ታዋቂው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ሆነው ተሾሙ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ከቀረቡለት አጀንዳዎች መካከል፣ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በዕጩነት የቀረቡትን ኮሚሽነር ሹመት ማፅደቅ ነበር።
በምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ለሚመራው ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ በዕጩነት ቀርበው ከነበሩት 88 ግለሰቦች መካከል፣ ባላቸው የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ ተመዝነው ብቁ ሆነው የተገኙት ዳንኤል (ዶ/ር) መሆናቸው ተገልጿል።
ዕጩ ሆነው የቀረቡት ዳንኤል (ዶ/ር) ከኮሚሽነር ኃላፊነታቸው በተጓዳኝ ሌሎች ሥራዎችን ለማከናወን እንዲችሉ እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ፋታ የማይሰጡ በመሆናቸው ጥያቄያቸውን ለጊዜው እንደማይቀበለው፣ ነገር ግን ወደፊት የሥራ አፈጻጸማቸው ታይቶ ሊፈቀድላቸው እንደሚችል በመግለጽ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል።
በዚህም መሠረት ግለሰቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ሆነው እንዲሾሙ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ምክር ቤቱ ተቀብሎ፣ በአንድ ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል። በመሆኑም ተሿሚው የቀድሞውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) ይተካሉ።
ተሿሚው ኮሚሽነር ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ሕግ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በቅርቡ የያዙ ሲሆን፣ በ1997 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ተካሂዶ በነበረው አገር አቀፍ ምርጫ ማግሥት በተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ ለእስር ተዳርገው ነበር።
ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ከአገር በመውጣት የዓለም አቀፉ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ አፍሪካ ኃላፊ ሆነው በኬንያ ያገለገሉ ሲሆን፣ በኋላም መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የታዋቂው ሒዩውማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ዳይሬክተር ሆነው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አገልግለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ባደረጉት የአሜሪካ ጉዞ ወቅት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድን እንዲመሩ ጥያቄ አቅርበውላቸው ጥያቄውን መቀበላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በዚሁ ወቅትም በተመሳሳይ ዳንኤል (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር እንዲሆኑ ያቀረቡላቸውን ጥያቄ ተቀብለው ነበር፡፡ የዶክትሬት ትምህርታቸውን እስኪያጠናቅቁና ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽነርነት ዕጩ የሚመለመልበት ሕጋዊ ሥነ ሥርዓት እስኪፈጸም ድረስ ሹመታቸው መዘግየቱን፣ የሪፖርተር መረጃዎች ያመለክታሉ።