በያሬድ ኃይለ መስቀል
የኢትዮጵያ ፖለቲካ የከርሞ ጥጃ ከሆነ ይኼው ሃምሳ ዓመታት አለፈው፡፡ ‹‹መግደል መሸነፍ ነው›› እያልን ግድያ አሁንም የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ ይመስለናል። ወንድምነት፣ የአገር ልጅነት፣ አብሮ መኖር፣ አብሮ መብላትና ሃይማኖት፣ ኃጥያት፣ የሚንቦገቦግ እሳት ያለበት ገሃነም የሚባሉት ነገሮች ሁሉ ልዩነት ሲመጣ ዋጋ ያጣሉ። ችግሩን በነፍስ ማጥፋት ልናስወግደው እንሄዳለን። በአንድ ላይ አብረው የታገሉ አብረው መከራ የተቀበሉ ወንድማማቾች ሳይቀር ግድያን እንደ መጀመርያና ብቸኛ የችግር መፍቻ መሣሪያ አድርገው ደግመው ደጋግመው ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ሲወስዱት ዓይተናል። ለዚህ ነው ሥነ ልቦናችን በደንብ መጠናት እንዳለበት የተሰማኝ፡፡
የሰሞኑ አሳፋሪ ተራ ግድያዎችን በተመለከተ በርካታ ተንታኞች ሐሳባቸውን እያቀረቡ ስለሆነ፣ እኔ ወደ ትንተና ሳልሄድ ወደ ምንጩ ሄጄ የእኛ ሥነ ልቦና ላይ ላተኩር መረጥኩ። የሚገርመው በዚህ ዓለም ላይ ከሚኖሩ ፍጡራን ሁሉ እንደ ሰው ደካማው ሆኖ የተፈጠረ ፍጡር የለም። በዚህ የበታችነቱ ሥነ ልቦና ይመስለኛል ግድያንና ጭካኔን ሙጥኝ ያለው። የት እንዳነበብኩት ትዝ አይለኝም፣ ግን ኤሪክ ሆፈር የሚባል ጸሐፊ ይመስለኛል እንዳለው የሰው ልጅ እንደ አንበሳ ጡንቻ የለውም፣ አሯሩጦ ሰብሮ አይበላም፡፡ እንደ ነብር የሰላ ጥፍርና ጥርስ የለውም። እንደ ጅብ እንኳን የሚዘነጥል ጥርስ አልተሰጠውም፡፡ ሮጦ እንኳን ማምለጥ የማይችል ፍጡር ነው፡፡ እንደ ዝንጀሮም ዛፍ ላይ ተንጠላጥሎ ራሱን የማዳን አቅም የለውም። የሚገርመው ይህ ደካማ ፍጡር ራሱን ከብርድ የሚከላከልበት ፀጉር ሳይሰጠው ራቁቱን ነው ወደ ምድር የተጣለው። ይሁንና ለሌሎቹ ያልተሰጠው የማሰቢያ አዕምሮ ተሰጥቶታል።
ፈጣሪ ሰውን ለገዳይነት የፈጠረው ቢሆን ኖሮ የመግደያውን ጡንቻ፣ ጥፍር ወይም ጥርስ ይሰጠው ነበር። የሰው ልጅ የተፈጠረው እንዲያስብ፣ እንዲመረምርና እንዲፈጥር ነው። መጽሐፉም እኮ ‹‹አርዓያችንን በመልካችን እንፍጠር አሉ›› አይደለም የሚለው? እንዲህ ክቡር ሆኖ እንዲያስብ አዕምሮ የተሰጠው ፍጡር ለምን ከእንስሳዊ ባህሪ ጋር ሙጥኝ አለ? የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይህንን ልክፍት ወይም ቁርኝት (Obsession) ይሉታል። ትልቁ የተሰጠው መሣሪያ አዕምሮና ልሳን ሆኖ ሳለ ለምን በእሱ ለመጠቀም አልፈቀደም ብሎ መጠየቅ ያሻል። እንዲህ ያለ ትልቅ ፀጋ እንደሌለው እንስሳ ነው ችግሩን እየፈታ ያለው። የሚገርመው አራዊትም የሰው ምኞት ቢገባቸው ኖሮ ምንኛ በፈጣሪያቸው ባዘኑ። እኛ እያለን ለሰው አዕምሮ ትሰጣለህ ባሉ።
አራዊት እኮ የራሳቸውን አምሳያ አይገሉም፣ አይበሉም። አንበሳ አንበሳን ሲገድለው፣ ጅብ ጅብን ሲበላው አይታይም። የሰው ልጅ ራሱን ለማሞገስ የዥንጀሮ ተረት ቢፈጥርም፣ አራዊት ከተሰጣቸው ሕገ ልቦና ዝንፍ አይሉም። አንበሳ ሲርበው ሚዳቋን ገድሎ ይበላል እንጂ ለሚዳቋ ጥላቻ የለውም። የሚገድለው ስለራበው ብቻ እንጂ የሚዳቆን ዘር ለማጥፋት አይደለም። ሚዳቆ ጠላቱ አይደለችም። ሆዱ ከሞላ ሌላ ሚዳቆ አያባርም፣ አያድንም፣ አይገድልም። ጥያቄው ይህ በምድር ላይ ደካማ ሆኖ ለመግደያ ምንም መሣሪያ ያልተሰጠው ፍጡር፣ ለምን ከእንስሳት በታች ወርዶ የራሱን አምሳያ በመግደል የችግሩ ሁሉ መፍቻ ብሎ ተቀበለ? ይህንን ሥነ ልቦና ከየት አመጣ? የሚለውን በደንብ መወያየት አለብን፡፡
ይህ ባህሪ ደግሞ በእኛ በኢትዮጵያውያን ላይ ጎልቶ መታየቱ ያሸማቅቃል። እኔ ተወልጄ በኖርኩበት ዘመን ሁሉ የኬንያ ፖለቲካኛ አብሮ አደጉን ጓዱን ቢሮው ገብቶ ረሸነው ሲባል አልሰማሁም። ቀይ ሽብር ነጭ ሽብር ተብሎ ጓደኛ ጓደኛውን ገደለው ሲባል አልሰማሁም። በሌሎች ጎረቤት አገሮችም ወንድም ወንድሙን ለሥልጣን ብሎ ረሸነ ሲባል አልሰማሁም። የራሱን የድርጅት አባል፣ የራሱን አጋር፣ አብረው የተማማሉትንና ለአንድ ዓላማ የተነሱትን ሳይቀር ቢሮ ገብቶ መረሸን፣ መጨራረስ ተፈጸመ ሲባል አልሰማሁም፡፡ በየጉድጓዱ ገድሎ ጥሎት ወይም መድኃኒት ብሎ መርዝ ሲያጎርሰው ታይቶ አይታወቅም።
የእኛ አገር ይህ ሥነ ልቦና መሠረቱ ካልተጠናና መፍትሔ ካልተገኘለት በዓመቱም ታጥቦ ጭቃ ነው የሚሆነው። ባለሙያዎች ሊጠይቁና ሊተቹ ይገባል። እኛ የሰው ልጆች ለመግደል የተሠራን ቢሆን ኖሮ እንደ አንበሳ መግደያው ይሰጠን ነበር። እኛ የተሰጠን ትልቁ መሣሪያ አዕምሮ ነበር፣ ማሰብ ነበር፡፡ እኛ የተሰጠን ራዕይ ነው፣ እኛ የተሰጠን ሐሳብን ወደ ድምፅ አውጥተን የምናስተላልፍበት ቋንቋ ነው። ይሁንና የተሰጠንን ትልቅ ፀጋ አልጠቀምንበትም። ይህንን ፀጋ ጥለን እንደ ነብር መግደያ ጥፍር ባይኖረን ሌላ ሰው በሠራው መሣሪያ ተጠቅመን ወንድማችንን፣ የአገራችንን ልጅ እንገድላለን።
‹‹ያለ ምንም ደም. . .›› ተብሎ በተጀመረው ለውጥ ማመዛዘን የማይችሉ 108 መንጋ ወታደሮች በአዳራሽ ተሰብስበው እጃቸውን እያወጡ፣ ለዚህች አገር ሕይወታቸውን የሰጡና በነፃነት ያቆዩንን የ70 እና የ80 ዓመት ታላላቅ 63 አርበኞች ረሸኑ። ከዚያ ተራማጅ የተባለው አጨበጨበ፣ ‹ብራቮ መንግሥቱ ቆራጡ መንግሥቱ› ተባለ። ግድያ ጨረቃ ላይ የሚያሳርፍ የፊዚክስ ግኝት እስከሚመስል የችግሩ መፍቻ ሕግ ሆነ።
አብረው ተማምለው ‹‹ሕይወታችንን አስይዘን›› ነፃ አወጣን ያሉ የደርግ አባላት እነ ኮሎኔል አጥናፋ አባተ፣ እነ ጄኔራል ተፈሪ በንቲ ሳይቀሩ በድንገት በጓዶቻቸው ታረዱ። ለኢትዮጵያ ሕዝብ እኩልነትና ለመሬት ላራሹ ታገልን ያሉ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ኮሌጅ ተማሪዎች ኢሕአፓና መኢሶን ተባብለው ተራረዱ። የአንድ ድርጅት አባል የነበሩትም አብረው ቀይ ሽብር ተፈጸመባቸው፡፡ አንጃ እየተባባሉ ወንድም ወንድሙን ገደለው። አብረው ለትግል የወጡትም በመርዝና በጥይት ተጨራረሱ። አሁንም ግድያን እንደ መጀመርያና መጨረሻ መፍትሔ አድርጎ መቁጠሩ ቀጥሏል።
አሁን ደግሞ አብረን ተጨቆንን፣ አብረን ነፃ አወጣን ያሉና ለተጨቆነው አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞና ሶማሌ ያሉ ሰዎች ወንድሞቻቸውን መግደል እንደ ቀላል መፍትሔ አድርገው ተቀበሉ። ለምን እንዲህ ያለ ሥነ ልቦና ያለው ፖለቲከኛና ነፃ አውጪ ፈላ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። የሚያሳዝነው ደግሞ ትልቅ አዕምሮ፣ የርቀት መመልከቻ ራዕይ፣ ሐሳቡን የመግለጫ ቋንቋ ያለውና በአርያ ሥላሴ አምሳልና ተግባር የተፈጠረ ሰው፣ ያልሠራውን የመግደያ መሣሪያ እያመለከ ግድያን እንደ ብቸኛ መፍትሔ አድርጎ ቆጠረ።
ይህ ለምን ሆነ ብለን መጠየቅ አለብን። ይህንን ችግር ካልተረዳን መተራረዱ ይቀጥላል። ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ የምንኩራራበትን ሽጉጥና ክላሽ ከመሸከም በላይ፣ ከምን እንኳን እንደተሠራ የመረዳት አቅም የሌለው አዕምሮ ነው መሣሪያ የሚያመልከው። ሩጫውና ጥድፊያው ወንድሙን መግደያ መሣሪያ በመታጠቁ ላይ ነው።
አንድ የካርቱን ቀልድ ትዝ አለኝ። ከዚህ ዓለም ውጪ ያሉ ሁለት ፍጥረታት (ኤልየንስ) ወደ ምድር ይመለከታሉ። ከዚያ አንደኛዋ አይገርምሽም ምድር ላይ ያሉ ሰዎች የኑክሌር ሚሳይል መሥራት ችለዋል ትላለች። ሁለተኛዋም ይገርማል ሰዎች ማሰብ ጀምረዋል ማለት ነዋ (Wow there is a sign of Intelligence Life) ትላለች፡፡ በመቀጠል አንደኛዋ መለስ ትልና አይመስልም፣ ምክንያቱም ሚሳይሉን የደገኑት እርስ በርሳቸው ላይ ነው ትላለች።
ቀልዱ ምድርን የሚያጠፋ ኑክሌር ፈልስፎ በምንኖርባት ምድር ላይ መደገን፣ የማሰብ ችሎታ ገና በምድር ላይ አልመጣም ለማለት ነው። ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የመጣው ትውልድ እንደ ጥንቱ እንኳን በፈረስ ጉግስ፣ በጦር አወራወር፣ በጎራዴ አመካከቱ የሚኮራ ሳይሆን ፈረንጅ በሰጠው ጠመንጃ ወንድሙን በመግደል ጀግና፣ ነፃ አውጪ፣ ፕሬዚዳንት፣ ገዥ ለመሆን የሚመኝ ደካማ ጭንቅላት መያዙ ነው። ለዚህ ነው በእንስሳት እንኳን የሌለው የችግራችን መፍትሔ መግደል ነው የሚለውን ሥነ ልቦና በደንብ መጠናት አለበት የምለው።
እኔ የሥነ ልቦና ተመራማሪ አይደለሁም፡፡ በአቅሜ ባነበብኩት ግድያ የበታችነት ሥነ ልቦና ውጤት እንጂ፣ የሐሳብ ወይም የሞራል የበላይነት አይደለም። ትልቅ ሐሳብ መፍጠር የሚታየውንም የማይታየውንም መመርመር የሚያስችል አዕምሮ የተሰጠን ፍጡራን ተናግረን ማሳመን፣ ተሟግተን መፍታት፣ በመረጃና በጽሑፍ ሐሳብ ማስቀየር የሚያስችል አዕምሮ፣ ልሳንና ጽሑፍ እያለን በመግደል እንኳን አሸነፍን እንላለን። እንደነ ፑሽኪን ዘመን ሩሲያ እንኳን ‹ወንድ ለወንድ ይዋጣልን› ተባብሎ ተቃጥሮ፣ ፊት ለፊት በመቆም ፈጥኖ ሽጉጥ አውጥቶ የመተኮስ ያህል እንኳን ድፍረት የማይጠይቅ ተግባር በእኛ አገር ነግሷል። አድፍጦ ወንድምን ማጥፋት ሆነ ሥራችን። ትውልደ ኢትዮጵያዊ የነበረውና በእኛም አገር ሐውልት የቆመለት ታላቁ የሩሲያ ገጣሚ ፑሽኪን፣ በወጣትነት ሕይወቱ የተቀጠፈው በዚህ ዓይነቱ ግጥሚያ ነበር።
ዓለም ቢቀየርም እኛ የ17ኛው ክፍለ ዘመን ጭንቅላት ይዘን እንዴት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተፎካካሪ እንደምንሆን ግልጽ አይደለም፡፡ ለምንስ ግድያ በእኛ አገር እንደ ማሳመኛ መሣሪያ አድርገው የሚወስዱ ሰዎች እንደ አሸን እንደፈሉ መመርመር አለብን። ጥርብ ግብዝነት ካልሆነ በስተቀር እኛ ጀግንነት የምንለው የመግደል ተግባር ጊዜ ያለፈበት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ግድያን እንደ ወንድነትና ጀግንነት የሚያየውን ሥነ ልቦና ደግመን ደጋግመን መፈተሽና መቀየር ያስፈልጋል።
ወንድነትና ጀግንነት የሚባለው ጊዜ ያለፈበት ብሂልን ከውስጣችን ማውጣት ያስፈልጋል። ጀግና ወንድሙን ከፈረንጅ በተሰጠው መሣሪያ የሚገድል ሳይሆን፣ የፊዚክስን ሕግጋት ተረድቶ ከአተም ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ጭንቅላት ያለው፣ ወይም የመሬት ስበትን ሚስጥር ተረድቶ ወደ ጨረቃ መመንጠቅ የሚያስችል ጭንቅላት ያለው እንጂ፣ ከፈረንጅ የተገዛ ብረት ተሸክሞ ‹ጀግና›፣ ‹ጀጋኑ› ብሎ በሚታበይ ጭንቅላት አይደለም። የተሸከመው ብረት ከምን እንደተሠራ መገንዘብ የማይችል አዕምሮ ተሸክሞ ወንድሙን መግደል ጀግንነት አይደለም።
ይህ ጀግንነት የሚባለው ከዓድዋ ድል በኋላ ጊዜው አልፏል። ጣሊያን ከ40 ዓመታት በኋላ ተመልሶ ሲመጣ ጭንቅላት እንጂ ጀግንነት ዋጋ አልነበረውም። ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር አብሮ የነበረው እንግሊዛዊው ጆርጅ ስፒርስ የተባለው ጸሐፊ በኦጋዴንና በወልወል ግንባር የነበረውን ሁኔታ ‹ቄሳር በአቢሲንያ› (Cesar in Abyssinia) በሚለው መጽሐፍ ውስጥ የመዘገበውን ማንበብ ይበቃል። አንዱ የኢትዮጵያ ጀግና ያሉትን መዝግቧል። ምን እናድርግ ከሰማይ ጋር መዋጋት (We Can’t fight the heaven) አንችል ነበር ያሉት፡፡
አዕምሮ በወለደው በሰማይ የሚበር አውሮፕላን ከላይ በሚረጭ መርዝ የኢትዮጵያ ጀግኖችን እንደ ቅጠል አረገፈ። ይህ እኛ የምንታበይበት የግብዞች ጀግንነትና ወንድነት ለታሪክ ጸሐፊዎች እንጂ፣ ለዘመናዊ ሕይወትና ነፃነት ዋጋ የለውም። ዛሬ የጣሊያን መንግሥት እንደያኔው 500 ሺሕ ወታደሮች በመርከብ ማጓጓዝ አያስፈልገውም፡፡ እነሱ ከመኝታ ቤታቻው ሆነው በኮምፒዩተር መስኮት እያዩና ሰው አልባ አውሮፕላን እየላኩ ከፈለጉ ቦምቡን፣ ከጨከኑ ደግሞ መርዙን ሊረጩብን ይችላሉ። ዛሬም እንደ ማይጨው የጦርነት ጀግና ‹‹ምን እናድርግ እንዴት አድርገን ከሰማይ ጋር እንዋጋ?›› የማያስብለን ምንም የአዕምሮ ውጤት በእጃችን የለም። እንዲህ ደካማ የሆንን ሰዎች እርስ በርሳችን በውሰት ብረት እየተጋደልን ጀግና ነፃ አውጪ ታጋይ ለመባል እንመኛለን። ከቅኝ ግዛት እንኳን የተላቀቁት እንደ ኮሪያና እስራኤል ያሉ አገሮች እግዚአብሔርን ካልፈሩ፣ የአዕምሯቸው ውጤት በሆነው መሣሪያ ዘር ማንዘራቸውን የሚያጠፋ አቅም ገንብተዋል።
እኛ ግን ዛሬም ጎሳ፣ ብሔር፣ ቋንቋና ሥልጣን እያልን መግደልን እንደ መፍትሔና ጀግንነት አድርገን የተሰጠንን ትልቅ አዕምሮ ላለመጠቀም እንቢ እያልን ነው። አገራችን የተሰጣቸውን የማሰብ ፀጋ የሚጠቀሙ ሳይሆን የግብዞች፣ የአክራሪዎችና የጥራዝ ነጠቆች ቤተ ሙከራ ሆናለች። እነሱ ሁሌም ጭፍራ አላጡም። ለዚህ ነው የመግደል ሥነ ልቦና በእያንዳንዳችን ውስጥ ተቀብሮ እንዳለ መመርመር ያለብን።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የዋይኤችኤም ኮንሰልቲንግ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ፣ ዓለም አቀፋዊ የፕራይቬት ኢኩቲ ኢንቨስተር በማምጣት የኢትዮጵያን ኩባንያዎች ለኢንቨስትመንት በማብቃት የማማከር ሥራ በማከናወን ላይ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡