Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበእግር ኳስ ተጨዋቾች ላይ አስገዳጅ የፀረ አበረታች ቅመሞች ምርመራ ሊጀመር ነው

በእግር ኳስ ተጨዋቾች ላይ አስገዳጅ የፀረ አበረታች ቅመሞች ምርመራ ሊጀመር ነው

ቀን:

ስፖርት የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቱን ለማሟላት የሚያደርገውን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን መሠረት በማድረግ የተመሠረተ፣ ሰዎች አቅማቸውን ከፍ ለማድረግ በሚያደርጉት ከፍተኛ ጥረት እየተሻሻለና እያደገ የመጣ ነው፡፡ ቀስ በቀስም በመወዳደር መንፈስ ደረጃ በደረጃ እየተስፋፋ በዓለም ኅብረተሰብ ዘንድ ተወዳጅነትና ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱ ይወሳል፡፡ ውድድሮችም በሒደት ሕጎች፣ ደንቦችና መመርያዎች እየተዘጋጁላቸው ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ የውድድር መንፈስ መፈጠር መጀመሩ ይነገራል፡፡

በዚሁ የተጀመረው የስፖርት ውድድር በጊዜ ሒደት የሥልጠናና መሰል ፕሮግራሞች በመታገዝ የውድድር አሸናፊዎች እንዲወጡና ዕውቅና እንዲያገኙ መደረጉን ተከትሎ፣ በተወዳዳሪዎች መካከል የአሸናፊነት መንፈስ እንዲፈጠር ሆኗል፡፡ ይሁንና ከአሸናፊነት ስሜትና ፍላጎት ጋር በተያያዘ በተለይ ተወዳዳሪዎች ተጨማሪ ኃይል ሰጪ (የአካል ብቃትን የሚጨምሩ) የተለያዩ ቅመሞችን በተለያዩ መንገዶች በመጠቀም የአሸናፊዎች ዕድል እንዲሰፋ ማድረጉ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ ይህም መሠረታዊ የሆነውንና የንፁህ ስፖርት የውድድር መርህ መስመሩን እንዲስት ምክንያት እየሆነ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ የችግሩ ሰለባ ከሆኑ አምስት አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗ የዓለም አቀፍ ፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ (ዋዳ) ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ይህ ቀደምቱ ባስመዘገቧቸው ድሎችና ታሪኮች ላይ ጠባሳ እያሳደረ መምጣቱ አይቀሬ ስለመሆኑ የዘርፉ ሙያተኞች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ኢትዮጵያ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 400/2009 የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት ማቋቋሟ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት፣ በቀጣይ ስለሚከውነው ተግባርና በችግሩ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ስለሚደረገው ቁጥጥርና ክትትል ባለፈው ረቡዕ ሰኔ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሆቴል ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ የጽሕፈት ቤቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴና ቀጣይ አቅጣጫዎች ማለትም ተቋሙ ከየት ተነስቶ ወዴት መሄድ እንደሚገባው በተለይም ከችግሩ ጋር ተያይዞ ባለድርሻ አካላት ማግኘት ስለሚገባቸው ትምህርትና ሥልጠና በተቋሙ የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አክሊሉ አዛዥ ገለጻ ተደርጓል፡፡

ኢትዮጵያ አትሌቶቿንም ሆነ ስፖርቱን በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ የሚገኘውን አስከፊ ወረርሽኝ ከምንጩ ለማድረቅ ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን በመቀበል፣ ስፖርቶቿን ለመጠበቅና ለመታደግ በአሁኑ ወቅት ጠንካራ የፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት በማደራጀት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደምትገኝም ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው በአትሌቲክሱ ያውም በተወሰኑ የሩጫ የውድድር ዓይነቶች ሲሆን፣ የችግሩ ተጠቂዎች ደግሞ በአብዛኛው ሴቶች መሆናቸው በውይይቱ ከተነሱት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

በሚዲያ ባለሙያዎቹ ለቀረቡት አስተያየቶች ማብራሪያ የሰጡት የተቋሙ ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ፋንታዬ ገዛኸኝ፣ ‹‹ክትትልና ቁጥጥሩ በሌሎችም ስፖርቶች ይደረጋል፡፡ አትሌቲክሱ ላይ በዋናነት ትኩረት የሚደረገው ሁሉም እንደሚያውቀው፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ ዋና የትኩረት አቅጣጫ በመሆኗ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ከታላላቅ የዓለም አገሮች በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት አንዷ ነች፡፡ ለዚህም ነው የችግሩ ሰለባ ከሆኑት አምስት አገሮች አንዷ ተደርጋ የተጠቀሰችው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እንደ አትሌቲክሱ ሁሉንም ስፖርቶች እኩል ዓይቶ ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል ለማድረግ አቅም ይጠይቃል፡፡ የአንድን አትሌት የሽንትና የደም ናሙና ወስዶ ፈረንሣይ ወይም ኳታር ወደ ሚገኘው ምርመራ ማዕከል ሲላክ ከ100 እስከ 150 የአሜሪካ ዶላር ክፍያ ይጠይቃል፤›› በማለት ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ መኮንን፣ በአትሌቲክሱ ላይ ጠንከር ያለ ክትትልና ቁጥጥር የሚደረገው ስፖርቱ ዓለም ላይ ካለው ስምና ዕውቅና አኳያ ቅድሚያ እንዲያገኝ ሆኗል፡፡ ይህ ማለት ግን የብዙዎችን ቀልብ በመሳብ ላይ የሚገኘው እግር ኳስና ሌሎች ስፖርቶች ዝም ተብለዋል ማለት እንዳልሆነና ከሚቀጥለው የውድድር ዓመት ጀምሮ በተለይ የእግር ኳስ አትሌቶች ሽንትና ደም ናሙና እንዲሰጡ የሚደረግበት አሠራር በመከተል ጠንከር ያለ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ ነው ያስረዱት፡፡

ለዚህም ሲባል ከትምህርት ዝግጅታቸው ጀምሮ ጠንካራ ሙያተኞች የተካተቱበት የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲቋቋም መደረጉን ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ መንግሥት ተቋሙን ለማጠናከር ካለው ፍላጎት በመነሳት ከበጀት ጀምሮ ማናቸውንም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በተቋሙ ውስጥ አሁን ያለውን ሠራተኛ በዕጥፍ ለማሳደግ ዕቅድ እንዳለም ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ የዕለት ዕለት እንቅስቃሴው ምን እንደሚመስል መረጃዎችን በተገቢው ሁኔታ እንደማይሰጥ፣ ከዓለም አቀፍ የፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ ሙያተኞች ለስብሰባ ሆነ ለተመሳሳይ ሥራዎች ሲመጡም ሆነ ሲመለሱ ጉዳዩን በመገናኛ ብዙኃን በኩል ለኅብረተሰቡ በማድረስ በኩል ከፍተኛ ዳተኝነት እንደሚስተዋልበት ቅሬታ ቀርቦበትም ነበር፡፡ እንዲያውም በቅርቡ የዓለም አቀፍ ተቋም ኃላፊዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው አገሪቱ ሁኔታውን ለመቆጣጠር በምን ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ግምገማ አድርጎ መመለሱ ቢሰማም፣ በጉዳዩ ብሔራዊ ተቋሙ ምንም ዓይነት ማብራሪያ አለመስጠቱ ተነግሯል፡፡  

‹‹ኢትዮጵያ አበረታች ቅመሞችን በሚመለከት በምን ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ፣ ከዓለም አቀፉ ተቋም በመጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች መገምገሟ እውነት ነው፡፡ ጉዳዩ በመገናኛ ብዙኃን በኩል ግልጽ እንዲሆን ያልተደረገው በራሱ በዓለም አቀፉ ተቋም ትዕዛዝ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ተቋሙ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቁ ሚስጥራዊ ምርመራዎችን የሚያከናውነው በግለሰቦች ላይ በመሆኑ የሚያስከትለውን ጉዳት ከግምት በማስገባት ነው፤›› በማለት ዋና ዳይሬክተሩ ክልከላው ከብሔራዊ ተቋሙ ጋር እንደማይገናኝ አስረድተዋል፡፡

በዕለቱ በአገሪቱ እየተከናወነ ያለውን ይኼን ተግባር ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ይረዳ ዘንድ ሳይንሳዊ ዘዴን የተከተለ የትምህርትና ሥልጠና የግንዛቤ ማስጨበጫ ማንዋል ተዘጋጅቶ ለመገናኛ ባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡ የሚዲያ ባለሙያዎች ፎረም ማቋቋሚያ ደንብም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት፣ ከኢትዮጵያ የፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት ጋር በመሆን ፎረሙን የሚመሩ አመራሮች ምርጫም ተከናውኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...