Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየለውጡ ጅማሮ በመንግሥትም ሆነ በሌላ ኃይል እንዲቀለበስ መፍቀድ የለብንም      

የለውጡ ጅማሮ በመንግሥትም ሆነ በሌላ ኃይል እንዲቀለበስ መፍቀድ የለብንም      

ቀን:

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ

“የምትመኘውን ነገር ተጠንቀቀህ ተመኝ የተመኘኽው ነገር እውን ሊሆን ይችላልና” አሜሪካዊ አባባል።

በቅድሚያ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ብርቅዬ በሆኑ የገር ዜጎች ላይ በተፈመው ግድያ ልባቸው ለተሰበረው የሟች ቤተሰቦች ወዳጅ ዘመድና ጓደኞች እንዲሁም በጥልቅ ላዘነው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን እመኛለሁ። ረያ ካርሰን የተባለች ዕውቅ ደራሲ፤ “The Bitter Kingdom” በሚለው መጽ“Peace is such hard work. Harder than war. It takes way more effort to forgive than to kill.” ትላለች። በግርድፉ ሲተረጎም “ሰላም ከባድ ሥራ ነው። ከጦርነትም ይከብዳል። ከመግደል ይልቅ ይቅርታ ማድረግ እጅግ ብዙ ጥረት ይጠይቃል” ማለት ነው።

በአገራችን የፖለቲካ ባህል እርስ በእርሳችን መገዳደል አዲስ ባይሆንም፣ የሰኔ 15 ቀን አሳዛኝ ግድያ የተለየ የሚያደርገው አብዛኛው ሕዝብና መንግሥት ይቅር ሰለመባባል እየሰበኩ ባሉበትና ወደ አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ እንዲሁም አዲስ የፖለቲካ አቅጣጫ ተስፋ ሰንቀን መንገድ በጀመርንበት ጊዜ መሆኑ ነው። ለመገዳደል አዲስ አይደለንም፡፡ በጠላትነት ለመፈራራጅና ተቧድነን ለመተላልቅ ዝግጁ ነን። በሐሳብ ተሟግተን ለመሸናነፍ ብዙ የሚቀረን ይመስላል። ሌላው ቀርቶ ዛሬ እንኳን ከዚህ ከደረሰብን መሪር ሐዘን ባለመማር በየጥጋችን፣ በየጎጣችን ተቧድነን የጦርነት ታምቡር እንደልቃለን። ሁሉም ጀግናው የእኔ ብሔር ነው፣ ጡንቸኛው እኔ ነኝ ይለናል። ሰከን ያሉ ሰዎች ገላጋይ እንዳይሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያው ትኩስ ጀግና እንደሱ ያላሰበውን፣ እሱ እውነት ብሎ የተቀበለውን፣ ያልተቀበለውን ያለምንም ምሕረት ያላትማል። ትዕግሥት የለም፡፡ “የሃሰት መረጃ ፋብሪካዎች” እንደ አሸን ፈልተዋል። ሁሉም ጣት ጠቋሚ ነው። ሁሉም በብሽሽቅ የጀገነ ነው። በዚህ የቁልቁለት መንገድ ላይ ሆነን ግን እንዴት ነው ወደ መቻቻል ፖለቲካ የምንሄደው? እኔ ያልኩት ብቻ መደረግ አለበት በሚል ግብዝነት፣ “ከእኔ በላይ አገር ወዳድ የለም” በሚል አጉል ጀብደኝነት አገር መገንባት አንችልም። ስንት ደም የፈሰሰበትን፣ ስንት ዋጋ የተከፈለበትን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የመገንባትና ሥልጣን የሕዝብ የማድረግ ሕልም ዕውን ለማድረግ የምችልበትን መንገድ እያጠበብን ስለዴሞክራሲ፣ ስለሰብዓዊ መብት ስለመናገርና መሰብሰብ ነፃነት ብናወራ ወሬ ብቻ ከመሆን አያልፍም። ምን ያህሉ የፖለቲካ ልሂቆቻችን ናቸው ከራሳቸው፣ ከድርጅታቸው፣ እንዲሁም ከጎጣቸው በላይ ለአገር የሚያስቡት?

“ለኦሮሞ ያልሆነች ኢትዮጵ፣፤ ለትግራይ ያልሆነች ኢትዮጵያ፣ ለአማራ ያልሆነች ኢትዮጵያ፣ ለሶማሌ ያልሆነች ኢትዮጵያ፣ ወዘተ ትበጣጠስ” በሚል ፈሊጥስ እንዴት ወደፊት መራመድ እንችላላን? ስለአያቶቻችንና አባቶቻችን ብልህነት፣ ይቅር ባይነትና መቻቻል ነጋ ጠባ የሚደሰኩር ትውልድ፣ ስለኢትዮጵያውያን ታላቅነት ደረቱን ነፍቶ የሚናገር ትውልድ እንዴት በራሱ ትውልድ ውስጥ መቻቻልን፣ ይቅር መባባልን ከልብ ተቀብሎ ተግቶ አይሠራም? የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ገና ሲታሰብ እንኳን እጅግ የሚያደክም ብዙ ችግሮች እና ፈተናዎች አሉባት። እንኳን እየተናቆርን ተባብረንና ተዋደንም ችግሮችዋን ለመፍታት ዘመናት ይፈጅብናል። ታድያ መቼ ነው ቆም ብለን የምናስበው? ዛሬ እኮ የፖለቲካ ብልጣ ብልጥነት በማሳየት አንዳችን አንዳችንን ለመብለጥ የምንተጋበት ጊዜ መሆን የለበትም። እንደ አውሮፓውያኑ፤ እንደ አሜሪካኖቹ እኮ አገራችን የፖለቲካ ቁማር የምትሸከምበት ትከሻ የላትም። መቼ ነው ይህ የመጠላለፍ ፖለቲካ፣ የመገዳደል ፖለቲካ የሚያበቃው? ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ለፈሰሰው ደም ተጠያቂዎች ሁላችንም ነን። አንድ ቡድን አንድ ብሔር፣ አንድ አካል ነው ብለን የምናስብ ከሆነ ተሳስተናል። እጅግ በጣም ተሳስተናል።

እስቲ ሁላችንም ባለፈው አንድ ዓመት የመጣንበትን መንገድ ዞር ብለን እንይ። ምን ያህል ወገን ተፈናቀለ? ምን ያህሉ ሞተ? ምን ያህሉስ ተሰደደ? እንደ ዜጋ ኃላፊነት ባለመውሰዳችን የአገሬ ጉዳይ የእኔም ጉዳይ ነው ባለማለታችን፣ ኮሽ ባለ ቁጥር መፍትሔ ፈላጊ ከመሆን ይልቅ ሰዎችን ለማውገዝና ለማንጓጠጥ የምንሽቀዳደም መሆናችን ነው ዛሬ ለደረስንበት አሳዛኝ ወቅት ምክንያቱ። እከሌ ነው ብለን ወደ ሌላው ጣት እንጠቁም ይሆናል፡፡ ራሳችንን በመስተዋት ብንመለክት ችግሩ እኛው ራሳችን ሆነን እናገኘዋለን። በተደጋጋሚ እንደተነገረው የአለን አንድ አገር ነው። ሌላውን ጎጥ ጎድቼ የእኔን ጎጥ እጠቅማለሁ ብለን የምናስብ ከሆነ፣ አርቀን ማሰብ ተስኖናል ማለት ነው። አንዱን ጎድቶ ሌላውን መጥቀም አይቻልም። ምክንያቱም ነገ ዕድሉ፣ ዕጣው ይዞራልና የዛሬው ተጎጂ ነገ ደግሞ ጎጂ ይሆናልና ልክ እንደ አሁኑ ዕጣ ፈንታችን ተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ መሽከረከር ይሆናል። ከዚህ አዙሪት ውስጥ ግን መውጣት እንዴት አቃተን? ለተቀረው ዓለም መፍትሔ የሚያበጁ ኢትዮጵያውያን እንዴት ለአገራቸው መድኃኒት አጡ?

ወገን ወገኑን በሚያፈናቅልበት አገር እንዴት ከድህነት መውጣት ይቻላል? ወገን ወገኑን በሚገድልበት አገር እንዴት በሰላም መኖር ይቻላል? ሁሉም ለጎጡ ወግኖ ለእኔ ጎጥ ብቻ በሚል ሕዝብ ውስጥ እንዴት የተባበረች አንድ አገር መፍጠር ይቻላል? ለማኤሪካውያን ጥቁሮች ነፃነት ታጋይ የነበሩት ማርቲን ሉተር ኪንግ በማያሻማ ሁኔታ እንዳስቀመጡት፣ እንደ ወንድማማች አብረን ለመኖር መማር አለብን፡፡ አለበለዚያ እንደ ቂል እርስ በእርስ እንጠፋፋለን። እኛ እየተከተልን ያለነው የቂል መንገድ ነው። ለምን? ማናችንም ዘለዓለማዊ አይደለንም። ለቀጣዩ ትውልድ እስከ መቼ ነው ቂም እና የመገዳደል ባህል ትተንለት የምንሄደው? ይህንን ሁላችንም ቆም ብለን ማሰብ አለብን።

ባለፈው ሳምንት በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ለተከሰተው አሳዛኝ ክስተት ወደድንም ጠላንም የእያንዳንዳችን የጣት አሻራ አለበት። ችግሩ የሁላችንም ነው፡፡ መፍትሔው የሚመጣውም ከሁላችንም ነው። ይህንን አምነን መቀበል አለብን። ይህ እንደማይደገምም በማያሻማ ሁኔታ ቃል መግባት አለብን። በእንደዚህ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ለተሰውት ብርቅዬ ዜጎች፣ “ነፍሳችሁን ይማር” ማለት ጉንጫ አልፋ ነው የሚሆነው። እነሱን የምናከብረው እርስ በርስ ይቅር ስንባባል ነው፡፡ እነሱን የምናከብረው የግድያ አዙሪቱን ስናቆም ነው። ስለጀግንነታቸው በማውራት አይደለም የምንዘክራቸው፡፡ የምንዘክራቸው ለሰላምና ለመቻቻል የቆምን የሰላም አርበኞችኛ የሰላም ጀግኖች መሆናችንን በተግባር ስናሳይ ነው። አንድ ነገር ከሆነ በኋላ መቆጨቱና ማንባቱ ትርጉም የለውም። እምባ ጠራጊ ከመሆናችን በፊት ሲጀመር ያ እምባ እንዳይፈስ ነው ተግተን መሥራት ያለብን። 

በመገዳደል የፖለቲካ ባህል ማንም አሸናፊ ሆኖ የሚወጣ የለም። ይህንን ከሶሪያ፣ ከየመን፣ እንዲሁም ከራሳችን ታሪክ መማር አለብን፡፡ ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር እኮ የትናንት ድርጊታችን ነው። አገራችን በድህነት አረንቋ የምትታመሰው ከዚሁ የግድያ አዙሪት ውስጥ አልወጣ በማለታችን ነው። በቀልን ከውስጣችን እናስወጣ። ከፍተኛ ቦታ የሰጠናቸው ጎጠኝነት፣ ሥልጣን፣ መጠላለፍ፣ ተንኮል፣ የፖለቲካ ቁማር፣ እንዲሁም የአድማ ፖለቲካ ከአስተሳሰባችን ተፍቀው ወጥተው ፍትሕ፣ ሰላም፣ ይቅር ባይነትና መተሳሰብ እዚህ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ሊቀመጡ ይገባቸዋል። እንተሳሰብ፣ አንድ እንሁን ማለት አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ይኑረን ማለት አይደለም፡፡ የሐሳብ ልዩነቶቻችንን በውይይትና በመቻቻል እንፍታቸው ለማለት እንጂ። በምንስማማው ላይ ተስማምተን፣ በማንስማማው ላይ ተቻችለን አገራችንን እንገንባ፣ ለቀጣዩ ትውልድም የተሻለ ነገር እናስረክብ።

ከዓመት በፊት የተጀመረው የለውጥ ጉዞ በምንም ሁኔታ በመንግሥትም ይሁን በሌላ ኃይል ሊቀለበስም ሆነ ሊዘገይ አይገባውም። ይህ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት፣ እጅግ ብዙ ብርቅዬ ዜጎቻችንን ያጣንባቸው መሠረታዊ የመብት ጥያቂዎችና ሥልጣንን ለሕዝብ የማስረከብ ሥራ አሁንም ገፍቶ መቀጠል አለበት። መንግሥት ባለፈው አንድ ዓመት ባሳየው ሆደ ሰፊነትና የመቻቻል የፖለቲካ ባህል እንዲዳብር የወሰዳቸው በጎ ዕርምጃዎች፣ አሁንም ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። ባለፈው አንድ ዓመት በብዛት ክርክርና ውዝግብ ያስነሳው “መንግሥት ዕርምጃ ይውሰድ፣ ሕግ ያስከብር” የሚሉ ጥሪዎችና ውትወታዎች ነበሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድም፣ “መንግስት ዲክታተር ለመሆን ጫፍ ላይ ነው ያለው” ሲሉ እባካችሁ ጉልበት እንድንጠቀም አትግፉን ዓይነት ተማፅኖ በተደጋጋሚ አሰምተዋል። ሰሚ ግን አልተገኘም። ብዙው የፖለቲካ “ሊቅ” ሲወተውት የነበረው ሕግ ይከበር መንግስት ደካማ ነው እያለ ነበር። እነሆ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአፈሳና እስራት ታጅቦ መንግሥት ጉልበቱን አፈርጥሞ ብቅ ብሏል። አሜሪካኖች “የምትመኘውን ነገር ጠንቀቀህ ተመኝ እውን ሊሆን ይችላልና” ይላሉ። አሁን ደግሞ እነዚያው ሕግ አስከብሩ፣ መንግስት ተዳክሟል ሲሉ የነበሩ ኃይሎች መንግሥት ሕግ ጣሰ ማለት ጀምረዋል። ይህ “የገመድ ጉተታ” የሚመስል ነገር እስከ መቼ እንደሚቀጥል ግልጽ አይደለም።

አንድ ግን መታወቅ ያለበት ነገር አለ። መንግሥት ሕግ ያስከብር ማለት፣ ያላግባብ ይሰር ወይም ይግደል ማለት አይደለም። ሕግ ያስከብር ማለት በወንጀል ጠርጥሮ የሚያስራቸውን ዜጎች በማስረጃ ይጠይቅ፣ ሰብዓዊ መብታቸውን ያክብር፣ ከወንጀል ነፃ ከሆኑ በአስቸኳይ ይፍታቸው። ወንጀል ሠርተዋል የተባሉትም በአስቸኳይ ክስ ይመሥረትባቸው። ክሳቸውም ለሕዝብ ግልጽና ፖለቲካዊ ያልሆነ፣ ግን ሕጋዊ በሆነ የፍርድ ሒደት ይረጋገጥ። ሕግ ከማስከብር ጎን ደግሞ ቀደም ብሎ መስፋት የጀመረው የፖለቲካ ምኅዳር እንዳይጠብ፣ ባለሥልጣናት ያላቸውን የመንግሥት ኃይል ተጠቅመው በማንም ላይ ፖለቲካዊ ዕርምጃ እንዳይወስዱ ማስገንዘብ፣ መከታተል፣ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በሚጠቀሙም ላይ ተገቢ ዕርምጃ መውሰድ ማለት ነው።

ሌሎቻችንም በአገሪቱ ፍትሐዊ ሥርዓት እንዲኖር ግፊት ማድረጋችንን መቀጠል ተጠርጣሪ የተባሉ ሰዎች ሲታሰሩ፣ ምንም መረጃ ሳይኖረን “ጎጤ ስለሆነ ነው የታሰረው” የሚለውን ትርከት ማቆም የሐሰት ዜናዎችን አለመቀበል አለማሰራጨት፣ እንደ ዜጋ ኃላፊነት መውሰድ፣ የሚሰማንን ነገር ሥርዓት ባለው መንገድ መግለጽ፣ ብሔር ተኮር ጥቃት ማቆም፣ ሕግ ማክበር፣ ከጥላቻ ፖለቲካ መታቀብ፣ የሚያጠፉ ሰዎችን መገሰጽ፣ ወንጀል ሲፈጸም ለሕግ አስከባሪ አካላት ማሳወቅ፣ የሌሎችን መብት ማክበርና እንደ ዜጋ ግዴታችንን መወጣት ይጠበቅብናል። ይህችን አገር ማዳን፣ መገንባት፣ ማሳደግና ከትውልድ ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ተቋማት ልንገነባ የምንችለው በሁላችንም ጥረት አስተዋጽኦና ትግል እንጂ በጥቂት ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ በመንግሥት፣ ወይም በፖለቲካ ድርጅቶች ብቻ አይደለም። ላለፈው አንድ ዓመት ተስፋ የሰነቅንበት ለውጥ እንዲመጣ ሁላችንም ጮኸናል፣ ሁላችንም እንደየመጠኑ ዋጋ ከፍለንበታል። ለውጡን ያመጣው ግለሰብ፣ አንድ ቡድን፣ ወይም አንድ ብሔር/ብሔረሰብ አይደለም። ለውጡም የመጣው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ በተደረገ ትግል አይደለም። እዚህ ለመድረስ ወደ ግማሽ ምዕተ ዓመት ገደማ ፈጅቷል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕይወት ገብረናል። በተለይ “ለውጡን ያመጣሁት እኔ ብቻ ነኝ” የሚሉ ኃይሎች ቆም ብለው ያስቡ። ከተባበርን አገራችንን ከውድቀት እናድናለን፡፡ እንደ ቂሎች ከተናቆርን አገር አይኖረንም። ኢትዮጵያን ዳግማዊት ሶሪያ ማድረግና አለማድረግ ምርጫው የእኛና የእኛ ብቻ ነው።  ቸሩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...