በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋና አቅርቦት ላይ የሚሰማራ የመንግሥት ኮርፖሬሽን ሊቋቋም ነው፡፡
የሚቋቋመው ኮርፖሬሽን በነዳጅና ጋዝ ፍለጋ ልማትና አቅርቦት ላይ ከመሰማራት ባለፈ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የነዳጅና ጋዝ ፍለጋ ላይ በተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ውስጥ የመንግሥትን ድርሻ በመያዝና በማስተዳደር፣ የአገሪቱን ጥቅም የሚያስጠብቅ እንደሚሆን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በአሁኑ ወቅት የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮ ፊውል ልማት ኮርፖሬሽን ተብሎ የሚጠራ ተቋም ተመሳሳይ ተልዕኮ ይዞ የሚገኝ ቢሆንም፣ እንደ አዲስ የሚመሠረተው የነዳጅና ጋዝ ምርት አቅርቦት የሚተካው እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህንን ኮርፖሬሽን የሚያቋቁም ረቂቅ ደንብ የተሰናዳ ሲሆን፣ ሪፖርተር ያገኘው ይህ ሰነድም በመግቢያ ክፍሉ ኮርፖሬሽኑ የሚቋቋምበትን ዓላማ ይዘረዝራል፡፡
በኢትዮጵያ ስድስት የነዳጅ አለኝታ አካባቢዎች ተለይተው ፍለጋ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ፣ ከእነዚህም መካከል በኦጋዴን አካባቢ ወደ አሥር ትሪሊዮን ኪዩብ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝና መጠኑ ገና በመለየት ላይ ያለ ፈሳሽ ነዳጅ መገኘቱንና ወደ ልማት ለመግባት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ መሆናቸውን ያስረዳል፡፡
‹‹ይሁን እንጂ ልማቱን እያካሄዱ ያሉ የውጭ ኩባንያዎች ስለሆኑ፣ የአገራችን ጥቅም ሊጠብቅ የሚችል መንግሥታዊ ተቋም ማቋቋም አስፈልጓል፤›› ሲል የረቂቅ ማቋቋሚያ ደንቡ መግቢያ ይገልጻል፡፡
ረቂቅ ሰነዱ የማቋቋሚያውን ኮርፖሬሽን ሥልጣንና ተግባር የሚዘረዝር ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አንዱ ኮርፖሬሽኑ ራሱ ወይም እንደ ሁኔታው ከሌሎች ባለሀብቶች ጋር በመሆን በነዳጅና ጋዝ ሥራዎች ኢንቨስትመንት ላይ መሳተፍ፣ ማልማትና ማምረት እንደሚቻል ይደነግጋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች ተወዳዳሪና አትራፊ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ዕገዛ የሚያደርጉለትን የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂና የዘመናዊ አስተዳደር ግብዓቶችን ለማግኘት የሚያስችለውን ጥናት በማካሄድ የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ፣ ሲፈቀድለትም ተግባራዊ ማድረግ ሌላው ሥልጣኑና ተግባሩ ነው፡፡
የነዳጅና ጋዝ መሠረተ ልማት ግንባታ ማከናወን፣ በሌሎች አካላት የተገነቡትንም የመሠረተ ልማት ሥራዎችና አሠራር የመቆጣጠር ኃላፊነት በረቂቁ ተሰጥቶታል፡፡ በግል ኩባንያዎች አማካይነት በሚካሄዱ የነዳጅና ጋዝ ልማት ሥራዎች ውስጥ የመንግሥትን ድርሻ በመወከል መሳተፍና ማስተዳደር፣ ሌላው የኮርፖሬሽኑ ሥልጣንና ኃላፊነት እንደሚሆን ሰነዱ ያመለክታል፡፡
በተጨማሪም የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚሰጠው የፖሊሲ አቅጣጫ መሠረት አክሲዮን የመሸጥ ወይም የመግዛት፣ እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ መሠረት ቦንድ የመሸጥና ዋስትና የማስያዝ፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ የገንዘብ ምንጮች ጋር የብድር ውል መደራደርና የመፈራረም ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሶማሌ ክልል በኦጋዴን የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት በማምረትና ወደ ጂቡቲ በሚዘረጋ ቧንቧ በማስተላለፍ ወደ ፈሳሽ የኃይል ምንጭነት የሚቀየረውን የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ቻይና ለመላክ፣ ፖሊጂሲኤል የተባለ የቻይና ኩባንያ በመሥራት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በዚህ የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ላይ የሚኖረውን 15 በመቶ የመንግሥት ድርሻ ሊያስተዳድር እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል ኒውኤጅ የተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ በዚሁ በኦጋዴን አካባቢ ተጨማሪ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ማግኘቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የሚቋቋመው ኮርፖሬሽንም በዚህ ሀብት ውስጥ የሚኖረውን የመንግሥት ድርሻ በባለቤትነት በመያዝ እንደሚያስተዳድር ይጠበቃል፡፡