Monday, May 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከአንድ ጊዜ በላይ ጥቅም ላይ የማይውሉ ፕላስቲኮችን ማምረት የሚከለክል ሕግ ሊወጣ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለሙያዎች ከክልከላ ይልቅ የፕላስቲክ ጥቅምና ጉዳቱን ማስገንዘብ ይቅድም ይላሉ

የፕላስቲክ ምርቶችና ፍጆታ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በመምጣት በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪው እስከ አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ሀብት የሚንቀሳቀስበት ግዙፍ የኢኮኖሚ አውታር ለመሆን በቅቷል፡፡ ይህም ሆኖ የብክለቱ መጠን እያየለ በመምጣቱ ምክንያት ከአንድ ጊዜ በላይ ጥቅም ላይ የማይውሉ የፕላስቲክ ምርቶች እንዳይመረቱ የሚከለክል ሕግ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመላኩ በመጪው ዓመት ፀድቆ ወደ ትግበራ ሊገባ እንደሚችል ታውቋል፡፡ 

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የፕላስቲክ ፋብሪካ ከተመሠረተ ከ100 ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን መዛግብት አገላብጠው ካጣቀሱና ስለ ፕላስቲክ ከጻፉ ባለሙያዎች መካከል የኬምስትሪና የፕላስቲክ ባለሙያው አቶ ሲሳይ ክፍሌ ያሳተሙት መጽሐፍ ይህንኑ እውነታ ከትቧል፡፡

አቶ ክፍሌ ‹‹የፕላስቲክ ውዳቂን ወደ ጥቅም በመቀየር የአካባቢ ብክለትን መቀነስ›› በተሰኘው የፕላስቲክ አያያዝ መመርያ አነስተኛ መጽሐፍ፣ በ1898 ዓ.ም. በእንግሊዛውያን አማካይነት የተሰኘውና ‹‹የኢትዮጵያ ሬይን ፕሩፍ ሞኖፖል›› ፋብሪካ ሥራ ጀምሮ እንደነበር የታሪክ ድርሳናትን ያጣቀሱት አቶ ሲሳይ፣ ኩባንያው ብዙም ሳይቆይ አንድም ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በማለፋቸው ሳቢያ፣ ወዲህም ሕዝቡ የሚሸምተውን ዕቃ በፕላስቲክ ማጠንጠሉን በማለመፍቀዱና ሊላመደውም ባለመቻሉ ሳቢያ ኩባንያው ለመዘጋት እንደበቃ አትተዋል፡፡

ይሁንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለና እየተበራከተ የመጣው የፕላስቲክ ውጤቶች ተጠቃሚነት ፍላጎት፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ብክለትነት በመቀየሩ ለበርካታ አገሮች ራስ ምታት ሆኖ ይገኛል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጉዳዮች ተቋም ወይም ዩኤን ኢንቫይሮንሜንት መረጃ መሠረት፣ በአሁኑ ወቅት 300 ሚሊዮን ቶን ፕላስቲክ ይመረታል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1950 ጀምሮ ከ8.3 ቢሊዮን ቶን በላይ ፕላስቲክ እንደተመረተ ተመራማሪዎችን የሚጠቅሰው ተመድ፣ ከዚህ መጠን ውስጥ ከ60 በመቶው በላይ ወደ ቆሻሻ መጣያዎችና ወደ የተፈጥሮ ሥፍራዎች ወይም ወደ ውኃ አካላትና ሌሎችም ቦታዎች ማምራቱን መረጃው ይጠቅሳል፡፡

የፕላስቲክ ምርት ከ500 ዓመታት በላይ ሳይበሰብስ የሚቆይ በመሆኑም የመጀመሪያው የፕላስቲክ ምርት አሁንም ድረስ እንደሚገኝ ይታመናል፡፡ ይህ በመሆኑም በየጊዜው እያደገ የመጣው የፕላስቲክ ውዳቂ ጫና ያሳሰባቸው አገሮች ከአንድ ጊዜ በላይ ጥቅም የማይሰጡ ፕላቲኮች እንዳይመረቱ እየከለከሉ ይገኛሉ፡፡ በአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ዘንድ ዕገዳው ሙሉ በሙሉ ከመጪው ዓመት በኋላ ሊተገበር እንደሚችል የሚጠቁሙ መረጃዎች ይፋ ተደርገዋል፡፡ በአፍሪካም እንደ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያና ሞሮኮ ያሉት አገሮችም ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም የሚሰጡ የፕላስቲክ ምርቶች በተለይም የዕቃ መያዣና መጠቅለያ ፕላስቲኮች እንዳይመረቱ የሚከለክሉ ሕጎችን በማውጣት እየተገበሩ ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶቹም ሕግ ወደ ማፅደቁ ገብተዋል፡፡

በአንፃሩ በኢትዮጵያ በ1999 ዓ.ም. የወጣው የደረቅ ቆሻሻ አዋጅ መሠረት፣ ‹‹ውፍረቱ 0.03 ሜትርና ከ0.03 ሚሊ ሜትር በታች ሆኖ በስበስሶ ከአፈር ጋርማይዋሃድ የፕሊስቲክ ከረጢት የማምረት ወይም ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የተከለከለ ነው፤›› ከማለቱ በቀር እንዲህ፣ በጠቅላላው ቀላል ክብደት ያላቸውና ከአንድ ጊዜ በላይ ጥቅም የማይሰጡ የፕላስቲክ ከረጢቶች ከነጭራሹ እንዳይመረቱ የሚከለክል ድንጋጌ አላሰፈረም፡፡

ይህም ሆኖ ውፍረታቸው 0.03 ሚሊ ሜትርና ከዚያም በታች የሆኑ ፕላስቲክ ከረጢቶች እንዳይመረቱ የሚከለክለው ሕግ ብዙም ሳይተገበር በመቆየቱ በርካታ ፕላስቲክ አምራቾች በምርት ሒደት ተሠማርተው መገኘታቸውን የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ከአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር ባደረገው አሰሳና ክትትል መገንዘቡን፣ በኮሚሽኑ የደረቅና የአደገኛ ቆሻሻዎች አወጋገድ የቁጥጥርና የተስማሚነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ገመቹ አስታውቀው፣ ክትትል ከተደረገባቸው 21 አምራቾች መካከል 14ቱ ሕጉን ተላልፈው መገኘነታቸውን  ገልጸዋል፡፡ ማስጠንቀቂያ ቢጣላቸውም 11 አምራቾች በተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ መሠረት ሊያስተካክሉ ባለመቻላቸው ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአገሪቱ ከ486 በላይ የፕላስቲክ አምራቾች ‹‹ፕላስቲክ መፈብረክ›› በሚል ፈቃድ ተሰጧቸው አሥር ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ካፒታል ተመዝገበው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እንዲህ ያለውን ችግር ለመከላከል የበለጠ ጉልበት ያለው ሕግ በመጪው ዓመት ሊወጣ እንደሚችል የገለጹት አቶ ግርማ፣ ከነጭራሹ እንዳይመረቱና ከውጭም እንዳይገቡ የሚያግድ ጠንካራ ሕግ ማውጣቱ በአካባቢና በሰዎች ጤና እየደረሰ የሚገኘውን ጉዳት መቀነስ እንደሚቻል ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የታሰበውም ሆነ በሌሎች አገሮች እየተደረገ ያለው የክልከላ ዕርምጃ የፕላስቲክን ጠቀሜታ በቅጡ ካለመገንዘብ እንደሆነ በመግለጽ የሚሞግቱት አቶ ሲሳይ፣ በየትኛውም የዕለት ተዕለት የሰው ልጆች ኑሮ ውስጥ ፕላስቲክን ማስገወድ የማይቻል እየሆነ በመምጣቱ አወጋገዱ ላይ ግንዛቤ መፍጠር ከክልከላ የተሻለ ውጤት እንደሚኖረው ያምናሉ፡፡ አልባሳት፣ መጫሚያዎች፣ ኮምፒውተሮች፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመመገቢያ ቁሳቁሶችን ጨምሮ በዙሪያችን የፕላስቲክ ውጤቶች ከፍተኛ ሚና ይዘው ይገኛሉ የሚሉት አቶ ሲሳይ፣ እንደውም የፕላስቲክ ውጤቶች በደንና በሌሎችም የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና በመቀነስ እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽኦ በማስተዋል፣ ይልቁን በየአካባቢው እንደ አልባሌ የሚጣለው ውዳቂ ፕላስቲክ ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኝ ሀብት በመሆኑ ይህንን መለወጥ እንደሚገባ ያብራራሉ፡፡

ምንም እንኳ ጣልያኖች የመጀመሪያዎቹን የፕላቲክ ከረጢቶችና የውኃ መያዣዎች እ.ኤ.አ. በ1957 ከፈለሱ ወዲህ ከጥቅማቸው ይልቅ ለአካባቢ ብክለትና ጉዳት እያደረሱ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ እየሆነ በመምጣቱ ተመድ ሳይቀር ከፍተኛ የቅስቀሳ ዘመቻ ከከፈተ ውሎ አድሯል፡፡

ክብደታቸው በመቶ ኪሎ ግራሞች የሚመዘኑ ትልልቅ የባህር አሳ አንበሬዎች ፕላስቲክ በመመገባቸው ሳቢያ አልታኘክና አልፈጭ ብሎ ሆዳቸው ውስጥ የታጨቀ የፕላስቲክ ውድቅዳቂ ለህልፈት መዳረጋቸውን የሚያሳዩ ዜናዎች ተደጋግመው ተሰምተዋል፡፡ በቅርቡ በፊሊፕንስ ውስጥ ከ30 ኪሎ ግራም በላይ የፕላስቲክ ውዳቂ በመመገቧ ለሞት የተዳረገች ነፍሰ ጡር አሳ አንበሬ የዓለም መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ እንደነበረች ይታወሳል፡፡ በአውስትራሊያም ተመሳሳይ ዘገባዎች ተስተጋብተዋል፡፡ ዳክዬዎች፣ አእዋፋት፣ የባህል ኤሊዎች፣ የዱር እንስሳትና ሌሎችም በፕላስቲክ ውጤቶች እየታፈኑ፣ እየታነቁና የበሉትም አልፈጭ ብሏቸው ለሞት ሲዳረጉ እየታዩ ነው፡፡

በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ክስተቶች ተስተናግደዋል፡፡ አዕዋፋት ብቻም ሳይሆኑ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ያለ ጥንቃቄ በየቦታው በሚጣሉ የፕላስቲኮች ቀረጢቶችና ዕቃ መጠቅለያዎች ችግር ሲደርስባቸው ይታያል፡፡ በተለይም የቁም እንስሳት በብዛት በየመንደሩ የሚጣሉ የፕላስቲክ ውዳቂዎችን እየተመገቡ ሲታወኩና ለሞት ሲዳረጉ ማየት የተለመደ ነው፡፡

ኮሚሽኑ እንዲህ ያሉ ተፅዕኖችን ለመቀነስ ቢነሳም፣ በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ መገኘቱ በአገር ውስጥ ለሚመረቱ ልዩ ልዩ የፕላስቲክ ውጤቶች እንዲበራከቱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ ይህንን ተከትሎም ከወዲሁ ተገቢው የፕላስቲክ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት በአስገዳጅነት ጭምር ካልተተገበረ በቀር የፕላስቲክ ውጤቶች ተፅዕኖ እስካሁን ከሚታየውም የከፋ ሊሆን እንደሚችል እየተገለጸ ነው፡፡

የተለያዩ የፕላስቲክ ምርቶችን ከሚያመርቱ 500 ያህል ድርጅቶች ባሻገር 80 ያህል ውኃ አምራቾች በፕላስቲክ ጠርሙሶች ምርቶቻችን ያሽጋሉ፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ የለስላሳ መጠጥንና ሌሎችም የሚያመርቱ ፋብሪካዎችም በየጊዜው በፕላስቲክ ውጤቶች የሚታሸጉ ምርቶች ላይ እያተኮሩ በመምጣታቸው የፕላስቲክ አወጋገድ ሥርዓቱ ትኩረት እንደሚያሻው ባለሙያዎቹም ሆኑ የመንግሥት አካላት ከወዲሁ እያሳሰቡ ይገኛሉ፡፡ ተጠቃሚው ኅብረተሰብ ግን ዋናው ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አካል በመሆኑ የፕላስቲክ አጠቃቀሙና አወጋገዱ ላይ ብሎም አካባቢ፣ የሰው ጤናና የእንስሳት አኗኗር ላይ የሚደርሰውን አደጋ በመገንዘብ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያሳስባሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች