Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ሪፖርት ጉድለቶች

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ሪፖርት ጉድለቶች

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

በከፍተኛ የአገሪቱ ቁንጮ ባለሥልጣን ለፓርላማ የሚቀርብ የኢኮኖሚ ሪፖርትን ሕዝብ በጉጉት እንደሚጠብቀው ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በተለይም ለእኛ የኢኮኖሚያችን ጉዳይ አሳሳቢ ለሆነ ሕዝቦች በጣም ይጠቅመናል፡፡ አምና የት ላይ ነበርን? ዘንድሮ የት ላይ ነው ያለነው? ለከርሞ የት እንሆናለን? ብለን መጨነቃችን አይቀርም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሪፖርቱን ለፓርላማ ያቅርቡት እንጂ፣ ሪፖርቱን የሚጽፉት የኢኮኖሚ ባለሟሎቻቸው ናቸው፡፡ ባለሟሎች ለአፄ ኃይለ ሥላሴም ጽፈዋል፣ ለኮለኔል መንግሥቱም ጽፈዋል፣ ለአቶ መለስ ዜናዊም ጽፈዋል፣ ለአቶ ኃይለ ማርያምም ጽፈዋል፣ ይኸው አሁንም ለዶ/ር ዓቢይ እየጻፉ ነው፡፡

የቱ ጥልቀት ያለው ሪፖርት እንደሆነ፣ የቱ ምሳ እየበሉ የተጻፈ እንደሆነ መዝነን መለየት የእኛ የሕዝቦች ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንዳቹ መረጃዎች ለመረጃ ያህል ብቻ የሚያገለግሉን ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ የኢኮኖሚ ትንታኔ የተሰጠባቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ለባለ ሀብቶች ስለሚሸጡት የመንግሥት ድርጅቶች የአሻሻጥ ቅደም ተከተል ጉዳዩ ቀድሞውኑ የተወሰነ ስለሆነ መረጃ ብቻ ነው፡፡

ሌሎቹ እንደ የሽንኩርት ዋጋ፣ ሠራተኛ በብዛት የሚቀጥሩ ድርጅቶች ወደፊት መቋቋምን የመሳሰሉ የማይክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮችና አጠቃላይ የዋጋ ንረት አመልካች፣ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙት ክፍያ ሚዛን መረጃዎች ሁኔታና የመሳሰሉ የጥሬ ገንዘብ ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ውጤቶችን የተመለከቱና የሥራ አጥ ቅነሳ መጣኝ፣ የመንግሥት ገቢና ወጪ ሁኔታና የመሳሰሉ የፊስካል ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለ ትንታኔ እንዲሁ እንደ ዋዛ የሚነገሩ አይደሉም፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት ምን ያህል ጥልቀት እንዳለውና የባለሟሎቹን በሳልና አርቆ አስተዋይነት ትንታኔ የጠየቀ መሆን አለመሆኑን ለመታዘብ አንዳንድ ያነሷቸውን ጉዳዮች እንመልከት፡፡

ከሽንኩርት ዋጋ እንጀምር፡፡ ከግንቦት ወር ይልቅ በሰኔ ወር ቀንሷል አሉ፡፡ ከባለሟሎቻቸው ካልሰሙ በቀር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ አባላትን እናንተ ለካ መርካቶ ከሄዳቹ ቆይታችኋል እንዳሉት እሳቸውም ቆይተዋል፡፡ ለመሆኑ የሽንኩርት ዋጋን ከግንቦት ይልቅ በሰኔ ወር መቀነስ ባለሟሎቹ የኢኮኖሚ ትንታኔ ብለው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያቀርቡ የፖሊሲ ውጤት ብለው ነው? ወይስ በረባ ባልረባው የከፍተኛ ባለሥልጣናትን ውድ ጊዜ ለመሻማትና ለራሳቸው ዕውቅና ለማግኘት ነው? የምግብ ምርቶች በተለይም የአትክልትና የፍራፍሬዎች ዋጋ ከወር ወር የሚቀያየርበት የራሱ ምክንያት አለው፡፡ የምርቶቹ ከቆዩ የመበላሸት ሁኔታና ግንቦት ወር የሠርግ ወር መሆኑ እንደ ምክንያት ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ ሌሎች በርካታ የፖሊሲ ውጤት ያልሆኑ ምክንያቶችን መጥቀስም ይቻላል፡፡

የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ክፍያ ሚዛንን መረጃ ሁኔታ እንመልከት፡፡ ሪፖርቱን በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ያልሰማሁ ቢሆንም፣ ዘንድሮ ኢትዮጵያ ያገኘችው የውጭ ምንዛሪ ከመቼውም ጊዜ እንደሚበልጥና ሃያ ይሁን ሃያ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ የሰማሁ ይመስለኛል፡፡ ከዚህም ውስጥ የተጣራ አገልግሎት ንግድ በአሥር በመቶ እንደጨመረ ተናግረዋል (በውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ክፍያ ሚዛን ገቢዎቹና ወጪዎቹ ተመሳሳይ ስያሜ ስላላቸው፣ የአገልግሎት ንግዶች ከገቢ ወጪ የተጣራ መጠኑ ነው የሚመለከተው)፡፡  ከሪፖርቱ ከአንድ ሳምንት በፊት በመገናኛ ብዙኃን ተነግሮ እንደሰማሁት፣ የአሥራ አንድ ወራት የቁሳዊ ሸቀጦች ኤክስፖርት ገቢ ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ ባለሟሎቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኼንን ሳይናገሩ በንግድ ሚዛኑ ውስጥ ዝቅተኛ ድርሻ ስላለው የአገልግሎት ንግድ ብቻ መንገራቸው ለምንድነው?

በአጠቃላይ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ክፍያ ሚዛን ሒሳብ ሠንጠረዥ በሁለት ዋና ዋና የመረጃ ዓይነቶች የሚከፈል ሲሆን፣ ሪፖርቱ እነዚህን ከፋፍሎ ሊመለከት ይገባው ነበር እላለሁ፡፡ የመጀመርያው የቁሳዊ ሸቀጦችንና የአገልግሎቶችን ንግድ ለመንግሥትና ለግለሰቦች በጊዜያዊ ዕርዳታ ስለሚመጡ የውጭ ምንዛሪዎች ሲሆን፣ መጠሪያ ስሙም መደበኛ ሒሳብ (Current Account) ይባላል፡፡ ንግዱ በእኛ ጥረት ላይና ዕርዳታው በለጋሾች መልካም ፈቃድ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ሁለተኛው የካፒታል ሒሳብ (Capital Account) ሲሆን፣ ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ የፕሮጀክቶች ካፒታል ዘላቂ ዕርዳታን፣ ብድርንና የውጭ ኢንቨስትመንትን የተመለከቱ የውጭ ምንዛሪ ወደ ውስጥ ፍሰቶችን የሚይዝ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ በውጭ ሰዎች መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ እነዚህን ሁለት ሒሳቦች ለያይተን ካልተመለከትን የትኞቹ በእኛ ጥረት ተገኙ? የትኞቹ በለጋሾች ፈቃድ ተገኙ? የወደፊት አንድምታቸውስ ምንድነው? ብለን መለየት አንችልም፡፡ የጥገኝነትና የተመፅዋችነት ደረጃችን እንዲያስቆጨን እነዚህ መረጃዎች ተለያይተው ሊቀርቡልን ይገባቸዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚውን ሁኔታ እንመልከት፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ሪፖርት ጥቅል ፍላጎትና ጥቅል አቅርቦት (Aggregate Demand and Aggregate Supply) አልተጣጣሙም ብለዋል፡፡ ይህ ለባለሙያዎቹ በጣም አሳፋሪ ቁንጽል ትንታኔ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ወር በሪፖርተር ጋዜጣ ባቀረብኩዋቸው ሁለት ጽሑፎች እንኳ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ሒሳብ መረጃ  (National Income Accounting Information) አያያዝ መሠረት የግብርና የኢንዱስትሪ የአገልግሎት በአጠቃላይ ጥቅል አቅርቦትና የግል ፍጆታ ወጪ፣ የመንግሥት ፍጆታ (መደበኛ) ወጪ፣ የግልና የመንግሥት መዋዕለ ንዋይ ወጪ፣ የተጣራ ኤክስፖርት ወጪ፣ በአጠቃላይ ጥቅል ፍላጎት እኩል እንደሆኑ ገልጬያለሁ፡፡

የተለያዩ ምርቶች ፍላጎትና አቅርቦት በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ የቁሳዊ ሸቀጦች ፍላጎትና አቅርቦት ናቸው እንጂ ያልተጣጣሙት፣ ጥቅል ፍላጎትና ጥቅል አቅርቦት እኩል ናቸው፡፡ የሕዝቡ ገቢ ለፍላጎት ለውጥ ወሳኝ ስለሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ የሥራ ሥምሪትን አሳድጎ፣ ፍላጎትንም ሆነ አቅርቦትን ብሎም ጠቅላላውን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የደመወዝና የገቢ መመጣጠን ላይ ማትኮር ቀዳሚ ፖሊሲዎ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በቅርቡ አንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሐዋሳውን ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሃያ ዶላር ያነሰ የወር ደመወዝ ጠቅሶ፣ የአገሪቱን ድህነት ሁኔታ አሳሳቢነት ከሌሎች አገሮች ጋር እያነፃፀረ መተንተኑ አይዘነጋም፡፡

ሌላው የባለሟሎቹን ድክመት ያየሁበት መስክ የጥሬ ገንዘብ ጉዳይን በተመለከተ ነው፡፡ ጥሬ ገንዘብና ገንዘብን አስመልክቶ በዚህ ዓመት ራሱን የቻለ መጽሐፍ አሳትሜአለሁ፡፡ በሪፖርተር ጋዜጣም ብዙ ጊዜ ጽፌአለሁ፡፡ ገንዘብ (Finance) የጥሬ ገንዘብና የሰነዶች (Money and Securities) ጥቅል ስም ሲሆን፣ ጥሬ ገንዘብ (Money) የምንዛሪዎችና የንግድ ባንኮች ብድር (Currency and Bank Credit) ጥቅል ስም ነው፡፡ መንገደኛ ሰው እነዚህን ቃላት አንዱን በአንዱ አወራርሶ ቢናገር የልማድ ጉዳይ ስለሆነ መቀበል ይቻላል፡፡ ስለአገር ፖሊሲ የሚናገር ባለሙያና የመንግሥት ባለሟል ግን፣ የኢኮኖሚ ትንታኔውን ትርጉም አልባ በማድረግ ትልቅ ጉዳት ያስከትላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካነሷቸው የኢኮኖሚ ጉዳዮች ውስጥ ቀልቤን የሳቡት የቁጠባና የመዋዕለ ንዋይ ሁኔታና በጨረፍታ የሰማሁት የፋይናንሲንግ ሞዴል ናቸው፡፡ የቁጠባና የመዋዕለ ንዋይ ፖሊሲ ለመንደፍ ጥሬ ገንዘብ ምን እንደሆነ፣ በጥሬነት ደረጃ (Liquidity Level) የተለያዩ ዓይነት ጥሬ ገንዘቦች ምን ያህል ወለድ እንደሚያስገኙ ማጥናትና መተንተን ያስፈልጋል፡፡ ከላይ እንደገለጽኩት የመንግሥት ባለሟሎች እንኳንስ ሊያጠኑና ሊተነትኑ ይቅርና ስሞቹንም በትክክል አይጠሩም፡፡

ዶ/ር ዓብይ አሁን አገሪቱ ባለችበት ሁኔታ የተበላሹትን ለማስተካከል ለኢትዮጵያ በጣም እንደሚያስፈልጓት አምናለሁ፡፡ እንደ ቀድሞዎቹ ባለሥልጣናት ራሳቸውን ባለሙያ ነን በሚሉ ሐሰትና ቁንጽል ነጋሪዎች ተጠልፈው ቢወድቁ፣ ጉዳቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነም አምናለሁ፡፡ እርስዎም ሆኑ ኢትዮጵያ በሰላም ቆይታችሁ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንድትጠቅሙ፣ በውሸት የሚቀርቡ የባለሟሎች መረጃዎችንና ትንታኔዎችን በነፃነት ከሚናገሩት ጋር እያነፃፀሩ ይጠቀሙ፡፡

እኔም የመንግሥት ባለሟል በነበርኩ ጊዜ ለደመወዜ እንጂ ለህሊናዬ ስላልሠራሁ፣ የደመወዝተኛን ችግር ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡ ራሴን ከደመወዝና ከመንግሥት ጥገኝነት ነፃ ካወጣሁበት ከአሥራ ሁለት ዓመታት ወዲህ ግን እንደ ልቤ ያመንኩበትን ስጽፍ፣ እውነትን ወይም ቢያንስ ባመንኩበት ላይ ተመርኩዤ ነው ከሦስት ወይም ከአራት ዓመታት በፊት በሪፖርተር ጋዜጣ ስለቀድሞው የኢሕአዴግ ካቢኔ ፀጉራም ውሻ ሳይታወቅበት እንደሚሞት የተናገርኩት ተፈጽሞ ዓይቼአለሁ፡፡ ውድ የኢትዮጵያ ልጅ ነዎትና ይህ በእርስዎ ላይ እንዲደርስ አልፈልግም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል  [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...