Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየተሻሻለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ረቂቅ ለውይይት ቀረበ

የተሻሻለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ረቂቅ ለውይይት ቀረበ

ቀን:

የተቀላጠፈና ፈጣን የወደብ አገልግሎት ማግኘት ለኢትዮጵያ ወሳኝ በመሆኑ የወደብ ጉዳይ የአገሪቱ ውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ፣ ከባለወደብ አገሮች ጋር ዘላቂ የወደብ አገልግሎትና የባህር በር መዳረሻ የማግኘት መብቷን በሚያረጋግጡ ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ትብብሮች ላይ በትኩረት እንደምትሠራ የሚያትተው ረቂቅ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለውይይት ቀረበ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በተለያዩ ሕጎችና ፖሊሲዎች ላይ ማሻሻያዎች ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ የሚገለጽ ሲሆን፣ የዚህ ሒደት አካል የሆነውና በ1994 ዓ.ም. የወጣውን የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚተካ አዲስ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት የተዘጋጀ ነው፡፡

የኢትዮጵያን አገራዊ ህልውናና ደኅንነትን ማስጠበቅ ዋነኛ ማጠንጠኛው እንደሆነ የሚገልጸው ረቂቅ ሰነዱ፣ የውጭ ግንኙነትና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲ በ1994 ዓ.ም. ከወጣ ጊዜ ጀምሮ የተከሰቱ አዳዲስ አዝማሚያዎችንና በቋሚነት የቆዩ ጉዳዮችን  ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ አምስት ዋና ዋና ጉዳዮችንና አዝማሚያዎችን በመነሻነት መውሰዱ በረቂቅ ፖሊሲው ተመላክቷል፡፡

በረቂቅ ፖሊሲው እንደ መነሻነት የተወሰዱት አምስት ዋና ዋና አዝማሚያዎችና ጉዳዮች ደግሞ አገራዊ ግንባታ፣ አገራዊ ክብር፣ የዜጎች መብትና ድንነት ማስጠበቅ፣ ቀጣናዊ የጂኦፖለቲካ ሁኔታ፣ ቀጣናዊ ውህደትና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታና አዝማሚያዎች የሚሉ ናቸው፡፡

አገራዊ ግንባታን በተመለከተ ረቂቅ ፖሊሲው፣ ‹‹በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የተቀመጠው የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ የመገንባት ራዕይ ገና ያልተጠናቀቀ ሥራ በመሆኑ ይህንን ራዕይ ለማሳከት የሚያስችሉ ሰላምና ደኅንነትን ማስጠበቅ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ተግባራት ያለመታከት ማከናወን፣ ፈጣንና ዘላቂነት ያለው ልማት ማረጋገጥና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማስፈን ይህ ፖሊሲ እንደ መነሻ የሚወስደው ቀዳሚ ጉዳይ ሆኖ ይቀጥላል፤›› በማለት፣ ከዋነኛ ማጠንጠኛዎች መካከል አገራዊ ግንባታ በግንባር ቀደምትነት እንደሚቀመጥ በማተት፣ የአገር ውስጥ ጥንካሬና ተግዳሮቶች ላይ ያተኮረና በዋናነት ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲን እንደሚያራምድ ያስረዳል፡፡

አገራዊ ክብርን በተመለከተ ደግሞ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛና የቀደምት ሥልጣኔዎች ባለቤት መሆኗ፣ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ አፍሪካዊ አገር ሆና መቆየቷ፣ የተለያዩ የእምነት ተከታዮች በመከባበር የሚኖሩባት አገር መሆኗ የአገሪቱ የስኬት ምንጭ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል እንደሆኑ በመጥቀስ፣ እስካሁን የተሳኩ ውጤቶችን እንደ መነሻና ማስፈንጠሪያ በመጠቀምና ያሉትን ክፍተቶች በማረም ወደ ላቀ የዕድገትና የሥልጣኔ ደረጃ መሻጋገር የፖሊሲው መነሻ ሆኖ እንደሚቀጥል ረቂቅ ሰነዱ ያመለክታል፡፡

የዜጎች መብትና ደኅንነትን ማስጠበቅ በሚመለከት ዜጋ ተኮር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ማካሄድ እንደ መነሻነት መወሰዱ የተገለጸ ሲሆን፣ ‹‹ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ ላይ ባለድርሻ እንዲሆኑና በየሚኖሩበት አገር የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ሆነው እንዲያገለግሉ ማበረታታት፣ ኢትዮጵያዊነትን ማዕከል ያደረገ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብን መገንባትና ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት የሚያስችል ውስጣዊና ውጫዊ አስቻይ ሁኔታ መፍጠር፣ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት አገር መብታቸውና ጥቅማቸው እንዲከበር መሥራት›› የረቂቅ ፖሊሲው መነሻ ሆኖ መወሰዱን ያትታል፡፡

ቀጣናዊ የጂኦፖለቲካ ሁኔታና ቀጣናዊ ውህደትን በሚመለከት ደግሞ፣ ‹‹በቀጣናው ዙሪያ የሚታየው ለውጥ የአገራችን ደኅንነትና ብሔራዊ ጥቅም ሥጋት እንዳይሆን የሚያደርግ፣ ዘላቂነት ያለው ፈጣን የወደብ አገልግሎት የማግኘት መብታችንን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፤›› በማለት ረቂቅ ሰነዱ ይገልጻል፡፡  

ከዚህ በተጨማሪም ‹‹በቀጣናው፣ በአኅጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያጋጥሙንን ተግዳሮች ለመፍታት፣ የሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ተልዕኮዎችን ይበልጥ ለማጠናከር፣ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ፖሊሲው በአገሮች የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ያለመግባት መርህ የተከተለ ዲፕሎማሲ የሚያራምድ ይሆናል፤›› ሲልም ያትታል፡፡

በዚህም መሠረት ረቂቅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው የሰላም ዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ፣ የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ ወቅታዊ ዓለም አቀፍ ጉዳዮችና ቀጣናዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን እንደ ስትራቴጂ መውሰዱን ያትታል፡፡

በ1994 ዓ.ም. የወጣው ፖሊሲ ኤርትራን በተመለከተ በዝርዝር የሚያትትና የኤርትራ መንግሥትንም ጀብደኛ በማለት ይገልጸው የነበረ ሲሆን፣ ለውይይት በቀረበው ረቂቅ ፖሊሲ ግን ጎረቤት አገሮች ከሚል ጥቅል ማብራሪያ በዘለለ፣ በእያንዳንዱ የጎረቤት አገር ስም ስለተዘጋጀው ዝርዝር የግንኙነት ማዕቀፍ የሚገልጸው የለም፡፡ ‹‹የውጭ ግንኙነት ፖሊሲው ለጎረቤት አገሮች ልዩ ትኩረት ይሰጣል›› በማለት ከጎረቤት አገሮች ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት በግርድፉ ይገልጻል፡፡

ረቂቅ ፖሊሲው አዳዲስ ዓለም አቀፍ ክስተቶችንና ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ሲሆን፣ በረቂቁ ውስጥም የአየር ንብረት ለውጥን፣ ፍልሰትንና ስደተኛነትን፣ የሳይበር ጉዳይንና የጠፈር ሳይንስ ጉዳይን በተመለከተ አገሪቱ የምትከተላቸውን አቅጣጫዎችን ያመላክታል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...