(ክፍል ሁለት)
በፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
ግራ የገባው ሕዝብና ምሁር
በአጠቃላይ ሲታይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዛሬው የተሻለ ሁኔታ ቢመጣለት በጣም ደስተኛ ነው። ቢያንስ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባትን ይፈልጋል። ይሁንና ያለበትንና የሚኖርበትን ሁኔታ በደንብ ይረዳ አይረዳ፣ ምን ዓይነት ኅብረተሰብ ይመኝ እንደሆነና፣ በጭንቅላቱ ውስጥ የሳለው አንዳች የኅብረተሰብ ሞዴል ይኑረው አይኑረው ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው።
በኅብረተሰብ ታሪክ ውስጥ አንዳች ዓይነት ሥርዓትን የሚፈጥሩ አብዛኛውን ጊዜ የፖለቲካ ሥልጣንን የጨበጡ ናቸው። በአንድ አገር ውስጥ በተለይም ደግሞ አምባገነናዊ አገዛዞች በሰፈኑባቸውና በጥልቀትና በስፋት የሚያስብ የነቃ የኅብረተሰብ ክፍል በሌለበት አገር አገዛዞች የሚያወጧቸውና ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ፖሊሲዎች በአቦ ሰጡኝ ነው። በተለይም ደግሞ በዓለም አቀፍ ኮሙዩኒቲው ግዳጅና ምክር ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚደረጉ ፖሊሲዎች የተረጋጋና ለፈጠራ የሚያመች፣ እንዲሁም ደግሞ ግብረ ገብነትንና ሥነ ምግባርን የሚያዳብሩ ማኅበረሰብ እንዲመሠረት የሚያግዙ ሳይሆኑ የተቃራኒውን እንዲሆን የሚያደርጉ ናቸው። ካለፉት 28 ዓመታት ጀምሮ በአገራችን ምድር እየባሰበት የመጣና በተለይም ወጣት ሴቶችንና በዕድሜ ገፋ ያሉትን የሚያስፈራና የሚያስቆጣ ሁኔታ ከሰማይ ዱብ ያለ ሳይሆን ሥልጣንን በጨበጡትና የሕዝባችንን ዕድል በሚወሰኑትና በውጭ ኃይሎች የተቀነባበረ ሴራ ነው። በተለይም ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋናው ዓላማውም ሳይንስና ቴክኖሎጂን በማዳበር የሰፊውን ሕዝብ ኑሮ በማሻሻል ጥበባዊና የተከበረ አገር መገንባት ሳይሆን፣ ደሃና ለማኝ፣ እንዲሁም ፈሪና አጎብዳጅ ኅብረተሰብ ለመፍጠር ነው። ከዚህ ስንነሳ ባለፉት 28 ዓመታት ከዚያ በፊት ታይተው የማይታወቁ የአገራችንን እሴቶች የበጣጠሱ ሁኔታዎች በመስፋፋት ሕዝቡ እንደ ማኅበረሰብና እንደ ኅብረተሰብ እንዳይኖር አድርገውታል። የሙስና መስፋፋት፣ ጥቂት ደመወዝ እያለው በጥቂት ዓመታት የብዙ መቶ ሚሊዮኖች ዶላርና ቁጥራቸው የማይታወቁ ንብረቶች ሀብታም መሆን፣ የዕፅ ሱስና የሴተኛ አዳሪነት መስፋፋት፣ የማጅራች መቺዎችና የኪስ አውላቂዎች እንደ አሽን መፈልፈልና ለሰፊው ሕዝብ ጠንቅ መሆን፣ ተፈጥሮአዊ ያልሆነ የወሲብ ተግባር መስፋፋትና አገሪቱም ለእንደዚህ ዓይነቱ አፀያፊ ተግባር ክፍት መሆኗ፣ ሰላዮች እንደፈለጋቸው መዋኘት መቻላቸውና በሥልጣን ላይ ያሉትንና የተወሰነውን ኤሊት በማባለግ ሀብት እንዲዘረፍ ማድረግ. . . ወዘተ. እነዚህና ሌሎች የአገርን ክብር እንዲጣስ ያደረጉት ሁሉ ከሰማይ ዱብ ያሉ የእግዚአብሔር ቁጣዎች ሳይሆኑ በሰው የተሠሩ ናቸው። እነዚህ ነገሮች በሙሉ ማን እንደፈጠራቸው፣ ለምንስ እንደዚህ ዓይነት አፀያፊ ተግባሮች እየተለመዱና ተቀባይነትን እያገኙ መምጣት እንደቻሉ የሚያጠና ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ባለመኖሩ በተለይም ሰፊው ሕዝብ ግራ ተጋብቶ እንዲኖር ተደርጓል። ሳይወድ በግድ ይህ ዓይነቱ አፀያፊ ተግባር እንደ አንድ የኑሮ ፍልስፍና አድርጎ እንዲቀበለው ሊደረግ በቅቷል።
በዚህ ዓይነቱ የተዘበራረቀ ሁኔታ ደግሞ በተለይም ወጣቱን የሚያሳስቱና መንፈሱን የሚሰልቡ ሃይማኖት መሰል ነገሮች በመስፋፋት አቅመ ቢስ አድርገውታል። የሰውን ጭንቅላት በማደንዘዝ እንፈውስሀለን በማለት ገንዘብ በመሰብሰብና ካዲላክ መስል መኪናዎችን በመግዛት የሚንደላቀቁ ‹‹ፓስተሮች›› ነን ባዮች የተከፈተላቸውን በርና የተለቀቀላቸውን ሜዳ በመጠቀም ባለፉት 28 ዓመታት በቀላሉ መፍትሔ የማይገኝለት ወንጀል ሠርተዋል፡፡ እየሠሩም ነው። በዚህ ላይ ምሁር ነን በማለት በየቴሌቪዥኑ እየወጡ ቃለ መጠይቅ የሚደረግላቸውና መልስ የሚሰጡ በአገሪቱ ምድር ላይ የሚታየውን ሁኔታ ለምን እንደተፈጠረ ከማስረዳትና መፍትሔ ከመሻት ይልቅ የሚሆን የማይሆነውን በመናገር በተለይም ወጣቱ ሀቁን ከውሸት እንዳይለይ ለማድረግ በቅተዋል፡፡ ዛሬም እያደረጉ ነው።
በመሠረቱ የምሁሮች ዋና ተግባር አንድ ኅብረተሰብ ዝብርቅርቅ በሆነና በተበላሸ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ከሆነ ዝም ብሎ ማየትና በችግሩ ላይ ሌላ ችግር መጨመር ሳይሆን ለእነዚህ ሁኔታዎች ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ማጥናትና መፍትሔ መሻት ነው። በተለይም በመንግሥትና በአገዛዙ፣ እንዲሁም በውጭ ኃይሎች ግፊት ተግባራዊ የሚደረጉትን የፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፖሊሲዎች በመመርመርና የሚያስከትሉትን ኅብረተሰብዓዊና ባህላዊ ጠንቆች ለሰፊው ሕዝብ በማሳየትና የተሻለ አማራጭ በማቅረብ የሕዝባቸው አለኝታ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው። ይሁንና ግን ምሁሩ ለሕዝብና ለአገር ጠበቃ ከመሆን ይልቅ በዓለም ኮሙዩኒቲው አማካይነት ተግባራዊ የሚሆነውን የኢኮኖሚም ሆነ ሌላ ፖሊሲዎች ዝም ብሎ የሚመለከት ከሆነ ለሚፈጠረው ምስቅልቅል ሁኔታ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ተጠያቂው እሱም ጭምር ነው። ዝም ብሎ የሚመለከት ምሁር ደግሞ ራሱን ነፃ ያላወጣና በራሱ ፍላጎት የሚገዛ ሳይሆን በውጭ ኃይሎች የሚጠመዘዝና እነሱን የሚያመልክ ነው። ስለሆነም እንደዚህ ዓይነቱ ምሁራዊ ኃይል ታላቁ የጀርመን ፈላስፋ ኢማኑኤል ካንት እንደሚለው ‹‹በፍላጎቱና በማሰብ ኃይሉ የማይገዛ ነው፤ ሰው መሆኑንም የሰረዘ ነው፤›› እንደዚህ ዓይነቱ ምሁር ኅብረተሰብዓዊ ጥቅምን ከማምጣትና አገር ከማስከበር ይልቅ ብሔራዊ ውርደትን ነው የሚያስከትለው።
ከዚህ ስንነሳ ባለፉት ሀምሳና አርባ ዓመታት የደረሱት አሰቃቂ ድርጊቶች፣ እንዲሁም ድህነትና ረሃብ ተስፋፍተው የአገራችን መለያዎች መሆናቸው የሚያመለክተው የምሁሩንም ድክመት ነው። ሰፋ ባለና በተወሳሰበ ዕውቀት እንዲያስብ ሆኖ ያልተዘጋጀው ምሁራዊ ኃይል፣ በተለይም እንደ ኢኮኖሚክስ የመሳሰሉትን ትምህርቶች ከአንድ አንፃር ብቻ በማየትና የአገራችንን ችግር ወደ ጠያቂነትና አቅራቢነት ብቻ (Demand and Supply) በመቀነስና የገበያ ኢኮኖሚ የተወሳሰበውን የኅብረተሰብዓችንን ችግር መፍቻ አድርጎ በመመልከቱ፣ ለተመሰቃቀለው የአገራችን ችግርና ለድህነትም መስፋፋት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠያቂ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አብዛኛው ምሁር ወይም የተማርኩ ነኝ የሚለው የሚያደላው ወደ ፖለቲካ ብቻ ነው። የፖለቲካ ጉዳይንም የሚመለከተው ሥልጣንን ከመጨበጥ አንፃር ብቻ ስለሆነ ፖለቲካ የሚባለው ግዙፍ ጽንሰ ሐሳብና ሳይንስ ከሌሎች የኅብረተሰብ ጥያቄዎች፣ ከፍልስፍና፣ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ እንዲሁም ከማኅበራዊና ከኢኮኖሚ ጥያቄዎች ተነጥሎ በመታየቱ የኅብረተሰብዓችንን ችግር መፍቻ መሆኑ ቀርቶ መፋለሚያና ግራ አጋቢ መሣሪያ ሊሆን በቅቷል።
ከዚህም ባሻገር ሕዝባችን ግራ የተጋባው በምሁራኑ ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ ነን በሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶችም ጭምር ነው። በመጀመርያ ደረጃ ተቃዋሚ ነኝ የሚል መደራጀቱንና ከሕዝብ ጋር ግንኙነት እንዳለው ማረጋገጥ መቻል አለበት። በየቀበሌው፣ በየወረዳዎችና በክፍለ አገር ከተማዎችና በመንደሮችም ጭምር ሰፋ ያለ የአደረጃጀት መዋቅር እንዲኖረው ያስፈልጋል። ተቃዋሚ ነኝ የሚል ድርጅት በምን ዓይነት ራዕይ ወይም ርዕዮተ ዓለም እንደሚመራ ማሳየት አለበት። ሥልጣን ላይ ካለው አገዛዝ በምን እንደሚለይ ለሰፊው ሕዝብ ማሳየት አለበት። ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና የሥነ ልቦና ችግሮች ካሉና ጎልተው የሚታዩ ከሆነ ምክንያቶቻቸውንና እንዴትስ ደረጃ በደረጃ መፈታት እንደሚችሉ መመርመርና መፍትሔ ማቅረብ አለበት። በተለይም ከውጭ የሚመጡ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በማጥናት፣ ተግባራዊ በሚሆኑበት ጊዜ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ኅብረተሰብዓዊ ጠንቆች ለሰፊው ሕዝብ ማስተማርና የተሻለም መፍትሔ ማቅረብ አለበት። እያንዳንዱ ድርጅት ወይም ፓርቲ የራሱ የሆነ የአገርንና የዓለምን ሁኔታ የሚዳስሱ ሳምንታዊ ጋዜጣና በየወሩ የሚታተምና ሰፋፊ ሀተታዎችን የያዘ መጽሔት ያስፈልገዋል። የፖለቲካ ድርጅቶች ጋዜጣዎችና መጽሔቶች የየፓርቲዎችን ራዕይ ማሳያዎችና ማንነታቸውንም የሚገልጹ ናቸው። በዚህ መልክ ያልተደራጀና ራዕይ የሌለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በመሠረቱ ሕዝብን ግራ ከማጋባት በስተቀር ለአገራችን የተወሳሰቡ ችግሮች እንደ አማራጭ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም። አገራችንም በፀና መሠረት ላይ እንድትገነባ የማድረግ ኃይልና ብቃትም ሊኖረው አይችልም።
ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ምድር ከመቶ በላይ የሚሆኑ ተደራጀን የሚሉ ‹‹ፓርቲዎች›› አሉ። ሁኔታውን ለሚከታተለው እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች ከረዥም ጊዜ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ጥናት በኋላ ማኅበራዊና የኅብረተሰብ ጥያቄዎችን በማንሳትና በማጥናት የተወለዱና ታንፀው የወጡ አይደሉም። በፓርቲ ደረጃ ተደራጀን የሚሉ ሁሉ በተለይም ባለፉት 28 ዓመታት በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነውን የኒዎሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲና ጠንቁን በማጥናትና በመጻፍ ሕዝቡን፣ በተለይም ወጣቱን ለማስተማር የሞከሩ አይደሉም። ስለሆነም በሀብታምና በደሃ መካከል ሰፊ የገቢ ልዩነት ሲፈጠርና አብዛኛው ሕዝብ ወደ ድህነት ዓለም ሲወረወር ዝም ብሎ የሚመለከቱ እንጂ ድምፃቸውን በማሰማትና በመጻፍ የሕዝብና የአገራችን ጠበቃ መሆናቸውን አላረጋገጡም። በተለይም አገራችን የአካባቢ ውድመት ሲደርስባት፣ ጫካዎች ሲመነጠሩ፣ ወጣቱን የሚያበላሹ ብልሹ ነገሮች ሲስፋፉ፣ የዕፅ ሱሰኛ እንዲሆን ሲደረግ፣ የተራድኦ ድርጅቶች የሚባሉት በመስፋፋት የአገራችንን እሴቶች ሲያፈራርሱ፣ ከተፈጥሮና ከኅብረተሰብ ሕግ ውጭ የሚሆኑ የሕንፃ አሠራሮች ሲሠሩ ዝም ብሎ በመመልከት የአገራችንን ውድመት ማፋጠን ችለዋል ማለት ይቻላል። ስለሆነም ግራ የተጋባው ሕዝብ አልፎ አልፎ የሚጠይቀው ጥያቄ እንደዚህ ዓይነቱ ተቃዋሚ ነኝ የሚል ኃይል ለምንድን ነው የሚያስፈልገው? ለምንድን ነው ግራ የሚያጋባን? እያለ ነው። የተቃዋሚው ኃይል ችግር ልክ እንደ አገዛዞቻችንም በውጭ ኃይሎች ላይ ያለው አመለካከት የተዛባና በጥናት ላይ የተመሠረተ አይደለም። አብዛኛው ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል የውጭ ኃይሎች ለአገራችን ዕድገትና መረጋጋት ጠንቅ መሆናቸውን በፍፁም የተረዳ አይመስልም። በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተዋቀረውን ዓለም አቀፋዊ የሚሊተሪ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ኃይል አሠላለፍና፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲዎች አማካይነትም በደካማ አገሮች ውስጥ በመግባትና ተፅዕኖ በማድረግ የሚፈጠሩትን ኅብረተሰብዓዊና ማኅበራዊ ውዝግቦች በደንብ ያላጠና ወይም ያልተረዳ በመሆኑ የካፒታሊስት አገሮችን እንደ ተፈጥሮአዊ አጋርና ዕርዳታ ሰጪ አድርጎ ነው የሚመለከታቸው። በሌላ አነጋገር ተቃዋሚው ኃይል ዛሬ በዓለም ላይ የሚታዩት የኢኮሎጂ ቀውሶች፣ የፖለቲካ ውዝግቦች፣ የማኅበራዊ ሁኔታዎች መናጋትና የአፍሪካ መንግሥታትም ችግሮችን መፍታት አለመቻል ወዘተ. ዋናው ምክንያት ካፒታሊዝም ልቅ በሆነ መልክ በዓለም አቀፍ ደረጃ መስፋፋቱን የሚቀበል አይደለም። ስለሆነም ተቃዋሚው ኃይል የዓለም ኮሙዩኒቲው የየአገሮችን ባህልና የተፈጥሮ ሁኔታ እንዲሁም የመንግሥታትን አወቃቀርና የሰፊውን ሕዝብ ሥነ ልቦና ሳያገናዝብ ተግባራዊ እንዲሆኑ ግፊት የሚያደርጋቸው ፖሊሲዎች አገራችን ውስጥ ለተከሰቱትና በጉልህ ለሚታዩት ቀውሶች ዋናው ምክንያት መሆኑን በፍፁም አይቀበልም። ለማመንም በፍፁም አይፈልግም። በአብዛኛው ተቃዋሚ ኃይል እምነት የውጭው ኃይል ከበስተጀርባው የሚያውጠነጥነው ምንም ተንኮል የለውም።
አጠቃላዩን የአገራችንን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የባህልና የሥነ ልቦናዊ ቀውሶች ስንመለከት የሕዝቡ ግራ መጋባት የሚያስደንቀን ሊሆን አይችልም። በአንድ በኩል አንድ አገዛዝ 28 ዓመታት ያህል ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበርና ከእነሱ ዕርዳታ በማግኘት አገርን ሲያተራምስና የአንድ ትውልድ ዕድል ብቻ ሳይሆን፣ የሁለትና የሦስት ትውልድ ሕይወት ሲያበላሽ ዝም ብሎ መመልከት የሕዝባችንን የንቃተ ህሊና ሁኔታ ያሳያል። በሌላው ወገን ደግሞ ምሁሩ ይህ ዓይነቱን የትውልድ ጠንቅ ዝም ብሎ መመልከቱና ለሕዝብ ጠበቃ ሆኖ አለመነሳቱን ስንመለከት የእሱንም የፖለቲካ ንቃተ ህሊና ደረጃ መጠየቃችን የማይቀር ነው። መማር ማለት ዝም ብሎ ማየት ወይም መቀበል አይደለም ብለን የምናምን ከሆነ የትምህርቱንም ይዘትና በአጠቃላይ ሲታይ የአገራችንን የኅብረተሰብ አወቃቀርና የሥነ ልቦና ሁኔታ የግዴታ መጠየቅ አለብን። እንደ ማኅበረሰብና እንደ ኅብረተሰብ መኖር አለብን የምንል ከሆነ ዛሬ ካለንበት ሁኔታ ባሽገር ማየት ያለብን ይመስለኛል። በምድር ላይ የሚታዩትን ምስቅልቅል ነገሮችና በየቦታው የሚካሄዱትን የእርስ በርስ ጦርነቶች ትችታዊ በሆነ መልክ መመልከትና መመርመር መቻል አለብን። ምክንያቶቻቸውን ለማወቅ የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ አለብን። አሁን ባለን አመለካከትና የማሰብ ኃይል ወደፊትም የምንገፋ ከሆነ በእርግጥም የአገራችንን ውድመት ማፋጠናችን የማይቀር ጉዳይ ነው። የግራ መጋባትና ዝም ብሎ የማየት ውጤት የመጨረሻ መጨረሻ መጥፋት ነው። እንደ ኅብረተሰብና እንደ ማኅበረሰብ አለመኖር ነው። ከዚህ በመነሳት ነው ከአንድ ዓመት ጀምሮ ይካሄዳል የሚባለውን ‹‹ለውጥ›› መመርመር የሚያስፈልገው። ይህ በአዲሱ የገዥ ኃይልና በብዙዎቻችንም ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘው ለውጥ የሚባለው ነገር በእርግጥስ እንደሚነገርለት ለውጥ ነው ወይ? ኅብረተሰብዓችን ከገባበት ማጥ ውስጥ ሊያወጣው ይችላል ወይ? በዚህ ዓይነቱ ‹‹የለውጥስ ሒደት›› የአገራችን መሠረታዊ ችግሮች ደረጃ በደረጃ ሊፈቱ ይችላሉ ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች ጠጋ ብለን እንመርምር።
ለመሆኑ በኢትዮጵያ ምድር ለውጥ እየተካሄደ ነው ወይ?
በመጀመርያ ደረጃ ለውጥ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት። ለውጥ ማለት አንድ ነገር ከነበረበት ሁኔታ ወደ ሌላ ነገር ሲለወጥ ተለውጧል ወይም ተቀይሯል ማለት ይቻላል። አንድ የጥሬ ሀብት ውስጣዊ ይዘቱ (Chemical Composition) ሳይቀየር፣ በኃይል (Energy)፣ በሰው የማሰብና የጉልበት ኃይል፣ እንዲሁም በማሽን ድጋፍ ከነበረበት ሁኔታ ለሰው ልጅ ጥቅም ወደ ሚያገለግል ፍጆታ ከተለወጠ ይህንን ለውጥ ብለን እንጠራዋለን፡፡ በዚህ መልክ የምንመገባቸው፣ የምንለብሳቸው፣ የምንጠቀምባቸው የረዥምና የአጭር ጊዜ ዕድሜ ያላቸው ነገሮች በሙሉ የተለወጡና ወደ ቀድሞ ሁኔታቸውም ሊመለሱ የማይችሉ ናቸው። ራሳቸውም ዛፎችም ሆነ ሰዎች በተወሰነ የተፈጥሮ ሕግ አማካይነትና በዲያሌክቲካል ሒደት ነው ከነበሩበት ሁኔታ በመለወጥ ዛሬ የምናየው ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት።
ወደ ኅብረተሰብም ስንመጣ ይህንን ዓይነቱን ክንውናዊ ሁኔታ እንመለከታለን። ልክ እንደ ጥሬ ሀብትም ኅብረተሰብዓዊ ክንዋኔና ለውጥ በሰው የማሰብ ኃይል ማኑፕሌት በመሆን ነው ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊሸጋገርና ሊቀየር የሚችለው። አንድን ኅብረተሰብ ሙሉ በሙሉ በዕቅድ አማካይነት መለወጥ ባይቻልም መልክና ሥርዓት ማሲያዝ የሚቻለው በማሰበ ኃይል አማካይነት ብቻ ነው። እነዚህም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ሲሆኑ የለውጡም ዓይነትና ውስጠ ኃይል (Dynamism) ማግኘት በአንድ አገር ውስጥ በሰፈነው ዕውቀትና ምሁራዊ ኃይል፣ እንዲሁም መንግሥታዊ አወቃቀር ይወሰናል። መንግሥትና በልዩ ልዩ ሙያ የሠለጠኑ ምሁራዊ ኃይሎች የተገለጸላቸው (Enlightened) ከሆኑ አንድ ኅብረተሰብ ጥበባዊና ፍትሐዊ በመሆን ለተከታታዩ ትውልድ የሚተላለፍ ይሆናል። ቴክኖሎጂና ሳይንስ ዋናው የሀብት ማመንጫ ዘዴዎች መሆናቸውን በመረዳት አነሰም በዛም የተረጋጋና ሰላም የሰፈነበት አገር መመሥረት ይቻላል።
ይሁንና ግን በኅብረተሰብ ታሪክ ውስጥ እንደታየው አንድን ኅብረተሰብ መለወጥ ወይም ዘመናዊ ለማድረግ አንድን የጥሬ ሀብት ወደ ፍጆታ ነገር እንደ መለወጥ ቀላል አይደለም። የሰው ልጅ ጭንቅላት የተወሳሰበና አፈንጋጭ ስለሆነ ውስጡ ከተዋቀረውና ከለመደው አስተሳሰብ ቀይሮ አርቆ አሳቢ ለማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነው። በተለይም ደግሞ አንድ የተወሰነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሚሊተሪያዊ አወቃቀር ከተዘረጋና የተወሰኑ ሰዎች እሱን በመጠቀም ፍላጎታቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉ ከሆነ የነበራቸውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታ (Economic and Social Status) ላለማጣት ሲሉ መሰናክል ይፈጥራሉ። በዚህ ላይ ደግሞ አንድ ዓይነት ርዕዮተ ዓለም ጭንቅላታቸው ውስጥ ከከተቱ የበላይነታቸውን ላለማጣት ሲሉ ወደ ኃይል የሚያመዝኑበት ጊዜ አለ። ከዚህም በላይ በተለያዩ ድሮች ከውጭው ዓለም ጋር የተሳሰሩ ከሆነ አንድ ላይ በማበር ወደ ውስጥ ፍትሐዊ አስተዳደርና ጥበባዊ የሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓትና ጠንካራ አገር እንዳይገነባ መሰናክል ይፈጥራሉ። የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠርና በቡድን በመደራጀት የተወሰነው የኅብረተሰብ ክፍል ከመሠረታዊ ጥያቄና ፍላጎት እንዲያፈነግጥ ያደርጋሉ። የሰው ጭንቅላት በማያስፈልግ ነገር እንዲጠመድ በማድረግ የራሳቸውን ጨዋታ ይጫወታሉ። የሚሆን የማይሆን ነገር በመፍጠር በአንድ ድርጅትም ሆነ በአንድ አገር ውስጥ በሕዝብ መካከል አለመተማመን እንዲፈጠር ያደርጋሉ። አንድ ሕዝብ ኃይሉን ሰብሰብ አድርጎ ለአንድ ዓላማ እንዳይነሳ የማይሆን ነገር ይነዛሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ አንድ ሕዝብና አዲስ የወጣት ትውልድ ለውጥ እያለ ከፍተኛ መስዋዕትነት ቢከፍልም የመጨረሻ መጨረሻ ሥልጣን በሌላ ኃይል በመያዝ የለውጡ ፍላጎት ደብዛው ይጠፋል። ይህንን ጉዳይ የጥቢው አብዮት በመባል በሚታወቀው በቱኒዚያና በግብፅ እንዲሁም በሊቢያ የተካሄደውንና ምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የምንመለከተው ሀቅ ነው። በተለይም ከመጀመርያውኑ በሳይንስ፣ በቲዎሪና በፍልስፍና የማይመረኮዝና ዓላማውም የማይታወቅ ትግል የመጨረሻ መጨረሻ እንደሚከሽፍ የታወቀ ጉዳይ ነው። ለማንኛውም ከአንድ ዓመት ጀምሮ በአገራችን ምድር ይካሄዳል ስለሚባለው ለውጥ አንዳንድ መሠረታዊ ነገሮችን እንመልከት፡፡ ለውጥ ሲባል ታች በተዘረዘሩት መልክ የሚታይና የሚካሄድ መሆን አለበት። ለውጥ ሲባል፣ ከታች ወደ ላይ የሚያድግ (Organic Growth) ነው፣ ሁለገብ (Holistic) መሆን አለበት። ፖለቲካዊ፣ መንግሥታዊ፣ የተቋማት፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የከተማና የመንደሮች ግንባታንና ሌሎችንም አንድን አገር እንደ አገር የሚያስቆጥሩትን ነገሮች ሁሉ የሚያጠቃልል ነው። ተከታታይነት (Sustainable) ያለው መሆን አለበት። በመንፈሳዊ ተሃድሶና በእውነተኛ ዕውቀት የሚደገፍና የሚመራ መሆን አለበት። ሰፊውን ሕዝብ ያሳተፈና ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም የሚሆን መሆን አለበት። አገር አቀፍ በሆኑ ተቋማት (Institutions) የሚመረኮዝ መሆን አለበት። እነዚህም ዘመናዊና የተቀላጠፉ ተቋማት መሆን አለባቸው፡፡ በየጊዜው በአዳዲስ የሥልጠና ዘዴዎች መሻሻል አለባቸው። የአገርን፣ የሰውና የጥሬ ሀብቶች የሚያንቀሳቅስና በራስ መተማመን (Selfreliance) የሚያዳብርና የሚደገፍ መሆን አለበት። ማንኛውም ሕይወት ያለው ነገር አትክልትንም ጨምሮ ውስጥ ባላቸው ኃይል የማደግ ችሎታ አላቸው። የውጭው ሁኔታ አጋዥ ነው። ለምሳሌ ዘር ሲዘራ ባለው ውስጣዊ ኃይል ሥርን፣ ግንድንና ቅጠላ ቅጠሎችን ያበቅላል። ከዚያም በኋላ ፍሬ ይሰጣል። ፀሐይ፣ ዝናብና ሚኒራሎች አጋዦች ናቸው። ሲበዙ ግን አትክልት የማፍራት ኃይላቸው ይቀንሳል ወይም ይሞታሉ።
ለውጥ ሲባል በመጀመርያ ደረጃ የሕዝብን መሠረታዊ ፍላጎቶች ማለትም፣ የተሟላ ምግብን፣ መጠለያን ወይም ቤትን፣ ሕክምናን፣ ትምህርትና ንፁህ ውኃን ማግኘትንና ሌሎች እንደ ልብስ የመሳሰሉትን የሚያካትትና የሚያሟላ መሆን አለበት፡፡ እነዚህን ማሟላት የማይችል ለውጥ አይባልም። ለውጥ ሲባል ትናንሽና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በማቋቋምና በማኑፋክቸር በመደገፍ ሕዝባዊ ወይም ብሔራዊ ሀብት የሚዳብርበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄድ መሆን አለበት። እውነተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በኒዎሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት አይደለም፡፡ ዓይነተኛ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በመንግሥት የተደገፈ ሁለገብ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲሆን ብቻ ነው። ስለሆነም እውነተኛ ለውጥ የውጭ ኃይሎችን ወይም የዓለም ኮሙዩኒቲውን ጣልቃ ገብነት የሚፃረር ነው። የመንግሥት መኪና ሙሉ በሙሉ ከመጨቆኛ መሣሪያነቱ ሲላቀቅና የሕዝብ አለኝታ የሆነ መንግሥታዊ መዋቅር ከተዘጋጀ ስለለውጥ ማውራት ይቻላል። ስለሆነም እንደዚህ ዓይነቱ መንግሥት ከውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ሙሉ በሙሉ የፀዳ ሊሆን ይችላል። ይህ ዓይነቱ አገዛዝ ፍትሐዊነትን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያበስር መሆን አለበት። እውነተኛ ለውጥ በግለሰብዓዊ ነፃነትና ተሳስቦ በመኖር የሚገለጽ ሲሆን፣ አርቲፊሻል የሆነ የብሔረሰብና የማንነት ጥያቄዎች ለመሠረታዊ ለውጥና ለሥልጣኔ ጠንቆች ናቸው። አንድ አገር ሁለንታዊ በሆነ መልክ እንዳያድግ የሚያግዱ ናቸው። የነፃነትን ብርሃን የሚያጨልሙ ናቸው።
ከነዚህ መሠረታዊ ሐሳቦች ስንነሳ ነው አንድ ዓመት ያህል በአገራችን ምድር ለውጥ እየተካሄደ ነው የሚባለውን አነጋገር መመርመር ያለብን። በእርግጥ ዶጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ከጨበጡ ጀምሮ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ለመፈታት ችለዋል። የእነዚህ ሰዎች መፈታት በሕዝብ ግፊትና ትግል፣ እንዲሁም በብዙ መስዋዕትነት የተገኘ ድል ነው። የአገዛዙ ቡራኬ አይደለም፡፡ አገዛዙም በድሮው መልኩ ሊቀጥል እንደማይችል የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም ይህንን የመሳሰለውን የእስረኞችን መልቀቅና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት መፈቀዱ በሕዝብ ተጋድሎ የተገኙ ውጤቶች ናቸው። ይሁንና አጠቃላዩን የፖለቲካ ሁኔታ ስንመለከት በተለይም 28 ዓመታት ያህል ሕዝብን ሲገድሉ፣ አገርን ሲያተራምሱ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት፣ ብሔረሰብን ከብሔረሰብ ጋር ሲያጋጩና የአገርን እሴት ባፈራረሱት ላይ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ዕርምጃ አልተወሰደም። በተጨማሪም የመንግሥቱ መኪና ለጊዜው ጋብ እንዲል የተደረገ እንጂ ከመጨቆኛ ባህሪው በመላቀቅ ዴሞክራሲያዊ ባህሪ ሲላበስና የሕዝብ አለኝታ እንዲሆን ሲዋቀር አይታይም። ሕዝብን ሲገድሉና ሲያሰቃዩ የነበሩ አንዳንዶቹ ከነበሩበት ቦታ ወደ ሌላ በመቀየር በሌላ መልክ ሥራቸውን እየሠሩ እንደሆነም የምንገነዘበው ሀቅ ነው።
በብዙ አገሮች ውስጥ አርጀንቲና፣ ቺሌና ብራዚል ድረስ እነዚህ አገሮች ከወታደራዊ አገዛዞች ወደ ሲቪል አገዛዝ ቢሸጋገሩም እስካሁን ድረስ በትርምስ ዓለም ውስጥ የሚገኙበት ዋናው ምክንያት በመንግሥት መኪናውና በፖለቲካው አወቃቀር ላይ መሠረታዊ የሆነ መሻሻል ባለመታየቱ ነው። በኅብረተሰብ ታሪክ ውስጥ መንግሥታዊ አወቃቀር ሥር ነቀል በሆነ መልክ ባልተሻሻለበት ወይም ለውጥ ባልተደረገበትና ባልተካሄደበት አገር ሰፋ ያለ ብሔራዊ ኢኮኖሚ መገንባትና የባህልም ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል የታወቀ ጉዳይ ነው። ‹‹ዓሳ መጠንባት የሚጀምረው ከራሱ ላይ ነው›› እንደሚባለው አነጋገር የፖለቲካና የመንግሥት ጥያቄ መሠረታዊ በሆነ መልክ እስካልተፈታ ድረስ የተወሳሰቡት የአገራችን ችግሮች በፍፁም ሊፈቱ አይችሉም። በሌላ ወገን ደግሞ የአገራችንን የመንግሥት መኪና አወቃቀር ስንመለከት በተለይም ከ1940ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ የተዋቀረው መንግሥታዊ መኪና ኢቮሊሽናዊ [ዝግመታዊ] በሆነ መልክ ከታች ወደ ላይ ከአገር ግንባታና ከሕዝብ ፍላጎት አንፃር በመታየት በተገለጸላቸው ሰዎች የተገነባ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ነበረበት። ስለሆነም ይህ ዓይነቱ መንግሥታዊ አውቃቀር ከፊዩዳላዊ ሥርዓቱ ጋር በመቀናጀት ለዕድገትና ለነፃነት እንቅፋት እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህም ባሻገር ኢኮኖሚው ውስጠ ኃይሉ ደካማ ስለነበር አዳዲስና የተገለጸላቸው ኃይሎችንና ምሁራንን በማፍራት በመንግሥቱ መኪና ላይ ግፊት ማድረግ አይቻልም ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳ ነው የየካቲቱ አብዮት ሊከሽፍ የቻለው። በአንፃሩ ራሳቸውን ችለው ወደ ሥልጣን ላይ የመጡ ኃይሎች፣ እንደ ሶቪየት ኅብረትና ቻይና የመሳሰሉ አገሮች ውስጥ አብዮቱ ከሞላ ጎደል ሊሳካና እነዚህም አገሮች ወደ ኃያል መንግሥትነት ሊለወጡ የቻሉት የመንግሥቶቻቸውን መኪናዎች ደረጃ በደረጃ ዘመናዊ በማድረግ ወይም በመለወጣቸው ነው። በተጨማሪም የነዚህ አገሮች የመንግሥት ተቋማት በውጭ የስለላ ኃይሎች አልተተበተቡም። ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደረግበትና አንድ ሰው ለውጭ ኃይሎች ሰላይ በመሆን አገርንና መንግሥትን የሚበድል ሥራ ከሠራና ከተያዘ በሞት ይቀጣል። እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ ደግሞ በልዩ ዘዴ ትክክል ተደርጎበት ይገደላል።
ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የዶ/ር ዓብይ አገዛዝ የመንግሥቱን መኪና ራዲካል በሆነ መንገድ ሊለውጥ የማይችልበት ሁኔታ አለ። በመጀመርያ ደረጃ የውጭው ኃይል ግፊት አለ። የውጭው ኃይል በእንደዚህ ዓይነቱ ለዕድገት ጠንቅ በሆነ የመንግሥት መኪና አማካይነት ነው ድህነቱና የሰላም ዕጦቱ እንዲራዘም የሚያደርገው። ምሁሩና ተቃዋሚው ኃይል ስለመንግሥት መኪናና ዴሞክራሲያዊ ባህሪ ስለመላበሱ ጉዳይ ይህንንም ያህል የተገለጸላቸው አይደሉም። የመንግሥት መኪና እንደ ታቦት የማይነካና የማይሻሻል ተደርጎ ነው የሚቆጠረው። ይህንን ትተን ወደ ኢኮኖሚ ጥያቄዎች ስንመጣ የዶ/ር ዓብይ አገዛዝ አሁንም ቢሆን ሕዝባችንን ካደኸየውና አገራችንን ካተራመሰው የኒዎሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለመላቀቅ አልቻለም። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ እውነተኛ ብሔራዊ ሀብትን ሊፈጥር በሚችል የፖለቲካ ኢኮኖሚ ፖሊሲና ድህነትን በሚፈለፍል የኢኮኖሚ መካከል ያለውን ልዩነት አገዛዙም ሆነ የፖሊሲ አውጭዎች የተረዱ አይመስለኝም። በሌላ ወገን ደግሞ የኢኮኖሚ ቲዎሪንና ፖሊሲን አስመልክቶ በአገራችን ምሁራን ዘንድ ምንም ዓይነት ውይይት አይካሄድም። የኢኮኖሚ ችግሮች በገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ብቻ ነው ሊፈቱ የሚችለው የሚለው አስተሳሰብ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘ ይመስላል። ስለሆነም የሚወራው ስለጂዲፒ ማደግና አለማደግ ነው እንጂ ድህነትን ስለመቅረፍና በምንስ ፖሊሲ አማካይነት ነው? ብሔራዊ ኢኮኖሚ መገንባት የሚቻለው በሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ላይ ውይይት ሲካሄድ አይታይም። ምሁሩም ሆነ መንግሥት ሕዝቡ በማይገባው ቋንቋ ነው የሚያወሩት። ሕዝባችን ስለጂዲፒ ማደግና ስለዶላር መጥፋትና አለመጥፋት ሳይሆን የሚያስበው እንዴት አድርጌ ከድህነት ልወጣ እችላለሁ? እያለ ነው ሌት ተቀን የሚያስበው። ልጆቼንና ራሴን ምን ነገር ነው የምመግበው? እያለ ነው የሚጨነቀው። የትስ አድራለሁ? ከቤቴስ ነገ እፈናቀላለሁ ወይ? በማለት ነው የሚያወጣውና የሚያወርደው። ስለሆነም የመንግሥት ዋና ተግባር ለሕዝብ በማይገባው ቋንቋ መናገርና በማይሆን ነገር ላይ መረባረብ ሳይሆን በቀላሉ ሊገባውና ችግሩን በሚያቃልልለት ጉዳይ ላይ ነው መረባረብ ያለበት።
ከዚህ ስንነሳ የአገዛዙ ግራ መጋባት ይህንን ያህልም የሚያስገርመን አይደለም። አገዛዙ በውጭ ኃይሎች ወይም ኤክስፐርቶች እየተመከረ የሚያካሂደው ፖሊሲና የመንግሥትን ሀብት ወደ ግል ማዘዋወር በመሠረቱ የሰፊውን ሕዝብ የድህነት ዘመኑን የሚያራዝም እንጂ የሕዝባችንን መሠረታዊ ችግሮች ሊፈታ የሚችል አይደለም። አብዮት ያካሄዱ አገሮችንና በመንግሥት ጣልቃ ገብነት አማካይነት መሠረታዊ ለውጥ የታየባቸውን አገሮች ሁኔታን ስንመለከት እነዚህ አገሮች በሙሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አላካሄዱም። እንደ ቻይና የመሳሰሉት አገሮች ከኋላ መያዝ የሚለውን ስትራቴጂና በራስ መተማመን የሚለውን ፖሊሲ በመከተል ነው የኋላ ኋላ ለገበያ ኢኮኖሚ ለውጥ የሚሆኑ መሠረቶችን ሊያዘጋጁ የቻሉት፡፡ ታውቆም ይሁን ሳይታወቅ በዚህ ዓይነቱ ሰፊውን ሕዝብ በማንቀሳቀስ ስትራቴጂና የኢንዱስትሪ ተከላ አማካይነት ነው፣ ቻይና ከድህነትና ከረሃብ ልትላቀቅና ዛሬ ደግሞ ወደ ኃያል መንግሥትነት ለመሸጋገር የምታመራው፡፡ ቻይና እዚህ ዓይነት ደረጃ ልትደርስ የቻለችው ሌሎች አገሮችን በመለመንና በዕዳ በመተብተብ ሳይሆን በራስ በመተማመን ብቻ ነው። የሰሜን ኮሪያም ዛሬ ባልስቲክ ሚሳይል መሥራት የቻለችው በቁጭትና በራስ በመተማመን ነው። አሜሪካኖች በከፈተቱ ጦርነት ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ አልቋል። አገሪቱ እንዳለ ወድማ ነበር። ከዚህ አሳዛኝ ሁኔታ በመነሳት ነው የተወሳሰቡ ቴክኖሎጂዎችን መሥራት የቻለችው። በአብዮቱ ጊዜ የተሟላ የማሽን ኢንዱስትሪና የመሣሪያ ፋብሪካ ለኢትዮጵያችን ለግሳለች። ጃፓንም ሆነ ጀርመን ቀደም ብለውም ሆነ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ወደ ሁለገብ የአገር ግንባታና የቴክኖሎጂ ዕድገት መሸጋገር የቻሉት በተጠና የመንግሥት ጣልቃ ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ነው እንጂ በእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና (IMF) በዓለም ባንክ በመምከርና በውጭ መዋዕለ ንዋይ አማካይነት አይደለም። በአውሮፓ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ውስጥ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ አሜሪካና ጀርመን በሌላ የውጭ ከረንሲ በመመካትና በመበደር አይደለም፣ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊጎናፀፉና ዓለምን ለመቆጣጠር የቻሉት። በዘመኑ ዶላርና ዩሮ የሌሎች አገሮችን ዕድገት አጨናጋፊ መሣሪያዎች ናቸው። ማታለያ መሣሪያዎች ናቸው። ውስጣዊ ዋጋ (Intrinsic Value) የላቸውም። በታሪክና በአገር ግንባታ ውስጥ በዕዳና በዕርዳታ ተመክቶ ያደገ አገር የለም። ታላላቅ ሥልጣኔዎች በሙሉ ዶላርና ዩሮ ከመፈጠራቸውና የዓለም ንግድ መገበያያ መሣሪያዎች ከመሆናቸው በፊት ተመሥርተዋል። ከተማዎች፣ ካቴድራሎችና መስጊዶች እንዲሁም ቤተ መንግሥቶች ተገንብተዋል። የዕደ ጥበብ ሥራዎችና ንግድ በየአገሩ አብበዋል። እነዚህ ሁሉ የተገነቡትና ማደግ የቻሉት ቀስ በቀስ ማደግ ከጀመረው የውስጥ የሥራ ክፍፍል ጋር ተያይዞ ካደገው የአገር ውስጥ ገንዘብ ጋር በመተሳሰር ነው። ስለሆነም ዶላርና ዩሮ የተዘበራረቀ ሁኔታ ከመፍጠርና ድህነትን ከማራዘም በስተቀር ሥርዓት ወዳለው ጥበባዊ ወደ ሆነ የአገር ግንባታ ሊያሸጋገሩን በፍፁም አይችሉም።
የምዕራብ አውሮፓን፣ የጃፓንን፣ የደቡብ ኮሪያን፣ የሶቪየት ኅብረትን፣ ዛሬ ደግሞ የሩሲያን፣ የሲንጋፖርንና የአንዳንድ አገሮችን የተስተካከለና የተሟላ የኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲ ስንመለከት ከታች ወደ ላይና ከላይ ወደ ታች በጣልቃ ገብ ፖሊስ አማካይነት ነው፣ እዚህ ዓይነቱ ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት። የጀርመንን ሁኔታ ስንመለከት፣ ጀርመን ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ስኬታማ ውጤት ልታመጣ የቻለችው በመጀመርያ ደረጃ መሠረታዊ የሕዝብ ፍላጎቶች ከተመለሱ በኋላ ነው። ሰፊውን ሕዝብ መንገድ ላይ እንዲጣል በማድረግና በጎጆ ቤት ውስጥ እንዲኖር በማድረግ አይደለም፣ የአንድን አገር ኢኮኖሚ በጠንካራ መሠረት ላይ ሊገነባ የሚችለው። በአገራችንና በብዙ አፍሪካ አገሮች ውስጥ ያለው የአስተሳሰብ ግድፈት የኢኮኖሚ ጉዳይ ከሕዝብ ፍላጎት ጋር ለመያያዝ ባለመቻሉ ነው። የሚተከሉት ኢንዱስትሪዎችም ሆኑ ተግባራዊ የሚሆነውም የእርሻ ፖሊሲ የውጭ አገሮችን ፍላጎት ለማርካት እንጂ በተቀዳሚ የሕዝባቸውን ፍላጎት ለማርካት አይደለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ አገዛዞች የፕላንቴሽን ኢኮኖሚ በማካሄድ ድህነቱና መዘበራረቁ እንዲራዘሙና ሕዝብም እንዲናቅ በማድረግ ላይ ናቸው። በተጨማሪም ሆቴል ቤቶችን በመሥራት ከፍተኛ ሀብት ይወድማል። አንድ አገር ወደ አስረሽ ምችነት እንድትለወጥ ትደረጋለች። ይህ ማለት ግን ጊዜውን ጠብቆ እንደ አስፈላጊነቱ ሆቴል ቤቶች አይሠሩ ማለት አይደለም። ሕዝብን ሜዳና ቆሻሻ ውስጥ እየጣሉ ሆቴል ቤቶችን መሥራት ከፍተኛ ወንጀል ነው። የሥልጣኔና የዕድገት ምልክት ሳይሆን የኋላ ቀርነት ምልክት ነው። የዚህ ሁሉ ዋናው ችግር የአገራችን አገዛዞች ሥልጣን ሲይዙ በመጀመርያ ደረጃ ዋናው ዓላማቸው ምን እንደሆነ አለመታወቁ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ለተወሳሰቡት ችግሮች መነሻዎቻቸው ምንድን ናቸው? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ጥናት ስለማይካሄድ ነው። ስለሆነም የዶ/ር ዓብይ አገዛዝ ከተሳሳተ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት (Macroeconomic Imbalances) በመነሳት ነው የአገራችንን የተወሳሰበ ችግር ለመፍታት የሚቃጣው፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ዓይነቱ መዛባት የመሠረታዊ ኢኮኖሚው አወቃቀር (Strucctural Crises) ነፀብራቅ (Manisfestation) ነው እንጂ በራሱ ለቀውሱ ዋና ምክንያት አይደለም። የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ኮሙዩኒቲው የአንድን አገር የኢኮኖሚ አወቃቀር በተሳሳተ መልክ ነው የሚረዱትና የሚያነቡት፡፡ በአስተሳሰባቸው ውስጥ ኅብረተሰብዓዊ አወቃቀርና የፖለቲካ ኃይል አሠላለፍ (Social Formations and Political Power Relationships) የሚባል ነገር የለም። እነዚህ ነገሮች ድህነትን በመፈልፈልና ኋላ ቀርነትን በማፈርጠም የሚኖራቸውን ሚና በፍፁም አይገነዘቡም፡፡ ስለዚህም ድህነትና ኋላ ቀርነት ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ስለሆነም የዓለም የገንዘብ ድርጅት የሚባለውና የዓለም ኮሙዩኒቲው አዳዲስ አገዛዞችን በማሳሳትና ጫና በማድረግ ቀውሱ ጥልቀት እንዲያገኝና የመፍቻ ዘዴም እንዳይገኝለት ያደርጋሉ። ይህን ዓይነቱን ፖሊሲ ከ60 ዓመታት በላይ ተግባራዊ ሲያደርጉ የቆዩበትና የበላይነታቸውም መግለጫ ስለሆነ የግዴታ ድህነትና አጠቃላይ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ስለሆነም አገዛዙ ከዚህ ዓይነቱ ድህነትን ፈልፋይ ከሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እስካልተላቀቀ ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛ ነፃነቱን ሊቀዳጅ በፍፁም አይችልም።
በአጭሩ የዶ/ር ዓብይ አገዛዝ ከላይ የዘረዘርኳቸውን 13 መሠረተ ሐሳቦች ሊያሟላ የሚችል አገዛዝ አይደለም፡፡ ስለለውጥ ያለውም አስተሳሰብ የተዛነፈና ኢሳይንሳዊ ነው። የአገራችንን ብሔራዊ ነፃነት የሚያስከብርና ሕዝባችንም እውነተኛ ነፃነትን የማግኘት ኃይሉ እየመነመነ ይሄዳል ማለት ነው። ስለሆነም ነው የዶ/ር ዓብይ አገዛዝ በዓለም አቀፍ ኮሙዩኒቲው ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘውና ተስፋ የሚጣልበት አገዛዝ እየተባለ የሚወደሰው፣ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ደፍ ደፍ በማለቱና ድህነትን ለመጨረሻ ጊዜ ከአገራችን ምድር ለማስወገድ ባለው የተወሳሰበ ስትራቴጂ አይደለም የሚመሠገነው። መሠረታዊ ለውጥ የማምጣት ፍላጎት ያለው ኃይል ቢሆን ኖሮና ፍንጭም ቢያሳይ እንደ ታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ዘመቻና ዛቻ ይካሄድበት ነበር። ለማንኛውም በአገራችን ምድር መሠረታዊ ለውጥን ማምጣትና አለማምጣት መቻል በዶ/ር ዓብይ አገዛዝ ላይ ብቻ የሚሳበብ አይደለም። የዶ/ር ዓብይ አገዛዝ ከድሮዎች አገዛዞች በተለይም ከወያኔ አገዛዝ የወረሳቸው የተወሳሰቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ቀውሶች አሉ። እነዚህ ቀውሶች ከአገዛዙ አቅም በላይ የሆኑ ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም ለዚህ ዓይነቱ አስቸጋሪ ሁኔታ የተዘጋጀን አይደለንም። ከመጮህና ከመተቸት በስተቀር አማራጭ የሆነ ሁለገብ ፖሊሲ አዘጋጅተን ማቅረብ አልቻልንም። አንዳንዶቻችን ከመንግሥቱ ጋር ተለጥፈን ዝም ብለን መጓዝን የመረጥን አለን። ሌሎች ደግሞ ከመተቸትና የማይሆን ጥያቄ ከማቅረብ በስተቀር ያለውን ችግርና ምንጩን በመረዳት መሰረታዊ የሆነ መፍትሄ ሲያቀርቡ አይታይም። ይህም ማለት ያለው ድክመት በሁላችንም ዘንድ ነው። ስለዚህ ችግሩ ሁላችንን የሚመለከትና አዲስ አስተሳሰብ እንድናፈልቅና እንድናዳብር የሚጋብዘን ነው ማለት ነው። ከዚህ በመነሳት ሰሞኑን የተወረወሩ አንዳንድ ሐሳቦችን በመዳሰስ ጽሑፌን ለመደምደም እፈልጋለሁ።
ተስፋ የሚጣልበት ወይም የከሸፈ መንግሥት (Failed State)!
ሰሞኑን በሁለት ግዙፍ ምሁራንና የአገራችን ተቆርቋሪ ነን በሚሉ ሁለት ጽሑፎች ለንባብ ቀርበው በተለይም በውጭው ዓለም የምንኖረውን ኢትዮጵያዊያኖች ግራ አጋብተውናል፡፡ ሁለቱም ዶ/ር ዓብይ ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ አገር ቤት በመግባት አንዳንድ ቦታዎችን ያዩና በውይይትም ሆነ በጥናት የተሳተፉ ናቸው። አንደኛው የዶ/ር ዓብይን አገዛዝ የከሸፈ ነው ሲል፣ ሌላው ደግሞ ተስፋ የተጣለበትና በዓለም አቀፍ ኮሙዩኒቲውም ሆነ በታወቁ ጋዜጦች ተቀባይነትን ያገኘና የሚወደስ ወጣት መሪ ነው በማለት የጦፈ ክርክር ተካሂዷል። ሁለቱም አቅራቢዎች አስተያየታቸውን በቲዎሪም ሆነ በኢምፔሪካል ደረጃ ሳያረጋግጡና መቋጠሪያ ሳይሰጡ ነገሩን ዘግተውታል። ሁለቱም ተቃራኒዎች የአሜሪካን ቲፎዞዎችና በአሜሪካ የበላይነት የሚያምኑ ናቸው። በመሠረቱ የሚያጣላቸው ነገር አልነበረም። ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስና ፕሮፌሰር አል ማርያም በመባል የሚታወቁና ብዙ መጣጥፎችንም ለንባብ ያቀረቡና የሚያቀርቡም ናቸው።
ከሻለቃ ዳዊት እንነሳ። ሻለቃ ዳዊት ጥቂት ሳምንታት ኢትዮጵያ ውስጥ ከቆየ በኋላ ያየውንና ለማንበብ የቻለውን አሜሪካ ከተመለሰ በኋላ የዶ/ር ዓብይን አገዛዝ የከሸፈና ፀጥታንም ማስጠበቅ ያልቻለ መንግሥት ወይም አገዛዝ ነው በማለት ይከሰዋል። የላይ ላዩን ሲታይ ይህ ውንጀላ ትክክል ነው ብሎ መቀበል ይቻላል። ይሁንና ሻለቃ ዳዊት የዶ/ር ዓብይ አገዛዝ የከሸፈ አገዛዝ ነው ሲል ያላያቸውና ለማየትም ያልቻላቸው አያሌ ጉዳዮች አሉ። አንድ መንግሥትና አገዛዝ ምን ምን ነገሮች ሲጎድሉት ነው የከሸፈ አገዛዝ የሚባለው? ምን ምን ነገሮች ሲሟሉ ነው ያልከሸፈስ ወይም የተሳካለት አገዛዝስ ተብሎ ሊወደስ የሚችለው? በተጨማሪም ይህ ሁኔታ እንዴት ሊከሰት ቻለ? ከመቅጽበት ወይስ እየተከማቸ የመጣ? በአገዛዙ ብቻ የተፈጠረ ወይስ የውጭ ተፅዕኖ ያለበት? የሚሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች በማንሳት አላስተማረንም እንድንወያይም አላደረገንም። ለማንኛውም የሻለቃ ዳዊትን ጽሑፍ ላነበበ ሰውየው ንፁህ በንፁህ መልክ የሚሊታሪ ሰው እንደሆነና ከሚሊታሪ ሎጂክ አንፃር እንደተመለከተው መረዳት ይቻላል። ይህም ማለት አጻጻፉና አመለካከቱ እንዲሁም ግንዛቤው ለአንድ ኅብረተሰብ እንደ ማኅበረሰብ ለመያያዝና ለመጠንከር የሚያስፈልጉትን ሰፋ ያለና በሳይንስና በቴክኖሎጂ እንዲሁም በማኑፋክቸር ላይ የተመሠረተን አገር እንደ መነሻ ወይም እንደ መነፃፀሪያ አድርጎ በመውሰድ አይደለም ሊያስተምረን የተነሳው። በዚህም ምክንያት የተነሳ የሰውን ልጅ ምንነትና በተሟላ የነፃነት ዓለም ውስጥ መኖርን እንደ አስፈላጊና ይህም ጉዳይ የአንድ አገር መንግሥት መሠረታዊ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ አይደለም የአገዛዙን ድክመት የሚነግረን፡፡ ከዚህም በላይ ስለተቋማት አስፈላጊነት በፍፁም አላነሳም። በተቋማትና በብቃትነታቸው አማካይነት ብቻ ነው፣ በአንድ አገር ውስጥ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሊመጣ የሚችለውና መረጋጋትም የሚኖረው።
እንደሚታወቀው ወይም ደግሞ ምናልባት አንዳንዶቻችን ጥናት አድርገን እንደሆን፣ የዛሬው አስቸጋሪ ሁኔታ ወይም የውድቀት ጉዳይ ዛሬውኑ በዶ/ር ዓብይ የአንድ ዓመት አገዛዝ ዘመን ከመቅጽበት የተፈጠረ አይደለም። ጉዳዩ የብዙ መቶ ዓመታት ታሪክ ያለው ሲሆን፣ የአገራችን አስቸጋሪ የኅብረተሰብ አወቃቀር ታሪክ ነፀብራቅ ነው ማለት ይቻላል። በተለይም የዛሬው ያልተሳካለት መንግሥት ጉዳይ መሠረቱ የተጣለው አፄ ኃይለ ሥላሴ ከስደት ከተመለሱና ሥልጣንን ከጨበጡ በኋላ ነው ማለት ይቻላል። በጊዜው የኢትዮጵያ መንግሥት መኪና ዘመናዊና ፊዩዳላዊ በሆኑ የአሠራር ዘዴዎች የሚገለጽ ነበር። ዘመናዊ የሚባለው በአዲስ አበባ ብቻ ላይ የተስፋፋ ሲሆን፣ በአብዛኛው ክፍለ አገሮች ውስጥ ዘመናዊ ተቋማት ያልነበሩና ሰፊው ሕዝብም ካለምንም አጋር የሚኖር ነበር ማለት ይቻላል። በአፄው የአገዛዝ ዘመን የነበረውን የአዲስ አበባንም ሁኔታ ስንመረምርም የተዘበራረቀና ተቋማትም ያልተሟሉ ነበሩ። የከተማው ዕቅድና የተቋማቱ ጉዳይ የተዘበራረቀው የኢኮኖሚ ነፀብራቆች ናቸው ማለት ይቻላል። ይህም ማለት የአፄው አገዛዝ በ20ኛው ክፍለ ዘመን አንድ መንግሥት ለአገሩ ማድረግ የሚገባውን የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የባህላዊ፣ የሥነ ልቦናና ሌሎች ለአንድ ኅብረተሰብ የሚያስፈልጉ ተቋማትን መዘርጋት ያልቻለና ምንም ያልታየው ነበር። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ አንዳንድ የረዥም ጊዜ ታሪክ ያላቸው የእስያ አገሮች ካለፉት ሥርዓቶች በመማርና ሰፋ ያለ ተቋማትን በመዘርጋትና በየጊዜው የመሻሻልን አስፈላጊነት በመረዳት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ፣ በዚያው ዘመን የአፄው አገዛዝ ይመካ የነበረው ንፁህ በንፁህ በወታደሩና በፀጥታ ኃይሉ ብቻ ነበር። ወደ ገጠርና ወደ ክፍለ አገር ከተማዎችም ስንሄድ የተዘበራረቁ ሁኔታዎችና ፊዩዳላዊ ሥርዓቶች እንደነበሩ እንረዳለን። በዚህም ምክንያት የተነሳ የአፄው አገዛዝ የሰፊው ሕዝብ ጉዳይ የማያገባውና የአንድን መንግሥት መሠረታዊ ተግባሮች ያልተረዳ ነበር ማለት ይቻላል። በየጊዜው በተደጋጋሚ የተከሰተውን ረሃብና በገጠሮችና በአንዳንድ ከተማዎች የተስፋፋውን ድህነትና የሴተኛ አዳሪነት እንደ አሸን መፍለቅ ስንመለከት በጊዜው የአፄው መንግሥትም የከሸፈ መንግሥት (Failed State) ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። የአፄው አገዛዝ ከፍተኛ የሆነ የርዕዮተ ዓለም ተቀባይነት ቢኖረውምና የሚመለክም አገዛዝ ቢሆንም አገዛዙና ሚኒስተሮቹ ከሕዝብ እርቀው የሚኖሩ ነበሩ። ሌላውን ትተን የኢኮኖሚና የእርሻ ሚኒስትሮች በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር የሕዝቡን አኗኗርና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን የሚያጠኑና ምን ምን ነገሮች መደረግ እንዳለባቸው ጥናት እንዲደረግ ትዕዛዝ የሚሰጡና የሚከታተሉ አልነበሩም። ከዚህ አጭር ሀተታ ስንነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱ የሆነ መንግሥትና አገዛዝ አልነበረውም። ዝም ብሎ ብቻ አንገቱን ደፍቶ የሚኖርና አምላክ ሆይ ደህና ቀን አምጣልኝ ብሎ የሚጸልይና የሚለምን ሕዝብ ነበር። እንደዚህ ዓይነቱን አገርና ሕዝብ ነው አፄውና አገዛዛቸው ጥለውልን የሄዱት።
ይህንን ጉዳይ አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ ከሞላ ጎደል ለማረም አንዳንድ የጥገና ለውጦች በመወሰድ ተፎካካሪ የመንግሥት መዋቅሮች ተተክለው ነበር። ገበሬውና ሠራተኛው በሙያ ማኅበሩ መደራጀት፣ የቀበሌ ማኅበራት መቋቋምና የሴቶችና ወጣቶች መደራጀትና ሐሳባቸውን መግለጽ፣ ሰፊውን የገጠር ኗሪ ሕዝብ ለማስተማር የተደረገው ዘመቻና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በገጠር ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሰማራትና ቀስ በቀስ የፊዩዳሉ ሥርዓት መንኮታኮት የሚያረጋግጡት በጊዜው አገራችን ወደ ተሻለ ዘመናዊነት በመሽጋገር ላይ እንደነበረች ነው። ይህ ዓይነቱ ለውጥ በውስጥና በውጭ ኃይሎች የተቀነባበረ ሴራ ሊከሽፍና አገራችንም የጦር አውድማ ለመሆን በቅታለች። በዚህ ዓይነቱ አገርን የማፈራርስ ሴራ ውስጥ በጊዜው አንዳንድ ለአሜሪካ ያደሩ ወጣት መኮንኖችም ተሳትፈውበታል። ወያኔም እንዲገባ ሁኔታውን አመቻችተውለታል።
ከዚህ ስንነሳና እነ ወያኔ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ተግባራዊ የሆነው የክልል አስተዳደር ለዘመናዊና ለተቀላጠፈ ተቋማት መቋቋም አመቺ ሁኔታ እንዳይፈጠር አግዷል። በየክልሉ ዋና ከተማዎች ምሁራዊ እንቅስቃሴ መዳበር አልቻለም። የየክልሉ አስተዳዳሪዎች ራሳቸውን ከማደለብና ሀብት ከመዝረፍ በስተቀር የሥራ ክፍፍል እንዲዳብር ለማድረግ አልቻሉም። በአንፃሩ በተለይም በኦሮሚያ ክልል የተስፋፋው የአበባ ተከላ አካባቢውን ሊያደቀው ችሏል። ድህነትና ውድቀት ሥር ሊሰዱ ችለዋል። በአጭሩ ያልተገለጸላቸው የየክልሉ አስተዳዳሪዎች አካባቢዎቻቸውን ዘመናዊና የሠለጠነ ማድረግ አልቻሉም። ሰፋ ያለ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲዳብር ማድረግ አልቻሉም። የባህል ማዕከሎችም በማቋቋምና በተለይም ወጣቱን በማስተማር የሕዝቡ የማሰብ አድማስ እንዲሰፋና እንዲዳብር ለማድረግ አልቻሉም። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በሌለበት ደግሞ ተቋማትን መመሥረት አይቻልም። ተቋማት በሌሉበት ቦታ ደግሞ ሕዝቡ የሚመካበት ነገር ስለማይኖረው በቀላሉ ለአደጋ መጋለጡ የማይቀር ግዴታ ነው። ወጣቱም በሙያ ሥልጠናና በሥራ እስካልተወጠረ ድረስ በቀላሉ የልዩ ልዩ ነገሮች ሰለባ መሆኑ የማይቀር ጉዳይ ነው። ይህ በራሱ ደግሞ ለጽንፈኛ ኃይሎች አመቺ ሁኔታን ይፈጥርላቸዋል። በአጭሩ የዶ/ር ዓብይ አገዛዝ የከሸፈ ነው ወይም ማስተዳደር አልቻለም ስንል ይህ ሁኔታ እንዴት እንደተፈጠረ ደረጃ በደረጃ ማጥናትና የተሻለ ሐሳብም መሰንዘር አለብን። ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ነገሩን ከብዙ ሁኔታዎች አንፃር ሳይመለከትና ሳይመረምር የሰነዘረው አስተያየት ሳይንሳዊ ግንዛቤ የሚጎድለው ነው። አቀራረቡ አሳሳች ነው። ለአገር ተቆርቋሪ ነኝ ብሎ ለማስመሰል የተጻፈና በሰፊው እንዳናስብና ስሜታዊ እንድንሆን የሚጋብዘን ነው።
የፕሮፌሰር አል ማርያም አቀራረብ ደግሞ እንመልከት። ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረ ማርያምም እንደ ሻለቃ ዳዊት አንዳንድ ቦታዎችን ተመልክቷል። ከሻለቃ ዳዊት ይልቅ ፕሮፌሰር አልማርያም ከዶ/ር ዓብይ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው። በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከሻለቃው ለየት ባለ ሁኔታ እንዲመለከተው ተገዷል። በእሱ እምነትም የዶ/ር ዓብይ አገዛዝ የከሸፈ አገዛዝ ሊባል የሚችል አይደለም። ኢትዮጵያ በታሪኳ ውስጥ መልካም ራዕይ ባለውና በዓለም ኮሙዩኒቲው ዘንድ ተቀባይነትን ባገኘ ወጣት መሪ የምትመራ አገር ነች ብሎ የተቀበለና የሚያምን ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ በዓለም ላይ አሉ የሚባሉ ጋዜጦች ሁሉ ዶ/ር ዓብይን ያደንቁታል በማለት ለማረጋገጥ ሞክሯል። ለተቀሩትም የአፍሪካ አገዛዞች ምሳሌ ለመሆን የበቃና ተፅዕኖም ሊያሳድር የሚችል ነው የሚል እምነት አለው።
በመሠረቱ እንደዚህ ዓይነቱ አባባል ከአንድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሚጠበቅ አጻጻፍ አይደለም። አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና ብዙ መጽሐፎችን ያነበበ በሌሎች የሚመራና እነሱን እንደ ምስክርነት መውሰድ ያለበት ሳይሆን፣ በራሱ ህሊና የሚገዛ መሆን አለበት። በምድር ላይ የሚታዩትን ነገሮችና አገዛዙ ተግባራዊ ሊያደርጋቸው የሚፈልጋቸውን ፖሊሲዎች መመርመር አለበት። የአገዛዙን ርዕዮተ ዓለም መመርመር አለበት። ከዚህም በመነሳት የሚታዩትን ችግሮች በምን ዓይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለመቅረፍ እንደተነሳ ማጥናት አለበት። በአጠቃላይ ሲታይ ብሔራዊ አጀንዳውንና ራዕዩን ማጥናት አለበት። ከዚያ በኋላ የራሱን ግምገማ መስጠት ይችላል። ይህንን ሳያደርግ የዝምብላችሁ ተቀበሉ አጻጻፍ የአምባገነንነትን ባህሪ ያሳያል። እኔ ምሁር ስለሆንኩ ከእኔ በላይ ማንም የሚያውቅና ፍርድም የሚሰጥ ስለሌለ ሁላችሁም አፋችሁን ዝጉ የሚል አጻጻፍ ነው ፕሮፌሰሩ ያስነበበን። ያም ተባለ ይህ፣ የፕሮፌሰሩ ዋና ድክመት አንድን መሪ እንደ ሙሴ ማየቱ ነው። እሱ ብቻ ነው ችግሩን መፍታት የሚችለው ብሎ ማመኑ ነው። በሌላ ወገን ግን ፕሮፌሰሩ የአገራችንን ሁኔታ ወረድ ብሎ በየቆሻሻ ቦታዎች ያሉትን ሁኔታዎች እየተዘዋወረ ቢያጠናና እዚያው አንድ ሁለት ቀን ቢያድር ኖሮ ምናልባት የችግሩን ውስብስብነት ሊገነዘበው በቻለ ነበር። ቤተ መንግሥት ገብቶና አድሮ ሲወጣ የሚኖር አስተያየት ሁል ጊዜ ሚዛናዊ ፍርድ ለመስጠት ያስቸግራል፡፡ የወያኔ አፍቃሪ ፈረንጆችም አዲስ አበባ ሄደው አገዛዙ ሸራተንና ሌሎች ዘመናዊ ሆቴል ቤቶች ውስጥ ጋብዟቸው ሲመለሱና የኢትዮጵያን ሁኔታ ሲጠየቁ ይሰጡን የነበረው መልስ አገሪቱ በጣም ተለውጣለች፤ ድህነትም በጣም ቀንሷል በማለት ነበር፡፡ በዚህ መልክ አብዛኛው ሕዝብ በድህነት ዓለም ቢኖርም አንዳንድ ሰዎች ከራሳቸው ምቹ ሁኔታና አቀባበል በመነሳት ሌላውም ሰው እንደ እነሱ ተመችቶትና ተደስቶ የሚኖር ይመስላቸዋል።
በአጭሩ የሁለቱን ምሁሮች አቀራረብ ስንመለከት አጻጻፋቸው ሶፊስቲያዊ ነው። ኃይል ያለው ትክክል (Might is Right) ነው የሚለውን የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምን የአመጽ ፖለቲካ የሚያንፀባርቁ ናቸው። አስተሳሰባቸው በእሱ ሎጂክ ውስጥ የተዋቀረ ነው። ወደ ውስጥ በመግባት በአገራችን ውስጥ የተፈጠረውን አስቸጋሪ ሁኔታ በመቃኘት አይደለም ሁለቱም ምሁሮች ብሶታቸውንና ደስታቸውን የሚጽፉልን። ሁለቱም የአገራችንን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህል ዕድገትና አወቃቀር በዲያሌክቲካዊ መነጽር በማየት የዛሬው ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ ሊያስረዱን በፍፁም አልቻሉም። እንደ ሌሎች አብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮችም ኢትዮጵያም የግሎባል ካፒታሊዝም መስዋዕት መሆኗን የተገነዘቡ አይደሉም። ስለ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ፣ የሚሊታሪና የኢኮኖሚ አወቃቀር ያላቸው አስተያየት ግልጽ አይደለም። በተለያየ ጊዜ ሥልጣንን የተቀዳጁ አገዛዞች በኢምፔሪያሊዝምንና በግሎባል ካፒታሊዝም ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሚሊታሪያዊ አወቃቀር ውስጥ በመካተት እንደሚታሹና ሕዝቦቻቸውም የድህነት ሰለባ እንደሆኑ በፍፁም የተገነዘቡ አይመስልም። ይህንንና የአገራችንን አስቸጋሪ የኅብረተሰብ ታሪክ ሒደት ነው ሻለቃ ዳዊትም ሆነ ፕሮፌሰር ገብረ ማርያም ሊመለከቱና ሊገነዘቡ ያልቻሉት፡፡ የአንድን አገር ተጨባጭና የፖለቲካ ሁኔታ በሳይንስና በንድፈ ሐሳብ በመደገፍ መተንተን ካልቻልን የግዴታ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ነው የምንደርሰው፡፡
መደምደሚያ
የአገራችን ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው። ድክመቱ የሁላችንም ነው። ዛሬ የምናየው የተወሳሰበ ችግር እየተደራረበ የመጣ ነው። በተለያዩ ጊዜያት አገራችንን ይገዙ የነበሩ ኃይሎች ተግባራዊ ያደረጓቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ሕዝባችንን የሚያስተሳስሩ አልነበሩም። የሳይንስንና የቴክኖሎጂን፣ የተቋማትን መገንባት፣ የከተማዎችን ጥበባዊ በሆነ መልክ መሥራት፣ የሥራ ክፍፍል መዳበርና በተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች መካከል መተሳሰር ያለባቸው መሆናቸውን ለመገንዘብ ባለመቻላቸው አገራችንና ሕዝባችንን አዝረክርከውና አድክመው ሄደዋል። የብሔራዊ ውርደት አከናንበውናል። ሰፋ ያለና በራሱ የሚተማመን ምሁራዊ ኃይል እንዳይዳብርና የሕዝባችንና የአገራችን አለኝታ እንዳይሆን ለማድረግ በቅተዋል። አገዛዞቻችን በራሳቸው ዓለምና ለራሳቸው የሚኖሩ እንጂ ከሕዝባቸው ጋር የሚያስተሳስራቸው አንዳችም ነገር አልነበረም። ስለሆነም ሕዝባችንን አደንቁረውና በውስጥ ኃይሎች እንድንቦረቦርና እንድንዳከም አድርገውን ሄደዋል። ይህ በራሱ ደግሞ ለዚህኛው ወይም ለዚያኛው የውስጥ ኃይል የመንቀሳቀሻ መድረክ በመፍጠር ከውስጥ ጦርነት አውጀውብናል። ብሔራዊ ስሜት እንዳይዳብርና በአንድነት ተነስተን ጠንካራ አገር እንዳንመሠርት ተደርገናል። ከዚህ ስንነሳ ሁኔታውን በሌላ የምሁራዊ መነጽር መመልከትና መመርመር ያለብን ይመስለኛል። አገር ልትፈርስ ነው እያሉ መጮኽ በራሱ የሚያመጣው ጥቅም ምንም ነገር የለም። ጭንቅላታችንን በአዲስ ምሁራዊ አስተሳሰብ እስካላነጽንና እስካላደስን ድረስ የአገራችን ሁኔታ ከመቶ ዓመት በኋላም በዚህ መልክ መቀጠሉ የማይቀር የታሪክ ግዴታ ነው። አሁን ባለን አመለካከትና ጩኸት ለሕዝባችንና ለአገራችን ፋይዳ ያለው ነገር ልንሠራ አንችልም። የጨለማውንና የድህነቱን ዘመን ከማራዘም በስተቀር አዲስ ኢትዮጵያን ልንገነባና ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ አንችልም።
ዋናው አስቸጋሪ ነገር በሁላችንም ዘንድ ያለው እጅግ ወደ ኋላ ቀር አስተሳሰብ ነው። ጭንቅላታችንን በኋላ ቀር አስተሳሰብ በመወጠሩ የተነሳ የነገሮችን ዕድገትና ውስብስብነት እንዳናይ ተገደናል። በዚህ ላይ ያልተገለጸላቸውና ፊውዳላዊ የሆኑ ኃይሎችና አክቲቪስቶች የፖለቲካውን መድረክ በመያዛቸው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠርን ሕዝብንና ወጣትን እያታለሉ ነው። የፖለቲካው ሜዳ ሁሉም እንደፈለገው የሚዋኝበት ሆኗል። ሁሉም ለአገር ተቆርቋሪ ነኝ ባይ ነው። እዚያው በዚያው ደግሞ የውጭ ኃይሎችን የሚማጽን ነው። የርዕዮተ ዓለም ጥራት የሌለውና አገራችን በምን ምን መሣሪያዎች መገንባት እንዳለባት የተገለጸለት አይደለም። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ግልጽ አስተዋጽኦ ማበርከት በፍፁም አይቻልም። ደቀ መዝሙሮችን ማፍራትም አይቻልም። በተለይም በውጭ ኃይሎች የሚደገፉትንና የሚንቀሳቅሱትን መቋቋም በፍፁም አይቻልም። እነዚህ ኃይሎች ህልማቸው የውጭ ኃይሎችን ጥቅም ማስጠበቅ ስለሆነ በአገራችን ምድር እውነተኛ ነፃነትና ብልጽግና እንዳይመጣ አጥብቀው የሚታገሉ ናቸው። በዚህ ዓይነት ያልተስተካከለ ትግል ውስጥና፣ አብዛኛው ደግሞ ከዕውቀት ይልቅ የላይ ላዩን የሚጋልብ ከሆነ ስለ አገርና አንድነት መጠበቅ ማውራት በፍፁም አይቻልም። ጥያቄው ይህንን ሁኔታ እንዴት መስበር ይቻላል? ነው። ስለሆነም ለዚህ መልስ መፈለግ ያለብን ይመስለኛል። መልካም ግንዛቤ!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡