Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሸዋል ዒድ በሐረር ሌላኛው የመተጫጨት ክብረ በዓል

ሸዋል ዒድ በሐረር ሌላኛው የመተጫጨት ክብረ በዓል

ቀን:

ከተማዋ ከዕድሜ ጠገብነቷ ባሻገር በርካታ ታሪካዊና ታላላቅ ቅርሶችን በማቀፍ  ዘመናትን ተሻግራለች፡፡ ከተቆረቆረችበት ሰባተኛ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በታሪክ መዝገቦች ላይ ስሟ ተደጋግሞ እንዲነሳ ምናልባትም በትንሽ ቦታ ላይ በርካታ ቅርስና የቱሪስት መስህብ መገኛ ከተማ መሆኗ ብቸኛ ያደርጋታል፡፡ ሐረር ሁለት የዩኔስኮ ሽልማቶችን ካገኙ ጥቂት የዓለማችን ከተሞች አንዷ መሆኗ ይነገራል፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ የአዳል ሙስሊም መንግሥት መቀመጫ በመሆን ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰችበት ዘመን እንደነበር የተለያዩ የታሪክ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

በተለይ የዓለም ቅርስ ባለቤትና የሰላም የመቻቻልና የአንድነት ከተማ የሚል ስያሜን ከመቸር ባሻገር ‹‹ሐረር ህያዊቷ ሙዚየም›› በመሰኘት ተሰይማለች፡፡

ከተማዋ ከምሥረታዋ ጀምሮ እስከ ሁለተኛው የእስልምና ጉዞ ወደ ሐበሻ ምድር፣ እንዲሁም ከሼክ አባድር የሐረር ጉዞ እስከ እንግሊዛዊው ተጓዥ ሪቻርድ በርተን ድረስ ቱሪስቶችን የመሳብ አቅም ያላት ከተማ ስትሆን በአሁኑ ወቅትም በርካታ ቱሪስቶች መዳረሻ አድርገዋታል፡፡

ሸዋል ዒድ በሐረር ሌላኛው የመተጫጨት ክብረ በዓል

የሐረር መገለጫ ከሆኑት ግንባር ቀደም ከሆነው አንዱ የሐረር ግንብና በሮቹ (ጁገል) አንዱ ነው፡፡ ጁገል ከኢትዮጵያ 11ዱ የዓለም ቅርሶች መካከል አንዱ ሲሆን ግንቡ በአሚር ኑር ቢን ሙጂሐዲን ከ1551 እስከ 1559 መገንባቱ ይነገራል፡፡ ግንቡ የተገነባው ከውጭ ወራሪ ራስን ለመጠበቅ ታስቦ ሲሆን፣ 3,334 ርዝማኔና 12 ጫማ ከፍታ ሲኖረው ስፋቱ ደግሞ በ66 ሔክታር ቦታ ላይ ያረፈ ነው፡፡

በአምስቱ መግቢያ በሮች በ24 መጠበቂያ ማማዎች (በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ይገኛሉ) ከ359 በላይ ቀጫጭን መንገዶችና እንዲሁም በርካታ ባህላዊ የሐረር ቤቶችን በመያዝ የ16ኛው ክፍለ ዘመን የሥነ ሕንፃ ጥበብን ዛሬም በጉያዋ ይዛለች፡፡ ታዲያ ከ23 በላይ ታላላቅ ቅርሶችን፣ አድባራትን፣ ባህላዊ መስህቦችንና ቅርሶችን በመያዝ በዩኔስኮ ያልተመዘገቡትን ለማስመዝገብ ደፋ ቀና እያለች ትገኛለች፡፡

ሐረር ለዘመናት ካቆየቻቸው ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶች መካከል አንዱ የሆነው ‹‹ሸዋል ዒድ›› በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ ጀምራለች፡፡ የምሥራቋ ታሪካዊት ከተማ ከመቆርቆሯ 405 ዓመት ጀምሮ አራተኛዋ የእስልምና ከተማ መሆኗ ይነገራል፡፡ ‹‹የበል አወልያ ወይም ፃደቀን ተራራ›› በመባል የምትታወቀው ሐረር ወደ ከተማዋ የመጡት 40 ወልሂዮዎች በአካባቢው እንቅስቃሴ ሲጀምሩ በኢትዮጵያ የረመዳን ጾም የማክበር ሁኔታ እንደተጀመረ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ሸዋል ዒድ ከረመዳን ቀጥሎ ያለው አሥረኛው ወር ሲሆን ተጨማሪ ስድስቱ ቀናት ተጹሞ በሰባተኛው ቀን ዒድ ይደረጋል፡፡ በሐረር የሚከበረው ሸዋል ዒድ ሃይማኖቱንና ባህሉን ያወራረሰ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ነገሮቹ ሰላት መስገድን፣ መስዋዕት መስጠትንና ሐጂ መሄድን ያካትታል፡፡

በሃይማኖታዊ ሥርዓቱ በተለይ ረመዳን መጾም ያልቻለ ወይም የረመዳን ሙሉ ጾም ችሎ ተጨማሪዋን ስድስተኛ ቀን ከጾመ ዓመቱን ሙሉ የጾመ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ መምህር ቶፊክ የሱፍ በሐረር አካባቢ በሽምግልናና አስታራቂነት ይታወቃሉ፡፡ እንዲሁም ‹‹ባለ ቀይ ፂም›› በሚል መጠሪያ ይታወቃሉ፡፡

መምህር ቶፊክ ሸዋል ከሴቶች ጋር በተለይ ተያያዥነት እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ የሴቶች የወር አበባ ከፍተኛ ቀን ስድስት በመሆኑ በረመዳን ወቅት መጾም ስለማይችሉ፣ የሸዋል ስድስት ቀናት የረመዳን ማካካሻ ተደርጎ እንደሚቆጠር መምህር ቶፊክ ይናገራሉ፡፡ መምህሩ የተፈጥሮ ጉዳይ ስለሆነ በተለይ በሴቶች ሸዋል ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው የሚያከብሯት ወቅት ነች ይላሉ፡፡

‹‹ክብረ በዓሉ ሃይማኖታዊ እንዲሁም ባህላዊ ሥርዓቶችን ያማከለ ነው፡፡ በዕለቱም ሁለቱም ኩነቶች ይከናወናሉ፤›› በማለት ሥነ ሥርዓቱን ለሪፖርተር ያብራራሉ፡፡ ከሃይማኖታዊ ክንውኑ ባሻገር ባህላዊ ሥነ ሥርዓቱ በጁገል ግንብ ውስጥ ከስድስተኛ ቀን ምሽት ጀምሮ በድምቀት ለተከታታይ ሦስት ቀናት ይከበራል፡፡

በሸዋል ባህላዊ ሥነ ሥርዓት ያላገቡ ሴቶች ካላገቡ ወንዶች ጋር የሚተጫጩበት ሌላኛው ክብረ በዓል ነው፡፡ በተለይ በጁገል ውስጥ የሚገኙ ከ359 በላይ ቀጫጭን መንገዶች ለመተጫጨቱ ድርሻቸው የጎላ ነው፡፡ የሸዋል ባህላዊ ክንውኖች እንደየዘመኑ የመፈራረቅ ሁኔታዎች ቢስተዋልም፣ ቀድሞ የነበረው ሥርዓት አስደሳች እንደነበር መምህሩ ያስታውሳሉ፡፡ በጊዜው ሥነ ሥርዓቱ በትምህርት ቤት ደረጃ ግንዛቤ ያልተሰጠው በመሆኑ ወጣቶች ከወላጆቻቸው በመማር ከትውልድ ወደ ትውልድ አስተላልፈው እዚህ አድርሰውታል፡፡  

መምህሩ በጊዜያቸው የነበረው የሸዋል ክብረ በዓልን ሲያወሱ፣ የመተጫጨት ሒደት ሴቷ በተለያዩ ባህላዊ አልባሳት ተውባና አምራ በእነዚያ ቀጫጭን መንገዶች ተመላልሳለች፡፡ በዚህ ወቅት ወንዱም ቀልቡ የሳባትን ልጃገረድ ከተመለከተ በኋላ ቤተሰቦቹ ዘንድ በመሄድ ያሳውቃል፡፡ ከዚያም ይላሉ መምህር ቶፊክ የልጅቷን መኖሪያ ሥፍራ፣ ቤተሰቦቿንና ፀባይዋን የሚያጠና የቅርብ ዘመድ ወደ ሥፍራው ይላካል፡፡ ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ቤተሰቦቿ ሽማግሌ ተልኮ ትዳራቸውን ይመሠርታሉ፡፡

‹‹ሁሉም ሒደት በወላጆች ዕውቅናና ፈቃድ ይከናወናል፡፡ ሙሉ ኃላፊነት በቤተሰቦች እጅ የተጣለ ስለሆነ ፍቺ የሚባል ነገር እምብዛም ነው፤›› በማለት መምህር ቶፊክ የሥርዓቱን በጎነት ያወሳሉ፡፡

ከዚህም ባሻገር የመተጫጨቱ ሁለተኛው መንገድ ሴቶች ሸዋል ከመድረሱ በፊት ገንዘብ አዋጥተው በቤት ውስጥ የሚሠሩትን የተለያዩ ምግቦች በማሰናዳት ሥራ ይጠመዳሉ፡፡ ሰፊ ግቢ ውስጥ ተሰብስበው ይመገባሉ፣ ይጫወታሉ፣ ይዝናናሉ፡፡ በዚህ ወቅት በቅርበት ሆነው ጎረምሶች በቅርብ ርቀት በሚመለከቷቸው ጊዜ በውበታቸው በመማረክ የሠሩትን ምግብ እንደ መንጠቅ በሚል ሰበብ ከልጃገረዶች ጋር በሚያደርጉት ጉስሚያ የመተጫጫ መንገድ ይፈጥራሉ፡፡

የቀድሞን የመተጫጨት ሒደትና የዘንድሮውን ሥርዓት ሲያወሱ ‹‹አሁን ወንዶች የታጠቁት ሱሪ ቶሎ ይፈታና በአጋጣሚው ይተዋወቁና ወደድኩሽ ወደድኩሽ በጥድፊያ ተጋብተው ቶሎ ይፋታሉ፡፡ ‹‹በድሮ ጊዜ ግን ወንድ ልጅ የሚታጠቀው ሱሪ ጥብቅ በመሆኑ ትዳሩም እንደዚያው የፀና ነው፤›› በማለት የነበረውን ልዩነት በምሳሌ ያስረዳሉ፡፡ ከመተጫጨቱ ባሻገር በሌሊት በሚከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ እናቶች ሐር ወይም ቀይ ልብስ በመልበስ ይደምቃሉ፡፡ ሐዘን ሲሆን በፀጉር (ፈር) በኩል ሲለበስ ሐዘን ላይ መሆናቸውንና አለመሆናቸውን መለያ መንገድ ነው፡፡ ጥቁር ልብስ ሲለብሱ ሐዘን ላይ መሆናቸውን ማረጋገጫ ነው፡፡

መምህር ቶፊክ ዕድሜያቸው 72 ተሻግሯል፡፡ በእነሱ የልጅነት ጊዜ የነበረውን የአያቶቻቸውን የሸዋል ክብረ በዓል በጥቂቱም ቢሆን ያስታውሳሉ፡፡ በጊዜውም ‹‹ቡናስር›› የተባለ ምግብ ይሰናዳል፡፡ ምግቡ የቡና ገለባ ከቅቤ ጋር በስሎ በስንዴ ተጋግሮ ከተነጠረ በኋላ እየተቆረጠ ይበላል፡፡

አባቶቻችን ‹‹ጣዑዋ ከሚባል በመጠጥ ጋር ምግቡን ካከፋፈሉን በኋላ የሚነበብ ነገር ያነቡልናል፤›› በማለት መምህር ቶፊክ ጊዜውን ያስታውሳሉ፡፡ ሴቶች ለሸዋል ከሚያከናውኑት የምግብና የመጠጥ እንዲሁም የጭፈራ መርሐ ግብር ባሻገር በየቀኑ በተጠራቀመው ገንዘብ በእጅ ሥራ የተለያዩ ስፌቶች ማለትም ኮፍያ፣ የመመገቢያ ዕቃዎች፣ ጌጣ ጌጦችና አልባሳት ሞኤ ጋር (የሙና ሙያ ቦታ) በሚባል ቦታ በጋራ ተሰብስበው ይሠራሉ፡፡

ሐጂ አህመድ አብዱራሂም ኑሯቸውን በሐረር ከተማ ካደረጉ 75 ዓመታት ሆኗቸዋል፡፡ ‹‹ድሮ ለመተጫጨት የሚከበር ቀን ነበር›› አሁን ግን ጊዜው ተለወጠ እንደ ፌስቲቫል እየተከበረ ነው በማለት አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡

ሐጂ አህመድ በሸዋል ላይ የዛሬዋ ባለቤታቸውን እንዳጩ አስታውሰው፣ ባህላዊውን መንገድ መከተላቸው እንደሚያኮራቸው ጠቆም አድርገዋል፡፡

‹‹በእኛ ጊዜ እናትና አባቶቻችን ለማንኛውንም ነገር ቅርባችን ነበሩ፡፡ የተሰማንንና የፈለግነውን ለእነሱ እናወያያለን፡፡ የዘንድሮ ወጣት ግን ያንን ባህል ትቶታል፤›› በማለት ልዩነቱን ይገልጻሉ፡፡

ከዘመን ዘመን ተሻግሮ ዛሬ ላይ የደረሰው ባህላዊ አከባበሩ ከዳግማዊ ምኒልክ ዘመቻ በኋላ ባህሉን የማክበር አጋጣሚዎች ቀዝቃዛ እንደነበረ ይነገራል፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ ዓይነት ክብረ በዓሎች በርካታ ሰዎች የሚሰበሰቡበትን አጋጣሚን ስለሚፈጥር አይፈቀድም፡፡ ግን በድብቅ ሲከናወን እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም ቢሆን ፖለቲካዊ ጉዳዮች ይከናወኑበታል በሚል ማከናወን እንደማይቻል ይነገራል፡፡ እንደ መምህር ቶፊክ አስተያየት ከሆነ በጊዜው ወጣቶች የጀመሀ ቦታቸው ላይ በመሰባሰብና በመገናኘት ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ይመክሩ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡

ክብረ በዓሉን ለማክበር በሐረር ከተማና አቅራቢያ አካባቢዎች ማኅበረሰብ በተጨማሪ በውጭ አገር የሚኖሩ የከተማዋ ተወላጆች ወደ ከተማዋ ይመጣሉ፡፡ የሐረሪ የባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ይኼን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘት ያለውን የሸዋል ሥነ ሥርዓት በዩኔስኮ ላይ ለማስመዝገብ ደፋ ቀና እያሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ወንዶች፣ ሴቶች፣ እናቶች፣ አባቶችና የተለያዩ ማኅበራት የሸዋል ዒድን ለማክበር ሌሊቱን ሙሉ በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ደምቀው ያድራሉ፡፡ ልጃገረዶችም እናታቸው ጉያ ሥር ሆነው በጎረምሶች ዕይታ ሥር ይወድቃሉ፡፡ በሸዋል ሴቶች ተውበውና አምረው ከእናታቸው ጋር ነው የሚታደሙት፡፡

ሐረር በሦስት ትልልቅ ሃይማኖቶች ማለትም እስልምና፣ ኦርቶዶክስና ካቶሊክ በ150 ሜትር በማይበልጥ ርቀት ውስጥ የሚገኙበትና በታሪክ አጋጣሚ ይህ ነው የሚባል የሃይማት ግጭት ያልተፈጠረባት ከተማ መሆኗ ልዩ ያደርጋታል፡፡ በሐረር ዕደ ጥበብ ሙዚየሞች፣ የባህል ማዕከል (ኦዳ ጋር)፣ የአርተር ራምቦው የስብሰባ ማዕከል፣ የሐረር ሳንቲሞችና መስጂዶች ከተማዋ የተለገሰችው ገፀ በረከት ነው፡፡

በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው የሸዋል ዒድን በዩኔስኮ ማስመዝገብ ሒደት ጠንክሮ እንደሚከናወን የክልሉ የቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ የሚከናወነውን የሸዋል ዒድ ሥነ ሥርዓት ፌስቲቫላዊ ይዘት እየያዘ መምጣቱ በተለይ በውጭ የሚኖሩ የከተማዋ ተወላጆች በጉጉት እንዲጠበቅ አስችሎታል፡፡ የወር ጾም ተጠናቆ ስድስተኛው ቀን ሲገባ ወደ የከተማዋ ተወላጆች ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ያመራሉ፡፡ ክብረ በዓሉ በቀጣይ በተለያዩ ደማቅ ሥርዓቶች እየተከበረ አገራዊ ይዘቱን ጠብቆ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖረው የክልሉ ባህል ቢሮ እንደሚሠራ አብራርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...