በገነት ዓለሙ
ሥራ ላይ ባለው በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 የተደነገገው ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብትና ነፃነት የገዛ ራሱ ግዴታና ኃላፊነት ያለው መሆኑ ብዙ ጊዜ የሚነገር ቢሆንም፣ የሚነገርበትና የሚደመጥበት መድረክና ከባቢ አየር ጤናማ ባለመሆኑ፣ ይልቁንም በታወቀው የጠላትነት ፖለቲካ ውስጥ ተዘፍቆ በመኖሩ በማናችንም ህሊና ውስጥ የረባ ቦታ ሳያገኝ ቆይቷል፡፡
ይህ መብት በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ መተማመኛ ሲያገኝ የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት (አንቀጽ 29) የመጀመርያው አይደለም፡፡ የ1980 ዓ.ም. የኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 47፣ ‹‹የኢትዮጵያውያን የንግግር፣ የጽሑፍ፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ትዕይንተ ሕዝብ የማድረግና በማኅበር የመደራጀት መብት የተረጋገጠ ነው›› ይል እንደነበረ፣ የ1948 ዓ.ም የንጉሠ ነገሥቱ ሕገ መንግሥትም በአንቀጽ 41፣ ‹‹በመላው የንጉሠ ነገሥት ግዛት ውስጥ በሕግ መሠረት የንግግርና የጋዜጣ ነፃነት የተፈቀደ ነው›› ብሎ መደንገጉን ለብዙዎች በተለይም ‹‹ሕገ መንግሥት ይከበር›› ከማለት ፋይዳ ጋር ይዘነጋናል፡፡
ሥራ ላይ ያለው፣ ማለትም ፀንቶ የሚገኘው ሕገ መንግሥት ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብትን ጨምሮ መሠረታዊ መብቶችንና ነፃነቶችን በሚዘረዝርበት ምዕራፍ መግቢያ ላይ፣ ‹‹በዚህ ምዕራፍ የተዘረዘሩት መሠረታዊ የመብቶችና የነፃነቶች ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋት፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችና ዓለም አቀፍ ሰነዶች ጋር በተጣጣመ መንገድ ይተረጎማሉ›› ይላል፡፡ የአማርኛው የአንቀጽ 13(2) ድንጋጌ፣ ‹‹ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋት›› እና ‹‹ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች የሚሏቸው (Universal Declaration of Human Right) እና (International Covenants) ስለመሆኑ በግልጽ አያስረዳም፡፡ ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 እኩልና ከእሱ ጋር የሚጠቀሰው፣ እየተጠቀሰም በሕግ አምላክ የሚባለው፣ እነዚህ ሁለቱ ውስጥ የሚገኘው አንቀጽ 19 ነው፡፡ የንግግርና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ‹‹ልዩ ግዴታዎችና ኃላፊነቶች›› ይዟል/አሉት የሚለውም ሁለተኛው ላይ የተጠቀሰው የአንቀጽ 19 ድንጋጌ ነው፡፡
አላዋቂዎችና በተለይም በመንግሥት ወገን ያሉ የመብቱና የነፃነቱ ተጠናዋቾች ‹‹ሲያስተምሩ››ን ‹‹ግዴታውን የተወጣ ይጠይቃል መብቱን›› እያሉ አወናብደው፣ ዛሬም ያልጠራ ውዥንብር ውስጥ ቢከቱንም ግዴታውና ኃላፊነቱ መጀመርያ ለመንግሥት አይደለም፡፡ ለመብቱና ለነፃነቱ ተገልጋዮች ለእርስ በርሳችን ነው፡፡ በዚህ ረገድ መብትን መጠየቅ ግብር ከፍሎ ነው ከሚለው ተራና የነተበ የዘወትር ልፍለፋ ጀምሮ፣ ‹‹መብትና ግዴታ አይነጣጠሉም›› ዓይነት ልፈፋን ጨምሮ ግዴታን፣ የመብትና የነፃነት ቅድመ ሁኔታ የሚያደርጉ ባዶ ‹‹ትምህርቶች›› እነሆ ዘንድሮ ካየነው ዓይነት ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረ፣ በመብትና በነፃነት የመባለግና የመማገጥ ሥርዓተ አልበኝነት የገዛ ራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
አገራችን ዓለምንም፣ እኛንም (እኩልም ባይሆን) ያስደነቀ፣ እስካሁን መንግሥት መገርሰስ ውስጥና የታጠቀውን ኃይል መከፋፈል ውስጥ ያልገባ፣ ነገር ግን ሲበዛ እያስፈራራና እያስደነገጠም መምጣት የጀመረ ሰላማዊ ለውጥ ውስጥ ናት፡፡ ይህን ለውጥ ግን አደጋ እየደጋገመ እየታከከው መጥቷል፡፡ ሁሉም የአደጋው ምክንያት ደግሞ ትግሎች ከሰላማዊና ከሕጋዊ ግቢ ውጪ እንዋል የማለታቸው ነገር ነው፡፡ ቅደም ተከተል ላይ መስማማት አለመቻላችን ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ የሁሉም የለውጥ ኃይሎች የመጀመርያው ደረጃ አብሮ የመሥራት ተልዕኮ ዴሞክራሲ የሚፈልጋቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት ነው፡፡ መሆንም ያለበት እሱው ነው፡፡ ለዴሞክራሲ መደላደል ግድና ተቀዳሚ ከሆኑ ማሻሻዎች በስተቀር አዘላለቃችንን የሚወስኑ አደጋዎችን እስከምናመክን ድረስ፣ በእንጥልጥል መቆየት የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮችን ጥያቄ አድርጎ ማንሳት ለውጡን ሰላምና ጤና እየነሱት ነው፡፡ ክልልም ሆነ ዞን የመሆን፣ የወሰንና የ‹‹ግዛት›› ይዞታ የአለኝታ ጥያቄ፣ የ‹‹ልዩ ጥቅም››ም ሆነ በዚህ ላይ ያለመ የአፀፋ መልስ ከሰላማዊና ሕጋዊ አድማሱ ካልወጣሁ እያለ የሚያስፈራራውን የትግል ሥልት የሚያግዝ ጣጣ እየሆነ መጥቷል፡፡
ዘላቂ ለውጥና ማሻሻያዎችን እናካሂድ ማለት፣ ከእየአቅጣጫው ለሚመጡ ጥያቄዎች እየተዋከቡ መገበር አለመሆኑን፣ ትንሹንም ትልቁንም ጥያቄዎች እያግተለተሉ አዙሪት መፍጠር ተቀዳሚውን የለውጥ ተግባራትን (ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ የመፍጠር ዴሞክራሲን የማደላደል ተቋማትን ገለልተኛ ማድረግ…) ከዕይታ እስከ ማጥፋት መንገድ የሚያስት መሆኑን ብዙዎች የለውጡ ‹‹ኃይሎች›› የጋራ መግባቢያ፣ የጋራ አደራ አላደረጉትም፡፡ ከሁሉም በላይ በዚህ አጋጣሚ መንግሥትን ወጥሬ ወይም አስጨንቄ ይህን ወይም ያንን ፍላጎቴን ላሟላ ከማለት ይልቅ፣ ይኼ ጊዜ ይለፍና የሚል አስተዋይነት ያልፈጠረባቸው መንግሥት ሥልጣን ውስጥ ያሉ ሰዎች ራሳቸው የኢትዮጵያን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 238 መጣስ ድረስ ተደናግረው አደናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የለውጥና የዴሞክራሲ ሁኔታ ውስጥም የአሠላለፍ ለውጥ የሚያስከትል አደገኛ እሳትም ጭረዋል፡፡
እግረ መንገዴን የወንጀል ሕጉ የመጀመርያው የወንጀል ድርጊት ዝርዝር የሆነውን አንቀጽ 238 ማስተዋወቅ አስፈላጊ ሆኖ ያገኘሁትና ትንሽ ማብራሪያ ያስፈልገዋል ብዬ በነገራችን ውስጥ ጣልቃ ማስገባት የፈለግሁት፣ ጥያቄው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ጭምር እስከ መሆን ደርሶ የ‹‹መፈንቅለ መንግሥት›› ነገር የብዙው ጯሂ አጀንዳ በመሆኑ ነው፡፡
የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 238 ‹‹በሕግ መንግሥትና በሕገ መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚደረግ ወንጀል››ን ይደነግጋል፡፡
- ማንም ሰው በኃይል፣ በዛቻ፣ በአድማ ወይም ሕገወጥ በሆነ በማናቸውም መንገድ አስቦ፣
ሀ. የፌዴራሉን ወይም የክልልን ሕገ መንግሥት ያፈረሰ፣ የለወጠ ወይም ያገደ እንደሆነ ወይም፣
ለ. በፌዴራሉ ወይም በክልል ሕገ መንግሥት የተቋቋመውን ሥርዓት ያፈረሰ ወይም የለወጠ እንደሆነ፣ ከሦስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት ለመድረስ በሚችል ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡
- ወንጀሉ ሲፈጸም በሕዝብ ደኅንነት ወይም ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ደርሶ እንደሆነ አድራጊው በዕድሜ ልክ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል ይላል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት የተመሠረተው ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ አሠራር የመንግሥትን ሥልጣን መያዝን በማውገዝና ውድቅ በማድረግ ላይ ነው፡፡ በኅብረቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ ሥልጣን ላይ የወጣ መንግሥት ከአባልነት የሚታገደው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ለውጡ የሚሸሸውን ሰላም የሚነሱት የጨዋታውን ሕግ አላከብር ብለው የሚያስቸግሩት፣ የተጀማመረውንና መበልፀግ ያለበት ዴሞክራሲያዊ ሁኔታው ያመጣውን የነፃነት አየር የሚበክሉት፣ በነፃነቱ የሚባልጉትና የሚማግጡት፣ ከሁሉም በላይ በነፃነቱ ላይ ወንጀል የሚሠሩት ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት በራሱ በውስጡ የሚያሸክመው ግዴታና ኃላፊነት የሌላው አድርገው በተለይም አመቸን ብለው በማኅበራዊ ሚዲያው አማካይነት ትርምስ የሚፈጥሩት የሳይበር/የዜሯንድ ጸሐፍት ናቸው፡፡ እነዚህ ጸሐፍትና የዩቲዩብ ለፋፊዎች ልዩ ልዩ ዓይነት ናቸው፡፡ በፌዴራሊዝም፣ በሕገ መንግሥት ላይ፣ በኢትዮጵያዊነትና በአንድነት ጭምር ይለያያሉ፡፡ ሁሉንም የሚያዋድዳቸውና አንድ የሚያደርጋቸው ግን በምንም ዘዴና በየትኛውም ዓይነት የመስዋዕትነት ክፍያ ሕዝብን አዋክቦ፣ አከታልፎና አሳክሮ በመማገድ ጭምር የለውጥ ኃይሉን የሕዝብ ድጋፍ ማሳጣትና ለውጡን መቀልበስ ነው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያው ዛሬ በውሸትና በሐሰት ብቻ ሳይሆን በሚቻለው ሥልት ሁሉ በሸፍጥና በጉልበት መንገዶች ጭምር ይህን ግብ የማሳኪያ፣ አገር የማተራመሻ መድረክ ሆኗል፡፡ ፀጥታን ማረጋገጥ፣ ዴሞክራሲን ማደላደል የሁሉም የጋራ አደራና ሥራ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ በሆነበት ወቅት፣ ኢንተርኔት የሚያዘጋና ኢንተርኔት የመዝጋቱንም ዕርምጃ እንደታወቀውና ከዚህ ቀደም እንደተለመደው መንግሥትን የመቃወሚያ፣ የማሳጫ አጀንዳ ማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ከዚህ ቀደም ኢንተርኔቱን መዝጋት ብቻ ምን ያህል መንግሥትን ለመቃወምና ለማሳጣት ምክንያትና አጀንዳ ሲሆን እናውቃለን፡፡ በቅርቡም የአሥረኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች አገር አቀፍ ፈተናዎች ተመሳሳይ የመንግሥት የ(‹‹ጥንቃቄ››) ዕርምጃዎች ምክንያት ሲሆን ዓይተናል፡፡ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. እና ከዚያ በኋላ የሰነባበተው የኢንተርኔት ግንኙነት የማቋረጥ የመንግሥት ዕርምጃ ግን፣ እንደተለመደው አቧራ ሲያስነሳና የትግል መሣሪያና የተቃውሞ ርዕሰ ጉዳይ ሲሆን አልሰማንም፡፡ ጥያቄውና ጭብጡ እንዲህ ማድረግ የኢንተርኔት ግንኙነትን ድርግም አድርጎ መዝጋት ጉዳት የለውም፣ ችግርም አያስከትልም አይደለም፡፡ ብዙ ሰው ዘንድ እጅግ በጣም ብዙ አገር ወዳድ ሕዝብ ውስጥ ዕርምጃው ‹‹ትባስን ትቶ፣ ትሻልን›› የመምረጥ ጉዳይ ሆኖ የተመረቀ ይመስላል፡፡
ሌላም አቧራ ሳያስነሳ ዝም ብሎ የታለፈ ወይም ታልፏል ሊባል የሚችል ጉዳይ ነበር፡፡ እንኳንስ ዘንቦ ዝም ብሎም ሁል ጊዜ ጤዛ በሆነበት አገርና ሁኔታ ውስጥ፣ የፌዴራሉ መንግሥት በክልል ጣልቃ የገባው ሕገ መንግሥቱን ጥሶ ነው ማለት የሚቀናው ተቃዋሚም፣ ታጋይም፣ አክቲቪስትም፣ ወዘተ የአማራ ክልልን የባህር ዳር የ‹‹መፈንቅለ መንግሥት›› ሙከራ የማክሸፍ የፌዴራል መንግሥቱን ዕርምጃ፣ በዚህ ማዕቀፍና ከዚህ ማዕዘን አንፃር ማየት ጊዜም ዓይንም አላገኘም፡፡ ይህን ሁሉ ያነሳሁት ሰዎች ምን ያህል ድንጉጥና በድንጋጤም ምን ያህል መርህን መርሳት የሚያደርስ ደረጃ እንደሚደርሱ እንደሆነ ለማስታወስ ነው፡፡ በበኩሌ የፌዴራሉ መንግሥት በሕግ የተደነገገም ሆነ ትክል ባህርያዊ (Inherent) የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣኑን አልፏል፣ ወይም አስፈላጊውንና ተገቢውን የሕዝብ ፀጥታና ጠቅላላ ደኅንነት ለመጠበቅ ባልሆነ ጉዳይ ኢንተርኔት ዘግቷል የሚል መከራከሪያ የለኝም፡፡ እንዲያ ያለ ክርክር ውስጥም አልገባም፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ሥርዓት ይበጅለት ብዬ ክርክር ውስጥ የምገባው ወይም ጤናማ ውይይትና ክርክር ቢነሳ የምወደው፣ በተለይ ከኋለኛው ከሁለተኛው ጉዳይ አኳያ የዕርምጃው ባለቤት በግልጽ እንዲታወቅ፣ የኢትዮ ቴሌኮም እስካሁን ብቸኛው የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ሚናና ተግባር፣ መብትና ግዴታ በግልጽና በሕግ እንዲወሰን ሐሳብ በማቅረብ ነው፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ የትዕዛዝ ሰጪው ባለሥልጣን የሥልጣን ዳር ድንበር፣ ትዕዛዙ የሚያካትተው የአድርጉ/አታድርጉ ልክ፣ ትዕዛዙንና የትዕዛዙን አፈጻጸም ገልጦ፣ ገላልጦ የሚያይ የበላይ የሥልጣን አካል ስለመኖር አለመኖሩ፣ በትዕዛዙ ምክንያት የተወሰደው ዕርምጃ ያደረሰው ጉዳትና ያስገኘው ጥቅም ሪፖርት የሚደረግበት ስለመሆኑ አለመሆኑ፣ ‹‹እንዲያው ዝም እንዲያው ዝም ይሻላል›› በማለት የሚታለፍ መሆን የለበትም፡፡
የመንግሥት በክልሎች ውስጥ ጣልቃ የመግባት ሥልጣን ልጓምም ገደብም የለውም አልተባለም፡፡ መብቶች ሁሉም ደግሞ ፍፁም አይደሉም፡፡ የፌዴራል መንግሥት ከክልል ጣልቃ የመግባት ሥልጣን ባሉት (አሉ በሚባሉት) ድኩም ሕጎችና ጽንፈኛ ፖለቲካ የተልከሰከሰውን ያህል የሚያስቸግርና ጠባብ አይደለም፡፡ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ አንድን ያህል ማለትም ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን የመጠበቅና የመከላከል ያህል የሰፋ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ አንድ የሚደነግገው የኢትዮጵያን መንግሥት ስያሜ ነው፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀር ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሚል ስም ይጠራል ይላል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93(4ሐ) መሠረት አንቀጽ አንድ የማይነካ/የማይገሰስ ‹‹መብት›› ነው፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር የሚወጡ ድንጋጌዎችና የሚወሰዱ ዕርምጃዎች በማናቸውም ረገድ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ አንድ የተቀመጡትን መብቶች የሚገድቡ ሊሆን አይችሉም ይላልና፡፡ በዚህ ሥሌትና ትርጉም የኢትዮጵያን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊካዊ የአስተዳደር ፍጥርጥር ከመጠበቅ፣ ሕገ መንግሥቱን ከማስከበር የበለጠ የዘወትርም የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣንም የሚጠይቅ ሥራ የለም፡፡
መብቶች ሁሉ ፍፁም አይደሉምና በእነዚህ ላይ ገደብ መጣሉ የማይቀር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬም ድረስ በተግባር ብቻ ሳይሆን በሕግ አወጣጥም ጭምር ችግር ሆኖ የኖረው (በተለይም ባለፉት ‹‹የዴሞክራሲ›› ዓመታት) በመብቶች ላይ የሚጣለው ገደብ፣ ገደብ የለሽ መሆኑ ነው፡፡ አጀማመራችን ግን በዚህ ረገድ በጣም የሚገርም ነበር፡፡ ኤርትራን በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር አንድ ያደረገው የፌዴራል አክት ሲታወጅና የፌዴራል አክቱም የመብቶች ዝርዝር የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አካል ሲሆን፣ ‹‹ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን መብቶች የሚወስኑ፣ የሌሎችን መብትና ነፃነት ለማክበርና በጠቅላላውም ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ሲባል እንዲፈጸሙ የሚያስፈልጉት ነገሮች ብቻ ናቸው›› ተባለ፡፡ ከዚያ በኋላ የወጣው የ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥትም በመብቶች ምዕራፍ መጨረሻ ላይ ‹‹የሌሎችን ሰዎች ነፃነትና መብት ለማክበር፣ ደግሞም የሚያስፈልገውን የሕዝብ ፀጥታና ጠቅላላ ደኅንነት ለመጠበቅ ካልሆነ በቀር፣ በዚህ ምዕራፍ ከዚህ በላይ ባሉት አንቀጾች ውስጥ መተማመኛ የተሰጣቸው መብቶች በሌላ በማንኛውም ምክንያት አይቀነሱም›› ተባለ፡፡ ሁለቱም የ1945 እና የ1948 ዓ.ም. የመብቶች ገደብ ድንጋጌዎች የ1948 (እ.ኤ.አ.) ዲክላሬሽን ኦፍ ሒዩማን ራይትስ ቅኝቶች ነበሩ፡፡ በዚያ መንገድ መገስገስን የሚያግዝ፣ የሚገራና የሚቆጣጠር የዳኝነት አካል ጎድሎን አሁን ለደረስንበትና ለውጡን አምጦ ለወለደው ቀውስና ጦስ ተዳረግን፡፡
አሁን በደረስንበት የሰኔ 2011 ዓ.ም. የዕድገት ይሁን የ‹‹መፈንቅለ መንግሥት›› ቀውስ ደረጃ፣ መንግሥት በክልሉ ጣልቃ የገባው በሥልጣኑ ውስጥ ሆኖ ነው? ኢንተርኔት የታገደው በመብቶች የገደብ ሥልጣን ውስጥ ነው? ብሎ መጠየቅ አጉል መሞላቀቅ ሆኖ ይሁን ወይም፣ ‹‹ታዲያ ከዚህ የበለጠ አደጋና ግዳጅ ከየት ይምጣ?›› ተብሎ፣ በተለይ ሁለተኛው ጉዳይ ግን በጣም አሳዛኝና የአገር ሕመም መሆኑ የአደባባይ ገመናችን ነው፡፡
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርቡ በጥያቄና መልስ ውስጥ ‹‹የበሬ ወለደ ተረት ተረት››፣ ‹‹የውሸት ሰበካና በሬ ወለደ ዘመቻ›› ያሉትን ይህን የኢንተርነቴት ጥቃት አገር ኢንተርኔት በመዝጋትም ተከላክላዋለች፣ ተገላግላዋለች ብለው አላመኑም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሁለት ዓይነት ዕርዳታ ጠይቀዋል፡፡ አንደኛ እነዚህን ‹‹ክፉ መርዘኛ፣ ኢትዮጵያዊ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች››ን ‹‹… እኔ እናንተን እዚያ ልቆጣጠር የምችልበት መንገድ ስለሌለኝ የእውነት አምላክ እግዚአብሔር አምላክ በእናንተ ላይ ይፍረድባችሁ ብቻ ነው የምለው፤›› ብለዋል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የእኛን የኢትዮጵያውያንን የማንጠር ችሎታና ብቃት ተማፅነዋል፡፡ እውነትና ውሸትን እንድናሰላስል ጠይቀዋል፡፡
የመጀመርያው እንደ ፖለቲከኛ የመፍትሔውን አቅጣጫ ባያሳይም የችግሩን ስፋት፣ የአደጋውን ዓይነት፣ የደረስንበትን አሳፋሪ ‹‹የዕድገት›› ደረጃ ያመላክታል፡፡ ምን ያህል የጨነቀና የጠበበ ምናልባትም ‹‹መላ የጠፋበት›› ችግር ውስጥ መውደቃችንንም ይናገራል፡፡
ሁለተኛው ጥያቄ ግን ከሌሎች ዘዴዎችና ሥራዎች ጋር ተባብሮ ጥቃቱን መከላከል የሚችል ፍቱን መከላከያ ነው፡፡ መስማትን፣ ማንበብን፣ ማስተዋልን፣ ማሰላሰልን፣ መጠየቅንና መጠርጠርን ይጠይቃል፡፡ የትምህርት ሥርዓታችን መደበኛውም መደበኛ ያልሆነውም ሐሳቦችንና መረጃዎችን የመፈልፈል፣ የማበጠር፣ በየዝምድናቸው የማያያዝ ክህሎትን አከርካሪው ባለማድረጉ ውድቀታችን የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማስተዋልን ጥቅም አውስተዋል፡፡ ማሰብ ማለት እኮ ማስተዋል፣ መረጃን በፈርጅ በፈርጅ መለየት፣ ማዛመድና መተንተን፣ መፈተሽ፣ ንጥረ ሐሳብ ማርቀቅ ማለት ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የሚሰማውና የሚነገረው ብጥስጣሽ ነገር በበዛበት ወቅት፣ እኛ ብቻ ልክ ከሚሉትም ሆነ የተጻፈ ነገር ልክ ከሚባለው ሕግ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ በተቻለ መጠን መልስ እስኪያገኝ ድረስ ተጠራጥሮ የማይጠግብ፣ ጠይቆ የማያባራ አዕምሮ ያሻል፡፡ በተለይም የጠላትነት ፖለቲካ ገና አልፈርስም ብሎ ለውጡን ተቀናቅኖ እየገነገነ መሄድ በሚፈልግበት አገር ውስጥ አለመጠየቅ፣ አለመጠርጠር፣ አለማጣውት፣ አለማውረድ፣ አርቆ አለማሰብ ለፀብ ደጋሾች መጫወቻ ያደርገናል፡፡ ለእርስ በርስ መተላለቅ ይዳርገናል፡፡ የሚነግሩንን ሁሉ መቅረብ ያለብን ክፍት በሆነ አዕምሮና ገለልተኛ በሆነ ስሜት መሆን አለበት፡፡ በተለይ ጉዳዩ በቀረበበት መልክ ስናነብና ስንሰማ ከተቋቋመ ሐሳባችን፣ ከፍቅራችን፣ ከጥላቻችን መባነን፣ ገልመጥ ማለት ከተሳነን ከሚደገስልን አደጋ መዳን አንችልም፡፡ እዚህ ላይ የተጠቃቀሱት ሐሳቦች የሚዲያ/የኢንፎርሜሽን መሠረተ ትምህርት (ሚዲያ ወይም ኢንፎርሜሽን) ተብሎ በየአገሩ ከፋሽን የበለጠ ዕውቅናና ተቀባይነት ያገኘ ነገር ነውና የኢትዮጵያ ሚዲያዎች፣ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ከወግ ባለፈ ሊተጉበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
‹‹የእውነት አምላክ እግዚአብሔር አምላክ በእናንተ ላይ ይፍረድ›› ከማለት እርግማንና ጸሎት/ስለት በላይ ሕዝብና መንግሥት ሃይ ሊላቸው የሚገቡም አሉ፡፡ ዛሬ ቴክኖሎጂው ሁሉንም መጻፍ የሚችለውን ሰው ያለ ምንም ውጣ ውረድ አሳታሚ መሆን እንዲችል አድርጎታል፡፡ በዚህ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው ግለሰቦች ጭምር አሉ፡፡ እነዚህና ተመሳሳይ ሰዎች የተጎናፀፉት ፀጋ፣ የሚገለገሉበት መብት ግን ከዚያ የከበደ ልዩ ግዴታና ኃላፊነት ያሸክማቸዋል፡፡ ብዙ ሰው በሚያገኙበት በዚህ መድረክ የሚነገር መረጃና የሚሰነዝር ሐሳብ የሕዝብ መብት ያለበትና ጓዳ ለጓዳ ከሚደረግ ጭውውት እጅግ በጣም የተለየ ነው፡፡ በመሰለኝ ከማውራት መቆጠብን፣ የመረጃ ምንጭን አስፍቶና አሰባጥሮ በቅጡ ማጣራትን፣ ግምገማና ሐሳብን ከመወርወር በፊትም ግራ ቀኝ ደጋግሞ እያመዛዘኑ የመፈተግ፣ የመሰለቅና የማብሰል ልፋትን ይጠይቃል፡፡ መድረኩ አስመሳዮችና ወገንተኞች አገር የሚያምሱበት መሆን የለበትም፡፡
ሕዝብ ከጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርም ሆነ ከአስተዋይ ፖለቲከኝነት የራቀና አንዱንም ያልጨበጠ ፀባይ እንቢ ማለትን በባትሪ ድንጋይ ለሚሰማው ሬዲዮ ሆነ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ለሚሠራው ስልኩ/ኮምፒዩተሩ ማሳወቅ ባህሉ ማድረግ አለበት፡፡ ዴሞክራሲን የሚጎዳ ድንቁርና እኔ ቤት፣ እዚያ ቤት፣ እዚህ አገር፣ እዚያ አገር ሳይባል ከተወገዘና ተቀባይነት እንዲያጣ ከተደረገና ለእውነትና ለሁሉም መብት ተቆርቋሪነትን በየትኛውም ዓይነት ወገንተኝነት መለካት ከተቋረጠ፣ ከእግዚአብሔር በታች ሕዝብም አገርን ከትርምስ መከላከል ይችላል፡፡ የመንግሥት የግልጽነትና የመረጃ ሰጪነት ሚና ደግሞ ብዙ ነገር ያቃልላል፡፡ በተለይም የለውጥ እንቅስቃሴ ዝምታን፣ ማድበስበስን፣ ምን እየተደረገ ነው በሚል ሹክሹክታ መብሰልሰልን አይወድም፡፡ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የሰጡትና እኩለ ሌሊት ካለፈ በኋላ የተሰማው፣ አማራ ክልል ተገኝተው የሰጡት መግለጫ ተደርጎ የተተረጎመው መልዕክት ምን ምን ብሎ መዋሸትና ተንኮል መሸረብ እንዳስቻለ ዓይተናል፡፡ የዚህ የቅርብ ምክንያት የመንግሥትና መንግሥት አከል እየሆኑ የመጡት የፓርቲ ሚዲያዎች ብቃትና ዝግጁነት ጉድለት ነው፡፡ መንግሥት ይህን ኃላፊነት የጎደለው የመንግሥት ሚዲያ አሠራር ራሱን ማረም፣ የገዛ ራሱን ብቃት ደግሞ ማሻሻል አለበት፡፡
በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለሕዝብ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ መስጠትና ትኩረቱንም ማንቃት ብዙ ነገር ይከላከላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ‹‹ጠላቶች››ንም ያመነምናል፡፡ የዕርምጃ አወሳሰዳችንንም ማጥራትና ግልጽ ማድረግ እንዲህ ያለ ነገር በመጣና አስገዳጅ በሆነ ቁጥር ይይዙት ይጨብጡት ከማጣት ይገላግላል፡፡ አፍን ሞልቶ፣ ደረትን ነፍቶ በነፃነትና በመብት ቋንቋ መናገርን ይባርካል፣ ይመርቃል፣ መማርና መሻሻልን ያመጣል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡