Saturday, December 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሰባተኛው የአፍሪካ ሆቴል ዓውደ ርዕይ ከ140 በላይ ድርጅቶችን አሳተፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገር ገጽታን ለመገንባት ብሎም ማኅራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ለማስመዝገብ የግል ዘርፉ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ሲገለጽ፣ በተለይ በሆቴልና ቱሪዝም መስክ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት የሚንታመንበት ዓውደ ርዕይ ሐሙስ ሰኔ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ሰባተኛው ‹‹ሆቴል ሾው አፍሪካ 2011›› የሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዓውደ ርዕይ በተከፈተበት ወቅትም ይህ ሐሳብ ተንጸባርቋል፡፡

‹‹ከመንግሥት በላይ የግል ዘርፉ የአገር ገጽታን መገንባት ይችላል፡፡ ይህም ሲባል መንግሥት የራሱን ፕሮግራም ሲቀርጽ የግል ዘርፉ ደግሞ እምነት እንዲጣልበት ያደርጋል፤›› ሲሉ አቶ ቁምነገር ተከተል የኦዚ ዓለም አቀፍ የሆቴል ፕሮጀክት አማካሪዎች መሥራችና ባለቤት ገልጸዋል፡፡

ለአራት ቀናት የሚቆየው የሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዓውደ ርዕይ 140 ድርጅቶች የተሳተፉበት ሲሆን፣ 500 የምርት ዓይነቶችን ተወክለዋል፡፡ በዓውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳይ (ዶ/ር) በመገኘት የንግድ ለንግድ ትስስሩን ከማጠናከር አኳያ እንዲህ ያሉ መድረኮችን መጠቀም የግድ እንደሚል ተናግረዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ሁነቶች በሆቴልና መሰል መስኮች ለተሰማሩ፣ በአስጎብኚነት ዘርፍ ለሚገኙ እንዲሁም በትራንስፖርት ውስጥ ላሉ በጥቅሉ በቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ውስጥ ላሉ አካላት የገበያቸውን መክፈቻ ቁልፍ የሚያገኙበት ብቻ እንዳልሆነ በመግለጽ፣ ሁነቶቹ ከሌሎች አገሮች የካበተ ዕውቀት ይዘው ከመጡ ተሳታፊዎች ጠቃሚ ልምዶችን ለመቅሰም ስለሚረዱ መድረኩን በሚገባ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል፡፡ በዓውደ ርዕዩ ላይ ከዲዛይን ጀምሮ በግንባታ፣ በቤተ ውበት፣ በግንባታ አጨራረስ መስክ የተሰማሩ በአገር ውስጥ ያሉና ከውጭ የመጡ ድርጅቶችም ተሳትፈዋል፡፡

ከተሳተፉት ድርጅቶች አንዱ የሆነው ማኪ ቤተ ውበትና አርት ጋለሪ ሲሆን፣ የማንኛውም ሕንፃ የውስጥ ውበት ጥበቃ ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡ ‹‹ዓውደ ርዕዩ ሆቴሎች፣ እኛን እንዲሁም ሌሎች ምርቶችን የሚይዙ ድርጅቶች በአንድ መድረክ ያሳተፈ በመሆኑ በቀላሉ መገናኘት እንድንችል ረድቶናል፡፡ ከዚህ በበለጠ መድረኩ የንግድ ትስስርም ይፈጥርልናል፤›› በማለት የድርጀቱ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ማራኪ ተጠምቀ ገልጻለች፡፡

‹‹ከንግድ ትስስሩ በተጨማሪም የእኛ ኢንቨስተሮች ዘመናዊ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ከማድረግ ባሻገር ቴክኖሎጂ የት እንደደረሰ ግንዛቤ እንዲጨብጡም ያደርጋል፤›› በማለት በአገር ውስጥ ያሉ የግንባታ ጥራት እንዲሁም የዲዛይን ችግሮች እንዲህ ባሉ መድረኮች አማካይት የዕውቀት ሽግግር በመፍጠር የአገር ውስጥ አምራቾችን የተሻለ ማድረግ እንደሚቻል አቶ ቁምነገር ገልጸዋል፡፡

ዓውደ ርዕዩን ለማዘጋጀት 3.5 ሚሊዮን ብር እንደወጣ የገለጹት አቶ ቁምነገር፣ ባለፈው ዓመት ከወጣው ወጪ አንጻር ይህ ሁለት እጥፍ ነው ይላሉ፡፡ ከተሳታፊ ድርጅቶች አንጻር ደግሞ እስከ 15 በመቶ ዕድገት መታየቱንም አክለዋል፡፡

በዕለቱ ከዓውደ ርዕዩ መክፈቻ ባሻገር በቱሪዝም መስክ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎችም ተሸልመዋል፡፡ ሽልማት ከተበረከተላቸው መካከል የቀድው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፣ የትራቭል ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሳምራዊት ሞገስ፣ ጋዜጠኛ ሔኖክ ሥዩም እንዲሁም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፎዚያ አሚን ይገኙበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች