Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ እባክዎ ፍትሕ ያስፍኑ!

የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ እባክዎ ፍትሕ ያስፍኑ!

ቀን:

በቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ከተማ ውስጥ በሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ ከፍተኛ ምዝበራ ተካሂዷል፡፡ በሕዝብ ተመርጠው ውክልና የሰጣቸውን ሕዝብ በሚገባ በማገልገል ተገቢውን የአክሲዮን ድርሻ የሚያከፋፍሉ መልካም የሕዝብ አገልጋዮች የመኖራቸው ያህል፣ የመረጣቸውን ሕዝብ ንቀው የአክሲዮኑን መንቀሳቀሻ ገንዘብና የአባላቱን ድርሻ ቀርጥፈው የበሉ፣ ባዶ ካዝና ያስረከቡም አሉ፡፡

 ክብርት ከንቲባ ዓለም ፀሐይ ሽፈራው በነበሩበት መድረክ በሕዝብ የተጋለጡ ኃላፊዎችን ታዝበዋል፡፡ ይህ እየታወቀ የሕዝብን ጉዳይ ቸል በማለት መዝባሪዎቹን በሕግ ቁጥጥር ሥር ማድረግ ሲገባቸው፣ ክብር ከንቲባዋ ግን አዲስ ምርጫ ማካሄዳቸው አግባብነት የለውም፡፡ ‹‹ነግ በእኔ›› እንደሚባለው መዝባሪዎቹ የዘረፉትን ገንዘብ መልሰው ላጠፉትም መቀጣት ሲገባቸው፣ በከንቲባዋ በኩል የሚታየው ዝምታ ግን አስገራሚ ነው፡፡ ከተመዘበረው ሕዝብ በአካልም በስልክም የፍትሕ ያለ በማለት ተማጽኖውን ቢያሰማም የከንቲባው ምላሽ ግን ዝምታ ሆኗል፡፡

በመሆኑም ክብርት ከንቲባ በተሰጠዎት ኃላፊነትና በሕዝብ ዘንድ ሊደረግልዎት ስለሚገባው አክብሮት ካሰቡ ፍትሕን ያስፍኑ፡፡ ሕዝብ ቢያንስ ፊት ለፊት የታየውን ማጭበርበር እያጋለጠና ያጠፉትን በአደባባይ እያቀረበ ባለበት ወቅት ተገቢውን አስተዳደራዊና ሕጋዊ ዕርምጃ አለመውሰድ ሕዝብን ቅሬታ ላይ የሚጥል ቸልተኝነት በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲታረም እንጠይቃለን፡፡

ሕዝብ ብልህ ነው፡፡ ለሕዝቡ ስትሉ ሁሉ ነገራችሁን ትታችሁ፣ ደማችሁንና ላባችሁን አፍሳችሁ ለሠራችሁት ሥራ ሕዝቡ ከገባውና ድካማችሁንም ዋጋ ከሰጠው፣ እናንተ ስለምትሠሩትና ስለምትለፉበት ጉዳይ ማስተዋል ከጀመረ ሕዝቡ ዋጋችሁን እንዲሁ ቸል እንደማይለው ሁሉ እናንተም ለሕዝቡ ባለውለታ መሆን አለባችሁ፡፡ ሕዝቡ የሚፈልጋችሁ እናንተ የማትፈልጉት አትሁኑ፡፡ ይልቁንም ሕዝብ እናንተን በባትሪ አፈላልጎ ለሹመትና ለሽልማት የሚያጫችሁ እንድትሆኑ ከፈለጋችሁ ፍትሕን ሲጠይቃችሁ ፍትሕን ስጡት፡፡ ‹‹የአገር ሀብት ወርቅና ቡና ብቻ ሳይሆኑ ሕዝቦቿም ናቸው፡፡ ‹‹ኃላፊነትን የሚሸከም ትውልድ ሲፈጠር አገር ትድናለች፡፡ ኃላፊነትን የማይሸከም ትውልድ ከተፈጠረ ግን አገር ትጠፋለች፤›› የሚለው አባባል መመርያችሁ እንዲሆን በማድረግ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ በመስጠቱ ላይ ትጋትን ጨምሩ፡፡

(ገለታ ዋቅጅራ፣ ከቢሾፍቱ)

***

ለዘውዲቱ ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያዎች ትመሰገናላችሁ!

ዕለቱ ግንቦት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠዋት ላይ ነበር፡፡ ከሳንቴ የሕክምና ማዕከል ሪፈር ተደርጌ ዘውዲቱ ሆስፒታል ደርሻለሁ፡፡ ድንገተኛ ክፍል ተገኝቼ ተጨማሪ ምርመራ ተደርጎልኝ አልጋ ከያዝኩ በኋላ ኦፕራሲዮን እንደምደረግ ተነግሮኝ ከጥቂት ደቂቃዎች ቆይታ በኋላ ወደ ኦፕራሲዮን ክፍሉ አመራሁ፡፡

ሆስፒታሉ ውስጥ በተገኘሁባቸው ጥቂት ሰዓታት ውስጥ እንዲህ ዓይነት የሕክምና ርብርቦሽና ይደረግልኝ የነበረው ክብካቤ በአገር ውስጥ የሚደረግ ሕክምና ሳይሆን ውጭ አገር የሚደረግልኝ ነበር የመሰለኝ፡፡

ከድንገተኛ ክፍል ጀምሮ አልጋ እስከያዙ በሽተኞች ድረስ የሚያደርጉት የሕክምና ርብርቦሽና ሐዘኔታ የተሞላበት የሕክምና ክትትላቸውን ስመለከት፣ አገራችን በሕክምናው ዘርፍ በዚህ ሁኔታ ከተቀጠለች ተስፋ የሚጣልባትና የእውነትም ቅን አገልግሎት የሚሰጥባት እንደምትሆን ተስፋ አድረግሁ፡፡

የቀን ተረኛ ሐኪሞች በሰዓታቸው የምሽቶቹም፣ የሌሊት ገቢዎችም፣ በሰዓታቸው ተገኝተው ለበሽተኞች የሚያስፈልጋቸውን ክትትል፣ መድኃኒትና ሌሎችም አገልግሎቶችን በትጋት ይሰጣሉ፡፡ በጠዋቱ ክፍለ ጊዜም ሁሉም ሐኪሞች ከነርሶችና ረዳት ሐኪሞቻቸው ጋር በመሆን ታማሚውን አገላብጠው ይመረምራሉ፡፡ ተጨማሪ መድኃኒት እንዲያገኝም ያደርጋሉ፡፡ እንዴት ደስ ይላል! በዚህ ሁኔታ በሽተኛ በቶሎ ይድናል፡፡ እውነትም ዘውድ ናቸው፡፡

በመጨረሻም ሌሎችም የመንግሥት ሆስፒታሎች በዚህ ደረጃ ላይ ይገኛሉ የሚል እምነት አድሮብኛል፡፡ የዘውዲቱ ሆስፒታል ዶክተሮችና ነርሶች አሁን እየሰጣችሁ ያላችሁት አገልግሎት እጅግ የሚያስመሠግናችሁ በመሆኑ፣ ከዚህ የበለጠ በመሥራት ሳይማር ያስተማራችሁን ሕዝብ ውለታ መክፈል ይጠበቅባችኋልና በርቱ፡፡ እየሠራችሁ ባላችሁበት ጥረት ውስጥ እኛም ከጎናችሁ በመሆን ስናግዛችሁ መንግሥትም የጥረታችሁ ፍሬ አብቦ እንዲፈካ እንደሚያደርግ ሙሉ ተስፋ አለኝ፡፡ በርቱ ልጆቻችን፡፡

(አቶ መኮንን ይረፉ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...