Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከአመራሮች ግድያ በኋላ የአማራ ክልል አመራሮች በአንድነትና በቁርጠኝነት እየሠሩ መሆኑ ተጠቆመ

ከአመራሮች ግድያ በኋላ የአማራ ክልል አመራሮች በአንድነትና በቁርጠኝነት እየሠሩ መሆኑ ተጠቆመ

ቀን:

የብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ባለቤትን ፖሊስ ይዟቸዋል

በአማራ ክልላዊ መንግሥት አመራሮች ላይ ግድያ ከተፈጸመ በኋላ፣ የመንግሥትም ሆኑ የፓርቲ አመራሮች በአንድነት በቁርጠኝነት እየሠሩ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በአመራሮቹ ግድያ ምክንያት ለክልሉ ተቆርቋሪ በመምሰል የሕዝብ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዳያገኙ የማደናቀፍ አጀንዳ ይዘው ለሚንቀሳቀሱ አካላት ዕድሉ የተዘጋ መሆኑን፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ለመገናኛ ብዙኃን ተናገሩ፡፡

- Advertisement -

አዴፓ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ አቋም ይዞ እየሠራ ቢሆንም፣ ከፊሉ የፓርቲው አባላት ለክልሉ የማይቆረቆሩና ከፊሉ የሚቆረቆሩ በማስመሰል የሚናፈሰው ወሬ፣ የተሳሳተና ከእውነት የራቀ መሆኑን ጠቁመው፣ ሁሉም አመራሮች በቁርጠኝነት እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአመለካከትም ሆነ በአቋም ምንም ዓይነት ልዩነት እንደሌለ አክለዋል፡፡

አዴፓ በፈተና ውስጥ የማለፍ የዳበረ የአመራር ልምዱን ተጠቅሞ፣ የተከሰተውን ወቅታዊ ችግር በመቋቋም በቁጭት እየሠራ መሆኑን አቶ ዮሐንስ ገልጸው፣ በክልሉ አመራሮች ላይ የተፈጸመው ግድያ ፓርቲውን፣ የክልሉንና መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የጎዳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ግድያ የተፈጸመባቸው ሦስቱም አመራሮች አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣ አቶ እዘዝ ዋሴና አቶ ምግባሩ ከበደ የመምራት ክህሎት ያዳበሩ፣ የተሻለ የሥራ ትጋት፣ ዕውቀትና ልምድ ያላቸውና በተለይ የክልሉ ሕዝብ ችግር የሚያንገበግባቸው አመራሮች መሆናቸው ሲታሰብ፣ የደረሰውን የጉዳት መጠን ከፍ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል፡፡

በወንጀል ድርጊቱ ዙሪያ ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን የመያዝና ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የጠቆሙት የጽሕፈት ቤት ኃላፊው፣ በየደረጃው ያለው አመራርም የበለጠ ግንዛቤ እንዲኖረው በማወያየት ላይ መሆናቸውንና እስከ ዓርብ ሰኔ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ፣ ከአምስት ሺሕ በላይ አመራሮች ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት በአመራሩ ላይ እልህ፣ ቁጭትና ወኔ መታየቱንና በተሻለ ጥንካሬ መሥራት በመቻሉም፣ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን በፍጥነት ወደ ሕግ ለማቅረብ መቻሉን አስረድተዋል፡፡ አዴፓ በፈተና ውስጥ ያለፈና ጠንካራ ታጋዮቹን ከጎኑ እያጣ አሁን ያለበት አቋም ላይ መድረሱን ጠቁመው፣ ምንም እንኳን እንደ እነ አምባቸው (ዶ/ር) ያሉ አመራሮችን ማጣቱ ቢቆጭም፣ አሁንም በበሳል አመራሮች የተሞላ ፓርቲ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ባልታሰበና ባልታወቀ ሁኔታ አመራሮቹን ማጣት ያሳዘነ ቢሆንም እነሱ ያነገቡትን የልማት፣ የሰላምና የአንድነት ዓላማ ከግብ ለማድረስ አዴፓ እንደሚሠራ አክለዋል፡፡ በአመራሮቹ ላይ የተፈጸመው ግድያ ለውጡን እንደማያደናቅፈውና አዴፓም የሕዝቡን የቆዩና ወቅታዊ ጥያቄዎች ለመመለስና ለመፍታት፣ በተቆርቋሪነትና በእልህ እየሠራ መሆኑንም አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡ ክልሉ የገጠመውን ወቅታዊ ፈተና በብቃት ለመሻገር የክልሉ ወጣቶች፣ ምሁራን፣ ሠራተኞችና ሁሉም የአማራ ሕዝብ ከአዴፓ ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

በክልሉ አመራሮች ላይ በተፈጸመው የግድያ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ቁጥር ከ218 በላይ መድረሱን የገለጹት ደግሞ፣ የክልሉ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰማኸን አስረስ ናቸው፡፡ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ እያደረገ ያለው የፌዴራል ምርመራ ቡድን እንደሆነ የሚነገረው ከእውነት የራቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ እያደረገ የሚገኘው የክልሉ መንግሥት የምርመራ ቡድን መሆኑንም አክለዋል፡፡

ክስተቱ ከተፈጠረ በኋላ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ከፀጥታ አካላትና ከፖሊስ አመራሮች ጋር በጋራ ሁኔታውን በመገምገም በዞን፣ በከተማ አስተዳደርና በወረዳ ደረጃ ሥምሪት ወስደው ችግሩ እንዳይባባስ ከፍተኛ ሥራ ማከናወናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በተያዙ ተጠርጣሪዎች ላይ የሚደረገው ምርመራ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በፌዴራል መንግሥት በኩል ዕገዛ ተደርጎላቸው እየተሠራ መሆኑን፣ በሒደቱም ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደማይፈጸምም ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ያሉት በተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት እንጂ፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው ወይም የማኅበራትና የተለያዩ አደረጃጀቶች አባል ስለሆኑ እንዳልሆነም አስረድተዋል፡፡

በቁጥጥር ሥር እየዋሉ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችም በክልሉ መንግሥት የፀጥታና የእስር ማዘዣ በመያዝ እንጂ፣ ክልሉ ሥልጣኑን ለፌዴራል መንግሥት አሳልፎ በመስጠት በፌዴራል የፀጥታ አካላት እንዳልሆነም አክለዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የአመራሮቹን ግድያ አቀነባብረዋል የተባሉትና ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ሕይወታቸው ያለፈው የብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ባለቤት ወ/ሮ ደስታ አሰፋ፣ ሐሙስ ሰኔ 27 ቀን አዲስ አበባ አሸዋ ሜዳ በሚባለው ሥፍራ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ የቡራዩ ከተማ ፖሊስም በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያደረገባቸው እንደሆነ ታውቋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...