Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክበመንግሥት ግዢዎች የጨረታ አወጣጥና አፈጻጸም ላይ ያጋጠሙ ችግሮች

በመንግሥት ግዢዎች የጨረታ አወጣጥና አፈጻጸም ላይ ያጋጠሙ ችግሮች

ቀን:

በበዛወርቅ ሺመላሽ 

የመንግሥት ግዢዎች አወሳሰናቸውና አፈጻጸማቸው ከብዙ አቅጣጫ ከፍተኛ ትኩረት የሚስቡ፣ የብዙ ሰው ዓይን የሚያርፍባቸው ነገሮች ናቸው፡፡ ከመንግሥት በጀት አንፃር እንኳን ብናየው ከአገሪቱ ዓመታዊ በጀት ከ60 በመቶ እስከ 70 በመቶ የሚሆነው ለመንግሥት ግዢ እንደሚውል የፀረ ሙስና ኮሚሽን ባወጣው ማስታወቂያ ጠቅሷል (ሪፖርተር ጋዜጣ 25 ጥቅምት 2011)፡፡ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውል የታቀደ ሀብት ሥርዓት የለሽ በሆነ መልክ “በሙስና ተተብትቦ” ለታቀደለት ዓላማ ሳይውል ቢቀር በአገርና በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ የታወቀ ነው፡፡ ይህ እንዳይደርስ ለመከላከል “የፌዴራል መንግሥት የግዢና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁ.649/2001” ወጥቶ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

አዋጁ የመንግሥት ግዢና የንብረት አስተዳደር በሕግ መሠረት መከናወኑን የሚቆጣጠር “ኤጀንሲ” አቋቁሟል፡፡ በግዢ ሒደት የሚያጋጥሙ ቅሬታዎችን የሚሰማ “ቦርድም” ጭምር፡፡ ከአዋጁ ሌላ የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በሰኔ 2002 (በታኅሳስ 2008 ተሻሽሏል) ያወጣው “የፌዴራል መንግሥት የግዢ አፈጻጸም መመርያ” አለ፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤትም የመንግሥት ንብረት የሚገዛና የሚያስወግድ “አገልግሎት” የተሰኘ አካል በደንብ ቁጥር 184/2002 አቋቁሞ ይገኛል፡፡

የመንግሥት ግዢዎች የብዙ ሰው ዓይን የሚያርፍባቸው ናቸው ብያለሁ፡፡ የአሜሪካ ኤምባሲ የሕዝብ አገልግሎት ሹም በአንድ ወቅት የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ሀብታቸውን “እንዲተክሉ” ከተፈለገ የግዢ ሥርዓቱና የጨረታ አወጣጡ በግልጽ የሚታይና የሚተነበይ እንዲሆን እንጠብቃለን ብሎ ነበር፡፡ በእንግሊዘኛ እንዲህ ነበር ያለው፣ “The only thing we ask for is a level playing field and transparency; transparent and predictable ways of procurement and bidding process . . .” በዚህ ረገድ ኢንተርናሽናል ገንዘብ አበዳሪዎችና ኢንተርናሽናል ባንኮች በየአገሩ የጨረታ ሕግ ላይ ልዩ ትኩረት ያሳርፋሉ፡፡ ተበዳሪ አገሮች የንብረት ግዢ ሕግ በሚያወጡበት ጊዜ እንደምሳሌ እንደ “ሞዴል” ሊጠቀሙ የሚችሉባቸውን የግዢ መመርያ እስከ ማዘጋጀት ይደርሳሉ፡፡ የእስያ ልማት ባንክ፣ የኢንተር አሜሪካ ልማት ባንክና የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. በ1983 በጥምረት ያዘጋጁትን መመርያ መጥቀስ ይቻላል፡፡

በኢንተርናሽናል ደረጃም ርዕሱ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ከመሆኑ የተነሳ UNCITRAL የተሰኘው የተባበሩት መንግሥታት የንግድ ሕግ ኮሚሽን እ.ኤ.አ. በ1994 ያወጣውን “ሞዴል” ሕግ እንደገና አሻሽሎ በ2010 አውጥቶታል (ካሮሊን ኒኮላስ የኮሚሽኑ የሕግ አማካሪ እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2010 የጻፈችውን ድርሳን ይመለከቷል)፡፡

    ከዚህ ከፍ ብሎ በጠቀስኩት የመንግሥት ግዢ አዋጅ ቁጥር 649/2001 መሠረት ስድስት (6) ዓይነት የግዢ ዘዴዎች ተዘርዝረዋል፡፡ እነዚህም አንደኛ ግልጽ ጨረታ፣ ሁለተኛ በመወዳደሪያ ሐሳብ መጠየቂያ የሚፈጸም ግዢ፣ ሦስተኛ በሁለት ደረጃ ጨረታ የሚፈጸም ግዢ፣ አራተኛ ውስን ጨረታ፣ አምስተኛ በዋጋ ማቅረቢያ የሚፈጸም ግዢና ስድስተኛ ከአንድ አቅራቢ የሚፈጸም ግዢ ናቸው፡፡ እነዚህን በአጭር በአጭሩ ለማስተዋወቅ ያህል፡-

ግልጽ ጨረታ (Open Tendering)

    ግልጽ ጨረታ Open Bidding ወይም Open Tendering የሚባለው ነው፡፡ ቃሉ እንደሚያመለክተው ጨረታው በማስታወቂያ በጋዜጣ፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን በሰፊው ተሰራጭቶ ብዙ ተወዳዳሪዎች የሚጠሩበትና የሚሳተፉበት ነው፡፡ ስለጨረታው ዝርዝር መግለጫ የያዘው ሰነድ የሚገኝበት ቦታ፣ ተጫራቾች ምላሽ የሚያቀርቡበት የጊዜ ገደብና ሥፍራ ሁሉ ተጠቅሶ በማስታወቂያው ይወጣል፡፡

 በግልጽ ጨረታ የሚካሄደው ግዢ የውጭ አገር አቅራቢዎች ለሚሳተፉበት ኢንተርናሽናል ግዢም ሆነ የአገር ውስጥ አቅራቢዎች ለሚሳተፉበት ብሔራዊ ግዢ ያገለግላል፡፡ የዕቃው ወይም የአገልግሎቱ ዋጋ ከተወሰነ እርከን ማለትም ለግንባታ ሥራ 150 ሚሊዮን ብር፣ ለዕቃ ግዢ 50 ሚሊዮን ብር፣ ለምክር አገልግሎት 7.5 ሚሊዮን ብር፣ ለአገልግሎቶች 21 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ ግዢው በኢንተርናሽናል ውድድር ሥርዓት እንዲካሄድ ሚኒስትሩ ያወጣው መመርያ ያስገድዳል፡፡ ማስታወቂያው ሰፊ ሥርጭት ባለው “ሚዲያ” እንዲለቀቅ፣ ለመጫረቻው ሰነድ ዝግጅት በቂ ጊዜ እንዲሰጥ፣ መግባቢያ ቋንቋው እንግሊዝኛ እንዲሆን ወዘተ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡

     በሌላ በኩል የሚገዛው ዕቃ ወይም አገልግሎት ዋጋ ላይ ከተጠቀሰው እርከን በታች በሆነ ጊዜ፣ ወይም ዋጋው ከዚያ በላይ ቢሆንም ምርቱ ወይም አገልግሎቱ በአገር ውስጥ ብቻ የሚገኝ በሚሆንበት ጊዜ ግዢው አገር ውስጥ ባሉ ተወዳዳሪዎች መካከል ይፈጸማል ማለት ነው፡፡

የመወዳደሪያ ሐሳብ በመጠየቅ የሚፈጸም ግዢ (Request for Proposals)

     ይህ የግዢ ዓይነት የምክር አገልግሎት ለመግዛት ሲፈለግ የሚያገለግል ነው፡፡ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቱ ግምታዊ የገንዘብ መጠኑ ከዘጠኝ መቶ ሺሕ ብር በላይ የሆነ የምክር አገልግሎት ሲፈልግ በቅድሚያ ፍላጎት ያላቸውን ዕጩ ተወዳዳሪዎች በመጋበዝ ጥሪ ያደርጋል፡፡ በጥሪው መሠረት ከቀረቡት ውስጥ ከሦስት ያላነሱ ከሰባት ያልበለጡ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ይመርጥና እነርሱ ብቻ የመወዳደሪያ ሐሳብ እንዲያቀርቡ ይጋብዛል፡፡ ቀጥሎም በጥራትና በዋጋ አወዳድሮ አሸናፊውን ይለያል ማለት ነው፡፡ የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር (ከዚህ በኋላ “ሚኒስቴር” እያልኩ የምጠራው) በሰኔ 2002 (በታኅሣሥ 2008 እንደተሻሻለ) ባወጣው መመርያ መሠረት የአገልግሎቱ ግምታዊ ዋጋ ከዘጠኝ መቶ ሺሕ ብር በታች በሆነ ጊዜ መሥሪያ ቤቱ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ከአቅራቢዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲመርጥ ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ (የአቅራቢዎች ዝርዝር የሚባለው በመንግሥት ዕቃ ግዢ መሳተፍ የሚፈልጉ አቅራቢዎች በኤጀንሲው ድረ ገጽ በተዘጋጀው ክፍል የተመዘገቡት ናቸው)፡፡

በሁለት ደረጃ ጨረታ የሚፈጸም ግዢ (Two Stage Tendering)

የመሥሪያ ቤቱን ፍላጎት በተሟላ ሁኔታ ለመግለጽ ባልተቻለበት ጊዜ ወይም ለሚገዙት ዕቃዎችና አገልግሎቶች ዝርዝር “ስፔሲፊኬሽን” ማዘጋጀት ባልተቻለበት ጊዜ መሥሪያ ቤቱ ጨረታውን በሁለት ምዕራፍ በመከፋፈል ግዢውን ማከናወን ይችላል፡፡ ይህ አካሄድ በሁለት ደረጃ ጨረታ የሚፈጸም ግዢ ይባላል፡፡

በዚህ የግዢ አካሄድ መሥሪያ ቤቱ በመጀመሪያው ዙር ተወዳዳሪዎች ዋጋን ያልጨመረ የመወዳደሪያ ሐሳብ እንዲያቀርቡ የጨረታ ጥሪ ያደርጋል፡፡ መሥሪያ ቤቱ የሚፈልገውን ዕቃ ወይም አገልግሎት አጠቃላይ በሆነ መልክ ገልጾ ሌላውን ዝርዝር ተወዳዳሪዎቹ ራሳቸው አሟልተው እንዲያቀርቡ በመጋበዝ፡፡ ከዚያም ተወዳዳሪዎቹ ያቀረቡለትን የመወዳደሪያ ሐሳቦች ከግዢ ፍላጎቱ ጋር ገምግሞ ሌላ የተሟላ ዝርዝር በማዘጋጀት ለሁለተኛ ጊዜ ተጫራቾች የመጫረቻ ሐሳባቸውን (ዋጋን ጨምሮ) እንዲያቀርቡ ጥሪ በማድረግ የሚከናወን ነው ማለት ነው፡፡ ይህ አካሄድ ላይ ከጠቀስኩት Request For Proposals ጋርና አንዳንድ ኩባንያዎች Request For Expression of Interest እያሉ ከሚያወጧቸው የጨረታ ጥሪዎች ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው መዘንጋት የለበትም፡፡

ውስን ጨረታ (Restricted Tendering)

    በመንግሥት ግዢ አዋጅ አንቀጽ 49 መሠረት ከሚከተሉት ሦስት ሁኔታዎች አንዱ ሲያጋጥም ግዢው በውስን ጨረታ ሊካሄድ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ይህም ማለት ጨረታው ሁሉም አቅራቢ ነኝ ባይ የሚጠራበትና የሚሳተፍበት ሳይሆን ውድድሩ በተወሰኑ/በተመረጡ (ቁጥራቸው ጥቂት በሆነ) አቅራቢዎች መካከል ብቻ የሚከናወን ማለት ነው፡፡

      የመጀመሪያው ሁኔታ ዕቃው ወይም አገልግሎቱ ከተወሰኑ አቅራቢዎች ዘንድ ብቻ የሚገኝ ሲሆን ነው፡፡ ሁለተኛው ሁኔታ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በመመርያ ካስቀመጠው የገንዘብ መጠን ያልበለጠ ሲሆን ነው፡፡ በመመርያ የተቀመጠው የገንዘብ መጠን ለግንባታ ሥራ ስድስት ሚሊዮን ብር፣ ለዕቃ ግዢ 1.5 ሚሊዮን ብር፣ ለምክር አገልግሎት ዘጠኝ ሚሊዮን ብር፣ ለሌላ አገልግሎት 1.2 ሚሊዮን ብር የሚል ነው፡፡ ሦስተኛው ሁኔታ፣ ጨረታ በተደጋጋሚ ወጥቶ “ተወዳዳሪ ያልተገኘ” ሲሆን ነው፡፡ የግዢው ዋጋ ላይ ከተቀመጠው የገንዘብ መጠን ያልበለጠ ሆኖ አቅራቢዎቹ ብዛት ያላቸው በሆነ ጊዜ “በአቅራቢዎች መዝገብ” ከተመዘገቡት ውስጥ ከአምስት ያላነሱ ተመርጠው እንዲወዳደሩ በማድረግ ይፈጸማል (ጊዜ መቆጠብና ወጪ መቀነስ ወሳኝ በሆነ ጊዜም ውስን ጨረታ ማካሄድ ይፈቀዳል ተብሎ በUNCITRAL ሞዴል ሕግ የተፈቀደው ሁኔታ በእኛ አዋጅ ውስጥ አልተካተተም)፡፡

በዋጋ ማቅረቢያ የሚፈጸም ግዢ (Request For Quotation)

    በዋጋ ማቅረቢያ (ጥሪ) የሚፈጸሙ ግዢዎች በጣም የተወሰኑ ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የገንዘብ ሚኒስትሩ በመመርያ ካወጣው ጣራ ያልዘለሉ መሆን አለባቸው፡፡ ይኸውም ለግንባታ ሥራ ግማሽ ሚሊዮን ብር፣ ለዕቃ ግዢ ሁለት መቶ ሺሕ ብር፣ ለምክር አገልግሎት አንድ መቶ ሃያ ሺሕ ብር፣ ለሌላ አገልግሎት ግዢ አንድ መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ፣ የሚገዙት ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ለገበያ የተዘጋጁ ወይም የታወቀ ገበያ ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ በውድድሩ ተሳታፊ የሚሆኑ ቢያንስ ሦስት አቅራቢዎች ከአቅራቢዎች ዝርዝር (Suppliers’ List) ውስጥ እንዲመረጡ ተደርጎ ለሚፈለገው ዕቃ ወይም አገልግሎት ዋጋ እንዲጠሩ (“ኮቴሽን” እንዲሰጡ) ይደረጋል፡፡ የገዢውን መሥሪያ ቤት ፍላጎት ያሟላውና አነስተኛ ዋጋ ያቀረበው ተወዳዳሪ አሸናፊ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ከአንድ አቅራቢ የሚፈጸም ግዢ (Direct Procurement)

    ይህ የግዢ ዓይነት በአዋጁ አንቀጽ 51 እና አንቀጽ 52 ተደንግጓል፡፡ ዕቃው ወይም አገልግሎቱ ከአንድ አቅራቢ ብቻ የሚገኝ ሲሆን፣ ከዚህ ብቸኛ አቅራቢ ግዢው ይከናወናል፡፡ ከመጀመሪያው አቅራቢ ተጨማሪ መለዋወጫዎች በሚያስፈልጉበት ጊዜ፣ ወይም ሥራው የግንባታ ዘርፍ ሆኖ በመጀመሪያው ውል ያልተካተቱ ድንገተኛ ተጨማሪ ሥራዎች ማሠራት ሲያስፈልግ፣ ወይም ግዢ የተከናወነበት ዓይነት ሥራ በድጋሚ እንዲሠራ ወይም እንዲቀርብ ሲያስፈልግ፣ ወይም በጣም አስቸኳይ በቶሎ ካልተሠራ ችግር የሚፈጥር ሆኖ በበላይ ኃላፊ የተፈቀደ ሲሆን፣ ከአንድ አቅራቢ ግዢውን ማከናወን ይቻላል፡፡

    ከዚህ ቀጥሎ የመንግሥት ግዢ አዋጅ በተለይ ጨረታ አወጣጥና አፈጻጸምን አስመልክቶ የደነገጋቸው ከቶውኑ ሊዘለሉ የማይገባቸው መራኅያንን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

ሀ. የመንግሥት ግዢ ሕግጋት ዓላማ

ስለመንግሥት ግዢ ሕግና ሥርዓት ሲነገር ማስፈጸም ወይም መተግበር የሚፈለጉት ዓላማዎች ምንድን ናቸው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ አጠቃላይ ዓላማው የመንግሥት ገንዘብ የሕዝብ ገንዘብ በመሆኑ ያላግባብ እንዳይባክን መከላከል ሆኖ ዓላማዎቹ በዝርዝር ሲታዩ፣

በግዢ የሚቀርበው ተፈላጊ ዕቃ ወይም አገልግሎት ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ መቅረቡን ማረጋገጥ ነው፣

  • ዕቃው ወይም አገልግሎቱ አቅምና ችሎታ ባለው አካል በሚፈለግበት ወቅትና ጊዜ መቅረቡን ማረጋገጥ ነው፡፡
  • ብዙ አቅራቢዎች ስለሚኖሩ በግልጽ በሚታዩ መሥፈሪያዎች ያለአድልዎ እንዲፎካከሩ ማድረግ ናቸው፡፡

እነዚህን ዓላማዎች በተግባር ማስፈጸም የሚቻለው ጨረታ በማውጣትና አሸናፊውን በሥርዓት በመምረጥ ነው፡፡ በመሆኑም የጨረታ አወጣጥ ደንቦች ለመንግሥት ግዢ ሒደት ፍጹም ወሳኝ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

ለ. የጨረታ ሰነድ አዘጋጅቶ ማሠራጨት

ገዢው የመንግሥት አካል እንዲቀርብለት የሚፈልገውን ዕቃ ወይም አገልግሎት ዓይነት ዝርዝር “ስፔሲፊኪሽን” እና በምን ያህል ጊዜ ውስጥ መቅረብ እንዳለበት ወዘተ በመጥቀስ የጨረታ ሰነድ ያዘጋጃል፡፡ የጨረታው ሰነድ ለአቅራቢዎች በተለያየ መንገድ እንዲሠራጭ ያደርጋል፡፡ ይህ ያስፈለገበት ምክንያት ችሎታ ያላቸውና ተፎካካሪ ዋጋ ማቅረብ የሚችሉ አቅራቢዎች እንዳይዘለሉ በማሰብ ነው፡፡

የጨረታ ሰነድ የገዢው መንግሥታዊ አካል ፍላጎት መግለጫ ነው፡፡ (የአዋጁን አንቀጽ 37 ይመለከቷል)፡፡ በገዢና በተጫራቹ መካከል ሊፈረም የሚችለውን “ኮንትራት” ይዘት፣ የዕቃውን “ስፔሲፊኬሽን”፣ ተጫራቹ ማሟላት የሚገባውን የብቃት መሥፈርት፣ ለእያንዳንዱ መሥፈሪያ የሚሰጠውን ነጥብ ወዘተ የያዘ ነው፡፡ ይህ የፍላጎት መግለጫ ሰነድ (ግብዣ ሊባልም ይችላል) ለተጫራቹ ሲደርስ ፉክክር ውስጥ መሳተፍ የሚፈልግ ተጫራች በተፈቀደው የጊዜ ገደብ ውስጥ አሸንፍበታለሁ የሚለውን የመጫረቻ ሐሳብ (“ፕሮፖዛል”) ያስገባል፡፡ ገዢው መሥሪያ ቤት ብቃት ያለው ተጫራች በሚፈለገው ጊዜ ውስጥ ከሌሎች አቅራቢዎች ዝቅ ባለ ዋጋ አቀርባለው የሚል ተጫራች ሲያገኝ የሐሳብ መገጣጠም ተፈጥሯልና (“ሚቲንግ ኦፍ ዘ ማይንድ”) ኮንትራቱ ይፈረማል ማለት ነው፡፡

ሐ. የጨረታ ማስከበሪያ

ጨረታውን ያወጣው የመንግሥት አካል ለጨረታ ሰነድ ዝግጅት ገንዘቡን፣ ጊዜውን፣ ጉልበቱን ካፈሰሰ በኋላ ለኮንትራቱ ፊርማ ሲዘጋጅ ጨረታ አሸናፊ ተብዬው ግን ኮንትራቱን ከመፈረም ወደ ኋላ ሊያፈገፍግ ስለሚችል ይህንን አደጋ ለመከላከል የተቀየሰው ዘዴ ተጫራቹ የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና (“ቢድ ቦንድ”) እንዲያሲዝ ወይም እንዲያቀርብ በመጠየቅ ነው፡፡

የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና ዝርዝር የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ባወጣው መመርያ ተደንግጓል (የመመርያውን አንቀጽ 16.16 ይመለከቷል)፡፡ ይኸውም ዋስትናው በጥሬ ገንዘብ ወይም ከታወቀ ባንክ በሚሰጥ የክፍያ ማዘዣ ቼክ ሆኖ መጠኑን በሚመለከት ከጠቅላላ ግዢው ከ0.5 በመቶ ማነስ የለበትም፣ ከሁለት በመቶ መብለጥ የለበትም ወይም ከብር 500,000 (አምስት መቶ ሺሕ) መብለጥ የለበትም በሚል ተቀምጧል፡፡

የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና ጥያቄ ኮንትራት ላለመፈረም ወደ ኋላ ለሚል ተጫራች ብቻ ሳይሆን እንዲያቀርብ የተጠየቀውን የውል ማስከበሪያ ዋስትና ላላቀረበም ተፈጻሚ ይሆናል፣ ማለትም ተጫራቹ ያስያዘው ዋስትና ይወረሳል ማለት ነው፡፡

መ. የውል ማስከበሪያ ዋስትና

የውል ማስከበሪያ ዋስትናንና የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትናን በወጉ መለየት ያስፈልጋል፡፡ የውል ማስከበሪያ ዋስትና (ፐርፎርማንስ ቦንድ) ውል የፈረመው ተጫራች በገባው ውል መሠረት ግዴታውን እንዲፈጸም ማስገደጃ ሲሆን፣ የጨረታ ማስከበሪያ ግን ከፍ ብሎ እንደተገለጸው አሸናፊ የሆነው ተጫራች ውል እንዲፈርም ማስገደጃ ነው፡፡

የውል ማስከበሪያ ዋስትና በመንግሥት ግዢ አዋጅ አንቀጽ 46 ላይ የሠፈረ ሲሆን፣ ዝርዝሩ ደግሞ የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ባወጣው መመርያ አንቀጽ 16.25 ተደንግጓል፡፡ ውሉን የፈረመው ተጫራች እንዲያሲዝ የሚጠየቀው የዋስትና መጠን ከውሉ ጠቅላላ ዋጋ አሥር በመቶ ማነስ የለበትም፡፡ ደግሞም ውሉን በፈረመ በ15 ቀን ውስጥ የውል ማስከበሪያውን ማስያዝ አለበት፡፡ በውሉ መሠረት ግዴታውን ከፈጸመ ዋስትናው ይመለስለታል፡፡ ካልፈጸመ ደግሞ በዋስትና ያስያዘው ገንዘብ ይወረሳል ማለት ነው፡፡

ሠ. አሸናፊ ተጫራች የመምረጥ ሒደት

በጨረታ አወጣጥ ሒደት ትልቁ ሥራ “ተገቢውን ሰው” መምረጥ ነው፡፡ ተገቢ የሚባለው ተጫራች “የቴክኒክ” መመዘኛዎችን ማሟላት አለበት፡፡ አነስተኛ ዋጋም ያቀረበ መሆን አለበት፡፡ ተገቢ የሚባለውን ተጫራች ለመምረጥ ደግሞ በቅድሚያ የማማረጫ መሥፈሪያዎችን ለይቶ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ የሚፈለገው ሥራ አውራ ጎዳና መገንባት ከሆነ ተጫራቹ ሊኖረው የሚገባ የቴክኒክ ብቃት፣ ቀደም ሲል ሠርቶ ያስረከባቸው ፕሮጀክቶች ብዛት፣ የካፒታልና የሰው ኃይል መጠን ወዘተ ተለይተው መቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡ አዋጁ ከዚህ አልፎ አንቀጽ 37 ለእያንዳንዱ መሥፈሪያ የተሰጠው ነጥብ (ይኼም ማለት ከመቶ ስንት እጅ እንደተሰጠው) መገለጽ እንዳለበትና ይኼም በጨረታ ሰነዱ ውስጥ መሥፈር እንዳለበት ደንግጓል፡፡ ሚኒስቴሩ ያወጣው መመርያም (አንቀጽ 16.19) ሥራው ከአድልዎ የፀዳ እንዲሆን በማቀድ “ጨረታ ሰነዱ ውስጥ ከተገለጸው መሥፈርት ውጭ ግምገማ ማድረግ አይፈቀድም” በማለት ደንግጓል፡፡ አሁንም አሠራሩ ፍትሐዊ እንዲሆን በማቀድ “አሸናፊ ተጫራቹ ባቀረበው ዋጋና ከዋጋ ጋር ግንኙነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ” ከአሸናፊ ተጫራች ጋር ድርድር ማድረግ እንደማይቻል አዋጁ በአንቀጽ 45.2 ደንግጎ ይገኛል፡፡

ከጨረታ ሒደት ጋር የተያያዙ መሠረታዊ መራኅያን ከብዙ በጥቂቱ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ናቸው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ በጨረታ አወጣጥና አፈጻጸም ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን አነሳለሁ፡፡

በጨረታ አወጣጥና አፈጻጸም ላይ ያጋጠሙ ችግሮች

ሀ. የጨረታውን ሕግ በውል አለማወቅ ችግር

በአንድ ወቅት በሪፖርተር እንግሊዝኛ ጋዜጣ እንደተዘገበው ሻኪል የተባለ ስንዴ አቅራቢ ድርጅት የውል ማስከበሪያ ዋስትና አላቀረበም ተብሎ ውሉ እንደተሰረዘበትና አቤቱታውንም ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር እንዳቀረበ ተጠቅሷል፡፡ በመሠረቱ የውል ማስከበሪያ ዋስትና ውል በተፈረመ ጊዜ አሊያም ሚኒስቴሩ ባወጣው መመርያ መሠረት በ15 ቀናት ውስጥ ማቅረብ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ አቅራቢው ያንን ካልፈጸመ አሲዞት የነበረውን የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና በውርስ ለመንግሥት ገቢ ማድረግና ቀጣይ ዕርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የሻኪልና የስንዴ አቅርቦቱ ጉዳይ ለረጅም ጊዜ ተንጠልጥሎ እንደቆየ በተደጋጋሚ በጋዜጣው ላይ ተዘግቧል፡፡ አቅራቢው አቤቱታ ካለው በአዋጁ መሠረት ለተቋቋመው “የአቤቱታ አጣሪ ቦርድ” ማቅረብ ሲገባው፣ ይህ ተዘልሎ አቤቱታው ለሚኒስትሩ እንደቀረበ ተዘግቧል፡፡

በሌላ ጊዜ አሁንም በዚሁ ጋዜጣ በጣም ከፍተኛ ሰብዓዊ ሰቆቃ የሚያስከትል ችግር (Grave Humanitazian Crisis) ባጋጠመበት ወቅት ስድስት መቶ ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለመግዛት ኢንተርናሽናል ጨረታ እናወጣለን ብለው የመንግሥት ንብረት ግዢ መሥሪያ ቤት (“አገልግሎት” ተብሎ የተሰጠውን መጠሪያ መጠቀም አልፈቀድኩም) ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል ተብሎ ተዘግቧል፡፡ እንደዚህ ዓይነት አስቸኳይና በአገር ደረጃ “ሂዩማኒቴሪያን ክራይሲስ” የሚፈጥር ሁኔታ ሲያጋጥም በውስን ጨረታ እንኳን ባይፈቀድ ከአንድ አቅራቢ ስንዴውን መግዛት እንደሚቻል በአዋጁ ተደንግጎ እያለ፣ ከቶውንም “በቂ ምክንያት” እስካለ ድረስ ከተፈቀዱት የግዢ ሥርዓቶች ውጪ ኤጀንሲውን አስፈቅዶ ስንዴውን መግዛት ሲቻል (አዋጁን አንቀጽ 16.5 ይመለከታል) ረጅም ጊዜ የሚፈጀው ኢንተርናሽናል ጨረታ መመረጡ ወይ ከፍርኃት የመነጨ ነው ወይ ሕጉን ካለማወቅ የመጣ ነው ያስብላል፡፡ (በጭንቅ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት አማራጭ መንገድ ስለመኖሩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያውቃሉ ማለት አይቻልም፣ ስለማይጠቀሙበት)፡፡

የግንባታ ሥራ ተቋራጮች ማኅበር እ.ኤ.አ በታኅሳስ 2011 የውጭ አማካሪ ቀጥሮ ባሠራው ጥናት የመንግሥት ንብረት ግዢ የሚፈጽሙ መሥሪያ ቤቶች ምንም እንኳን ሕጉን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት የተጣለባቸው ቢሆንም፣ በአዋጅ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን እንደማያከብሩ ምክንያቱ ደግሞ የግዢ ሕጉን (የጨረታ ደንቡን ጨምሮ ማለት ነው) አለማወቃቸው እንደሆነ በጥናቱ አረጋግጧል (Baseline Survey, 2011, P. 46)፡፡

ለ. ያለጨረታ ግዢ ማከናወን

ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ከፌዴራል መንግሥት በጀት ተመድቦለት የሚተዳደር የመንግሥት መሥሪያ ቤት የመንግሥት ግዢ አዋጁን መመርያውን ሁሉ የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበት የታወቀ ነው፡፡ በተለይ የመሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ ደግሞ በግዢና በንብረት አስተዳደር ሥራ የሚመድባቸው ሠራተኞች በሙያው በቂ ሥልጠናና ክህሎት ያላቸው መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት አዋጁ በአንቀጽ 8 (ሐ) ደንግጎ ይገኛል (ለብሔራዊ ደኅንነትና ለአገር መከላከያ የሚቀርቡ ግዢዎች በሌላ ልዩ መመርያ እንደሚስተናግዱ ልብ ይሏል፣ አንቀጽ 1.2 (ሀ))፡፡ 

ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ስንቶቹ (ከመቶ ስንት እጅ) ሕጉን እያከበሩ ይገኛሉ? ስንቶቹስ እየጣሱት ነው? የሚል ጥያቄ ቢነሳ መልስ ለማግኘት ከፍ ብዬ ከጠቀስኩት Baseline Survey ውጪ ሌላ ራሱን የቻለ ጥናት የሚያስፈልገው ነው፡፡ ያ ጥናት በእጅ ሳይገባ አብዛኛዎቹ እያከበሩት ነው ወይም አብዛኛዎቹ እየጣሱት ነው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የመንግሥት ግዢ አዋጅ ከሚደነግገው ውጪ አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች በተደጋጋሚ ያለጨረታ ግዢ መፈጸማቸው ሲነገር፣ ሲሰማ ግርምትን መጫሩ አይቀርም፡፡

ለምሳሌ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ባካሄደው ጥናት “በተገጣጣሚ ሕንፃ አካላት ማምረቻ ድርጅት መመርያውን (ሕጉን) በጣሰ መልኩ በተደጋጋሚ ሥራዎች ያለጨረታ ውድድር በቀጥታ ለግለሰቦች የሚሰጥበት ሁኔታ መኖሩን የኮሚሽኑ የጥናት ውጤት እንደሚያሳይ” በናሽናል ኮንስትራክሽን መጽሔት (ሰኔ 2009) ተዘግቧል፡፡

ሌላው በእንግሊዝኛ ምኅፃረ ቃል “ሜቴክ” በመባል የሚጠራው የብረታ ብረት ኮርፖሬሽን ከ2004 እስከ 2010 ባለው ጊዜ ውስጥ የሠላሳ ሰባት ቢሊዮን ብር የውጭ አገር ግዢ ሲፈጽም ግዢዎቹ በሙሉ የተከናወኑት ያለጨረታ እንደሆነ፣ የአገር ውስጥ ግዢዎችም ቢሆኑ ያለጨረታ “አጋር” ብሎ ከሰየማቸው ግለሰብ ነጋዴዎች ከገበያ ዋጋ በብዙ እጥፍ በሚበልጥ ግዢዎች ሲፈጽም እንደነበር በወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከሰጡት መግለጫ መረዳት ተችሏል (አዲስ ዘመን 5 ኅዳር 2011)፡፡

ሐ. በተወዳዳሪዎች መምረጫ መሥፈርት ላይ ያለ ችግር

በጨረታ የተካፈሉ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ የሚያገለግሉ መሥፈሪያዎችን በጨረታ ሰነዱ ውስጥ መጥቀስና ለእያንዳንዱ መሥፈሪያ የተሰጠውን ነጥብ መግለጽ እንደሚገባ፣ እንዲሁም መሥፈሪያዎቹ በተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመሠረቱ መሆን እንደሚገባቸው፣ እንዲሁም “በጨረታ ሰነድ ያልተመለከተ የመወዳደሪያ መሥፈርት በጥቅም ላይ ሊውል እንደማይችል” በመንግሥት ግዢ አዋጅ አንቀጽ 37 (ቀ)፣ አንቀጽ 43 (8) (ለ)፣ አንቀጽ 43 (6) ተደንግጓል፡፡ የሥራ ተቋራጮች ማኅበር ባስጠናው “ቤዝላይን ሰርቬይ” (በገጽ 41 እና 86) በመሥሪያ ቤቶች የሚዘጋጁት የማወዳደሪያ መሥፈርት ግን ተጨባጭነት የጎደላቸው፣ ለአንዳንድ ተወዳዳሪዎች የሚያደሉ፣ በሰነዱ ከተቀመጡት መሥፈርት ውጪ በሌሎች መመዘኛዎች ግምገማ እንደሚካሄድ ለጥናቱ ግብዓት የሰጡ የሥራ ተቋራጮች ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ በኅዳር 2008 ባዘጋጀው “ብሮሹር” በዚሁ ርዕስ ዙሪያ የሚከተለውን አሥፍሯል፡፡  

“የጨረታ ሰነድ ወይም የቅድመ ብቃት የማወዳደሪያ መሥፈርቶች (Sic) ግልጽነት የሚጎላቸው መሆኑ፣ ለአተርጓጎም የማይመች በተለያየ መልኩ መተርጎም በሚያስችል ደረጃ ያሉ አገላለጾችን መጠቅም፣ ለሥራው ተመጣጣኝ ያልሆኑ የመመዘኛ መሥፈርትና ደረጃ ማስቀመጥ፣ . . . የተወሰኑ ተወዳዳሪዎችን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሌሎች የመሥራት ብቃትም ሆነ አቅም ያላቸውን ተጫራቾች በቅድመ ብቃት ስም እንዲወድቁና የፋይናንስ የውድድር ምኅደር እንዲጠብ የሚያደርግ ነው፡፡”

ሌላም አለ፡፡ ናሽናል ኮንስትራክሽን መጽሔት (ሐምሌ 2009) የፀረ ሙስና ኮሚሽን በቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ላይ ያዘጋጀውን ሪፖርት ጠቅሶ በማማረጫ መሥፈርት ዙሪያ ያለውን ድክመት ዘርዝሯል፡፡ እንዲህ በማለት፡-

  1. የሥራ ተቋራጩ የሚያንቀሳቅሰው ገንዘብና ሀብት ሀምሳ በመቶ ነጥብ ተመድቦለታል፡፡ ይህ ግን የሥራ ውጤታማነትን የሚያሳይ አይደለም፣
  2. መልካም ሥራ አፈጻጸም ከፍተኛ ነጥብ ሊመደብለት ሲገባ አምስት በመቶ ብቻ ተመድቦለት ይገኛል፣
  3. የግንባታ ማሽነሪ አቅርቦት ዓይነትና ሁኔታ በግልጽ መቀመጥ ሲገባው ይህ አልተደረገም፣
  4. የተዘጋጀው የማማረጫ ሰነድ በኢንተርፕራይዙ መሪዎች ወይም የበላይ አካል መጽደቅ ሲገባው ይህ አልተደረገም፡፡

መ. ግዙፍ የጨረታ ሕግ ጥሰቶች

የመንግሥት ግዢ አዋጅ አንቀጽ 43 (8) “በጨረታ ግምገማ የቴክኒክ መመዘኛዎችን ማሟላቱ የተረጋገጠና አነስተኛ ዋጋ ያቀረበ ተጫራች” በጨረታው አሸናፊ ሆኖ እንደሚመረጥ በግልጽ ደንግጓል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ “ዓይን ባወጣ” ጥሰት አሥራ አራት የትንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ኃላፊዎች ዝቅተኛ ዋጋ ላቀረበ ተጫራች ሳይሆን ከፍተኛ ዋጋ ላቀረበ ተጫራች የአሸናፊነት ውሳኔ ሰጥተዋል ተብሎ ክስ እንደቀረበባቸው በፎርቹን ጋዜጣ ወጥቷል፡፡

ተጫራቾች ባቀረቡት የመጫረቻ ዋጋ ላይ መደራደር ወይም ዋጋቸውን እንዲለውጡ/እንዲያሻሽሉ መጠየቅ ፈጽሞ የተከለከለ ነው (የአዋጁን አንቀጽ 43 (7) እና የመመርያውን አንቀጽ 16.22 (2) ይመለከቷል)፡፡ በተግባር ግን የሚሠራው ይህን ድንጋጌ በመጣስ ነው፡፡ እንደ እንግሊዝኛው ሪፖርተር ጋዜጣ ከሆነ የኢትዮጵያ የግብርና ንግድ ኮርፖሬሽን አግሪ ኮሞዲቲስ ኤንድ ፋይናንስ “ዜድቲኢ” ለሚባል ድርጅት አምስት መቶ ሺሕ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ በ179.67 ሚሊዮን ዶላር አቀርባለሁ በማለቱ አሸናፊ መሆኑን ከገለጸለት በኋላ ዋጋውን እንዲቀንስ ጠይቆ አቅራቢው 21.1 ሚሊዮን ብር እቀንሳለሁ እንዳለና ይህም ትልቅ የገንዘብ ማዳን እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ሠ. ከጨረታ ማስከበሪያና ከውል ማስከበሪያ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥም ችግር

ስለጨረታ ማስከበሪያና ስለውል ማስከበሪያ ይዘት ከላይ ገልጫለሁ፡፡ አሸናፊ መሆኑ የተነገረው አቅራቢ ውል ካልፈረመ የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትናውን ወዲያው ለመንግሥት አስገብቶ ቀጣይ ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ውል ፈርሞ በ15 ቀናት ውስጥ የውል ማስከበሪያ ዋስትናውን ካላመጣ አሁንም ያንን ለመንግሥት አስገብቶ ወደ ቀጣይ ዕርምጃ መሄድ ግድ ይላል፡፡

አሁን ሰሞኑን በእንግሊዝኛው ሪፖርተር ጋዜጣ እንደሠፈረው “ዋይፋግ” የተባለ ድርጅት ከወራት በፊት 400,000 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለማቅረብ ውል ከፈረመ በኋላ ተፈላጊውን አሥር ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውል ማስከበሪያ ሳያቀርብ ለወራት ዘግይቶ እንደነበር፣ በዚህም ሳቢያ የስንዴ ግዢው ለረጅም ጊዜ እንደተጓተተ አሁን ግን ተፈላጊውን ዋስትና እንዳቀረበ ዘግቧል፡፡ አዋጁንና መመርያውን ተከትሎ ከፍ ብዬ እንደጠቆምኩት ግዢውን በቶሎ በተቀላጠፈ መንገድ ማካሄድ ሲገባ፣ ይኼን የመሰለ “ዝርክርክነት” ለምን ሊከሰት እንደቻለ ሊመረመር የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር የሚመሳሰል በፎርቹን ጋዜጣ ወጥቷል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ኤጀንሲ 50,084 ሜትሪክ ቶን “ፌሮ” ለመግዛት ያወጣው ጨረታ ሰባት ወር እንደፈጀ፣ “ስቲሊ አርኤምአይ” የተባለ ኩባንያ በአንድ ቢሊዮን ብር ለማቅረብ ቢያሸንፍም፣ በገንዘብ ምንዛሪ ለውጥ ምክንያት ዕቃውን ማቅረብ እንዳልቻለ ተዘግቧል፡፡

ሌላም ምሳሌ አለ፡፡ የክትትልና የአፈጻጸም ክፍተት የታየበት፡፡ ከሳሽ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ተከሳሾች እነ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በሆኑበት መዝገብ (መዝገብ ቁጥር 162106 – ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንበር መጽሔት 18ኛ መንፈቅ የካቲት/መጋቢት 2009) ከሳሹ የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትናው ጸንቶ ባለበት ጊዜ ውስጥ ተጫራቹን ሐውክ ኢንተርናሽናል ድርጅት ግልጽ በሆነ ቋንቋ አሸናፊነቱን ገልጦ ውል እንዲፈርም መጠየቅ ሲገባው፣ “ለቅድመ ውል ውይይት” መጋበዙ ከዚያም አልፎ የጨረታ ማስከበሪያው ጊዜ እንዲራዘም መጠየቁ በፍርድ አደባባይ እንዲረታ አድርጎታል፡፡

ረ. የሙስና፣ በጨረታ ሒደት የመመሳጠር ችግር

የጨረታና የሙስና ነገር ሲነሳ የ“ሜቴክ” ሕገወጥ ሥራዎች እንደምሳሌ ይጠቀሳሉ፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ ምልልስ (5 ኅዳር 2011 አዲስ ዘመን ጋዜጣ) “ለአብነት ያህል አንድ ድርጅት በአንድ ጊዜ ብቻ የ205 (ሁለት መቶ አምስት) ሚሊዮን ብር ግዢ ያለጨረታ ከኮርፖሬሽኑ ፈጽሟል” ብለው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ይኼ “ጉድ” የሚያሰኝ ነው፡፡

ከዚህ ርዕስ ጋር በተያያዘ ጌታሁን ዓለሙ የሚባል ጸሐፊ በካፒታል ጋዜጣ  በሕንፃ ግንባታ ንግድ ሥራ “ሪል ስቴት” ጨረታ የሚፈጸሙትን አሳፋሪ ሙስናዎች እንዲህ ብሎ ገልጾታል፡፡

“…Tenders are hijacked. This is particularly a known practice for large scale construction. A group of contractors/bidders gang up and decide what to put as an offer in each bid and know who will be the winning bidder. This will do two things. One, as all are bidding any ways, it will allow them to act as if they are competing with the outside world but in essense it is an orchestrated action. Secondly, the winner bidder will have a jacked up price but it is the lower than its set up counterparts. The winning contractor pays the rest some amount, which is known as RENT (mostly added to the project bid proposal inflated price) and everyone is happy except the project itself …”  

በጥሩ አማርኛ ለመተርጎም ያስቸግራል፡፡ ጨረታ ሲወጣ የውሸት ተወዳዳሪዎች ዋጋቸውን ሰቅለው ያቀርባሉ፡፡ ከእነሱ ውስጥ አንዱ እንዲያሸንፍ የተፈለገው ዋጋውን ዝቅ አርጎ ያቀርብና አሸንፈሃል ሲባል የተወሰነ ገንዘብ (“ኪራይ” በመባል የሚጠራ) ለነኚያ አብረው ለዶለቱት ጓደኞቹ ይሰጣቸዋል የሚል ነው ባጭሩ፡፡ “Oh Shame! Where is thy blush?” (አልቦ ዘመድ፣ ብርሃኑ ድንቄ 1987 ገጽ 24) ማለት ይኼኔ ነው፡፡ [ብርሃኑ ድንቄ የሼክስፒርን ጥቅስ ሐምሌት ውስጥ የሚገኘውን አጉል አርጎ ተርጉሞታል፡፡ “ኃፍረት ሆይ! ቅላትሽ ወዴት አለ?” በማለት፡፡ “ኃፍረት ሆይ!  አቤት ድርቅናሽ” ብሎ  ቢተረጉመው ይሻል ነበር]፡፡

ከጨረታ አወጣጥና አፈጻጸም ጋር የተዛመዱ ችግሮችን አጠቃላይ በሆነ መልኩም ቢሆን ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ፡፡ የመንግሥት ግዢ አዋጁን ከነኮተቱ ያለማወቅ ችግር፣ አሊያም ጨርሶ ሕጉ ከሚደነግገው በተቃራኒ ለምሳሌ ዝቅተኛ ዋጋ ካቀረበው ጋር ሳይሆን ከፍተኛ ዋጋ ካቀረበው ተጫራች ጋር ውል መዋዋልን የመሳሰሉ ጥሰቶች ዓይተናል፡፡ የመንግሥት ግዢ ሕግ የድንጋጌዎቹ የአንቀጾቹ መብዛት በጠቅላላ (የመከላከያ ግዢ መመርያን ሳይጨምር) ከአንድ ሺሕ በላይ የመሆናቸው ነገር ለችግሩ አንድ ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ሕጉ እንደገና ተከልሶ ቢታይ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በክለሳው ጊዜ ሕጉ ዋና ዋና አንኳር የሆኑ ድንጋጌዎችን ለይቶ አስገዳጅ እንዲሆኑ፣ ሌሎች ዝርዝር ድንጋጌዎችን ግን የአስገዳጅ ሳይሆን “የጠቋሚ” ወይም “የአመላካች” መልክ እንዲላበሱ በማድረግ ወይም ሌላ አማራጭ በመሻት ሊከናወን ይችላል፡፡

በመንግሥት ግዢ ማለት መንግሥት ዕቃ ወይም አገልግሎት በሚገዛበት ሒደት ብዙ ተዋናዮች ናቸው የሚራወጡት፡፡ በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ የግዢ “ዲፓርትመንት” አለ፡፡ የግዢ አጽዳቂ ኮሚቴ አለ፡፡ ጊዜያዊ የግዢ ገምጋሚ ኮሚቴ አለ፡፡ የመሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ አለ፡፡ ከፍተኛ ግዢዎችን የሚፈጽም “አገልግሎት” የሚባል ራሱን የቻለ ሌላ መሥሪያ ቤት አለ፡፡ የመንግሥት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ አለ፡፡ የእነዚህ ሁሉ አለቃ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ ተቋማት ባሉበት ነው እነዚህ ሁሉ ከላይ የጠቀስኳቸው ጥፋቶች የተከሰቱት፡፡ እናም የግዢው ሒደት መዋቅር እንደገና ሊፈተሽ ይገባዋል፡፡ እዚህ ላይ የኬንያን ልምድ መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡ በኬንያ በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር ያለ አንድ “ዲፓርትመንት” ነው የመንግሥት ግዢውን ሥራ የሚቆጣጠረው፡፡ ዋናው ዳይሬክተር ሁለት ምክትሎች አሉት፡፡ አንዱ ምክትል ዳይሬክተር የቁጥጥር፣ የሥልጠናና የግምገማ ሥራዎችን ይከታተላል፡፡ ሌላው ምክትል ዳይሬክተር የሕግና የፖሊሲ ጉዳዮችን ይከታተላል፡፡ ዲፓርትመንቱ ግዢ አያካሄድም፡፡ (Masot, ICLQ, V.54 No. 3 (July 2005)) በርግጥ የኬንያን አካሄድ እንቅዳ የሚል ሐሳብ የለኝም፡፡ ብዙ አማራጮች ስለሚኖሩ መዋቅሩ ይፈተሽ ለማለት ነው፡፡

ሌላው ስለመንግሥት ዕቃ ግዢ የሚደነግጉ ሕጎችን በስፋት ማስተማር፣ ተከታታይ ሥልጠናዎችን መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በኮሌጅ ደረጃ ጭምር እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት “ሰብጀክት” ለተማሪዎች መሰጠት አለበት፡፡ በዚህ ረገድ በአልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ procurement and supply management የሚል ትምህርት በኮሌጅ ደረጃ መስጠት መጀመራቸው መልካም ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡

የግዢው ሒደት ለጥቅማ ጥቅምና ለጉቦ የተጋለጠ ስለሆነ የቅርብ ክትትል፣ የቅርብ ቁጥጥር ያስፈልገዋል፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ያሉ ኦዲተሮች “ሒሳብ ወጣ ሒሳብ ገባ” በሚል ሳይሆኑ ግዢዎች ሕጉን በመተላለፍ በተፈጸሙ ጊዜ ያንን ማጋለጥ ይኖርባቸዋል፡፡ የመሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ ግዢዎች “በአዋጅ የተመለከቱ የግዢ መርሆችን የጠበቁ መሆናቸውን ያረጋግጣል” ተብሎ የተጣለበትን ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡ ካልተወጣ በአዋጁ አንቀጽ 77 (1) (ሐ) መሠረት መከሰስና መቀጣት አለበት፡፡ ሌሎቹም የግዢ ክፍል ሠራተኞች እንዲሁ አለበለዚያ ሕጉ ለምን ወጣ?

በሌላ በኩል የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊና ሌሎች ሠራተኞች ሕጉን ቢተላለፉ መከሰስና መቀጣት አለባቸው እንዳልኩት ሁሉ የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊና የግዢ ሠራተኞች ሕጉን ተከትለው በመሥራት ጥሩ ውጤት ባበረከቱ ጊዜ ሽልማትና ሰርቲፊኬት ሌላም ማነቃቂያ በመስጠት ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ ነውርን ለሚጠየፍ ሠራተኛ ልዩ ክብር ብንሰጥስ ምናለበት?

ለመንግሥት ግዢ ክንውን ብዙ ሀብት የምናፈስበት የኢኮኖሚ ዘርፍ ስለሆነ ልዩ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል፡፡ በመሆኑም አዋጁን በትክክል ሥራ ላይ ያላዋሉ ኃላፊዎችንና የግዢ ሠራተኞችን ጥፋት የሚከታተል፣ የሚመረምር ልዩ የምርመራ “ስኳድ” በፖሊስ መሥሪያ ቤት ማቋቋም ወቅታዊና አስፈላጊ ነው፡፡

በመንግሥት ግዢዎች ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በከፊልም ቢሆን ለመቅረፍ በአዲስ መነፅር መቃኘት ያስፈልጋል የምለው ለዚህ ነው፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...