አንዱ አለፈ ሲባል ሌላ ችግር ይወለዳል፡፡ አለፍነው ብለን ስናምን ሌላኛው አደጋ እየተጋረጠ ስናዘግም ዘመናት አልፈዋል፡፡ አሁንም በአገራችን እያጋጠሙን ያሉት ችግሮች በዚህ አዙሪት የሚሽከረከሩ ናቸው፡፡ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ወደፊት መራመድ ያቃተው አካል፣ ባፈጀ ሐሳብ ውስጥ ሲታትር ይታያል፡፡ ያሳዝናል፡፡ በቅን የታሰበ ሒደትን ይቃረናል፡፡ እንዲህ ያሉ ወገኖች ከመንገድ የሚያኖሩት ዕንቅፋት ብዙ ጥፋት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከሰሞኑ የሰማነው አሳዛኝና አንገት የሚያስደፋ ድርጊት አንዱ ማሳያ ነው፡፡
በመጠፋፋትና አሁንም እኔ በሚል ክፉ በሽታ የሚፈጸሙ እኩይ ተግባራት አገርን ወደኋላ ይጎትታል፡፡ ለዜጎች የዘላለም ቁጭት ያኖራል፡፡
አገር የጥቂት ልትሆን እንደማትችል እየታወቀ እንኳን ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› እንዳለችው እንስሳ፣ መልካም ነገሮችን በማሰናከል ለመኖር የሚሹ ወገኖች የኢትዮጵያን አየር እየተነፈሱ መኖር እንዴት እንደሚቻላቸው ግራ ያጋባል፡፡ ጉልበት እንዳለው የሚታወሰው መንግሥት መጪውን ጊዜ ያለ ዱላና ጥይት መሻገር እንደሚችል እያመለከተ፣ ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ መውሰድ ሲገባ ከዚህ ማፈንገጥ ጤነኝነት አይሆንም፡፡ ዛሬም ወደኋላ ተመልሶ መነጋገርና መተማመን እየተቻለ ለዚህም መልካም አጋጣሚዎች ስለመኖራቸው እየተሰበከ፣ ዘሎ ጥይት ቃታ ላይ ጣትን ማሾለክ ከምንም በላይ ያማል፡፡ መጥፎ ምሳሌም ነው፡፡ አድብቶ መተኮስ የሚመርጥ ካለ መንግሥት እንደሚለው ጉልበቱን መጠቀምና ሕግን ማስከበር ይኖርበታል፡፡ የእስከዛሬ የዜጎች ጩኸትም አሁን የበለጠ ድምፅ ይኖረዋልና፡፡ ሕግ ይከበር!
በአዲስ አስተሳሰብ ለመጓዝ የሚሹ ዜጎች ለውጡ ያለደም እንዲሻገር መሻታቸው የሚበልጠው መንገድ በመሆኑ ነው፡፡ ከለውጡ መሪዎችም እስካሁን የተገነዘብነው በመነጋገር ይህን አገር መገንባት ይችላል የሚል ቢሆንም፣ በጎውን ነገር ትቶ ይቅር ለመባባል የማይሻውን ግን እሹሩሩ እያሉ መቀጠል የማይቻል ስለመሆኑ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ መልካም እሳቤ ባሻገር በሰላምና በመነጋገር ለውጥ ለማምጣት የሚቸገሩ ወገኖች ግን የሰው ሕይወት ካልጠፋ ወይም ወንበሩንም ጠረጴዛውንም እኔ ካልያዝኩ በሚል፣ በግልጽ መተኮስና መግደል ውስጥ ከገቡ መንግሥት መንግሥቱን ማሳየት አለበት፡፡
ወትሮም የእኔ ብቻ የሚል መንፈስ ያለውን ወገን የቱንም ያህል መልካም ቢታሰብለት፣ ይህንን እውነት ለመቀበል ይቸግረዋል፡፡ ስለዚህ ቀስ በቀስ ስንንከባለል የመጣው ችግር ከፍ እያለ ሄዶ የአገር ፈርጦችን በጭካኔ ወደ መግደል ከተገባ ያስቸግራል፡፡
ከሰሞኑ ሕይወታቸውን ያጡ ውድ የአገር መሪዎች ጉዳይም ሲታይ ስለምን ይህ ሆነ? ማለታችን አይቀርም፡፡ በርካታ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ አንዱ ሌላኛውን በጥይት ለማነጋገር የተፈለገበት ምክንያት ግራ ያጋባል፡፡ ለሕዝብ በሚሰጡት አገልግሎትና ለአገር በሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ብዙ የሚታመንባቸው እነዚህ ዜጎች፣ የጥይት እራት እንዲሆኑ ለምን ተፈረደባቸው የሚለውን ሚስጥር ለማወቅ ኢትዮጵያውያን ይጓጓሉ፡፡
ግን የዚህች አገር የቁርጥ ቀን ልጆች ላይመለሱ ሄደዋል፡፡ ቀጣዩ ጥያቄ ደግሞ እንዲህ ያለው መንገድ ይህችን አገር ወዴት ይወስዳታል? የሚለው ነው፡፡ ደግሞ እንዲህ ያለው ዘግናኝ ተግባር ላለመፈጸሙ ምን ማስተማመኛ አለ? ዜጎችን እንዲህ ካለ አሸማቃቂ ድርጊት ለመጠበቅ ምን ሊሠራ ታቅዷል የሚለው ሁሉ በአግባቡ መልስ ማግኘት አለበት፡፡
የለውጡ መሪዎች ነገሮችን በእርጋታና በመነጋገር መፍታት እንደሚቻል ጥረት ማድረጋቸው የሚደገፍና አሁንም መቀጠል ያለበት እንደሆነ ቢታመንም፣ በንግግር የማያምነውን ለአገር መፈራረስ ምክንያት የሚሆነውን ግን እንዲህ ባለው መንገድ እያባባሉ መቀጠሉ ዋጋ የሚያስከፍል አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡ ሰሞኑን የሆነውን ልብ ይሏል?
እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎችን ዜጎችን በማሳዘን አገር ወዴት እየሄደች ነው የሚለውን ከማሳሰብ ባሻገር፣ ኢኮኖሚውን በመቆንጠጥ የዜጎችን ሕመም ያብሰዋል፡፡ የኢኮኖሚው ጉዳይ አሁንም ብዙ ሊሠራበት የሚገባ እንደሆነና ከዚህም ከዚያም እየተነገረ እንዲህ ዓይነቱ አደጋ መከሰቱ ሕመሙን ይጨምራል፡፡
እንኳን እንዲህ ዓይነት ነገሮች ታክለውበት በሰላሙም ጊዜ በሆነውና ባልሆነው የሚንገጫገጨው ኢኮኖሚያችን፣ ችግሮች በተደጋገሙ ቁጥር ወደ በለጠ አዘቅት እንዳይገባ መታሰብ አለበት፡፡
እንደ ዜጋ ፖለቲካው ላይ ብቻ በመንጠልጠል ያውም ውጤት ለማይኖረው ነገር የሚደረግ ክፉ ሥራዎች ገንዘብ ያሳጣሉ፡፡ ገበያውን ያግላሉ፡፡ አቅዶ ለመሥራት የሚደረግን መፍጨርጨር ያሳንሳሉ፡፡ ይህ ድምር ውጤት ደግሞ ኢኮኖሚውን በእጅጉ ይጎዳልና መንግሥት በብርቱ እንዲያስብበት ይገባል፡፡
ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃርም እንዲሁ ነው፡፡ ባልተረጋጋ ሁኔታ መልካም አገልግሎት አይኖርም፡፡ የተሻለ ለማገልገልም አይታሰብም፡፡
ሰላም የሁሉም መሠረት እንደሆነ የበለጠ የምንረዳውም ውሎ አድሮ በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳርፈውን ጠንካራ ቡጢ እየተረዳን ስንሄድ ነው፡፡ አሁን በተወሰነ ደረጃ የሚታየው ጉዳት ውስጥ ውስጡን አሸረሸረው ዳግም ለማንሠራራት የሚከብድ በመሆኑ፣ ዜጎች በሠለጠነ መንገድ በመነጋገር አገርም ኢኮኖሚንም ዜጎችንም መታደግ ያስፈልጋል፡፡ አሁንም መንግሥት ሕግ አስከብሮ ጤናማ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ይፈጠር፡፡ ያለበለዚያ በደንበራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ እንዳይሆን መፍራት ነው፡፡