በከባድ ክብደት የዓለም የቦክስ ሻምፒዮን የነበረው ታዋቂው ማይክ ታይሰን ‹‹የመጀመርያውን ቡጢ እስኪቀምስ ድረስ ሁሉም ቦክሰኛ ዕቅድ አለው፤›› ብሎ ነበር:: ቦክሰኞች ተፎካካሪያቸውን ለማሸነፍ የሚያስችላቸውን ዘዴዎች በደንብ አጥንተውና ተዘጋጅተው ወደ ፍልሚያው ቦታ ይገባሉ:: ሆኖም ከባድ የሆነ ቡጢ ፊታቸው ላይ ሲያርፍ ምድርና ሰማዩ ይዞርባቸውና የተዘጋጁበት ዕቅድ ሁሉ እንደ ጉም ብን ብሎ ይጠፋባቸዋል:: ማይክ ታይሰን ወደ ግጥሚያ ከመግባቱ በፊት እንዲህ ዓይነት ተግዳሮት እንደሚገጥመው በሚገባ እንደሚያውቅ ከዚህ አነጋገሩ መረዳት ይችላል:: የንግግሩ ዋናው ጭብጥ ግን አንድ ቦክሰኛ አሸናፊ መሆን የሚችለው ፊቱ ላይ ያረፈበትን ቡጢ በፅናት ተቋቁሞ፣ ይዞት የመጣውን ዕቅድ ከነባሪያዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ለድል መብቃቱ ላይ ነው::
በአገራችን ኢትዮጵያ “በድንገት” የተከሰቱት የለውጥ አራማጆች ‹‹በይቅርታ እንሻገር፣ በፍቅር እንደመር›› የሚል መርህ ይዘው ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግናና እውነተኛ ዴሞክራሲ ለመምራት ከተነሱ ከዓመት በላይ ሆነው:: በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በለውጡ ላይ ብዙ “ቡጢዎች” አርፈውበታል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኔ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ ከዘረዘሯቸው ቡጢዎች በተጨማሪ፣ በክልሎችና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያሉ አለመግባባቶችና ተግዳሮቶች፣ በአንዳንድ ክልሎች መካከል ያሉና የነበሩ የጦርነት እምቢልታና ነጋሪቶች፣ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ከፍተኛ የሆኑ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎች፣ ውዥንብሮች፣ ከምናምንቴዎች የሚወጡ ተራ ስድቦች፣ አሉባልታዎችና እርሳቸው እንዳሉት እኛ የማናውቃቸው ሌሎች ሴራዎች በለውጡና በመሪዎቹ ላይ ከተሰነዘሩት ከባድ፣ መካከለኛና ቀላል “ቡጢዎች” ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው::
እነዚህ ቡጢዎች በውድ ወገኖቻችን ላይ የሕይወት፣ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት፣ በአገራችን ላይ ብርቱ ጠባሳ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ደግሞ ድንጋጤን ከዚያም ሐዘንን፣ ከዚያም ሥጋትን፣ ከዚያም ውዥንብርን፣ ከዚያም ተስፋ መቁረጥን እንደ ደረጃቸው አስከትለዋል እያስከተሉም ነው:: የለውጡም መሪዎች ሰዎች ስለሆኑ በሕዝቡ ውስጥ ለተከሰቱት እነዚህ ስሜቶች ሰለባ ለመሆናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ይታይ የነበረው ሐዘን፣ ቁጭትና የልብ ስብራት ምስክር ነው:: የቡጢዎቹ ዋና ዓላማ ለውጡ በታሰበለት ጎዳናና መርህ እንዳይሄድ በማድረግ ማጨናገፍና የለውጡን አራማጆች ወይ በዝረራ አለበለዚያም በበቃኝ ከጨዋታው ውጪ ማድረግ ነው:: ቡጢዎችን ተከትለው የሚሰጡ አንዳንድ መግለጫዎች፣ ዛቻዎች፣ ስድቦችና የሴራ ትንታኔዎች የዚህ ዓላማ ተቀጥላ ናቸው:: ከመንግሥት አካላትም ወጥነት የጎደላቸው መግለጫዎች ለሴራ ተንታኞች ሰፊ በር በመክፈት ለዚህ ዓላማ እንደ ግብዓት በመሆን ማገልገላቸውን ልብ ልንል ይገባል::
ሌተና ጄኔራል አበባው ታደሰ በጄኔራል ሰዓረ መኮንን የአስክሬን ሽኝት ላይ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ‹‹አንድነትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ መቻቻልንና ብልፅግናን›› ነው:: ሕዝብ ለውጡን አይቃወምም:: ዕርቀ ሰላምን፣ ይቅርታን፣ ፍቅርን፣ ዴሞክራሲንና ብልፅግናን የሚቃወም ሕዝብ እንዴት ሊኖር ይችላል? በሕዝብ ስም ግን ለእነዚህ መልካም እሴቶች አደናጋሪ ትርጉም በመስጠት በለውጡ ላይ ቡጢ የሚያሳርፉ መኖራቸውን ግን በዓይናችን እያየን ነው:: በልመና በምትኖርና ብድሯን መክፈል ባልቻለች በዚህች ደሃ አገር ውስጥ ይኼ ሁሉ ልዩ ኃይል፣ ይኼ ሁሉ ሚሊሽ፣ ይኼ ሁሉ ዝግጅት፣ ይኼ ሁሉ የጦር መሣሪያ እንዲኖረን በተለያዩ ደረጃ ያሉና መሠረታዊ የምጣኔ ሀብት ዕውቀት ያላቸው መሪዎቻችን ለምን እንደፈለጉ ለእኔ ግልጽ ባይሆንልኝም፣ ለውጡ አቅጣጫውን ስቶ ወደሌላ መንገድ ከሄደ ግን በአገራችንና ሕዝቧ ላይ የሚያስከትለውን ውድመት በዝርዝር ለማሰብ እኔ በግሌ አልፈልግም:: ፈጣሪ ከዚህ ይጠብቀን::
ዕርቀ ሰላም ለማውረድ ኮሚሽን ቢቋቋምም ያለ ሁላችን ተሳትፎ በጥቂት የኮሚሽን አባላት ብቻ ዕርቀ ሰላም ማምጣት አይቻልም:: እነርሱን ከመጠበቅ ይልቅ ቢያንስ ለጥቂት ሳምንታት ለቡጢ የምናደርጋቸውን ዝግጅቶችንና ድርጊቶችን በማቆም ለሰላም፣ ይቅርታና ዕርቅ ያለንን ተነሳሽነት በተግባር ብናሳይ ምናለበት? ቢያንስ አንድ ክልል ወይም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወይም አክቲቪስት ወይም የአገር ሽማግሌ ወይም የሃይማኖት መሪ ወይም መምህራን ወይም የታክሲ አሽከርካሪዎች ወይም ጋዜጠኞች ወይም አርቲስቶች ወይም ሌሎችም በኢትዮጵያ ውስጥ ደም የማይፈስበት ሳምንታት እንዲኖሩ ጥሪ ቢያደርጉ፣ ሌሎች ጥሪውን ተቀብለን፣ ቀን ቆርጠን፣ ያለሴራ፣ ያለግጭት፣ ያለሞት መኖር እንዲለምድብን ይህን ብናደርግ ምን ክፋት አለው? እስቲ እንጀምር? እስቲ አገራችን ከደም ትረፍ? ወገኖቼ ሁሉም ነገር በእያንዳንዳችን እጅ ላይ ነው:: ውድ የሆኑ ወገኖቻችንን ደም ያፈሰሰ፣ ውርደት እንጂ ክብር የማያሰጥ፣ ኪሳራ እንጂ ሽልማት የማያስገኝ የጥፋት ትዕይንትን ከመመልከት አገርንና ሰውን በሚፈውስ ተግባር ላይ ጊዜያችንን ብናጠፋ አይሻልምን?
ለለውጡ መንስዔ የሆነው የሕዝብ እንቢተኝነትና ተቃውሞ ቢሆንም ለውጥን ግን ሕዝብ መምራት ስለማይችል የለውጡ አቅጣጫና ግብ ከፀሐይ በታች በመሪዎቹ ቆራጥነት፣ ፅናት፣ ብልሃት፣ ችሎታ፣ ልምድ፣ ብስለትና ዝግጅት መዳፍ ውስጥ ነው:: ምንም እንኳ ከዚህም ከዚያም የሚሰነዘሩ ቡጢዎች ቢኖሩም ለውጡን የሚመሩት ሁሉ ለማሸነፍ እንደተዘጋጀና ቡጢዎች ሲያርፉበት ዕቅዱን ከሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች ጋር በማጣጣም ተስፋ ሳይቆርጥ እስኪያሸንፍ ድረስ በፅናት እንደሚቧቀስ ቦክሰኛ በመሆን፣ ተስፋ ሳይቆርጡ፣ የተነሱበትን ዓላማና መርህ ባለመልቀቅ የኢትዮጵያን ታላቅነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ፈር ቀዳጅና መሠረት ጣይ በመሆን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ታሪክ እንደሚሠሩ እምነቴ ፅኑ ነው:: በተቃርኖ የቆሙትን ወደ መሀል በመሳብ፣ መሀል ላይ የቆሙትን ከለውጡ ዓላማዎች ጋር አብረው እንዲቆሙ በመጋበዝ፣ ለለውጡ ስኬት የሚደክሙትን በማበረታታትና በመደገፍ እንደተለመደው ብልሃት የተሞላበት በሳል አመራር እየሰጡ የቡጢዎችን መጠንና አቅም እየቀነሱ እንደሚቀጥሉ ተስፋ አደርጋለሁ::
የለውጡ ዓላማዎችና ግቦች እንኳን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ለውጭ አገር ሕዝቦች ጭምር አጓጊ ናቸው:: ከአፍሪካ መሪዎች እንዴት መልካም ነገር ይወጣል ብለው በመገረም ስኬቱን የሚከታተሉ ብዙ ናቸው:: እኛ ኢትዮጵያውያን የጉዳዩ ባለቤት ስለሆንን የለውጡ መሪዎች በቡጢዎች ብዛት ተስፋ እንዳይቆርጡና የተነሱበትን ዓላማ ስተው ወደኋላ እንዳይመለሱ በቃልና በተግባር ልንደግፋቸው ይገባል:: ናፓሊዎን እንዳለው ‹‹ዓለማችን በበለጠ እየተጎዳች ያለችው በክፉ ሰዎች ዓመፅ ሳይሆን በመልካም ሰዎች ዝምታ ነው››:: በዚህ ጉዳይ ዝምታ ወርቅ አይደለም፡፡
(ከዋካንዳ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ)