Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአሳሳቢው የአገራችን የሥራ ሥነ ምግባር

አሳሳቢው የአገራችን የሥራ ሥነ ምግባር

ቀን:

በጌታቸው ደምሴ ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር)

ያደጉ አገሮች እንዴት ሠለጠኑ ብለን ስንጠይቅ በርካታ መልሶች ማግኘታችን አይቀሬ ነው፡፡ ከመልሶቹ መካከልም ጠንካራ ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በመንደፍና በመተግበር ወይም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመገንባት ወይም የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት በመሆን ወይም የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የፈጠረባቸው መነቃቃት እያልን ልንዘረዝር እንችላለን፡፡ አዎ እነኚህ ለሥልጣኔ አስፈላጊ ምክንያቶች (Necessary Conditions) ሊሆኑ ይችላሉ ነገር ግን በቂ (Sufficient Conditions) አይደሉም፡፡ ከፍ ብለው ለሥልጣኔ ወይም ለዕድገት ከተጠቀሱት አስፈላጊ ጉዳዮች በተጨማሪ የሰው ኃይል በአገር ዕድገት ላይ የሚጫወተው የማይተካ ሚና ከፍተኛ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሆኖም የአገሮች ሥልጣኔ በወሳኝ መልኩ በሰው ኃይላቸው ንቁ ተሳትፎ ዕውን ይሆናል ስንል ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎች እንድናነሳ ይገፋፋናል፡፡ አንደኛው ጥያቄ የሰው ኃይል መኖሩ በራሱ ለአገሮች ተፈላጊው ዕድገት ያመጣላቸዋል ወይ? የሚል ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ምን ዓይነት የሰው ኃይል ሊኖራቸው ይገባል? የሚሉ ናቸው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማም በእነኚህ ጥያቄዎች ላይ በማተኮር ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አስተሳስረን በማስረጃ በተደገፈ መሞገት፣ አሁን ለገባንበት አገራዊ የሥራ ሥነ ምግባር ጉድለት ፈተና በጥንቃቄና በተጠና መልኩ ለማለፍ ይረዳል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሌሎች የሥነ ምግባር ዓይነቶች የዚህ ጽሑፍ አካል አለመሆናቸው ለውድ አንባቢዎች ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

በእርግጥ የሰው ኃይል መኖሩ ለአገር ዕድገት አጠያያቂ አይደለም ሆኖም አገሮች ምን ዓይነት የሰው ኃይል ሊኖራቸው ይገባል የሚለውን ጥያቄ ተንተርሰን የየአገሮች የዕድገት ተሞክሮ ድርሳናት፣ ስናገላብጥ ‹‹በሥነ ሥርዓት የታነፀ የሰው ኃይል›› መኖር ወሳኝ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ለመሆኑ በሥነ ሥርዓት የታነፀ ኃይል ስንል ምን ማለታችን ነው? እንዴትስ ሊፈጠር ይችላል? ይህ ኃይል ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል የሚለየው ምንድነው? ከሥራ ፈጣሪዎች (Entrepreneur) ጋር ያለው አምሳያነትና ልዩነት ምን ይመስላል? የሚሉት በጥቂቱም ቢሆን እንመለከታለን፡፡

የሰው ኃይል ለአንድ አገር ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በጨረፍታ ስንመረምር በዚሁ ክበብ ውስጥ የሚገኙ ሦስት ኃይሎች እናገኛለን፡፡ ሁለቱ ኃይሎች ተደጋጋፊና ተመጋጋቢ ሲሆኑ አንደኛው ግን በተቃራኒ የቆመ ኃይል ነው፡፡ ከሁለቱ ኃይሎች የመጀመሪያዎቹ ሠርተው የማይጠግቡ ወይም ሥራ ፈጣሪዎች (Entrepreneur) ሲባሉ ሁለተኛዎቹ በሥነ ሥርዓት የታነፁ ኃይሎች ይባላሉ፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የማለገ ኃይል ነው፡፡ ከሳቴ ብርሃን ተሰማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት (1951) ማለገ ማለት ሥራን ከመሥራት ቦዘነ፣ ለሥራ አልያዝ፣ አልታዘዝ አለ፣ እየወሰለተ አልሠራ አለ፣ ውልምጥ ውልምጥ አለ፣ የማይጨበጥ ማለጋ ሰውን ሆነ ሲል ይገልጸዋል፡፡ 

እስቲ በቅድሚያ ሠርተው የማይጠግቡ ኃይሎች ተብለው የተፈረጁትን እንመልከት፡፡ እነኚህ ኃይሎች ከማኅበረሰብ ውስጥ እንደ እንቡጥ ጽጌሬዳ ብቅ የሚሉና በአንድ አገር የፖለቲካ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ በተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው የሚታወቁ ናቸው፡፡ በቁጥር ደረጃ ከሁለቱም ኃይሎች ጋር ሲነፃፀሩ በጣም አነስተኛ ቢሆኑም፣ የመፍጠር ችሎታቸውን ተጠቅመው ማኅበረሰብን ለመለወጥ ከፍተኛ የሆነ ተዓምር ይሠራሉ፡፡ አገራዊና ማኅበረሰባዊ ትሩፋታቸው ከፍተኛ ነው ሲባልም ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ለአገር ልማት የሚውል ገቢ በማመንጨት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን፣ ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣትና በሥነ ሥርዓት የታነፀ ኃይልን በመፍጠር ጉልህ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ከዚህ በመነሳትም ልማትና ተስፋን በጉጉት ከሚጠብቅ ማኅበረሰብ ለእነኚህ ኃይሎች ከበሬታ ሊቸራቸውና በስስት ሊመለከታቸው ይገባል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኙት በሥነ ምግባር የታነፁ ኃይሎች ለመማር የሚተጉ፣ በአገር ልማትና ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ የሚሳተፉ፣ በሥራቸው ለህሊናቸው ሰላም በማጎናፀፍ የሕይወት መዓዘን የሚያጣጥሙ፣ ቤተሰብን የሚያኮሩ፣ አገርንም በመልካም ስም የሚያስጠሩ ናቸው፡፡   

ሠርቶ የማይጠግብ ኃይልና በሥነ ሥርዓት የታነፀ ኃይል ይህንን ታላቅ አገራዊና ሕዝባዊ ኃላፊነት ለመወጣት ከሚጠበቅባቸው ዋነኛውና መሠረታዊው ነገር ስለሥራ ሥነ ምግባርና መርሆዎች ጠንቅቆ ማወቅና የሕይወት ሀሁ በማድረግ ለመተግበር ቁርጠኞች መሆን ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? በአጭሩ ሥራ ከሕይወታቸው ጋር የተሳሰረች ቢባል ገላጭ ይሆናል፡፡ ይህ ኃይል ለሥራ ያለው አተያይ ከፍ ያለ ነው ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ሥራን ያፈቅራል ማለት ነው፡፡ ይህ ኃይል በተሠማራበት ሥራ ሁሉ ቀዳሚ እርካታው ሥራውን በተቀመጠለት አኳሃንና ጊዜ ማከናወን ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ኃይል ለሌሎች ብሎ ሳይሆን፣ ንቃትና ማስተዋልን በተላበሰ ለራሱ በፈቀደውና በሚስማማው መንገድ ሥራውን ያከናውናል ማለት ጭምር ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ለታይታ ሳይሆን፣ ከልቡ ሥራውን ያከናውናል ማለት ነው፡፡ ይህ ኃይል ወደ ሥራ ገበታው በየ ዕለቱ የሚተመው ወደ ሥራ መሄድን ብቻ በማሰቡ ሳይሆን፣ በሥራው መገኘቱ ለሕይወቱ መልካም መዓዛንና ፍሬን እንደሚያፈራለት ከልቡ በማሰቡ ጭምር ነው፡፡ ያሰበውን ለማሳካትም ሆኖ ይኖራል፡፡ ይህ ኃይል ከሥራ ጋር በሚያደርገው የማያቋርጥ መስተጋብር ክህሎቱን እያዳበረ ስለሚሄድ ተጠቃሚነቱንም በዚያው ቁመት እያሳደገ፣ የተቀጠረበት ድርጅትም ሆነ አገሩንም ይጠቅማል፡፡

በመሠረቱ ይህ ኃይል የሚፈጠርበት የራሱ ዓውድ ይኖረዋል፡፡ ይህ ኃይል ለመፍጠር የበርካታ ክፍሎች (የግለሰቡ፣ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ የትምህርትና የሃይማኖት ተቋማትና መንግሥት) ተሳትፎ ወሳኝ ይሆናል:: በርካታ መስዋዕትነትም ይጠይቃል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ቁጭት፣ ታማኝ መሆንና በፅናት መቆምን የመሳሰሉ እሴቶች የራስ ማድረግና እንዳይሸረሸሩ ነቅቶ መጠበቅ ይጠይቃል፡፡ ቁጭት አንድን ነገር ለመሥራት ከውስጥ የሚፈነቅለው ግለትና ያን ግለት ተከትሎ የሚፈጠረው የመሥራት ተነሳሽነት ወይም ፍላጎት ነው፡፡ ታማኝ መሆን ደግሞ ውስጥህን የሚነግርህና የማኅበረሰባዊም ሆኑ ተቋማዊ መርሆዎችን፣ እሴቶችንና የአሠራር ልማዶችን በሚገባ በማጥናት ከራስ ጋር አዋህዶ መጓዝን ይጠይቃል፡፡ ቁጭትንና ታማኝነት በአንድነት በመጣመር አጠቃላይ መሆንና መድረስ ወደሚገባን ግብ በጥንቃቄ ለመራመድና ፍሬውን ለማጣጣም የምንጠቀምበት ከፍተኛ እሴት ደግሞ በፅናት መቆም ነው፡፡ እንደዚህ ያለ ሰብዕና የተላበሱ ኃይሎች በሥነ ምግባር ለመታነፅ ዝግጁነት ይኖራቸዋል ሠርቶ መርካት ደግሞ የራሳቸው ንብረት ማድረግ የሚችሉ ናቸው፡፡ የዚህ ስብስብም ብዙ በሥነ ምግባር የታነፀና ሠርቶ የማይጠግብ ኃይሎችን ይፈጥራል፡፡ አንዱ ከአንዱ እየተማረና ሐሳብ እየተለዋወጠ ሥራን ያዳብራል፡፡ አገርን ያሳድጋል፡፡ አገርን ያኮራል፡፡ እሴቶችም እንዳይጠፉና እንዳይመናመኑ መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነትና ጥበቃ ሊያደርግላቸው ይገባል፡፡ በትምህርት፣ በባህልና በሃይማኖታዊ አስተምህሮት በስፋት መካተታቸው ማረጋገጥና ድጋፍ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ እሴቶቹ እየተመናመኑ ሲሄዱ ሦስተኛው ዓይነት የሰው ኃይል በስፋት ይፈጠራል ምግባሩም ልፍስፍስ ማኅበረ ግንኙነት ሆኖ አውደልዳይ፣ የራስ ያልሆነ የሚመኝ፣ በአቋራጭ መክበር የሚሻ፣ ለሥራ ፈጣሪዎች ክብር የማይሰጥ፣ ውሸትና ግብዝነት ማተቡ ያደረገ ዋልጌ ኃይል ይሆናል፡፡ በቁጥር ሲበረክትም ሕዝብንና አገርን ማወክ ሥራው ይሆናል፡፡ በስተመጨረሻም ጥቂትና ብርቅዬ የሆኑትን ሠርቶ የማይጠግቡትንና በሥነ ሥርዓት የታነፁት ኃይሎች አላላውስ በማሰኘት የክሽፈት ወይም የመዝቀጥ እሽክርክሪት ያፋጥነዋል፡፡

እንግዲህ ያደጉ አገሮች የሚገኘው ሠርቶ የማይጠግብ ኃይልና በሥ ምግባር የታነፀ ኃይል አገሩን ለመለወጥ ሲል ከላይ የተዘረዘሩትን እሴቶች ለማዳበርና ለመጠበቅ በርካታ መስዋዕትነት ከፍሏል፣ አገሩንም አሳድጓል፡፡ ራሱንም ጠቅሟል፡፡ እሴቶችንም በጠንካራ አለት ገንብቶ በመንከባከብና በማሳደግ ከትውልድ ወደ ትውልድ እያስተላለፈ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ዛሬ ያደጉ አገሮች የዚህ አኩሪ ኃይል ባለቤት ሊሆኑ በቅተዋል፡፡

ከላይ በተዘረዘሩት የሰው ኃይል አሠላለፍ ተነስተን ከእኛ አገር ዓውድ ጋር ስንመረምር ዛሬ ዛሬ የሦስተኛው ኃይል እየተበራከተ መምጣቱን ለመረዳት ብዙም የሚከብድ አልሆነም፡፡ ጥቂት ሰዎች የሚያንፀባርቁት ነው ብሎ ሀቁን በማጣጣል ማለፍ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ይልቁንስ በዚህ ፍጥነት ከተንደረደርን ደግሞ መዳረሻችን ምን ሊሆን እንደሚችል ወይም ምን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል የማኅበራዊ ሳይንስ ጠበብቶችን እያስጨነቀ ያለ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ እስቲ ለዚሁ የሚያስረዱልኝ የግል ትዝብቶቼን ላስቀምጥ፡፡ በአገሬ ሠርተው የማይጠግቡ ሳስብ መሥፈርቱን ዘርግቼ የሞሉልኝ በምሳሌነት የማነሳቸው ሦስት በቅርብ የማውቃቸው ድርጅቶች አሉ፡፡ ይህን ስል ግን ሌሎች የሉም ማለቴ እንዳልሆነ አንባቢዎቼ እንዲረዱልኝ ከይቅርታ ጋር እጠይቃለሁ፡፡ ከእነኚህ ድርጅቶች ያገኘሁት መረጃ በመደበኛው የጥናት መንገድ ተከትሎ የተገኘ ሳይሆን፣ ባደረግናቸው የግል ውይይቶች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የውይይቶቹ ፋይዳ፣ በጽሑፉ የተጠቀምኳቸው ታሪኮችና የጥናት ውጤት የሚያስተላልፈው መልዕክት ለሥራ ባህርያችን መሠረት እያደረግናቸው ያለነው እሴቶች፣ የአዕምሮ እሳቤዎቻችንና መለኪያዎች፣ ግምቶቻችንና ማንነታችን ደረጃ የሚያመላክት ይመስለኛል፡፡

ለትዝብቴ መሠረት የሆኑኝ ድርጅቶች ዘለቅ ብዬ ስመረምር የሚያመሳስሏቸው ነገሮች እንዳሉ ተረዳሁ፣ የሚመሯቸው ሰዎች በጎልማሳነት ዕድሜ ክልል የሚገኙ፣ የተማሩና ትህትናቸው እጅግ የበዛ፣ ድርጅቶቻቸው በዕውቀትና በብርቱ ጥረት የገነቡ፣ ሌሎች ሠርተው የማይጠግቡ ኃይሎች ለመፍጠር ቀን ከሌት የሚዋጁ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ይህ ቁመናቸውን ባሰብኩ ጊዜም ምናለ እንደ እነሱ የመሰሉ ቢበራከቱልን እላለሁ፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል እንደሸረሪት ዙሪያቸው የከበባቸው ጠልፈው ለመጣል የተዘጋጁ ድሮች ባየሁና በሰማሁ ጊዜ ድካም ይሰማኛል፣ ለአገሬም አዝንላታለሁ፡፡ የተጠነጠነው ድር በቀጠሯቸው ኃይሎች ብቻ የተወሰነ አይደለም በሌሎችም ጭምር እንጂ፡፡ ዙሪያቸው በከበቧቸው ተቋሞች፣ በማኅበረሰብና በመንግሥት አሠራሮችና አስተሳሰቦች ጭምር ከፍተኛ የሆነ “የደፈቃ” ተግባር ሲፈጸምባቸው ማየትና መስማት ጠዋት እንዳልኩት ልብን ይሰብራል፡፡ ይህን ስል ግን ሠርተው የማይጠግቡ ኃይሎች ብፁአን ናቸው እያልኩ እንዳልሆነ መረዳት ይጠይቃል፡፡ የራሳቸው የሆነ ግለሰባዊም ሆነ ተቋማዊ ባህሪዮች የምንገነዘብበት ሁኔታ እንዳለና ለዕድገታቸው መሰናክል የሆኑ አሠራሮችና ልምዶች ራሳቸው በፈቀዱት ልክ የሚዳክሩ መሆናቸውም መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

ወደ መጀመርያው ምልከታዬ ልለፍ እንደዚህም ይገለጻል፡፡ በቀጠሮ ከተገናኘሁት የኮንስትራክሽን ድርጅት ባለቤት ከሆነው ወዳጄ ቁጭ ብለን ምሳ እየበላን ነው፡፡ ዘወትር እንደምናደርገው ጥቂት ስለቤተሰብ ከተጨዋወትን በኋላ በዕለቱ ስለሆነው የነገረኝ በጣም ያስደምማል፡፡ ‹‹ታውቃለህ ዛሬ ጠዋት በወር 20 ሺሕ ብር ስከፍለው የነበረ መሐንዲስ አሰናብቼ መምጣቴ ነው፤›› አለኝ፡፡ “ለምን” ብዬ ጠየቅኩት፡፡ ‹‹ምክንያቱማ በሦስት የኮንስትራክሽን ድርጅቶች በወርኃዊ የደመወዝ መክፈያ ሊስት/ፔሮል ውስጥ መኖሩን ስለደረስኩበት ነው፤›› አለኝ፡፡ ምናልባትም አንዳንዶቻችን “ፐ“ ይህማ አሪፍ ነው! ወይም “ታዲያ ምን ይጠበስ” እንል ይሆናል፡፡ በመሠረቱ ይህ መሐንዲስ ሃያ አራት ሰዓት ቢሠራ የሚቃወም ያለ አይመስለኝም፣ መልካም ተግባር ነው ሀቁ ግን አገራችን ያለው የሥራ ባህሪና የራሳችን የመሥራት አቅምና ተነሳሽነት ይህንኑ እንድናደርግ ይፈቅድልናል ወይ? በስፋት እንደተለመደውም እኛ የምንታወቀው ባንዲራ ከወረደ ወይ ወደ መኝታ አልያም ወደ መጠጥ ቤት መሄድን ነው፡፡ ይህ መሐንዲስ በወዳጄ ድርጅት ለመሥራት የተቀጠረው በኮንትራት ሳይሆን፣ በቋሚነት ነው ታዲያ በቋሚነት የተቀጠረ ሰው እንዴት ሆኖ ነው በተመሳሳይ ጊዜ ሦስት ድርጅቶች ደመወዝ መክፈያ ሊስት ስሙ ሊገኝ የቻለው የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ መልሱ አጭርና ግልጽ ነው የሥራ ባህሪ በመጠቀም፡፡ መሐንዲሶች የሥራቸው ባህሪ ተዘዋዋሪ ወይም ተንቀሳቃሽ ያደርጋቸዋል፡፡

ይህ መሐንዲስም የድርጅቱ ፕሮጀክቶች የሥራ ሒደት ለመከታተልና ለመቆጣጠር ከአንዱ ሳይት ወደ ሌላው ሳይት ይንቀሳቀሳል፡፡ ይዘዋወራል፡፡ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ለሌሎቹ ተመሳሳይ ድርጅቶች ፊርማውን አኖረ ማለት ነው፡፡ ችግሩ ፊርማውን ማኖሩ ላይ ሳይሆን፣ ፊርማውን ላኖረላቸው ድርጅቶች ተፈላጊውን አቅምና ጊዜ ይሰጣቸዋል ወይ? በሥራው ላይ የሚያሳድረው የብቃትና ታማኝነት ጉዳይ ሲመዘንስ? ይህ የተገነዘበው ወዳጄም ‹‹የተቀጠረበትን ሥራ ለማሳካት ባለመቻሉ›› በሚለው በቂ የሕግ ድጋፍ መሠረት አድርጎ ሠራተኛው ለማሰናበት የወሰደው ዕርምጃ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

በውጭ ዓለም አንድ ሰው ሁለትና ከዚያ በላይ ሥራዎች መሥራት የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌም ጃማይካዊው ሬኖ ዴቮን ጎርዶን ወይም በመድረክ ስሙ Busy Signal በምሥል በድምፅ ተደግፎ በግሩም የትወና ችሎታው የሚያቀነቅነው One Way (አራት የሥራ መስኮች በሬስቶራንት አስተናጋጅነት፣ ታክሲ በመንዳት፣ ነዳጅ በመቅዳትና ጋራዥ ሠራተኛነት) በተመደበ ጊዜና ጥራት ሥራውን ለማከናወን እንደ ዝሃ ዘጊ ከአንዱ የሥራ ቦታ ወደ ሌላ የሥራ ቦታ ሲመላለስ ስንመለከት ሰው በመልካም የሥራ ሥነ ምግባር በመታነፅ በተገቢ ጊዜና ቦታ እየተገኘ ሕይወትን ማጣጣም እንደሚችል ጠቃሚ ትምህርት እንወስዳለን፡፡ ይህ ሲሆን ግንኙነቱ በስርአት ይመራል፡፡ ኮንትራቱ ሳይሸራረፍ ማክበር የሁሉም ግዴታ የገቡ አካላት ይሆናል፡፡እዚህ አገር የምናየው ግን መሸዋወድ ነው፡፡ በእርግጥ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለእንደዚህ አይነቱ እድል ሊያመቻችን አለመቻሉ የታወቀ ቢሆንም መሸዋወዱ የራስ ያልሆነ ፍለጋን ወይም በአቋራጭ ለመክበር የሚደረግ ሩጫ በመሆኑ ወደ ምንፈልገው በሥነ ምግባር የታነፀ ኃይል ግንባታ የማያደርሰን እንዲያውም ዕንቅፋት ፈጣሪ በመሆኑ ከወዲሁ በፅኑ ልንታገለው የሚገባ ግለሰባዊ የሥነ ምግባር ጉድለት ነው፡፡

ሁለተኛው ምልከታዬ የሚወስደኝ ወደ አንድ የኦዲት ድርጅት ነው፡፡ ከድርጅቱ ባለቤት ለረዥም ጊዜ እንተዋወቃለን፣ በተገናኘን ጊዜም ስለሥራውና ስለወደፊት የድርጅቱ ዕቅዶች አንስተን ሐሳብ ለሐሳብ እንለዋወጣለን፡፡ አንድ ጊዜ ስለሠራተኞች ምርታማነት ጉዳይ አንስተን ስንጨዋወት እንዲህ አለ ‹‹የሠራተኞች ምርታማነት ለማሳደግ የተለያዩ ሥልቶች ብጠቀምም አልቻልኩም፤›› አለ ‹‹ለመሆኑ ምንድነው ያደረግከው?›› ብዬ ጠየቅኩት፡፡ ወዳጄ ሠራተኛው ተጨማሪ ገንዘብ የሚያስገኝለት አንድ የሚደነቅ አሠራር ዘርግቷል፣ ይኸውም ማንኛውም የድርጅቱ ኦዲተር በውል በተገለጹ ቀናት ውስጥ የተሰጠውን የኦዲት ሥራ አጠናቅቆ ሪፖርቱን ካስረከበ ከኮንትራቱ 30 ፐርሰንት ያገኛል የሚል ነበር፡፡ ይህ አዲስ አሠራር የጥቂት ሠራተኞች ቀልብ ቢገዛም አብዛኞቹ ግን ፍላጎት አላሳዩም፡፡ ይህንኑ ያጫወተኝ የድርጅቱ ባለቤት ለምን ብዬ ስጠይቀው የሰጠኝ መልስ የሚያስደምም ነበር፡፡ ‹‹ምክንያቱም ከሌላ ድርጅት የሚያገኟት የማትረባ ገንዘብ በማስቀደማቸው ነው፤›› አለኝ፡፡ ልክ በመሐንዲሱ እንዳየነው ኦዲተሮች በሥራቸው ባህሪ ተንቀሳቃሽ ናቸው፡፡ ይህ ባህሪ ደግሞ በቀላሉ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡ የአንዱ ደንበኛ ጋ ሥራቸውን ይጥዱና ለሌላ ድርጅት ይሠራሉ በዚህም የኦዲት ሥራው ይስተጓጎላል፡፡ ረዥም ጊዜም ይወስዳል፡፡ ችግር መላ ይፈጥራል እንዲሉ ይህ ችግር ለማስታገስ ነበር ወዳጄ የሞከረው፡፡

ድርጅቶች ሠራተኛውን ተጠቃሚ ለማድረግ በስፋት ከሚጠቀሙባቸው ሥልቶች መካከል ቦነስ መስጠትን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሠራተኛው የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖረው ማድረግ ይገኙበታል፡፡ ብዙ አገሮች ይህንን አሠራር በመከተል የሠራተኞቻቸውን ምርታማነት ለማሳደግ ተጠቅመውበታል፡፡ ድርጅቶች የቦነስ መርሐ ግብራቸው ለመተግበር ከሚጠቀሙበት ቀመር የድርጅቶቻቸው ዓመታዊ የምርትና የትርፍ ሁኔታ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ አንድ ማምረቻ በሙሉ የማምረት ኃይሉን ተጠቅሞ ሲሠራ ከፍተኛ ገቢ ያገኛል በተቃራኒው በልዩ ልዩ ምክንያቶች ማምረቻው በዝቅተኛ ኃይሉ እንዲሠራ ሲገደድ ደግሞ የሚያገኘው ገቢ በእዚያኑ ልክ ይቀንሳል ትርፉም አነስተኛ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ምርትና ትርፍ ከፍ ሲል በእዚያው ልክ የሠራተኛው ተጠቃሚነት ከፍና ዝቅ ይላል ማለት ነው፡፡ በዚህ እሳቤ መሠረት በጃፓን የሚደረገው የቦነስ አሰጣጥ የተመለከትን እንደሆነ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ እያንዳንዱ ተቀጣሪ ለማምረቻው ያደረገው አስተዋጽኦ በመመዘን አጥጋቢ ካልሆነ ራሱ ሠራተኛው ቦነሱን መውሰድ የለብኝም ይላል፡፡ ይህ ማለት አንድ ሠራተኛ ቦነስ አልፈልግም ሲል ማምረቻው ያገኘው ገቢ መጠን በማሥላት በምርት ሒደቱ የሠራተኛው ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን፣ በመረዳት ሊከፈለኝ አይገባም ማለቱ ነው፡፡ ታዲያ እንደዚህ ዓይነቱን ሲጀምር ለራሱ ሲቀጥልም ለድርጅቱና ለአገሩ ታማኝ የሆነ በሥነ ሥርዓት የታነፀ ኃይል ለዚች አገር ከየት ይምጣ?

ሦስተኛው ምልከታዬ አንድ በቅርብ ጊዜ በመጠጥ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሥራ የተሠማራ ወዳጄ ይወስደኛል፡፡ ለረዥም ጊዜ አለመገናኘት በኋላ፣ በአንድ ምሽት በነበረን የእራት ቆይታ ያጫወተኝ ነው፡፡ ይህ ወዳጄ ይህንን ፋብሪካ ለመክፈት ያደረገው እልህ አስጨራስ ግብግብና የከፈለው መስዋዕትነት በቅርብ የማውቅና ተቃዋሚ ምስክር ነኝ፡፡ መስዋዕትነቱ ሳስበው በእርግጥም እነኚህ ሠርተው የማይጠግቡ ኃይሎች በውስጣቸው የሆነ የአይበገሬና አልወድቅም ባይነት ስሜትና ብርታት ያላቸው መሆኑን በእሱ ውስጥ ተመልክቻለሁ፡፡ ታዲያ እሱም እንደሌሎቹ በሠራተኛ ምርታማነትና የሥራ ሥነ ሥርዓት ላይ ተመሳሳይ ችግር እንዳጋጠመው ይገልጻል፡፡ ለአብነትም ፋብሪካው በአንድ ወቅት በገበያና በሌሎች ምክንያቶች ያጋጠመው የአጭር ጊዜ ምርት መስተጋጎል ጋር ተያይዞ የሆነውን እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፡፡ ፋብሪካው የማቆም ሁኔታ አጠናቅቆ ጥቂት የሥራ ትዕዛዝ ያገኛል፣ የማምረት ሥራውንም ይጀምራል፡፡ የመጀመርያ የሆነውን ምርት ወደ ደንበኞች ለማድረስ አንድ መኪና ከነተሳቢው ገብቶ በሚጭንበት ወቅት በዕረፍት ላይ የነበረ ሠራተኛ ሰምቶ ኖሮ እየሮጠ በመምጣት በምርት ተግባር ላይ የነበረውን ሠርቶ የማይጠግበው ባለቤት ‹‹ጋሼ እንግዲህ ሥራ እየተፈጠረ ስለሆነ ደመወዝ ትጨምርልኛለህ አይደል?›› ብሎ እንደጠየቀው አጫውቶኛል፡፡ በእርግጥ በአገራችን ድርጅቶች ለሠራተኞቻቸው የሚከፍሉት ወርኃዊ ክፍያ አነስተኛ እንደሆነ ይታወቃል (በኢንዱስትሪ ፓርክ የሠራተኞች የደመወዝ ይጨመርልን ጥያቄ ልብ ይሏል) ነገር ግን ከአጠቃላይ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ጋር ማስተያየት ደግሞ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ድርጅቶች ለሠራተኞቻቸው ከሚከፍሉት በተጨማሪ የአንድን ምርት የማምረቻ ወጪዎች ዝርዝር ጠጋ ብሎ መመልከቱም የሚበጅ ይመስለኛል፡፡ 

በሌላው መስክ የሚታየው የሥራ ሥነ ምግባር የሚብስ እንጂ የሚሻል እንዳልሆነ መታዘባችን አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ ማኔጅመንት ኢንስቲቲዩት በ2018 ያደረገው ጥናት ያመላከተን ነገር ቢኖር ሁኔታው ከግለሰብ የሥነ ምግባር ጉድለት አልፎ ማኅበረሰባዊ የሥነ ምግባር ዝቅጠት ላይ መድረሳችን በግልጽ ያመላክተናል፡፡ በአገራችን በፐብሊክ ሰርቪስ 1.5 ሚልዮን ሠራተኞች እንደሚኖሩ የጥናቱ ውጤት የሚገምት ሲሆን፣ ከስምንት የሥራ ሰዓት አምስት ሰዓት ብቻ ለመንግሥት ሥራ እንደሚውልና ቀሪው ሦስት ሰዓት እንደሚባክን ይህ ደግሞ 500 ሺሕ ሠራተኞች ያለ ሥራ ደመወዝ እንደሚከፈላቸው ወይም ደግሞ በዓመት ስድስት ቢልዮን ብር ያለ ሥራ ክፍያ እንደሚፈጸም አረጋግጧል፡፡ ለመሆኑ ይህ የማኔጅመንት ኢንስቲቲዩት ጥናት ውጤት ምን ሥዕል እያሳየን ነው ብለን መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ጥናቱ ሠራተኛው ያለ ሥራ የሚያሳልፈው ጊዜ ታሳቢ በማድረግ የተሠራ እንደሆነ ከሪፖርቱ አውቀናል፡፡ ያላወቅነው ተቋሞቹ ከዓመታዊ የአገልግሎትና የምርት ቀጥታ ተያያዥነት ያላቸው የጥራትና የንብረት አያያዝና አጠቃቀም ወዘተ. ታሳቢ ቢሆኑ ኖረው ምናልባትም ሥዕሉ ከዚህ የከፋ ሊሆን ይችላል ብሎ መሞገት የሚያስኬድ ይመስለኛል፡፡ ያም ሆኖ ግን መንግሥት ከሚያስተዳድረው ሲሶውን ወይም 33.3 ፐርሰንቱ በሥነ ምግባር የታነፀ አለመሆኑን ያመላክታል ማለት ነው፡፡ ይባስ ብሎም አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ እንዲሉ በየዓመቱ እንደዚህ መጠኑ ከፍ ያለ የአገር ሀብት በኃላፊዎች ፊት ወራሪነት መከናወኑ ጉዳዩ አሳሳቢና አስቸኳይ መፍትሔ የሚያሻው እንደሆነ እንረዳለን፡፡

በብዙ መንግሥታዊ አገልግሎት ሰጪዎች ሰውን ያስመረረ በጠራራ ፀሐይ የሚደረግ ወረራ መመልከት የሕይወታችን አካል ከሆነ ሰነባብተናል፡፡ እንደ ወረዳና ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች ከግንባታ ጋር በተያያዘ ተገልጋዩ ለሚያቀረበው ሕጋዊ ጥያቄ የሚሰጠው ሕጋዊ ያልሆነ መልስ ስናይ፣ ተገልጋይ ለሚያቀርበው የመብራት ቀጥሉልኝ ጥያቄ (ያውም በፈረቃ ለሚገኘው፡፡ ግን ይህ ውኃ የሚሉት በቤታችን፣ በመብራታችን፣ በግብርናችን እስከ መቼ ድረስ ነው የበላይ ሆኖ የሚቀጥለው?) በመብራት ኃይል ሠራተኞች የሚሰጠው ግብረ መልስ (የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በቅርብ ጊዜ ማለጋዎቹ ሠራተኞች ሕዝቡን ማስመረራቸው  በሬዲዮ ማስታወቂያ ማስነገሩ ጥሩ ሆኖ ይህንን ፈተና የመወጣት ኃላፊነቱን የተገልጋዩ  አድርጎ መቅረቡ እኛ ነግረን ነበር. . . ለማለት ይመስላል) እና በሌሎች ተቋሞቻችን የሚታየው የአገልግሎት ህፀፅ የመዝቀታችን ሌሎች ማሳያዎቻችን ናቸው፡፡ ለዚሁ ጥሩ ምሳሌ ይሆነኝ ዘንድ የአንድ ወዳጄን የሰሞኑንን ገጠመኝ ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡ ወዳጄ መንጃ ፈቃዱን ለማሳደስ ፈልጎ የጤና ምርመራ ለማድረግ ወደ አንድ ጤና ጣቢያ ጎራ ይላል፡፡ ታዲያ ያጋጠመውን ነገር ሲያጫውተኝ ይህ የሥራ ኃይል ወዴት እያመራ እንደሆነ፣ በገሐዱ ዓለም የደረሰብንን የሥነ ምግባር ዝቅጠቱ ምን ያህል እየሰፋ እየሄደ እንዳለ እንገነዘባለን፡፡ ወዳጄ ጤና ጣቢያው የሚጠይቀውን ምዝገባና ተያያዥ ጉዳዮች ካከናወነ በኋላ ተራው ደርሶ ወደ ምርመራ ክፍሉ ይገባል፡፡ መርማሪውም ዓይንህን በግራው መዳፍህ ሸፍን፣ የቀኙን ቀይር ሲል ከቆየ ባኋላ ‹‹ዓይንህ ችግር አለበት›› ይለዋል፡፡ የተጠየቀውን ያለችግር የመለሰ መሆኑን የሚያውቀው ወዳጄም ‹‹ምንድነው የምትለው እኔ ችግር የለብኝም›› ይላል፡፡ የሌባ ዓይነደረቅ እንዲሉ  ‹‹በምርመራው ያረጋገጥኩት ዓይንህ ችግር እንዳለበት ነው፣ ሆኖም እኔ ስለሆንኩኝ ግዴለም አሳልፍሃለሁ ለማንኛውም ውጪ ጠብቅ፤›› በማለት ይደግምለታል፡፡ ወዳጄም ግራ በመጋባት እንደተነገረው ወደ ውጭ ይወጣል፡፡ ከጥቂት ቆይታ ባለሙያው ብቅ ብሎ ‹‹እንግዲህ የሻይ በለኝና ወረቀትህን ውሰድ›› ይለዋል፡፡ ይህ ገጠመኝ  በግ ለመሸጥ ወደ ገበያ ሲሄድ የነበረውን ሰው ‹‹አንተ ውሻውን አትለቅም?›› እያሉ ተራ በተራ ባደረሱበት የሥነ ልቦና ጫና ‹‹እየጎተትኩት ያለሁት እውነትም ውሻ ነው›› ብሎ ራሱን በመጠራጠር በጉን ለሦስት ቁጭበሎች (የዳቦ ስም አታውጡለት ተብሏል ሌቦች) ያስረከባቸው ሰው ታሪክ እንድናስታውስ ያደርገናል፡፡ ይህ ባለሙያም ያደረገው ይኸው ነው፣ በተቀናጀና ግራ በማጋባት የሰው አዕምሮ ሰልቦ ዘረፋ ማካሄድ፡፡

የሚገርመው ነገር ለአብነት የተጠቀሱት ሠራተኞች ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ ተብለው ሲጠየቁ የሚሰጡት የመደበቂያ መልሳቸው “ኑሮ ስለተወደደብን ነው!” የሚል የፌዝ መልስ ይሰጣሉ፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ ተገልጋዩ ይህንን “ሰበብ” “Pretext” ታግሎ መብቱን ማስከበር ሲገባው ቅቡል እያደረገው መሄዱ፣ ተቋሞችም በተጠያቂነት (Accountablity) መርህ ለመሥራት ዝግጁነትና ቁርጠኝነት አለማሳየታቸው የድምር ውጤቱ መዝቀጥ መሆኑ ተጨማሪ ማመልከቻ ነው፡፡ እነኚህ በሥነ ምግባር ያልታነፁ ሠራተኞች ምንዳቸው የግብር ከፋዩ አስተዋጽኦ እንዳለበት ዕውቅና ካለመስጠታቸውም በላይ ለአገልግሎት ተቀባዩ ያላቸው ንቀትና እብሪት የወለደው “የምን ያመጣል” አስተሳሰብ ስንመረምር የሥራ ቦታ ሥነ ምግባር ባፍጢሙ እንደተደፋ መገንዘብ ይቻላል፡፡ 

አገራችን የኢንቨስትመንት መዳረሻ እናደርጋታለን የሚል መሪ ቃል በየጥጉና በባለ ሥልጣኖች አፍ ጠዋት ማታ ሲነገር ይደመጣል፡፡ ይህ ጥሩ ሐሳብ ነው፡፡ ሕዝቡም ተስፋ ያደርጋል፡፡ በመላው ዓለም ባሉት የአገሪቱ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች የሚደረገው ኢንቨስተሮችን የማሳብ እንቅስቃሴ ተገቢና የሚደገፍ ነው፡፡ ሆኖም ምኞታችን ምኞት ሆኖ እንዳይቀር በርካታ ጥያቄዎች መመለሰ ይኖርብናል፡፡ በኢንቨስትመንት መዳረሻ አገራዊ ራዕያችን ምን ይመስላል? ፖሊሲውና ስትራቴጂው የማኅበረሰባችን እውነታ መሠረት ያደረገ ነው ወይስ ከሌሎች አገሮች እንዳለ የተቀዳ ነው? የምናወጣቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አፈጻጸማቸው ምን ይመስላል? ስለአፈጻጸሙ በተግባር የሚታይ ማስረጃ ማቅረብ ይቻለናል ወይ? ማስረጃ ማቅረብ የምንችልባቸውና ማቅረብ የማንችልባቸው ጉዳዮችስ የትኞቹ ናቸው? ማስረጃ ማቅረብ በማንችልባቸው ጉዳዮች ከተለዋዋጭ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፍላጎቶች በመነሳት ወቅታዊ ግምገማ በማድረግ ለማረም የምናደርገው ጥረት ምን ይመስላል? የአሠራር መፍትሔስ አበጅተንላቸዋል ወይ? ከሁሉም በላይ ግን ቀልጣፋ፣ ተዓማኒና ምርታማነትን ምግባሩ የሆነ የሰው ኃይል ለመፍጠር ተከታታይነት ያላቸው ምን ዕርምጃዎች (በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤት፣ በሃይማኖት ተቋሞች፣ በመንግሥት ወዘተ.) እየተወሰዱ ናቸው? የሚሉ ሊያስጨንቁን ይገባል፡፡

መኪና ተጭኖ በወጣ ቁጥር ደመወዝ ይጨመርልኝ የሚሉ የፋብሪካ ሠራተኞች፣ ተጨማሪ ገንዘብ የሚያገኙበትን ትተው ሌላ ጉዳይ ላይ የሚልከሰከሱ ሠራተኞች፣ በየንግድ ድርጅቶች በራፍ መኪና ሲቆምና ሲነሳ ሰው የሚያስቸግሩ የጥበቃ ሠራተኞች፣ ከክፍል ወደ ክፍል ለመሸጋገር ኩረጃን የሚናፍቁ ችግኞቻችን፣ ሳይሠሩ ለመክበር የሚመኙ ሠራተኞችና አለቆች በበዙበት አገር ማኅበረሰብ በእጅጉ ይጎዳል፡፡ ይህ ጉዳትም በበረታ መልኩ በሁለቱም ኃይሎች ያርፋል፡፡ ድንበር አይከልለውም የሚባለው ሠርቶ የማይጠግበው ኃይል ተነሳሽነት፣ ዕውቀት፣ ድፍረት በማቀጨጭ ያላቸውን መዋዕለ ንዋይ ይዘው እብስ እንዲሉ ገፊ ምክንያት ይሆናል፡፡ ሌላኛው ደግሞ በሥነ ምግባር የታነፀው ኃይል ከሁሉም በላይ ትጋቱ ይቀንሳል፣ በነፃ ተወዳድሮ የላቡን ፍሬ ለማግኘትና ሰላምን አጣጥሞ የመኖር ፍላጎቱም ይገዳደራል፡፡ ምንም እጅግ የሚያምር ፖሊሲና ስትራቴጂ በቦታው ላይ ቢገኝ በሥነ ምግባር የታነፀ ኃይል በሌለበት ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ተመራጭነታችንም ሆነ ተደማጭነታችን በእጅጉ እንደሚጎዳው መረዳት ይኖርብናል፡፡ የሥራ ቦታ ሥነ ምግባሮች ለማሻሻል ምን መደረግ አለበት የሚልና ተዛማጅ የመፍትሔ ሐሳቦች ወደፊት ይዤ እመጣለሁ፡፡ እስከዚያው እንደመውጪያ ልብንና ህሊናን የሚኮረኩረውን ከመኪያ ኃይሉ ዘፈን በተዋስኩት ስንኝ የዛሬውን ልቋጥረው፡፡

ና ፍቅር እንውለድ

ና ፍቅር እንሥራ

ህሊናው የነቃ፣ ምግባሩ የፈራ

እንደ ዕንቁ የሚያበራ

ና ትውልድ እንውለድ

ና ትውልድ እናፍራ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የቢዝነስና ኢንቨስትመንት አማካሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...