Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

የዘመናችንን ፖለቲከኞች ሁኔታ ሳስበው አንድ ቀልድ የሰማሁበትን ጊዜ ባላስታውስም ግን ፈጽሞ አይረሳኝም፡፡ እንዲህ ላቅርበው፡፡ ሰውየው በጠዋት ተነስቶ ወደ ጉዳዩ ሊሄድ የግቢውን በር ከፍቶ ሲወጣ፣ አንዱ ከፊት ለፊት ያለው ትልቅ የመኖሪያ ቪላ ግንብ ላይ ጆሮውን ለጥፎ ያየዋል፡፡ በሰውየው ሁኔታ በመገረም ቀረብ ብሎ ሲያየው ጆሮውን ግንቡ ላይ ለጥፎ የሆነ ነገር የሚያዳምጥ ይመስላል፡፡ አለባበሱ ንፁህና ፅዱ የሆነው ሰውዬ አኳኋን ቢያስገርመውም ቸኩሎ ስለነበር ይሄዳል፡፡ ጉዳዩን ጨራርሶ ለምሳ ወደ ቤቱ ሲመለስ ያ ሰው አሁንም ጆሮውን ግንቡ ላይ እንደለጠፈ ያገኘዋል፡፡ በሰውየው ይኼን ያህል ሰዓት በዚህ ሁኔታ መቆየት ግራ በመጋባት፣ ‹‹ምንድነው የምትሠራው?›› በማለት ጥያቄ ያቀርብለታል፡፡ ሰውየውም ፈገግ ብሎ፣ ‹‹ና እባክህ ይልቅ አዳምጥ፤›› ብሎ ጠጋ ይልለታል፡፡ እሱም ምን ይሆን እንዲህ የሚያዳምጠው ብሎ ጆሮውን ለተወሰኑ ደቂቃዎች ለጥፎ ይቆያል፡፡ ነገር ግን ምንም ማዳመጥ ባለመቻሉ፣ ‹‹ምንም ነገር ማዳመጥ አልቻልኩም፤›› ይለዋል፡፡ ያ ጉደኛ ሰው፣ ‹‹አይገርምም እኔም ምንም ማድመጥ አለመቻሌ ነው የገረመኝ. . .›› ብሎት በቆመበት ጥሎት ሄደ፡፡ ይህ ቀልድ ግራ የሚያጋቡብንን ፖለቲከኞች የሚወክልልኝ ይመስለኛል፡፡

ሰውየው የአዕምሮ ታማሚ መሆኑን ከአካባቢው ሰዎች ከሰማ በኋላ ከት ብሎ ስቆ፣ ‹‹አልተመረመርንም እንጂ እኛም እኮ ወፈፍ ያደርገናል፤›› ብሎ ነበር አሉ፡፡ አዎ! የአዕምሮ ታማሚዎችን ጉዳይ እያነሳን በሚያስቀው ስንስቅ፣ በሚያሳዝነው ስናለቅስ እንታያለን እንጂ፣ በእርግጥም ሙሉ ምርመራ ብናደርግ በራሳችን ላይ አስገራሚ ውጤት እናገኛለን፡፡ በተለይ ፖለቲከኞቻችን ቢመረመሩ መልካም ነው፡፡ አንድ ጊዜ የምሠራበት መሥሪያ ቤት አዲስ አለቃ ተሹሞ ይመጣል፡፡ ይኼ አለቃችን በረባ ባልረባው መቆጣት ልማዱ ነው፡፡ ከሠራተኞች ጋር ያለው ግንኙነት በአጭር ጊዜ በመበላሸቱና ጭቅጭቅ ስለበዛ ከሥራ ይልቅ ነገር ተስፋፋ፡፡ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ሰላም ጠፋ፡፡ ነገሮች ከአቅም በላይ ሆነው የመሥሪያ ቤቱ ቦርድ ዘንድ ተደረሰ፡፡ ከቦርድ አባላት አንደኛው ምራቃቸውን ዋጥ ያደረጉ በሳል ሰው ስለነበሩ ከሰውየው ጋር ጊዜ ወስደው ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘው፣ በዚህ መሠረት ለቦርዱ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርቡ ስምምነት ተደረገ፡፡

እኝህ ታዋቂ የሕግ ባለሙያና መምህር የነበሩ በሳል ሰው ከአለቃችን ጋር የግማሽ ቀን ውይይት አድርገው ያቀረቡት ሪፖርት አስገራሚ ነበር፡፡ አለቃችን በልጅነቱ እናትና አባቱን በማጣቱ ያደገው ዘመድ ተጠግቶ ነው፡፡ ዘመዶቹ ደግሞ እንደ ልጆቻቸው በሚገባ ተንከባክበው ከማሳደግ ይልቅ፣ ጉልበቱን በመበዝበዛቸው ትምህርት የጀመረው ዘግይቶ ነበር፡፡ ቆይቶም ቢሆን የትምህርት ዕድል ያገኘው በሌሎች ግለሰቦች ዕርዳታ ነበር፡፡ ነገር ግን በዘመዶቹ በደረሰበት እንግልት ምክንያት ተጠራጣሪና ቁጠኛ እንዲሆን በመገደዱ፣ ከሰዎች ጋር መግባባት ዳገት ሆኖበታል፡፡ ችግሩን አውቆ ለማረም ቢሞክርም ትዕግሥት ስለሌለው ችግሩ ውስጥ እንደሚዘፈቅ ግልጽ ሆነ፡፡ እዚህ መሥሪያ ቤት ከመጣ ወዲህ ደግሞ፣ የአንዳንድ ሰዎች አስተያየት የበለጠ ስለሚያናድደው ግጭት መፈጠሩን ይናገራል፡፡ እኝህ በሳል ሰው በሰጡት መደምደሚያ ሰውየው የሥነ አዕምሮ ሐኪም ካገኘ ይስተካከላል የሚል ነበር፡፡ በዚህ ማሳሰቢያ መሠረት አለቃችን ሕክምና ወስዶ የተረጋጋ ሰው ሆነ፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ በፍቅር ተወደደ፡፡ እስካሁን ድረስ የብዙዎቻችን የቅርብ ወዳጅ ነው፡፡ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ተመርምረው ሕክምና ቢያገኙ እንደዚህ አለቃችን ይፈወሱ ነበር፡፡

- Advertisement -

የአዕምሮ ችግር የቅርብ ክትትል የሚያስፈልገው ነው፡፡ አንዳንዱ ድብርት ይይዘውና ከሰው ጋር መነጋገር አይፈልግም፡፡ ይባስ ብሎም በዙሪያው ያሉትን ጠላት አድርጎ ለፀብ ይጋበዛል፡፡ አንዳንዱን ደግሞ ወሬኛ ያደርገውና አንዱን ከአንዱ ሲያላትም ይውላል፡፡ በቅርቡ አንዷ የሥራ ባልደረባችን ከምትቀራረባት የሥራ ባልደረባዋ ጋር ትጣላለች፡፡ በደህናው ጊዜ ሁለቱ ምሳ የሚበሉት፣ ቡና የሚጠጡት፣ በዕረፍታቸው ጊዜ ሲኒማ ወይም ቴአትር የሚገቡት በመቀራረብ በፈጠሩት ጓደኝነት ነበር፡፡ ሲጣሉ ግን አንደኛዋ የጓደኛዋን ሚስጥር የሚባሉ ጉዳዮች ዘክዝካ ታወራለች፡፡ ለሰው የማይነገሩ ገመናዎችን ጭምር እያወጣች ላገኘችው ሁሉ ታሠራጫለች፡፡ በዚህ ድርጊቷ የተናደደ አንዱ የሥራ ባልደረባዋ፣ ‹‹አንቺ ምን ሆነሽ ነው እንዲህ የምታብጂው?›› ሲላት፣ ስቴፕለር ወርውራ ጭንቅላቱን ስትለው ደም በደም ይሆናል፡፡ ይህ አልበቃ ብሏት ጫማዎቿን በየተራ እያወለቀች ስትወረውር በገላጋይ ብዛት ተያዘች፡፡ በዚህ መሀል ከጣሪያ በላይ የሚሰማው ጩኸቷ ችግር እንዳለባት ያሳብቅ ነበር፡፡ በኋላ ግን እንደተረዳነው ተደብቆ ነው እንጂ የአዕምሮ ሁከት አለባት፡፡ በፈጸመችው ወንጀል ምክንያት እስር ቤት ለዓመታት ቆይታ እንደነበር ታወቀ፡፡ ይህች ሴት የሥነ አዕምሮ ሕክምና ሳታገኝ ነበር በቀጥታ ወደ ሥራ ዓለም ገብታ ስትቸገር የነበረው፡፡ 

ባለፈው ሳምንት ሃያ ሁለት የሚባለው አካባቢ የሚገኙ ሱቆችን በዓይኔ እየጎበኘሁ ስራመድ ጥቁር ሰማያዊ ቀለም ቪትዝ መኪና የያዘች ወጣት ሴት በእጇ ምልክት ታሳየኛለች፡፡ የእጅ ምልክቱ ‹‹ና›› የሚል ነው፡፡ ምን ፈልጋ ነው በማለት ቀረብ ስላት፣ ‹‹የእኔ ወንድም እዚህ አካባቢ ጥሩ ምሣ የት ይገኛል?›› ስትለኝ የምትቀልድ መሰለኝ፡፡ ‹‹በጣም ስለራበኝ ነው እባክህ አሳየኝ. . .›› እያለች ኮስተር ብላ እንደገና ስትጠይቀኝ፣ ወደ ቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል አቅጣጫ እያሳየኋት የአንድ ምግብ ቤት ስም ነገርኳት፡፡ እሷ ግን፣ ‹‹በእናትህ ብቻዬን ከምሆን አባላኝ፡፡ አይዞህ የአንተንም ምሣ እኔ እችላለሁ. . .›› በማለት ስትቅለሰለስ፣ ከምሣው ይልቅ የእሷ ቁንጅና ማርኮኝ መኪናዋ ውስጥ ገብቼ ተያይዘን ሄድን፡፡ ያዘዝነው ምሣ ቀርቦ ስንበላ፣ ‹‹ዋው! ምርጥ ምግብ ነው. . .›› እያለች ስታጣድፈው ለቀናት ምግብ ቀምሳ የማታውቅ ትመስል ነበር፡፡ ሁኔታዋ አስገርሞኝ፣ ‹‹ሰሞኑን ምግብ አልበላሽም እንዴ?›› ስላት፣ ‹‹አንተ የደላህ ነህ፡፡ ምግብ በዓይኔ ከዞረ ዓመት አልፎኛል. . .›› እያለች የቀረበውን ምግብ ማጥረግረጉን ቀጠለች፡፡

አሃ! ነገር አለ፡፡ አሁን ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ እኔ ከሦስት ጉርሻዎች በላይ ሳላገኝ አንድ በየዓይነቱ ከተጋቢኖ ሽሮ ጋር ተደምስሷል፡፡ ለአስተናጋጁ በእጇ ምልክት ካሳየች በኋላ ሲመጣላት፣ ‹‹የአሁኑን ዓይነት ሁለት ምግብ ድገመን፤›› ብላ ጣቶቿን መላስ ጀመረች፡፡ ምግቡ እስኪመጣ የመጣላትን ኮካ በቄንጥ እየጠጣች ያለ ምንም ወሬ ተቀመጥን፡፡ ደግሞ የታዘዘው ምግብ ሲመጣ፣ በበፊቱ ፍጥነት መታ መታ አድርጋ ‹‹ዕፎይ!›› ብላ ተነፈሰች፡፡ እኔ ሁኔታዋ አስደንግጦኝ ሳያት፣ ‹‹ብላ እንጂ ለምን እንደ ሐበሻ በትዝብት ታየኛለህ?›› ስትለኝ ሳላስበው ሳቅ አመለጠኝ፡፡ እንደገና በመጀነን የቀረበውን ምግብ መጎራረስ ስትጀምር የእኔ የመብላት ፍላጎት ሞቶ ነበር፡፡ ለተወሰነ ጊዜ እንደ ነገሩ ከበላላች በኋላ እጇን ለመታጠብ ሄደች፡፡ እኔም ተከተልኳት፡፡ ከሁኔታዋ በጣም ፈጠን ስለምትል በጥንቃቄ እየተከታተልኩዋት ነበር፡፡

እጃችንን እየታጠብን፣ ‹‹ለመሆኑ ምግብ በዓይኔ ከዞረ ዓመት ሞላኝ ያልሽኝ እንዴት ነው የሚታመነው?›› ስላት ከጣሪያ በላይ እየሳቀች፣ ‹‹የምወስደው መድኃኒት ከቁርስ እስከ ምሣ ያለውን ጊዜ ዓመት ያደርግብኛል. . .›› ስትለኝ የባሰ ደነገጥኩ፡፡ እንደ ምንም ብዬ እየፈራሁ እየቸርኩ፣ ‹‹የምን መድኃኒት?›› ስላት፣ ጭንቅላቷን በሌባ ጣቷ ስትጠቁመኝ በቆምኩበት ደነዘዝኩ፡፡ ይህችን የመሰለች ልጅ ቤተሰብ የላትም? እንዴት ሆኖ ነው የአዕምሮ ሕሙማን መድኃኒት እየወሰደች አዲስ አበባን የሚያህል ከተማ ውስጥ መኪና የምትነዳው? ለካስ ይህች ቆንጆ በቅርቡ ነው ከአዕምሮ መታከሚያ የወጣችው፡፡ እስካሁን በውኔ ይሁን በቅዤት ለመለየት የቸገረኝ እስኪመስል ድረስ ቀንና ሌሊት ያባንነኛል፡፡ የሆነስ ሆነና ከእስር ቤትም ሆነ ከተለያዩ ቦታዎች የተሰባሰቡ ፖለቲከኞች በነገር ሲቆሳሰሉ፣ ከዚያ አልፎ ተርፎ ጠመንጃ እየተኮሱ ሰው ሲገድሉ፣ ገዳይን ጀግና ሲሉና አገር እንድትታመስ የነገር እሳት ሲያንቀለቅሉ በጤና አይመስለኝም፡፡ ለማንኛውም መታከምን የመሰለ ነገር የለምና ፖለቲከኞች እባካችሁ ራሳችሁን አሳምናችሁ ተመርመሩ፡፡ ችግር ካለም የሐኪም ምክርና ሕክምና ተከታተሉ፡፡  በእናንተ ያልታወቀ ችግር ምክንያት ሕዝብና አገር አይበጥበጡ፡፡

(ዓለማየሁ ውቤ፣ ከባልደራስ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...