ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ኢኮኖሚው እንደ ፖለቲካው ጭንቅ ውስጥ ቆይቷል፡፡ በርካታ ፈተናዎችንም አስተናግዷል፡፡ ወሳኝ የሚባሉ ዕርምጃዎች ባይወሰዱ ኖሮ ችግሩ አገሪቱን ቀውስ ውስጥ ይከታት ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ከዕርምጃዎቹ መካከል ለአብነት የሚጠቀሰው በኢትዮጵያ ላይ ተከማችቶ የቆየውን የውጭ ብድር ዕዳ ለመክፈል የተደረገው ጥረት ነው፡፡ ጥሩ ባይሳካ ኖሮ ተንገዳጋጁ ኢኮኖሚያችን የከፋ ችግር ይገጥመው ነበር፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሕገወጥ ንግድ፣ ኮንትሮባንድና ሌላውም የህቡዕ እንቅስቃሴ ኢኮኖሚውን ሲያናውጠው ከርሟል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከአሥር ቢሊዮን ዶላር በላይ ሊደርስ እንደሚችል በብዙ ትንታኔ ጭምር እየታገዘ ሲነገርለት የቆየው የወጪ ንግድ፣ እንኳንና እንደታሰበው ጭርሱኑ የኋሊት መጓዙ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል፡፡
በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶች በዕለት ተዕለት የንግድ ልውውጦች ላይ የፈጠሯቸው ተፅዕኖዎች ተደማምረው፣ ኢኮኖሚው በወጉ እንዳይራመድ ጎትተውታል፡፡ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ትከተል የነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲና የተጓዘበት መንገድ መንሻፈፉ የፈጠረው ተፅዕኖ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ በብድር ላይ የተመሠረተው የአገሪቱ የገንዘብ ፖሊሲና በዚሁ አኳኋን በየቦታው የተጀመሩት ግዙፍ ግንባታዎች በጅምር መቅረታቸውና ከታለመላቸው በላይ ገንዘብ እየበሉ ሲጓተቱ መቆየታቸው ያስከተለው ጣጣና መዘዙ በዝቷል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ግንባታቸው አልቆ የገቢ ምንጭ በመሆን ዕዳቸውን ይከፍላሉ ተብለው ሲጠበቁ፣ ዕዳቸውን መክፈል ቀርቶ ግንባታቸው ተወለካክፎ ጅምራቸውን ለማስጨረስ ተጨማሪ ወጪና ድካም እየጠየቁ ነው፡፡ ትርፋቸው ፈተና ብቻ ሆኗል፡፡
አዝጋሚነታቸውና ከታለመላቸው በላይ የትየለሌ ወጪ መጠየቃቸው አገሪቱ ስትመራበት በነበረው ፖሊሲ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ፣ የፕሮጀክቶቹ መንገጫገጭም ሊፈጠር ይችል የነበረውን የሥራ ዕድል ጭምር እንዲጨልም በማድረግ ጭምር ጉዳታቸው ሊጠቀስ ይችላል፡፡ እንዲህ እንዲህ ያሉ ክስተቶችን እንዘርዝር ብንል ማባሪያ የሌላቸውን ችግሮች እናገኛለን፡፡ ይህ ሁሉ ኢኮኖሚው ጭንቅ ጥብብ እንዲለው አስገድዷል፡፡
የትናንቱ የተዛነፈ አካሄድና መዘዙ የነገ ጉዞ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳረፍ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን እየተንከባለለ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ድምር ውጤቱ ይታይ ከተባለ አገሪቱን በዕዳ በመዝፈቅ የመንግሥት የተለጠጠ የፋይናንስ ወጪ፣ እስካሁን ካደረሰውም በላይ ሌላ ዕዳ እንዲያመጣ ጋብ መደረግ እንዳለበት ይታመናል፡፡ የእስከዛሬው ብድርን መሠረት ያደረገ የመንግሥት ኢንቨስትመንት ዛሬ ላይ የተጫነበት ዕዳ አገሪቱን ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ መክተቱም የሚታይ ነው፡፡
ለ2012 በጀት ዓመት ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነውን ለዕዳ ክፍያ መመደቡም ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በብድር የገነባቻቸው በርካቶቹ እንደ ኃይልና ስኳር ልማት ያሉ ፕሮጀክቶች ይህ ነው የሚባል ፋይዳ ማስገኘት ሳይችሉ በምትኩ ዕዳ ከፋይ ሆና ዓመታትን እንድትቆጥር አስገድደዋታል፡፡ ይህም ቀጣዩን የኢኮኖሚ መሥመር የሚመጥንና ቢያንስ አካሄዱን ሊያስተካክልላት የሚገባ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው፡፡
ከዚህ አንፃር ሲታይ፣ ዘለግ ያለ ሕክምና የሚሻውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንደነበር ይዞ መቀጠል እንደማይቻል በመረዳት የሚካሔዱ ማስተካከያዎች በአፋጣኝ መተግበር ይኖርባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል በቀደመው አሠራር አገር ዕዳ የተሸከመችባቸው ፕሮጀክቶች ያስከተሉበትን ውጥንቅጥ እንዳልተፈጠረ በመመልከት ኢኮኖሚው አልተገራም የሚሉ ጩኸቶች ሲደመጡ ግራ ያጋባሉ፡፡
ሰሞኑን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት እንደሰማነው መንግሥት በተለይ በ2011 ዓ.ም. ኢኮኖሚው የበለጠ ጉዳት እንዲያስከትል የሚያስችሉ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ እርግጥ ነው ከነበረው ችግር አንፃር መንግሥት ያከናወናቸው ሥራዎችና አንዳንድ ውሳኔዎቹ እንዲሁም የተከማቸ ዕዳ ለመክፈል ያደረገው ጥረት ኢትዮጵያን ከማጥ ፈቀቅ እንዳደረጋት ያመለክታሉ፡፡
ሆኖም የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት አሁንም ብዙ የሚቀረው መሆኑን ገበያው ይነግረናል፡፡ አንዳንድ ምርቶች ከልክ በላይ ዋጋ ተቆልሎባቸው ከሸማቹ ራስ ምታት ሆነው የመገኘታቸው ነገር አሁንም በብርቱ እንዲታሰብበት የሚያደርግ ነው፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን ኢኮኖሚውን ለማከም እየተደረገ ያለውን ጥረት ማጎልበት እንዳይቻል ገበያውን ባልተገባ ዋጋ በመናጥ ችግሩን ለማባባስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እዚህም እዚያ መታየታቸው ነው፡፡
ሸማቹ አብዝቶ የሚጠቀምባቸው ምርቶች ላይ ሆን ተብሎ ዋጋ እንዲጨመር በማድረግ የሚሠሩ ያልተገቡ ተግባራት ልጓም የማይበጅላቸው ከሆነ የኑሮ ውድነቱ አሁን ታየ ከሚባለው መሆኑ አይቀርም፡፡
በራስ ወገን ላይ የሚፈጸመው እንዲህ ያለው ድርጊት ለምን? ብዙዎች አገር ያለችበትን ፈታኝ ሁኔታ በመረዳት ማገዝ ሲገባ ትኩሳቱን የበለጠ ለመጨመር ሆን ተብሎ የሚሠሩ ሻጥሮች ኢኮኖሚው ላይም ሆነ ሸማቾች ላይ ጫና ከመፍጠር ባለፈ ችግን ለማርገብ የሚደረጉ ጥረቶች ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡
የአቅርቦት እጥረት አለ በሚል ሰበብ በአንዳንድ ምርቶች ላይ የተደረገው ጭማሪም ቢሆን በምንም መመዘኛ ቢሆን ለመቀበል የሚከብድ ነው፡፡ ዋጋ ጭማሪ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ቢኖረው እንኳን በአቦሰጠኝ የሚደረግ መሆኑ የዚህች አገር የገበያ ሥርዓት አሁንም በብርቱ ሊታሰብበት የሚገባ መሆኑን ነው፡፡
እንዲህ ያለው ችግር ሰው ሠራሽ መሆኑን በምንረዳው አንዳንድ ምርቶች ላይ ቁጥጥር ተጀመረ፣ የተከማቹ ምርት ተገኘ ሲባል ገበያው ጋብ ማለቱ ነው፡፡ ሌላው መገለጫ ደግሞ እዚሁ ከተማ ውስጥ ለምሳሌ አትክልትና ፍራፍሬ አንዱ ቦታ በረከሰ ሲሰጥ ሌላኛው ገበያ ላይ በአንድ ኪሎ ሰባትና ስምንት ብር ዋጋ ተቀጥሎ ሲሸጥ ማየታችን ችግሩ የምርት እጥረት ሳይሆን ኃላፊነት የጎደለው ስግብግብነት መሆኑ ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ ከሰሞኑ እጥረት አለባቸው የተባሉ አንዳንድ ምርቶች በአንዳንድ መጋዘኖች ተከማችተው ተገኙ መባሉ በራሱ ድርጊቱ ሰው ሠራሽ መሆኑን ነው፡፡ በነገራችን ላይ ኢኮኖሚው አሁን ችግር አለበት ከተባለ በግልጽ መነገር ያለበት ለተፈጠረው ችግር አንድ መንግሥትን ብቻ ተወቃሽ ማድረግ አግባብ ላይሆን ይችላል የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ የኑሮ ውድነትን እንዳይባባስ ዜጎች የራሳቸውን ዕገዛ ማድረግ አለባቸው፡፡ ሕገወጦችንም ለመከላከል የሸማቹ ሚና ከፍ ያለመሆኑን በመገንዘብ ኃላፊነታቸው በሚገባ በመወጣት ራሳችንንም መጥቀም ይኖርብናል፡፡