Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጠማማው በዛና ቀና ከየት ይገኝ!

ሰላም! ሰላም! በትግል ያልተገኘ ሰላም ከሽንፈት ይብሳል ነው የሚባለው? ነው  ወይስ ድሎቻችን ነፃነትን ብቻ የተመለከቱ ነበሩ? ግራ ስጋባ እኮ አንዳንዴ የምናገረውን አላውቅም። እናም ግራ ገብቶኝ ምሁሩን የባሻዬን ልጅ ባዋየው፣ ‹‹ሊጠቀልለን ከነበረው ቅኝ ገዥ ስንፋለም የውስጡን ጉልበተኛ ኮትኩተን እያሳደግን የዕፎይታ እንጂ የሰላም ጊዜስ አልነበረንም፤›› አይለኝ መሰላችሁ? ዕፎይ አልኳ ወዲያው። መቼ የጭንቁ ጊዜ እንደሚመጣ አይታወቅማ እንዳባባሉ። እስኪ ከአንዳንድ አባባል እየራቃችሁ፡፡ ከአባባል ብቻ ሳይሆን ከአንዳንድ ነገረኞች ጭምር። ምን ላድርግ ብላችሁ ነው? የወገኔን ንቃተ ህሊና የማያዳብር ከንቱ ነገር እንዳያጠፉ ቀና አስተሳሰብ ላይ የዘመቱ በዝተዋላ። አጃኢብ! በፈጣሪ ይሁንባችሁና ኮሎኒያሊስት ወራሪን ዓድዋ ላይ በጨበጣ ውጊያ ድባቅ የመምታት ጀግንነትና ብልኃት የነበረን ሰዎች፣ እንዲያው ቢያቅተን ቢያቅተን ለፍሬከርስኪ አሉባልታዎች እናንሳለን? እስኪ አስቡበት። ታዋቂነት በስም ማጥፋት የሚገኝ የሚመስላቸው ከንቱዎች በዙ እኮ፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ከንቱዎች በዝተው የሚጠቅሙ ሲመናመኑ ያሳዝናል፡፡

ለነገሩ ይኼ የሚያሳየው ከቀደምት ወራሪ ጠላቶቻችን እኩል ዛሬ አጠገባችን ያሉት የእኛው የሆኑት ሲባል፣ እንዲሁ ዋዛ እየመሰለን መሸወዳችን ይደንቀኛል። ከቴም ዋዛ! እንዴት? እንዴት ማለት ጥሩ። እንደምታውቁት አገራችንን ተፈጥሮ ከለገሳት መልካም የአየር ንብረት (እሱም ዕድሜ ማራዘሚያ ካልተበጀለት ያከተመለት ይመስላል) በነፃ ከምንስበውና ከምናስወጣው ‘ኦክስጂን’ በቀር በነፃ አይደለም በሳንቲም፣ ሦስቴ ጎርሶ ማደር አሁንም ህልም ነው። ዛሬም ድርቅ ያደርቀናል። የኑሮ ውድነቱ ያንገበግበናል፡፡ ሰላማችን እየተቃወሰ ምርታማ መሆን እያቃተን ነው፡፡ ስለዚህ. . . ልብ አድርጉ . . . ዛሬ በአጋጣም ብንጠግብ ነገን በጥርጣሬ እናያለን። ታዲያ ከወጣቱ ትውልድ ይልቅ ‘ኢንቨስት’ ማድረግ የሚቀናን ተራ ነገር ላይ ቢሆን ምን ይገርማል? በአጭሩ በቃ ምን ልበላችሁ የዕፎይታ ጊዜያችንን በአግባቡ ሳንጠቀምበት የቀረነው በራሳችን ችግር ይመስለኛል። ጥፋትን እናስተምራለን እንጂ ልንማረው ኖሯል? ‘ክፋትን’ ማለቴ ነው ወገኖቼ!

ከየት ወዴት ነበርን? እሺ በቃ ቅጥልጥሎሹን እንተወውና የተበጣጠሰውን እናገጣጥመው። ሰሞኑን ከወደ አሜሪካ የሚደወልልኝ የስልክ ጥሪ ልነግራችሁ አልችልም። አጫውቻችሁ እንደሆነ እንጃ እንጂ ይህች አሜሪካ በደካማ ጎናቸው እየገባች ያገተችብኝ ብዙ አብሮ አደግ ወዳጆቼን ነው። ይደውላሉ አላነሳም። ‹‹እነዚህ ሰዎች ዛሬም ና ሊሉኝ ነው?›› እያልኩ ሲጠራ ሳይለንት፣ ሲጠራ ሳይለንት። ኋላ ማንጠግቦሽ ናት፣ ‹‹እባክህ በሰላም አይመስለኝም የጨቀጨቁህ አንሳላቸው፤›› ብላ ወተወተችኝ። ‹‹ተያቸው አሁን የሰሞኑን መያዣ መጨበጫ የሌለው ወሬ ሰምተው ‘መጥተህ አሳይለም ጠይቅ’ ሊሉኝ ነው። ርቆ ስለተራራው ማውራት እንደሆነ ጫፉን እንደመንካት ያለ ስሜት አለው፤›› አልኳት። የምሬን እኮ ነው። አንዳንዴ ግን የእኔም ጥርጣሬ ልክ ያለው አይመስልም፡፡

እኛ ድሮ የሠፈር ጉልቤ ሲያስቸግረን የምናደርገውን አታስታውሱም? ሲበቃ ይበቃላ። ስለዚህ ተሰብስበን መጀመርያ በየት በየት ሮጠን ቤት እስክንደርስ የሚፈጅብንን ጊዜ፣ ቀኑን ሙሉ ዲስኮ ሰዓታችንን አሥር ጊዜ እያየን ስንዘጋጅ እንውላለን። መሮጫ መንገዱን ብቻ ሳይሆን ፍጥነትን መትሮ ጠላትን ማጥቃት እንለው ነበር። አይ ልጅነት። ዛሬም በስተርጅና እዚያው የጠላትና የወዳጅ ሽኩቻ ውስጥ መኖራችንን ሳስብ ይገርመኛል። ብቻ የማንጠግቦሽ ውትወታ ሲበዛብኝ ‹‹ሃሎ!›› አልኩ። እንጃ በቅጡ የእግዜር ሰላምታ የሰጡኝ ከአምስቱ ሁለቱ ብቻ ናቸው። ሳነሳላቸው፣ ‹‹አንበርብር መጪው ጊዜ አይታወቅም። ይኼውልህ እንደታሰበው ሳይሆን ዶናልድ ትራምፕ እንደገና ካሸነፈ በቃ ማቄን ጨርቄን ሳልል ከች ስለምል ከአሁኑ ቤት እያፈላለግክ ሰንብት፤›› አሉኛ አንዱ በአንዱ ላይ። ትናንት፣ ‹‹መጥተህ አሳይለም ጠይቅና . . . ፈታ ብለህ ኑር’ ስትሉኝ አልነበረም ወይ? ‘ዩ ኤስ አሜሪካ ኢዝ አሜዚንግ’ ምናምን የት ተቀበረ?›› ብላቸው ‘ካርድ’ ምናምን ብለው ስልኩን ይዘጋሉ። አያድርስ አሉ ባሻዬ ነገር እንዳሁኑ የተገለበጠ ሲመስላቸው!

የነገርኳችሁ ወዳጆቼ በጠቅላላ በሕገወጥ መንገድ አሜሪካ እንደገቡ አውቃለሁ። ግን ከዚያ በላይ የማውቀው አሜሪካ የብዙኃን እናት ከየት ለምን ወዴት ሳትል፣ የነገሯትን አምና የሆዷን በሆዷ ይዛ ‘ዋናው የሰው ዘር መሆናችሁ ነው’ ብላ፣ ሁሉን ዕድል ሰጥታ ተንከባክባ መያዟን ነበር። ታዲያ አሁን ምን ተፈጠረ? ስከንፍ ሄጄ የባሻዬን ልጅ፣ ‹‹ይኼ ዶናልድ ትራምፕ በቢንላዲን የተተካ አሸባሪ ነው?›› ስል ጠየቅኩት። ‹‹ኧረ ተው። ማን ነው እንዲያ ያለህ? ወሳኙ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እኮ ነው፤›› ብሎ ተገረመብኝ። አንዳንዴ እኮ ደላላ መሆን ጉዳቱ እዚህ ላይ ነው። የባሻዬ ልጅ ብዙ መረጃ ስለሰውዬው ካስጨበጠኝ በኋላ ግን፣ ዳግም ከተመረጠ እንኳን እዚያ እዚህም በሰላምና በነፃነት መኖር የምችል አልመስልህ አለኝ። በቀደም ዕለት የሰሜን ኮሪያን መሬት ሃያ ዕርምጃ ተራምዶ ገባ ሲሉኝ፣ ይኼ ሰውዬ ነገረ ሥራው አልገባ ብሎኝ እቆዝማለሁ፡፡ ወዳጆቼ የእኛ ነገር ግራ ቢያጋባኝ እኮ ነው አትላንቲክን በሐሳብ ተሻገሩ የምለው፡፡ ሌላ ዓላማ የለኝም፡፡

በተያያዘ ነገር ብዬ ስቀጥል (ነገር እንጂ ዜና ሲያያዝ የማይመስጠን ስለበዛን) ከአሜሪካ ለጉብኝት ወደ እናት አገራቸው ኢትዮጵያ የመጡ ወጣቶች ለሦስት ወራት የሚያርፉበት ‘ግራውንድ ፕላስ ዋን’ ላሳያቸው ተያይዘን ተጓዝን። መኪና ተከራይተዋል። ዶላር ዘርዝረዋል። በቃ ጭሰት ላይ ናቸው። እየሄድን. . . ‹‹እንዴት ናት ታዲያ አገራችን? አድጋለች አይደለም?›› በማለት ሳይሉኝ ጀመርኩ። ‹‹ዋት?!›› ብላ አንደኛዋ ሳቀችብኝ። ቻለው አንበርብር እያልኩ በውስጤ ሲቀባበሉብኝ ዝም። ‹‹‘ሉክ’ እስኪ እዚያ ጋ ሰውዬው ምን እንደሚሠራ?›› ስባል ዞሬ ሳይ. . . አንዱ መንጋጭላውን መዳፉ ላይ አመቻችቶ አስደግፎ ተቀምጦ ሥራውን ሲሠራ አያለሁ። ‹‹‘ዶንቺው ጋይስ ሃቭ’ የሕዝብ ‘ቶይሌት?›› ስትለኝ ሌላይቱ፣ ‹‹ነበረን ግን እየሞላ ሲያስቸግር ተዘጋ መሰለኝ. . .›› ብዬ መቀባጠር። ‹‹ዋት ኢዝ’ ዕድገት? ‘ሉክ’ እስኪ. . .›› ስባል አሁንም በሕጉ መሠረት ቅድሚያ የሚገባውን ተሽከርካሪ አንዱ በእልህ ደርቦ ቀድሞ መንገድ እየዘጋ እጁን አውጥቶ ይሳደባል። እኔ ራሴ በድንጋጤ ግራ ገባኝ፡፡

አላስችለኝ ሲል፣ ‹‹እኔ እኮ ጥያቄዬ ከትናንት ዛሬ አዲስ አባችንን እንዴት አገኛችኋት ነ. . .፤›› ብዬ ሳልጨርስ፣ ‹‹እንዴ በእኛ ጊዜ እኮ ሕዝብ ፊት መፀዳዳት ቀርቶ ሲያስነጥስህም ተሳቀህ ነበር። እየው እየው ደግሞ ይኼን. . .›› ብላ ሦስተኛይቱ ፊቴን ጠመዘዘችው። አስገኘው ተብሎ የተላከብኝ ሳይሆን አይቀርም የቆመ መኪና ጎማ ላይ ኃፍረቱን ያለ ኃፍረት እያራገፈ ሽንቱን ይሸናል። ኧረ መንገዱን፣ ኧረ ፎቁን፣ ኧረ ኮንዶሚኒየሙን . . . ምን ያላልኩት አለ አንዴ ገልመጥ ብላችሁ እዩት ብል ማን ሰምቶኝ። ‹‹ትመጣለህ ዶላር ትዘረዝራለህ ትበላ ትጠጣና ስትጨርስ ወንድሜ ‘ኖ መኒ ኖ ፈኒ’ እያልክ መጓዝ ነው፤›› ብለው ጨረሱት። ከዚያ በላይ ሽንጤን ገትሬ ብሟገት ማሰሪያው ‘ነን ኦፍ ዩር ቢዝነስ’ የምትል የዳያስፖራ ዓረፍተ ነገር ናት ብዬ እኔም ‘ቢዝነሴን’ አስቀደምኩ። ለነገሩ ገብቶ መውጣቱም ከኢንቨስትመንት አይተናነስም. . . እያልን እንፅናና እንጂ! የኮሌራ ወረርሽኝ ስንቶችን ማጥቃቱን ቢሰሙ፣ ‹ሳትፀዳዱ እየበላችሁና እየጠጣችሁ ነው እንዴ ፖለቲካው ላይ ፊጥ ያላችሁት› ቢሉኝ ማን ዋስ ሊሆነኝ ነው፡፡

በሉ እንሰነባበት። ቤቱን አከራይቼ አንድ ቅጥቅጥ አይሱዙም እጄ ላይ ነበር እሱን ተገላግዬ ኮሚሽኔን ተቀባበልኩ። ከዚያ ባለፈ ባገደምኩበት ይኼ ነገር ጠማቂ በሽሙጡና በስላቃዊ ንግግሩ እየተተናኮለ ሲያስቸግረኝ፣ ሳላስበው ያለ ሰዓቱ ግሮሰሪ መጎለት አሰኘኝ። ይኼን እያሰብኩ ባሻዬ ደወሉ። ‹‹ምነው?›› ስላቸው ‹‹ችግር ተፈጥሯል ቶሎ ድረስ!›› ብለው ጆሮዬ ላይ ዘጉብኝ። ስበር ሄድኩ። ስደርስ ባሻዬ ሠፈርተኛውን ለልማት የታጠረ ቆርቆሮ አጥር ሥር ሰብስበው ያወራሉ። ጠጋ ብዬ ሳዳምጥ ለካ የሠፈራችን ጎረምሶች አንድ በአንድ ‹‹የዓድዋ ድል ምንድነው?›› የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ወድቀው ኖሯል። የስብሰባው አስፈላጊነት መመለስ አለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን፣ ባለማወቃቸው አለማፈራቸውና አለመሸማቀቃቸው ጭምር መሆኑ ነው። ልጅ ድሮስ ያልተነገረውን ከየት ሊያመጣው ኖሯል! የአያት ቅድመ አያቶቹን የጀግንነትና የአርቆ አሳቢነት ታሪክ በቅጡ ያልተማረ ትውልድ ቢሳሳት አይገርምም፡፡ አውቆ አጥፊው በበዛበት በዚህ ዘመን ይህ ምን ማለት ነው፡፡

ባሻዬ፣ ‹‹በእውነቱ ወልደናል አትበሉ። ታሪኩን የማያውቅ ትውልድ ማለት እኮ ለእናት ለአባቱ አይመለስም። በእስራኤልም የአባቶቹን ታሪክ የማያውቅ ጡንቻውና ወኔው እንደ ላባ የሳሳ ትውልድ ተነሳ’ ይላል የዜና መዋል ዘጋቢ. . .›› እያሉ ይደሰኩራሉ። በዚህ መሀል አንዱ ከአጠገቤ የተቀመጠ፣ ‹‹እንዴት ታሪክ ይናቃል? ከዓድዋ በኋላ እኮ ይህች አገር ተፈርታ፣ ተከብራ፣ ተወድሳ፣ አርዓያ ተደርጋ፣ ማንም ሳይጠጋት ኮርታ ያኮራችን ናት፤›› ይላል። ሌላው ደግሞ ከዓድዋ ውርደት በኋላ መስሎኝ ያውም አርባ ዓመት አድብቶ ጣሊያን ተመልሶ የመጣው?›› አለው። ያ ወደኔ ዞረና፣ ‹‹ጣሊያን ተመልሶ መጥቶ ነበር እንዴ? እኮ ከዓድዋ በኋላ?›› ብሎ አረፈው። ይኼን ስሰማ ባሻዬን ቀስ ብዬ፣ ‹‹እስኪ ልጆቹን ትተው ከወላጆቻቸው ጀምሩ?›› አልኳቸው። ልጆቹን ትተው ወደ ወላጆቻቸው ዞሩ። ‘የባሰ አታምጣ’ አሉ፡፡ የባሰ መጣ ስላችሁ! ባሻዬ የሰሙትን ሰምተው ማታውን ግፊታቸው ጨምሮ ሲያንቆራጥጡን አደሩ።

ቆይ ግን ሳናስተምር ትውልድ ወቀሳና ሽሽቱ ወዴት ነው? ከታሪክ ወይስ ከራስ ሽሽት? ከመለደፍ ምናለበት አንዳንድ ቀን ማጤን ቢቀድም? ልጅየው ነው አባት ወይስ አባትየው ነው ልጅ? በበኩሌ እንነጋገርበት ብያለሁ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ደውሎ ግሮሰሪያችን ተቀጣጠርን፡፡ እኔም ነገር እየበላሁ ሄድኩ፡፡ ስደርስ ግሮሰሪው ጢም ብሎ ሞልቶ ነበር፡፡ የእኛ ሰው ሺሕ ዓመት አይኖርም እያለ መጠጣት ልማድ ማድረጉ ሲታወሰኝ፣ እኔም አንዱ መሆኔን ለአፍታም አልዘነጋሁም፡፡ እንደ ጲላጦስ እጅን እየተጣጠቡ ንፁህ ነኝ ማለት ከንቱነት ነው፡፡ ይህንን አንረዳም ወይም መስማት አንፈልግም የሚሉ ግን ትችታቸው ከመብዛቱ የክፋታቸው መጠን መጨመር ሲታወሰኝ ሰውነቴ ያተኩሳል፡፡ ገና ገብቼ ከመቀመጤ ከተፎው አስተናጋጅ ያላበው ቢራ ሲያመጣልኝ በትንፋሽ ከጨለጥኩ በኋላ በአንገቴ ዞር ዞር ስል የባሻዬ ልጅ ደረሰ፡፡ እሱም የቀረበለትን ቢራ ካንደቀደቀ በኋላ፣‹‹ውሎ እንዴት ነበር?›› ሲለኝ ነገርኩት፡፡ ‹‹አንበርብር! የዘመኑን ነገር ለዘመኑ ሰው ተወው የሚባል አነጋገር አለ፡፡ እኔና አንተ ያለፉትን ዘመናት እያሰብን ማሳሰቢያ ወይም ምክር ቢጤ ጣል ማድረጋችን መልካም ነው፡፡ ነገር ግን የውሳኔው ባለቤት ትውልዱ ነው፡፡ በሰላም መኖር፣ ከችጋር ተላቆ መበልፀግ ወይም እርስ በርሱ እየተጠዛጠዘ በረሃብ መማቀቅ የትውልዱ ውሳኔ ነው፡፡ የእኛ ትውልድ ኃላፊነት እንደኛ የመከራ ፅዋ እንዳትጨልጥ ተጠንቀቅ ማለት እንጂ፣ በዚህ ግባ በዚህ ውጣ ማለት አይደለም፤›› ሲለኝ አልዋጥልህ አለኝ፡፡ ‹‹ምነው እባክህ ምሁር ሆነህ ይህንን እንዴት ትላለህ?›› ስለው፣ ‹‹ጠማማ አክቲቪስት ነኝ ባይ በበዛበት ዘመን ቀና ከየት ይገኛል ብዬ ነው መከራ የማየው?›› ሲለኝ የስንቶች ተስፋ መቁረጥ እሱ ውስጥ ታየኝ፡፡ ለካ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደው አይደለም ትውልዱን የሚበክሉትን እግዜር ይይላችሁ ያሉት፡፡ መልካም ሰንበት!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት