Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአይሆንንም ትተሸ ይሆናልን አስቢ!

አይሆንንም ትተሸ ይሆናልን አስቢ!

ቀን:

በኢትዮጵያ ሳልሳዊ የሽብር ዘመን ይመጣ ይሆን?

ከተሾመ ብርሃኑ ከማል

እንደ መንደርደሪያ

በአገራችን ኢትዮጵያ የሽብር ግድያ መቼ እንደተጀመረ ጸሐፊው የጠለቀ መረጃ ባይኖረውም የመጀመርያው በኢጣሊያ ጊዜ፣ ሁለተኛው በደርግ ሥርዓት እንደነበረ ግን የመጀመርያውን ከነበሩት፣ ሁለተኛውን የዓይን ምስክር በሆነበት እንደተከናወነ  ያውቃል፡፡ ሁለቱም የሽብር ድርጊቶች የተከሰቱት መሪዎችን ለመግደል ከተደረገ ሙከራ ሲሆን፣ የዘመነ ኢጣሊያው ጄኔራል ግራዚያኒ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በቤተ መንግሥት ዲስኩር ሲያደርጉ በተወረወረባቸው ቦምብ በመቁሰላቸው ነበር፡፡ ሁለተኛው ሽብር የተጀመረው ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ቤተ መንግሥት በሚገኘው ቢሯቸው አምሽተው አራተኛ ክፍለ ጦር ወደ ነበረው ቤተ መንግሥታቸው በሚሄዱበት ጊዜ፣ ያኔ አብዮት አደባባይ ዛሬ መስቀል አደባባይ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ መስከረም 13 ቀን 1969 ዓ.ም. ነበር፡፡

በዚህም መሠረት የኢጣሊያ መንግሥት አብዛኛውን የኢትዮጵያ ግዛት ተቆጣጥሬያለሁ ብሎ ቢያወጅም፣ በኢትዮጵያውያኑ ዘንድ ተቀባይነት ስላልነበረው ተቋውሞ በየአቅጣጫው ቀጠሎ ነበርና ማርሻል ፒየትሮ ባዶጋሊዮን ሰኔ 9 ቀን 1928 ዓ.ም. በመተካት በተሾመው ማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ ላይ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. የግድያ ሙከራው ተካሄደ፡፡ በዚህም ጊዜ የኢጣሊያ ታጣቂዎች ኢትዮጵያዊያንን በግለሰብና በቡድን፣ በተናጠልና በጅምላ መጨፍጨፍ ጀመሩ፡፡ ኢትዮጵያዊያን በየቤቱ፣ በየሜዳውና በተጠረጠሩበት ቦታ ሁሉ ተገደሉ፡፡ በዚህ ግድያ 30 ሺሕ ያህል ኢትዮጵያውያን በግፍ ተገደሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ግማሽ ያህሉ በዕድሜያቸው ወጣቶችና የተማሩ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ነገሩ በመግደል ሳይወሰን ሕዝቡን በቋንቋና በሃይማኖት በመከፋፈል ሽብሩን አፋፍሞ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ከኢጣሊያ ወረራ በኋላ የተከሰተ የጎላ የሽብር ተግባር በአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ባይኖርም፣ እዚህም እዚያም የተከሰቱ አመፆችን ለማዳፈን የተወሰደ ዕርምጃ እንደነበረ ይታወቃል፡፡   

ሌተና ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታ ‹‹አብዩቱና ትዝታዬ›› በሚል ርዕስ በጸሐይ አሳታሚነት በ2008 ዓ.ም. ለንባብ ባበቁት መጽሐፋቸው ስለሽብር ታሪክ ሲያወሱ፣ ‹‹ሽብርና ሥርዓተ አልበኝነት ለመጀመርያ ጊዜ በከፋ መልኩ የተከሰተው እ.ኤ.አ ከ1789 እስከ 1799 ድረስ በፈረንሣይ አገር በተካሄደው አብዮትና የሽብር አገዛዝ ተብሎ በሚጠራው ወቅት ነው፤›› ካሉ በኋላ በሩሲያ፣ በሀንጋሪና በኢጣሊያ እንደተካሄደ ይገልጻሉ (ገጽ 209-210)፡፡

ሽብር በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የሚከሰት ሲሆን፣ በሕጋዊ መንገድ ጠላቱን ለማስወገድ ያልቻለ በሽብር ለማስገደል የሚሻ እንዳለ ሁሉ ሕግ ባለመፈቀዱ ምክንያት የፈለገውን ለመግደል ያልቻለም፣ ‹‹ግደል ግደል አለኝ…›› የሚል ዛር የተጠናወተው ሰውም ዕድሉን ካገኘ በሽብር ለመግደል ፍላጎት ሊኖረው ይችላል፡፡ ይህን ባህርይ በመጠኑ ለመግለጽ ይቻል እንደሆነ ሰላማዊ ሰውን በትንሽ ጠብ ምክንያት ገድለው ጫካ የገቡ፣ ወይም ተይዘው ወህኒ የወረዱ ሰዎችን በምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡

አንዳንድ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ለማርካት የሚሹ ሰዎችም እንዲሁ፣ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ አገር ማበጣበጥ ፍላጎት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ሰዎች ከሙሉ ጤነኞች ጋር የሚመደቡ ባይሆኑም ‹‹ደም የጠማቸው ሰዎች›› ተብለው የሚጠሩ ወይም የሚታሙ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጣም ጥሩ የሚባል ችሎታ ያላቸው ነገር ግን ጠላቶቻቸው ያጠመዱባቸው ወጥመድ ባለማወቅ በገንዘብ፣ በሥልጣን ወይም በሌላ መናኛ ነገር የሚገዙ አሉ፡፡ እነዚህ ደም የጠማቸው ሰዎች ወደ ግድያ ሲሰማሩ የሰው ሕይወት የሚቀጥፉ ላይመስላቸው ይችላል፡፡ 

እነዚህ ሰዎች በሲቪሉም፣ በወታደሩም፣ በምሁሩም፣ በገበሬውም፣ በነጋዴውም በአጠቃላይ የኅብረተሰቡ አባላት ሆነው መኖራቸው ቢሆንም፣ ከዚህ ሁሉ በላይ አስከፊ የሚሆነው ግን ከአገር ጠላት ጋር ለመግጠም ወታደራዊ ሥልጠና ባገኙ ሰዎች የተፈጸመ እንደሆነ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በጥቅሉ ጠላትን እንደምን በድፍረት (ሌሎች ቃላት ላለመጠቀም ጥንቃቄ የተደረገበት ጽሑፍ መሆኑን ልብ ይሏል) ድል ለማድረግ የሠለጠኑ ስለሆነ፣ በሽብር ተግባር ከተሰማሩ ውጤቱ የከፋ እንደሚሆን መረዳት አያስቸግርም፡፡

በሰው እጅ ከተገደሉ ዓለም የሚያስታውሳቸው መሪዎች

ዓለማችን ታላላቅ ሰዎቿን በነፍሰ ገዳዮች እንዳጣች የሚታወስ ሲሆን ከትላንት መማር ትልቅ ቁም ነገር በመሆኑ በፖለቲካ ምክንያትም ሆነ በግል ጥላቻ፣ በሃይማኖትም ሆነ በፍልስፍና፣ በቅናትም ሆነ በምቀኝነት ወይም በሌላ ምክንያት በዓለማችን በመሪዎች ላይ ተፈጽመዋል፡፡

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው እነዚህ የፖለቲካ መሪዎች ከሟች ወገን ሆነን ‹‹መገደል አልነበረባቸውም፣ በእብሪት የተፈጸመ ግድያ ነው፣ ሰላማዊውን የአስተዳደር ዘመን የሚያውክ ግድያ ነው፣ ዴሞክራሲውን ሒደት የሚያጨናግፍ ግድያ ነው›› እንደምንለው ሁሉ፣ ከዚህ በተፃራሪ የቆሙት ደግሞ ትክክለኛነታቸውን ለማስረዳት ሊሞክሩ ይችላሉ፡፡ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካም ትክክል አይደለም ተብሎ የተገለጸው አመቺ ሁኔታ ከተገኘ እንደ ትክክል ሊወሰድ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በእነ ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ በተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት የተገደሉ የሥርዓቱ የፖለቲካ መሪዎች መፈንቅለ መንግሥቱ ቢሳካ ኖሮ ትክክል ተደርጎ ሊወሰድ ይችል የነበረ ሲሆን በመክሸፉ ግን፣ እስከ ዘውዳዊው ሥርዓት መወገድ ድረስ ሲኮነን ቆይቷል፡፡ ይኸው  ግድያ ደርግ ሥልጣን ሲይዝ እንደ ትክክል የተወሰደ ሲሆን፣ ደርግ ራሱም የዘውዳዊው ሥርዓት ቁንጮዎችንና ሌሎች መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ የሞከሩትን ገድሏል፡፡ ግድያውም በአብዮታዊ ዕርምጃና በፍርድ እንደነበር መንግሥት አልካደም፡፡

ጸሐፊው እንደሚያስታውሰው ‹‹በነጭ ሽብርም›› ሆነ ‹‹በቀይ ሽብር›› ተሰማርተው የነበሩት ሦስት አራት ዓይነት ሲሆኑ፣ ሁሉም የመግደል ፍላጎት የነበራቸውና ለእነርሱ መልካም አጋጣሚ የተፈጠረላቸው፣ ደም ጥማት ያቃጠላቸውና ይህንን ፍላጎታቸውን ለማርካት የተዳፈነ ፍላጎት የነበራቸው፣ በፖለቲካ መሪዎች በቀላሉ የተታለሉ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ መደባቸው ምክንያት ‹‹በደል ሲደርስባችሁ ነበር›› የተባሉና በዚህም ምክንያት የመበቀል ፍላጎታቸው በማርካት ወደ ሥልጣን ለመምጣት ወደር የሌለው ምኞት የነበራቸው፣ ወይም በመግደል የመቆየት ዓላማቸውን ለማሳካት የሚሹ ይገኙባቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ጠመንጃ ቢይዙ የያዙት ጥይት እስኪያልቅ ድረስ የሚያርከፈክፉ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ገዳዮችም ጥይቱን በሟች ላይ የሚያርከፈክፉት እየተደሰቱ ሊሆን ይችላል፡፡ ድምፅ የሌለው የጦር መሣሪያ (ጩቤ፣ ሳንጃ፣ ጎራዴ፣ ሠይፍ፣ ዱላ) ቢሆንም የመግደል ተልዕኳቸውን በተመሳሳይ ሁኔታ ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡

ዊልያም ብሮይለስ የተባሉ ቀደም ሲል ማሪን ሲባል የነበረውና የኒውስዊክ መጽሔት አዘጋጅ የነበሩት ታዋቂ ጋዜጠኛ በ1984 (እ.ኤ.አ) ባቀረቡት ጽሑፍ እንደገለጹት፣ ድርጊቱን የሚፈጽሙት ሰዎች ደስታ እየተሰማቸውም ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዶቹ ጭራሹንም የሕፃናት ጨዋታ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ከማለም፣ ጣታቸውን ቃላ ላይ አስቀምጦ ከመሳብ፣ የሚገድሉት ሰው ሲንፈራፈር ከማየት የተለየ ነገር አይደለም፡፡ የጥይቱ ድምፅም ሙዚቃ መስሎ ሊሰማቸው ይችላል፡፡ እናም በፖለቲካ ምክንያት የሚገደሉ ሰዎች ሕይወታቸው የሚቀጠፈው በእንዲህ ያሉ አረመኔዎች መሆኑን ልብ ልንለው ይገባል፡፡

ዊልያም ብሮይለስ እንደሚሉት እነዚህ ሰዎች እንዲህ ያለውን አረመኔያዊ ግፍ እንዲፈጽሙ ሆን ተብሎ የሠለጠኑም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በእርግጥም ሕዝብ በተሰበሰበበት መሀል፣ ወይም ገበያ፣ ወይም ትርዒት በሚታይበት ሥፍራ ቦምብ ታጥቀው ራስን በራስ የማጥፋት ዕርምጃ በመውሰድ ለከፍተኛ ሕዝብ እልቂት ምክንያት የሚሆኑት የረጅም ጊዜ ሥልጠና እንደሚወስዱ የታወቀ ነው፡፡ አንዳንዶቹም በአፍዝ አደንግዝ ዘዴ (ሂፕኖቲዝም) ሠልጥነው ለግድያ የሚሠማሩ ናቸው፡፡

በጦርነት የሚሰማሩ ወታደሮችና የሽብር ተግባር

ኢ.ኤፍ ደርቢንና ጄ. ባወልባይ የተባሉ የሥነ ባህርይ ተመራማሪዎችም ቢሆኑ፣ አምባጓረኞችና ጦር አውርድ ብለው ጦር የሚሰብቁ ሰዎች ከአሸባሪዎች ጋር ያልተራራቀ ሥነ ባህርይ ሊኖራቸው እንደሚችል ጠቅሰው፣ እነዚህ ሰዎች ጀግኖች መሆናቸውን ለማረጋገጥ ኢሰብዓዊ የሆነ ዕርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ያብራራሉ፡፡ ስለሆነም የሚወሰደው ዕርምጃ ኢሰብዓዊ እንዳይሆን አስቀድሞ ማዘጋት እንደሚያስፈልግ የሚመክሩ የሥነ ባህርይ ሳይንቲስቶች አሉ፡፡ ምንም እንኳ በሰዎች ውስጥ የሚገኙ አውሬያዊ ባህርያት በሚገባ ባለመሠልጠናቸው ምክንያት ጭምር በተደረጉ ጦርነቶች ኢሰብዓዊ ግድያዎች ቢኖሩም፣ ኢ. ኤፍ ደርቢንና ጄ. ባወልባይ እንደሚሉት ጦር ግንባር የሚሠለፉ ሰዎች ኢሰብዓዊ ድርጊት እንዳይፈጽሙ ከእነሱ ጋር የሥነ ባህርይ ምሁራን መሰማራት እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡ ከዚህም በላይ ወታደሮች ሲሠለጥኑ በአሻንጉሊት ላይ የሚወስዱትን ጭካኔ የተሞላበት ዕርምጃ፣ ሕይወት ባለው ሰው ላይ ለመውሰድና ጀግንነታቸውን ከማሳየት ወደኋላ ስለማይመለሱ የሚወስዱት ዕርምጃ የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡

በአንፃሩም ግዳጅ የተሰማራ ኃይል ጠላቱ ፊቱ ተደቅኖ ርህራሔ ካሳየ እርሱ ራሱ ሊገደል ስለሚችል፣ ሁኔታውን አቅልሎ ማየትና በግዳጅ ወቅት ስለርህራሔ መስበክ ስለማያዋጣ የነገሩን ውስብስብነት ያመለክታል፡፡ ማለት የሚቻለው በጦርነቱ ያልተካፈለ ሰላማዊ ሰውን በጭካኔ አለመግደል ይሆናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እጃቸውን የሰጡ፣ የተማረኩ፣ ምንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ያልታጠቁ ወታደሮች እንዳይገደሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሕግ ይደነግጋል፡፡ ሆኖም በጦርነት ወቅትም ቢሆን ተመጣጣኝ ያልሆነ ዕርምጃ በመውሰድ ሰላማዊ ሰዎችን የገደሉ ሰዎች ሲጠየቁ መልሳቸው ‹‹ነገሩ ጦርነት መሆኑ ቀረ እንዴ? እንደምን የመለሳለስ ባህርይ ልናሳይ እንችላን?›› ብለው ሊመልሱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በመጋቢት 1968 ደቡብ ቬትናምን ለመርዳት ሄደው የነበሩ 105 አሜሪካኖች በደቡብ ምዕራብ ቬትናም ሰን ማይ በምትባለው ቀበሌ 500 የሚሆኑ ምንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ያልነበራቸው ሰዎችን ጨፍጭፈዋል፡፡ በወንዶቹ ላይ ግብረ ሰዶም በሴቶች ላይ ደግሞ በጽሑፍ መግለጽ የሚቀፍ ድርጊት ፈጽመዋል፡፡ ይህን አጸያፊ ተግባር ከፈጸሙ በኋላ ወደ ካምፓቸው ሲመለሱ መኖሪያ ቤቶቻቸውን አውድመውባቸዋል፡፡ በዚህ አስከፊ ተግባር የተሰማራው ወታደራዊ ቡድን አባል ሴቶች ከሚገደሉ ቢደፈሩ ይመርጡ ነበር ሲል ገልጿል፡፡ ሌላው ደግሞ፣ ‹‹እንደዚህ ያለው ተግባር በወቅቱ አስጸያፊ መሆኑን ጉዳዩን በደስታ ሲፈጽሙት ለነበሩት ወታደሮች ቀልድ ይሆን ነበር›› በማለት አስረድቷል፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ ሽብር ማካሄድ የጦርነቱ አካል ነበርና፡፡ ወታደር ሲታዘዝ መፈጸም ግዴታው ነበርና፡፡ በእጅጉ የሚያሳዝነው ግን ይህን ተግባር የፈጸሙት የሄግ ኮንቬንሽን (1899 እና 1907)፣ የኑረምበርግ መርህን (1946)፣ የጀኔቫ ኮንቬንሽን (1949) አሳምራ በምታውቀው አሜሪካ ወታደሮች የተፈጸመ ድርጊትና በጦር መሪዎቿ የተሰጠ ትዕዛዝ መሆኑ ነው፡፡

በጦርነቱ መስክ እንደዚህ ያለው ሽብር ሲከሰት በእስር ቤትም ተመሳሳይ የሆነ የሽብር ሥራ ሊፈጸም ይችላል፡፡ በእስር ቤት የሚፈጸመውን ሽብርና ግፍ የተሞላበት ቅጣት በአንድ ዓመት ውስጥ አይረሳም በሚል ግምት የምናልፈው ቢሆንም፣ ድርጊቱን የሚፈጽሙት ግፈኞች በአለቆቻቸው ስላታዘዙ ብቻ ሳይሆን ሰውን የማሰቃየት ድብቅ ፍላጎት ያላቸው መሆናቸውን ግን ሳልጠቁም አላልፍም፡፡

በአንዳንድ ሰላማዊ ሠልፎች የሚከሰት የሽብር ተግባር

በአንድ አገር መንግሥትን በመደገፍ ወይም በመቃወም፣ የፖለቲካ ድርጅትን በመደገፍ ወይም በመቃወም ወይም የሕዝብ ተቃውሞ ወይም ድጋፍ በሚያስፈገው ጉዳይ ሰላማዊ ሠልፍ ሊደረግ ይችላል፡፡ ሆኖም ሁሉም ሰላማዊ ሠልፍ በሰላም ተጀምሮ በሰላም ላይጠናቀቅ ይችላል፡፡ ሰላማዊ ሠልፉን ወደ አስከፊ ሁኔታ የሚለውጡት አዘጋጆቹ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ያንን አጋጣሚ በመጠበቅ ዓላማቸውን ለማስፈጸም የተዘጋጁ ሰዎች፣ ቡድኖች ወይም ኃይሎች በወጠኑት እኩይ ዓላማ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ዓላማቸውን በስውር ለማስፈጸም የሚሹ ኃይሎች ዓላማቸውን በተራቀቀ ወይም ባልተራቀቀ መንገድ ለማስፈጸም የተለያዩ ዘዴዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ‹‹የደመወዝ ጭማሪ ይደረግልን›› ብለው በሚጮሁ ሰላማዊ ሠልፈኞች መካከል ተገኝቶ፣ ‹‹ደመወዛችንን የከለከሉንን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሆኑ ከሥልጣናቸው ይነሱልን›› የሚል መፈክር ሊያስተጋቡ ይችላሉ፡፡

አንዳንድ ሰላማዊ ሠልፎች ሃይማኖታዊ መብትን ከማስከበር ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ቢችሉም፣ ያንን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም አንዱን ሃይማኖት በሌላው ሃይማኖት ላይ የሚያነሳሳ መፈክር ሊያስተጋቡ፣ ወይም ሃይማኖትን ሰበብ አድርገው በግል ወይም በቡድን የደረሰባቸውን በደል ለመበቀል ሲሉ በፀጥታ አስከባሪዎች ላይ ድንጋይ የሚወረውሩ ወይም ጥይት የሚተኩሱ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

የመንግሥት የፀጥታ ሰዎችም ከተሰጣቸው ትዕዛዝ ውጪ አጋጣሚውን በመጠቀም የመምታት፣ የመደብደብ፣ የመግደልና የማሰቃየት ተግባር ሊያከናውኑ ይችላሉ፡፡ በአንዳንድ ሰላማዊ ሠልፎችም ተመሳሳይ የሆኑ የሽብር ድርጊቶች ሊፈጸሙ ይችላሉ፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ ደግሞ በሰላማዊ ሠልፍ የሚሳተፍ ሁሉ ዓላማውን በሚገባ ያውቃል ማለት ከቶ አይደለም፡፡ ሲሠለፉ ዓይቶ ሊሠለፍ፣ ወይም ግርግሩን ተጠቅሞ ኪስ ሊያወልቅ የሚሠለፍ ይኖራል፡፡ በዚህ ሠልፍ የሚጎዳው እንዲህ ያለው ሰው ሊሆን ቢችል ነገሩ አብሮ አይሄድም፡፡

ለምሳሌ ጎንደር ውስጥ በ1990ዎቹ በአንድ ባህታዊ ነኝ የሚል በሚል ግለሰብ አነሳሽነት በፀጥታ አስከባሪዎችና በነዋሪዎች መካካል ግጭት ተነሳና ፖሊሶች ይሞታሉ፡፡ ከሕዝቡ መካከልም ግንባር ቀደም አጥቂ ከነበሩት ውስጥ ይያዙና ቃላቸውን ለፖሊስ ከዚያም ለፍርድ ቤት ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ጊዜ አንዱ ‹‹አቶ እከሌ በዚህ ረብሻ ላይ መሳተፍዎን ለፖሊስ ቃልዎን ሰጥተዋል?›› ሲባሉ፡፡ ‹‹አዎን ነበርኩ ብዬ ሰጥቻለሁ›› ይላሉ፡፡ ዳኛውም ቀጥሎ፣ ‹‹በረብሻው ፖሊሶች መሞታቸውን ያውቃሉ?›› ሲባሉ፣ ‹‹አዎን አውቃለሁ›› ይላሉ፡፡ ዳኛው መግደል ወንጀል መሆኑን ያውቃሉ?›› ተብለው ሲጠየቁ ግን፣ ‹‹የምን ወንጀል ፖሊሱ የሞተው ገጥሞን መስሎኝ!›› አሉና መለሱ ይባል፡፡ 

ለመሆኑ በአገራችን ወደ ሽብር ዕርምጃ የሚወስድ ሁኔታ አለ?

ምንም እንኳን የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የሚያቀርበው የተረጋገጠ መረጃ ባይኖረውም፣ እንደ ነባር ጋዜጠኛ ግን ወደዚያ የሚወስዱ ነገሮች የሉም ማለት የሚያስደፍር አይደለም፡፡ ይልቁንም ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. የተከሰተው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ይህን እውነታ የሚያመለክት ይሆናል፡፡ ‹‹የሰኔ 15 ዓ.ም. የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ በግብታዊነት የተከሰተ ነው?›› ብለን ስንጠይቅም ታሪካዊ መሠረት ይኖረው እንደሆነ በጥልቅ መመርመር ያስፈልጋል፡፡

ታሪካዊ ነው የምንል ቢሆን ታሪኩ ከማን ይጀምራል? ብለን ብንጠይቅ በአክሱምና በዛጉዌ፣ በዛጉዌና በሸዋ ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት፣ በሸዋ ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥትና በአዳል ሡልጣኔት፣ በአዳል ሡልጣኔትና በኦሮሞ የመስፋፋት ታሪክ፣ በኦሮሞ የመስፋፋት ታሪክና በዘመነ መሳፍንት፣ በዘመነ መሳፍንትና ከዚያ ቀጥሎ በመጡ የፖለቲካ መሪዎች መካከል የተከሰተውን የጦርነት ታሪክ ማስታወስ ይቻላል፡፡ ሆኖም ረዥሙን ታሪክ በአጭር ጽሑፍ ማቅረብ ስለሚያስቸግር ከደርግ ሥርዓት ተነስተን እንደሚከተለው እንመልከተው፡፡

በደርግ ጊዜ የተከሰተው ሽብር

ይህን የታሪክ ግጭት ከ1967 እስከ 1983 ዓ.ም. በሥልጣን ላይ የነበረው የደርግ መንግሥት በማርክሳዊ ሌኒናዊ ንድፈ ሐሳብ ሊያለዝበው ሞክሮ ነበር፡፡ ሆኖም፣

  1. ምሥራቅ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ጦርነት የከፈተችው ሶማሊያ፣
  2. ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ትግል ስታደርግ የነበረችው ኤርትራ፣
  3. ወታደራዊ አገዛዝ እንዲወገድ ያላሰለሰ ትግል ሲያደርግ የነበረው ኢሕአፓ፣
  4. ቀደም ሲል ከዘውዳዊው መንግሥት ቀጥሎም ከደርግ ቁርሾ የነበረው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕውሓት)፣
  5. ከሕወሓት ጋር ተመሳሳይ አቋም የነበረው የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ)፣
  6. የምዕራብ ሶማሌ ነፃ አውጭ ግንባርና ሌሎችም ሲቻል ግንባር በመፍጠር ሳይቻል በተናጠል የደርግን መንግሥት አዳከሙት፡፡

ደርግ መንግሥት እጁን ከመስጠቱ በፊት የኃይል ዕርምጃ እየወሰደ ሶሻሊስት ኅብረተሰብ ለመገንባት ጥረት አድርጓል፡፡

ይህም ሆኖ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ጥያቄው የተነሳው ከሕዝቡ ወይም ከስልተ ምርቱ ሳይሆን፣ ከዓለም የኃይል ሚዛን የተነሳ ነው፡፡ በመሆኑም ደርግ የአፄ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣኑን ከተረከበ በኋላ፣ በመጀመርያ ፊቱን ያዞረው ወደ ምዕራብ አገሮች ቢሆንም ምዕራብ አገሮች የተጠበቀውን ዕርዳታ ሊቸሩት አልቻሉም፡፡ ስለዚህም ፊቱን በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ምሥራቅ ለማዞር ተገደደ፡፡

ከተገደደባቸው ምክንያቶች ውስጥም አንደኛው እንደ ኢሕአፓ ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶች፣ እንደ ሻዕቢያ፣ ሕወሓት ያሉና የምዕራብ ሱማሌ ነፃ አውጪ ድርጅት የመሳሰሉት ፊታቸውን አዙረው ስለነበር፣ ከዚህም በላይ እነ ሶማሊያ፣ አብዛኛዎቹ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች፣ እንደ አልጄሪያ፣ ሊቢያ፣ ግብፅ፣ አንጎላ፣ ሞዛምቢክ ያሉ የአፍሪካ አገሮች የሶቪየት ኅብረት እገዛን ያገኙ ስለነበር ኢትዮጵያን ከወቅታዊ አደጋ ለማዳን ፊቱን ወደ ምሥራቅ አገሮች ማዞር ወቅቱ የጠየቀው ግዴታ ነበር፡፡ ከምሥራቅ አገሮች ጋር ሆኖም ሶሺያሊስት አብዮት በማካሄድ ላይ መሆኑን ይፋ  አደረገ፡፡ በማዞሩም የምሥራቅ አውሮፓ አገሮችን የወታደራዊ፣ የማቴሪያልና የሞራል ድጋፍ ለማግኘት የሶማሊያን ወረራ ተቋቋመ፡፡ ዳር ድንበሩንም አስከበረ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተቃወሙትን በሽብር ጭምር መግደል ጀመረ፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ የዓለም የፖለቲካ አቅጣጫ ተቀየረ፡፡ ኢትዮጵያን በወታደራዊ፣ በማቴሪያልና በሞራል ሲደግፉ የነበሩ አገሮች ራሳቸውን ችለው ለመቆም አልቻሉም፡፡ እንደ ሶቪየት ኅብረት፣ ዩጎዝላቪያ፣ ቼኮዝሎቫኪያ ያሉት አገሮች እንደ ቡሄ ዳቦ ተከፋፈሉ፡፡ ሁሉም ራሱን ለማዳንም በየአቅጣጫው መሮጥ ጀመረ፡፡ ኢትዮጵያም የምዕራብ አገሮች ተፅዕኖ መቋቋም አልቻለችም፡፡ ኢኮኖሚዋ በጦርነት ምክንያት ደቀቀ፡፡ የኤርትራ ነፃነት ግንባርና ሕወሓት ድል ቀናቸው፡፡ ሆኖም ቢሞክርም በ1983 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን የመጣው የኢሕአዴግ መንግሥት፣ ብሔር ብሔረሰብን መሠረት ያደረገ ፌዴራላዊ የፖለቲካ መስመር ሲከተል በተለያየ ርዕዮተ ዓለም የተከፋፈለውን የየፖለቲካ አንጃ ወደ አንድ አቅጣጫ ማሰባሰቡ አልቀረም፡፡

የኢሕአዴግ 27 የአገዛዝ ዓመታትና ሽብር

ኢሕአዴግ ደርግን እንዳሸነፈ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶችን በማሰባሰብ የሽግግር መንግሥትን የመሠረተ ሲሆን፣ ከሽግግር መንግሥቱ መሥራች አባላት ጋርም ለተወሰነ ጊዜ አብሮ ለመሥራት ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ ሆኖም ካሰባሰባቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የሚፈልገውን ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት ለመመሥረት እንደማይችል የተገነዘበው አንድም አስቀድሞ ነው፣ ይህም ካልሆነ በቶሎ ነው፡፡

በዚህም መሠረት ከኦነግ ጋር የነበረው ግጭት በጥቂት ወራት ውስጥ እየፈጠጠ መጣ፡፡ በኦነግ ስም የሚፈጸሙ ጥፋቶችም እየጎሉ መጡ፡፡ ኦነግም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚሰነዘርበትን ጥቃት ለመቋቋም አልቻለም፡፡ ለምሳሌ በበደኖ፣ በወተር፣ በቤኒሻንጉል፣ በሶማሌና በሌሎችም አካባቢዎች የሚፈጥረው ግጭት እየጎላ መቅረብ ጀመረ፡፡ በአጭር ጊዜም የሽግግር መንግሥቱን ትቶ ወጣ፡፡ እነዚህ ኃይሎች እነማን ናቸው? ኦነግ የሽግግር መንግሥቱን ትቶ ከሄደበት ጊዜ ጀምሮም እስካለፈው አንድ ዓመት ድረስ ከሽብርተኛ ቡድን ጋር የሚደመር ሆነ፡፡

ኦነግ የሽግግር መንግሥቱን ጥሎ እንደወጣ የምዕራብ ሶማሌ ተከተለ፡፡ ከዚያም የደቡብ ኅብረት አባላት ተወገዱ፡፡ ከሽግግር መንግሥቱ በኋላ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት መሰል ሥርዓት ለመመሥረት ቢሞክርም እንደታሰበው ሊሆን አልቻለም፡፡ ስለሆነም የደርግ ወታደራዊ አምባገነን መንግሥት ተወግዶ የኢሕአዴግ አምባገነን መንግሥት ለማካሄድ ጥረት መደረግ ተጀመረ፡፡ ሥርዓቱን የሚቃወሙ ሁሉ ፀረ ሕዝቦች ሆኑ፡፡ የፀረ ሕዝቦች አፈራረጅም ከደርግ አፈራረጅ ጋር በእጅጉ ተመሳሳይ ሆነ፡፡ በርካታ ድርጅቶችም በአሸባሪነት ተፈረጁ፡፡ በኢሕአዴግ መዳከም ዋዜማም በየቦታው ሽብር ተከሰተ፡፡ በሃይማኖት ተቋማት፣ በፖለቲካ ድርጅቶች፣ በትምህርት ቤቶች፣ ወዘተ ሁከት በረከተ፡፡ ሁከቱን ለማፈንም ሰዎች ለእስር ቤት ተዳረጉ፡፡ በእስር ቤትም ኢሰብዓዊ ድርጊት ተፈጸመባቸው፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት የታየ መልካምና መጥፎ ገጽታ

በዶ/ር ዓብይ አህመድ የሚመራው የኢሕአዴግ መንግሥት እንደ ምን ወደ ሥልጣን እንደመጣ የታወቀ በመሆኑ፣ እዚህ ላይ ለጊዜው የምሰጠው ማብራሪያ ባይኖርም በርካታ አበይት ተግባራት በአጭር ጊዜ መከናወናቸው አሌ አይባልም፡፡ በተለይም ለ20 ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮ ኤርትራ ድንበር በመክፈት የሁለቱ አገሮች ወንድማማች ሕዝቦችን ማገናኘታቸው ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡ በመሆኑም ተለያይተው ይኖሩ የነበሩ አባትና እናት፣ እህትና ወንድም፣ በሃይማኖት ተቋማት መካከል የነበረውን መከፋፈልና ጥል ለማስወገድ መጣራቸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ መልካም ስም ማትረፋቸው፣ በሽብር የተፈረጁትን ነፃ ማውጣታቸው፣ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ለመሥራት ፍላጎት ማሳየታቸው፣ ወዘተ በበጎ ጎኑ የሚታይ ነው፡፡ እነዚህም ጅምሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ድጋፍ ልንሰጣቸው ይገባል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በአንዳንድ ነገሮች ባለመስማማታቸው ፊታቸውን ሊያዞሩባቸው አይገባም፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ ግን በፍጥነት የዕርምት ዕርምጃ ካልወሰዱ በስተቀር መንግሥታቸው አደጋ ላይ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ዕምቅ የሆነ የሽብርና የሁከት እንቅስቃሴ ይኖር እንደሆነ አሠራራቸውን መፈተሸ ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ የሽብር ተግባሩ የተከሰተው ቁጥሩ እጅግ ብዙ የሆነ ሕዝብ ለእርሳቸው ያለውን ድጋፍ ለመግለጽ ወደ መስቀል አደባባይ በዘለቀበት ዕለት ነበር፡፡ በዕለቱ በተጣለው የእጅ ቦምብ የቆሰሉና የሞቱ ሲኖሩ ድጋፍ ሊሰጡ ከመጡት ሰዎች ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የፈጠሩት ሽብር ግን በቀላሉ የሚታይ ምልክት አልነበረም፡፡

ዶ/ር ዓብይ ወደ ሥልጣን ከመምጣቸው በፊት ወደ አዲስ አበባ የሚያስገቡ መንገዶች እንደተዘጉት ሁሉ፣ ከአማራ ወደ ትግራይ የሚወስዱ መንገዶች ተዘግተዋል፡፡ በሌሎችም ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ ዝርፊያም ተከስቷል፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በሶማሌና በደቡብም ክልሎች ግጭቶች ተፈጥረዋል፡፡ ብዙ ሰዎችም ሞተዋል፣ ቆስለዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ ለረሃብም ተጋልጠዋል፡፡ የወጣት ቡድኖች እዚህም እዚያም ሥርዓት አልበኝነትን የሚፈነጥቁ ድርጊቶች ሲፈጠሩ መንግሥት ሕግ ማስከበር የተሳነው የመሰለበት ሁኔታ አለ፡፡

በመጨረሻም ሥርዓት አልበኞች ባደራጁት ኃይል መፈንቅለ መንግሥት ተቃጣበት፡፡ ይህ ተቃጣ የተባለው መፈንቅለ መንግሥት በእርግጥም ከግለሰቦች ግጭት ባለፈ መፈንቅለ መንግሥት ከሆነ ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ጽጌ አምስት ሰዎችን በመግደል ብቻ ሥልጣን ይይዛሉ ብሎ መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ መንግሥት ሌሎች የተቀነባበሩ ሴራዎች ይኖሩ እንደሆነ ደግሞ ሊነግረን ይገባል፡፡ ለምሳሌ ብርጋዴር ጄኔራሉ በተመሳሳይ ቀን ተመሳሳይ እንቅስቃሴ አድርገው ቁልፍ ሰዎችን በመግደልና በቁልፍ ቦታዎች አባላቱን በማሰማራት፣ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃንን በቁጥጥር ሥር በማድረግ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ ማቀዳቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ይኖር እንደሆነ ማብራራት ያስፈልጋል፡፡ አሁንም በዚሁ መፈንቅለ መንግሥት ጠንሳሽ ቡድን ሽብር ለመፈጸም የተሰማሩ ኃይሎች ይኖሩ እንደሆነ ማስጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡ ያለበለዚያማ እንደምን መፈንቅለ መንግሥት ይሆናል? 

የተቀነባበረና ስፋት ያለው ሙከራ ካልሆነ የሚያሠጋው ድንገተኛ የሆነ እንቅስቃሴ ነው፡፡ በዚህ ጸሐፊ ግምት ከቴሌቪዥን መረጃዎች እንደተገነዘብነው በርካታ የጦር መሣሪያዎች በግለሰቦች እጅ ገብተዋል፡፡ ገበሬዎች በሬዎቻቸውንና እህላቸውን እየሸጡ ራሳቸውን በጦር መሣሪያ እያስታጠቁ ነው፡፡ በገጠሩ አካባቢ ዝርፊያ እየተከሰተ ነው፡፡ በደቡብ ወሎና በሰሜን ሸዋ የተከሰተው ግጭት ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው፡፡ በጎንደር በተለይም በቅማንት አካባቢ የተከሰተው ችግርም ከዚህ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ሲታይ መወገድ ያለባቸው ችግሮች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ፣

  1. አስተዳደር  ክልሎች መካከል ያለው ወሰን፣
  2. እስካሁን የታየው በክሎሎች መካከል ያለው ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት፣
  3. በኢኮኖሚውና በማኅበራዊ ኑሮው ውስጥ የሚታየው ቀውስ፣
  4. በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የሚታየው ችግር ይገኙበታል፡፡

እነዚህ ችግሮች ካልተፈቱና እልባት ካለተሰጠ በስተቀር እንደ ከዚህ ቀደሙ በለዘብተኝነት መቀጠል አይቻልም ይሆናል፡፡ ስለዚህም አንድም፣

‹‹ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም

በቀና መንፈስ እንከኗ ይውደም››

ብሎ ጀምሮ በመራራው ትግላችን የአድህሮት ኃይላትን በቁጥጥር ሥር እናደርጋለን እንዳለውና ኢትዮጵያን በደም ጎርፍ ለማጥለቅለቅ በአደባባይ እንደፎከረው ደርግ መሆን ይመጣል፡፡ ያለበለዚያም የሚፈራው መፈራረስ ዕውን ይሆናል፡፡ ከዚያ በኋላ የፈረሰውን መጠገን ይከብዳል፡፡

በእርግጥም በአሁኑ ጊዜ የደርግ የመጀመርያ ዓመት የነበረበትን አዝማሚያ የሚፈነጥቅ ሁኔታ በትንሹም ቢሆን እየተከሰተ ያለ ይመስላል። ማንም ቢሆን ራሱን ካላቀ፣ በልቡ ትዕቢትና ዕብሪት ካስገባ፣ እርሱን አስወግጄ ብቻዬን እኖራለሁ ካለ፣ ትናንት በራሴ ላይ ፈንጭቷልና ዛሬ እኔ በተራዬ ልፈንጭበት የሚል የበቀልና የቂም መንገድ ከተከተለ ያለ ምንም ጥርጥር  ስምምነት ሊኖር አይችልም፣ አንድነት አይኖርም፡፡ ለውጡ በአንድ ዓመት ውስጥ የብዙ ዓመታት መሸርሽር ደርሶበት እንደሆነም ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

 እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ልዩነት ምንጊዜም የሚኖር፣ የማይጠፋ ነባራዊ እውነታ ነው። ያለ ተቃራኒ የተፈጠረ የለም።  ምንጊዜም ልዩነት ከሰው አዕምሮ/ልቦና ጋር የተያያዘ ነው። ሌላ ቢቀር አንድን ነገር እኩል አናይም። እኩል አንሰማም። እኩል አንቀምስም። እኩል አንዳስስም። እኩል አንረዳም። እኩል ባለመሆኑ ልዩነት አለ። አሉታዊና አዎንታዊ አስተሳሰቦች አንድ ላይ እየተሳሳቡ ይኖራሉ። በአሉታዊና አዎንታዊ ውህደት አዲስ ነገር ይፈጠራል። ያለ አሉታና ያለ አዎንታ አንድነት የለም። ይህን መካድ ሲኖር ልዩነት ይጎላል። መግባባት አይቻልም።

ይልቁንም በአንድ ወቅት የተቆሳሰሉ ሰዎች ተሸናፊ ሆነው ላለመገኘት የማያከራክረው ሁሉ ሊያነታርካቸው ይችላል። ሀቁ ይህ ሆኖ እያለ በጥላቻ ተሞልቶ ጥላቻን መንዛት፣  በእልክ ተሞልቶ በየፈፋው ማቅራራት፣ ወንድም ከወንድም ጋር ማጋጨት፣ ምክንያት እየፈለጉ ስምና ዝናን ማጠልሸት፣ ጉባዔ  እየጠሩ ነገሮችን ማበላሸት፣ መልካም ስምንና ዝናን ማጉደፍ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ማጋጨት፣ መንገድ መዝጋት፣ ካፈራው ንብረቱና ሀብቱ እየዘረፉ ማባረር፣ ማፈናቀል፣ መግደልና መገዳደል ይህም ሁሉ ሲሆን ዝም ብሎ ማየት አግባብ አይደለም። ስለዚህ በጥሩ ሁኔታ ተጀምሮ የነበረው ለውጥ እንዳይወይብና መልኩን እንዳይቀይር የሚታየውን የመከፋፈል አጀንዳ ዘግቶ፣ የመሸዋወድ አጀንዳ ሰርዞ፣ በራስ ቡድን ችግርን ለመወጣት ከሚደረገው የትግል ሥልት ወጥቶ ሁሉን ኢትዮጵያዊ ወደ የሚያሳትፍና ኢትዮጵያን ወደ ትክከለኛ የዴሞክራሲ መስመር መግባት ያስፈልጋል፡፡ እጁን ዘርግቶ የተቀበለን ሕዝብ ማክበር ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...