ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ችግሩ በውይይት እንዲፈታ ጠይቀዋል
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2011 ዓ.ም መርሐ ግብር ሊጠናቀቅ አንድ የጨዋታ ፕሮግራም ብቻ በቀረበት በአሁኑ ወቅት አንጋፋው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ‹‹ጥያቄዎቼ ተገቢውን ምላሽ አላገኙም›› በሚል ከሁለት አሠርታት በላይ ተሳትፎ ሲያደርግ ከቆየበት የፕሪሚየር ሊግ ራሱን ያገለለ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናም በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያቀረበው የፍትሕ ጥያቄ መልስ ሊያገኝ እንደሚገባ ፌዴሬሽኑን ጠይቋል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ክለቡ በደብዳቤ ላቀረበው ጥያቄ መልሱም በደብዳቤ ተሰጥቶታል እያለ ነው፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በመደበኛ መርሐ ግብሩ ይዞት የነበረው የጨዋታ ፕሮግራም፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ የ28ኛ ሳምንት ጨዋታው በአዲስ አበባ ስታድየም ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር የነበረ ቢሆንም፣ ፌዴሬሽኑ የፀጥታ ሥጋት አለ በሚል ጨዋታው በይደር እንዲተላለፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ይሁንና በይደር የተላለፈው የሁለቱ ቡድኖች በተያዘለት ፕሮግራም መሠረት ሳይከናወን ቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ ወልዋሎ አዲግራት ቀጣዩን የ29ኛ ሳምንት ጨዋታ እንዲያደርጉ መወሰኑ ‹‹በሕግ አግባብ ትክክል አይደለም›› በሚል ቅዱስ ጊዮርጊስ የፌዴሬሽኑን ውሳኔ እንደማይቀበለው፣ ለ29ኛው ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር ወደ ጎንደር እንደማያመራ ለፌዴሬሽኑ ቢያስታውቅም በፌዴሬሽኑ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ ባለሜዳው ፋሲል ከተማ በፎርፌ ሦስት ነጥብና ሦስት ንጹህ ጎል እንዲያገኝ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
በውሳኔው ያልተስማማው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀን 27/10/2011 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጻፈው ደብዳቤ፣ ክለቡ ያቀረባቸው ጥያቄዎች ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድሮች ራሱን ያገለለ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ምክንያቱን ሲያብራራ የፌዴሬሽኑ የሊግ ኮሚቴ የቅዱስ ጊዮርጊስን የሜዳ ተጠቃሚነት ለማሳጣት፣ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ሊያደርገው የነበረውን ጨዋታ በዝግ ወይም አዳማ ከተማ ላይ ተጫወቱ በማለት ጨዋታው ሁለት ጊዜ እንዲቋረጥ አድርጓል፡፡
ይህን ጨዋታ ከዚህ ቀደም የተቋረጡ የሌሎች ክለቦች ጨዋታዎችን ባስተናገደበት ሁኔታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን አለማስተናገዱን በመጥቀስ ፌዴሬሽኑ ላይ ያለውን ቅሬታ ጭምር በመግለጫው አካቷል፡፡ መግለጫው አክሎ እንደሚያስረዳው ከሆነ፣ በ29ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ለፋሲል ከተማ የተሰጠው ፎርፌ አግባብነት የሌለውና አድሏዊ መሆኑ፣ በዚህም ቅዱስ ጊርጊስ አዲስ ከመጡት የፌዴረሽኑ አመራሮች ጋር በመተባበር፣ በመቻቻልና በመተጋገዝ ሲሠራ ቢቆይም ተቋሙ በሚወስናቸው ኢ- ፍትሐዊ እርምጃዎችና አላግባብ የተወሰነበት ፎርፌ እስኪነሳ ክለቡ በውሳኔው እንደሚጸና አስታውቋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ፣ በተቀመጠው ደንብና መመርያ መሠረት ውሳኔዎችን ሲያስተላልፍ መቆየቱን ገልጾ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ላይም የተላለፈው ተመሳሳይ ነው ሲል ተናግሯል፡፡ የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንትና የሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ሲንከባለሉ የመጡ በርካታ ችግሮች ባሉበት በአገሪቱ የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ ተጨማሪ ችግሮች ተቋሙ ላይ ሌላ ጫና እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ይህም ሆኖ የውድድር ዓመቱ መርሐ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለማጠናቀቅ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መገኘታችን ሊያስመሰግነን ሲገባ፣ እንደነዚህ የመሰሉ ያውም በንግግርና በውይይት መፍታት የሚቻልበት ዕድል እያለ ወደ አላስፈላጊ ነገር መገባቱ ትክክል እንዳልሆነም አስረድተዋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በውድድር ዓመቱ በተለይም ከቅዱስ ጊዮርጊስና ከኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለቦች እየተነሳበት ያለው የሕግ ክፍተት በጊዜ መፍትሔ ካልተቀመጠለት መጨረሻው እንደማያምር ምልክቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ በዚያ ላይ ማንነትንና ብሔርን መነሻ ያደረጉ አለመግባባቶች ከክልል ክልልም አልፈው አንዳንድ ክልሎች ከአዲስ አበባ ክለቦች ጭምር ግጭቶች መጀመራቸው የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ሰበባብቷል፡፡
ይህንኑ አስመልክቶ ኮሎኔል አወል፣ ‹‹ችግሮቹ የሁላችንም ችግሮች ናቸው፣ በጋራ ተወያይተን የጋራ መፍትሔ ማስቀመጥ እንዳለብን አምናለሁ፡፡ ፌዴሬሽኑም አሁን እጁ ላይ ያለውን መርሐ ግብር ለማጠናቀቅ ካልሆነ፣ ቀጣዩን የውድድር ዓመት በተመለከተ እንዴት ይሁን የሚለውን የሚያጠና 12 አባላት ያሉት የጥናት ቡድን አቋቁሞ እየሠራበት ነው፡፡ ጥናቱን ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲወያዩበት ይደረጋል፣ ከዚያም የሚበጀውን ራሳቸው ክለቦቹ በሚወስኑት መሠረት የውድድሩ ቀጣይ ዕጣ ውሳኔ የሚያገኝ ይሆናል፤›› በማለት መልሰዋል፡፡
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጋር ተያይዞ የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለቦች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላይ የሚያቀርቡት አቤቱታ የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲቀመጥለት ከተቋሙ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ምክትል ከንቲባው በእግር ኳሱ ላይ እየታየ ያለው የስፖርታዊ ጨዋነት አጀንዳዎች ዙሪያ ሁለቱ ክለቦች የሚያነሷቸው ችግሮች አጽንኦት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አቶ ኢሳያስ ጅራና ምክትል ፕሬዚዳንቱ ኮሎኔል አወል አብዱራሂምን በጽሕፈት ቤታቸው በማነጋገር መጪው የውድድር ዘመን ከመጀመሩ በፊት ይህ ችግር እልባት ማግኘት እንዳለበት ተማምነው ቅድመ ዝግጅቱም ከወዲሁ መጀመር እንዳለበት ያሳሰቡት ባለፈው ዓርብ ሰኔ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ነበር፡፡