የአፍሪካ መድኃኒት አምራቾች በድጎማ የሚገቡ የውጭ ምርቶች ከገበያ እያራቋቸው እንደሚገኙ ገለጹ
ባለፈው ዓመት በሩዋንዳ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ወቅት የተፈረመው ከታሪፍ ነፃ አኅጉር አቀፍ የንግድ ስምምነት 52 አገሮችን ቢያካትትም ተግባራዊ ወደ መሆን የሚሻገርበትን ውሳኔ ማግኘት የቻለው ግን ከጥቂት ቀናት በፊት ነበር፡፡
ይኸውም ጋምቢያ ለስምምነቱ መተግበር የሚያስፈልገውን ዝቅተኛ ኮታ በማሟላት ውሳኔዋን በማሳለፏ፣ እስካለፈው ሚያዝያም 22 ፈራሚ አገሮች በፓርላማዎቻቸው አማካይነት ስምምነቱን በማፅደቃቸው ወደ ትግበራ እንደገባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ይፋ አድርጓል፡፡
ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ በቆየውና ቀጣናዊ የንግድ ፎረም ወቅት እንተገለጸው፣ 22 አገሮች እስካለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ድረስ በፓርላማ ያፀደቁትን የስምምነት ሰነድ ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን አስረክበው ነበር፡፡ ጋምቢያ ማክሰኞ ሰኔ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀረጥና ከታሪፍ ነፃ አኅጉር አቀፍ የንግድ ስምምነቱን ሰነድ ለኅብረቱ በማስረከቧ፣ በመጪው ወር መጀመርያ ሳምንት በኒጀር በሚካሄድ ጉባዔ፣ ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የንግድ ስምምነቱ በይፋ እንደሚታወጅና ወደ ትግበራ መግባቱ እንደሚበሰር ታውቋል፡፡
ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የጋራ ንግድ ስምምነቱ በአፍሪካ አገሮች መካከል የእርስ በርስ ንግድን በማጠናከር ረገድ እስካሁን የነበረውን ዝቅተኛ የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነት ወደ 52 በመቶ እንደሚያሳድገውና እስከ 90 በመቶ የታሪፍ ቅናሽ ለማስመዝገብ እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡ በአሁኑ በአፍሪካ መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት ከ15 በመቶ በታች ሲሆን፣ በአገሮቹ መካከል ተደራራቢ ቀረጥና ታክስን ጨምሮ በርካታ የንግድ ክልከላዎች እንደሚታዩበት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የንግድ ስምምነቱ ለትግበራ ምዕራፍ እየተቃረበ መምጣቱን ተከትሎ፣ በየኢኮኖሚውና በንግድ መስኮች ላይ ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ ከሰሞኑም በአፍሪካ የመድኃኒት አምራች ዘርፍ ላይ በማተኮር በአፍሪካ ቀንድ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ የሁለት ቀናት ስብሰባ፣ ከሐሙስ ሰኔ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተካሒዷል፡፡
በስብሰባው እንደተገለጸው በአፍሪካ ጤና ክብካቤው ዘርፍ ከውጭ የሚገባው ልዩ ልዩ መድኃኒት እስከ 70 በመቶ እንደሚደርስ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ቬራ ሶንግዌ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ይሁንና በአፍሪካውያን አምራቾች ዘንድ ከሚመረተው ውስጥ ሁለት በመቶው ብቻ ገበያ እንደሚያገኝ የጠቀሱት ሶንግዌ፣ ከውጭ ለሚገባው መድኃኒት ከ14.5 ቢሊዮን ዶላር በየዓመቱ ወጪ እንደሚደረግ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2030 የመድኃኒትና የጤና መጠበቂያ ምርቶች ከ259 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ሊደረግ እንደሚችል ትንበያዎችን ያጣቀሱት ዋና ጸሐፊዋ፣ አፍሪካውያን ኩባንያዎች በአኅጉራዊው የንግድ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡
ይህ ይባል እንጂ የአፍሪካ አምራቾች ግን የገበያ ዕድሉ እየተነፈጋቸው በአንፃሩ ከውጭ ለሚገቡ መድኃኒቶች ድጎማ የሚሰጥበት ማበረታቻ ስለሚደረግላቸው፣ የአፍሪካ አምራቾች ከገዛ ገበያቸው ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ፣ ኢንፎቴክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የተሰኘውን ኩባንያ በሊቀመንበርነትና በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩት ሚስተር አሊ ሙፉሩኪ ገልጸዋል፡፡
እንደ ሚስተር ሙፉሩኪ ማብራሪያ አፍሪካ በየቀኑ ከ80 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ሀብቷን ለውጭ መድኃኒት ግዥ በማዋል እያጣች ነው በማለት፣ አፍሪካ የጤና አጀንዳዋን መልሳ የራሷ እንድታደርግ ጠይቀዋል፡፡ አፍሪካ ያሉባት የጤና ችግሮች ለመቅረፍ ዕርዳታ የሚሰጡት የምዕራብ አገሮች፣ በዚያው ልክ አፍሪካ የረዥም ጊዜ የገበያ መዳረሻቸው በማድረግ ስትራቴጂ ይቀርፃሉ ያሉት ሚስተር ሙፉሩኪ፣ የአፍሪካ ቀጣና የንግድ ስምምነት ለአፍሪካ ኩባንያዎች መልካም ዕድል ይዞ በመምጣቱ በዚህ ዕድል ለመጠቀም የሚያስችል እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካን አኅጉራዊ የጋራ ንግድ ስምምነትን ከፈረሙና ካፀደቁ አገሮች አንዷ መሆኗን ያስታወሱት፣ የኢትዮጵያ የንግድ ዋና ተደራዳሪና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ አቶ ማሞ እስመለዓለም ምሕረቱ ናቸው፡፡ በመድረኩ አቶ ማሞ ኢትዮጵያ ስምምነቱን ስለተቀበለችበት ጉዳይ ሲያብራሩ፣ የአፍሪካን ብልጽግና ለማምጣትና የፓን አፍሪካ ይዘት እንዳለው በመገነዘቧ፣ ከዚህም ባሻገር የኢኮኖሚ ፍላጎት ስላላትም ጭምር ፈራሚ አባል መሆኗን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በጎረቤት አገሮች ሰፊ የገበያ ዕድል ቢኖራትም ወደ ውጭ ከምትልከው ምርት አኳያ ወደ ጎረቤት አገሮች የምትልካቸው ምርቶች ከ20 በመቶ ያነሱ ስለመሆናቸው ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል የአውሮፓ ኅብረት ለአፍሪካ የጋራ ንግድ ትብብር ድጋፍ የሚውልና የኢንቨስትመንት ዕድል ለማስፋፋት ብሎም እስከ አሥር ሚሊዮን ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል የ40 ቢሊዮን ዩሮ ዕርዳታ ለመስጠት ማቀደኑን አስታውቋል፡፡ ይህ ድጋፍ በአፍሪካና አውሮፓ አኅጉሮች መካከል የጋራ የንግድና የኢንቨስትመንት ማዕቀፍ ለመፍጠር ባለፈው ዓመት ከተደረገው ስምምነት ጋር እንደሚያያዝ፣ በአውሮፓ ኅብረት ልዑል የአፍሪካ ኅብረት ተጠሪ አምባሳደር ራይነሪ ሳባቱቺ አስታውቀዋል፡፡