዝብን በመናቅ በሴራና በደባ መተናነቅ ማብቃት አለበት፡፡ በሕዝብ ስም መቀለድ ይብቃ! የኢትዮጵያ ሕዝብ ይከበር!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...

ምርጫ ቦርድ ፓርላማው ያፀደቀለትን 304 ሚሊዮን ብር አለማግኘቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ሰኔ 2016 ዓ.ም. በአራት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰብዓዊ ቀውስና በውድመት የታጀቡ ግጭቶች በአስቸኳይ ይቁሙ!

በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ተጀምሮ አማራና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው የሁለት ዓመቱ አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢገታም፣ ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል የተጀመረው...

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...