ላለፉት 15 ዓመታት በሥራ ላይ የነበረው የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96፣ አካል ጉዳተኞችንና ሴቶችን ተጠቃሚ አድርጎ ተሻሻለ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ባደረገው አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 47ኛ መደበኛና ዘጠነኛ ልዩ ስብሰባው ያሻሻለው የሠራተኛና አሠሪ አዋጅ፣ ስድስት አንቀጾችን ማሻሻሉም ታውቋል፡፡
በአሠሪና ሠራተኛ መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከርና ምርታማነትን እንዲጨምር ማሻሻሉ ተገቢ መሆኑ የተገለጸው ይኸው አዋጅ፣ በተለይ በነፍሰ ጡር የወሊድ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ሰፊ ውይይት አድርገውበታል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ከምትወልድበት ቀን ቀደም ብሎ አንድ ወር፣ የሥራ ቀናት የቅድመ ወሊድ ፈቃድ እንድትወስድ ይደነግጋል፡፡ ከወለደች በኋላ 60 የሥራ ቀናት ወይም የሁለት ወራት የድህረ ወሊድ ፈቃድ አንዲሰጣት ይደነግግ ነበር፡፡
በተሻሻለው የድንጋጌ አንቀጽ ድኅረ ወሊድ ወደ ዘጠና ቀናት ወይም ሦስት ወራት ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ ከምትወልድበት ቀን በፊት የነበረው 30 የሥራ ቀናት ግን እንደነበር ፀንቷል፡፡
ከድኅረ ወሊድ በኋላ እንዲጨመር የተደረገው፣ ‹‹90 የሥራ ቀናት›› እንዲባል ክርክር ተደርጎበት ነበር፡፡ በመሆኑም የተጠየቀው አንቀጽ ፋብሪካዎችና የመንግሥት ያልሆኑ ተቋማት ቅዳሜና እሑድ፣ እንዲሁም የበዓል ቀናት ሥራ ስለሚሠሩ፣ በእነዚህ ተቋማት የሚሠሩ ሴቶችን እኩል ተጠቃሚ ስለማያደርግና ወጥ የሆነ አሠራር ለመዘርጋት ሲባል ‹‹ለ90 ተከታታይ ቀናት›› የሚለው ሐረግ መወሰዱ ተገልጿል፡፡