Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበዕውቀት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ የመግባቢያ ውይይት ለማድረግ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ የመግባቢያ ውይይት ለማድረግ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

ቀን:

‹‹ያ ትውልድ መወያየት አቅቶት በማያጨራርሱ ሐሳቦች ተጨራርሷል››

አቶ ኃይሌ ገብሬ፣ የአገር ሽማግሌ

በኢትዮጵያ ለስድስተኛ ጊዜ በ2012 ዓ.ም. መገባደጃ አካባቢ ይከናወናል ተብሎ የሚጠበቀውን አገራዊ ምርጫ መነሻ በማድረግ፣ ለ18 ወራት በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ የመግባቢያ ውይይት በቅርቡ ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ፡፡

- Advertisement -

ብሔራዊ ውይይቱ ‹‹ሁሉን አካታች፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ የመግባባት ውይይት›› በሚል መሪ ቃል የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮችን ጨምሮ በዘጠኙም ክልሎች እንደሚካሄድ፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች በተለይ በሰላምና በፍትሕ ላይ በመሥራት የሚታወቁ አራት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አስታውቀዋል፡፡

ውይይቱ ሁሉን አካታች የሆነና የሁሉም ሐሳቦች ግብዓት ለብሔራዊ መግባባት መሆናቸው በተለያዩ አገሮች ተሞክሮዎች መረጋገጡን፣ በኢትዮጵያም በተለይ አሁን ባለው ጽንፍ የረገጠ መራራቅን ለማቅረብ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎችንና ሌሎች ለተራራቀ ሐሳብ መንስዔ ናቸው ተብለው በተለዩ ዘጠኝ መሠረታዊ ነገሮች ላይ ጥልቅ ጥናታዊ ምርምሮችን በማዘጋጀት ለውይይት መዘጋጀታቸውን የገለጹት የኢንተር አፍሪካ ግሩፕ፣ ዓለም አቀፍ የዴሞክራሲ ምርጫ ኢንስቲትዩት፣ የአውሮፓ ኅብረትና ኢንተርናሽናል ሪቫይቫል ሚኒስትሪ ናቸው፡፡

አራቱን ድርጅቶች የወከሉ ኃላፊዎች ሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል ከመገናኛ ብዙኃን ተወካዮች ጋር ባደረጉት የመጀመርያ ስብሰባ ላይ የተገኙት የኢንተርናሽናል ሪቫይቫል ሚኒስትሪ (IRM) የቦርድ አባልና የአገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ኃይሌ ገብሬ፣ የ‹ያ ትውልድ›ን ተሞክሮና ልምድ በማካፈል አሁን ያለው ትውልድ ምን ማድረግ እንዳለበት ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ኃይሌ እንደተናገሩት፣ እሳቸው አባል የሆኑበት ቦርድ ‹‹ማግባቢያ ቦርድ›› ይባላል፡፡ ዋናው ዓላማው ኢትዮጵያ ወደፊት እያራመደችው ባለው ዴሞክራሲያዊ ሒደት ሰላማዊ ሽግግር በማምጣት የሁሉም ሐሳብ ተስተናግዶ፣ ሁሉንም የምታቅፍ ኢትዮጵያ ሆና ማየት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹የማንም ሐሳብ ትልቅ፣ የማንም ሐሳብ ትንሽ የለም፤›› የሚሉት የአገር ሽማግሌው፣ ውይይት ሲደረግ የአንዱ ሐሳብ የሌላው ውስጥ እንደሚገባ ጠቁመው፣ ውይይት ከሌለና መነጋገር ካልተቻለ የአንዱ ሐሳብ በሌላኛው ውስጥ ስለማይገባ መግባባት እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡ ሐሳብን ብቁ የሚያደርገው ጊዜና ሁኔታ ነው ብለው፣ አንድ ሐሳብ በአንድ ወቅት ትክክል፣ ብቁና ጠንካራ ሊሆን እንደሚችል፣ በሌላ ወቅት ደግሞ ያው ሐሳብ ብቁ፣ ትክክልና ጠንካራ ላይሆን ይችላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው ሐሳብ ትክክል፣ ብቁና ጠንካራ ለመሆን ወይም ላለመሆን ወሳኙ ጊዜ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

‹‹እንደምታውቁት የእኛ ትውልድ (ያ ትውልድ) ብዙ የከፈለና ብዙ እሳት ውስጥ የገባ ነው፡፡ ዛሬ ግን ያ ትውልድ የፀፀት ትውልድ ሆኗል፣›› ያሉት አቶ ኃይሌ፣ አቶ ክፍሉ ታደሰ በ‹‹ያ ትውልድ›› የመጀመርያ ዕትም መጽሐፋቸው ውስጥ ከትበው ያስቀሩትን አንድ ሐረግ በአስረጅነት ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ብርሃነ መስቀል ረዳና እጮኛው፣ እንዲሁም አቶ ኃይሌ ፊዳ በደርግ እስር ቤት ውስጥ ታስረው ሲገናኙ፣ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ተራማጆች ተወያይተን የኢትዮጵያን ችግር መፍታት አቅቶን አንድ ላይ እስር ቤት ተገናኘን፤›› ማለታቸውን አስታውሰው፣ ‹‹መወያየት አቅቶን ተጨራርሰናል፡፡ ብንወያይ ኖሮ ሐሳቦቹ የሚያጨራርሱ አልነበሩም፡፡ ተወያይተን ቢሆን ኖሮ እነዚያን የመሳሰሉ ወንድሞቻችንን ልናጣ ቀርቶ በሐሳቦቻችን ልዩነት ላይ ዝንብ እንኳን ሊሞት አይችልም ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ሐሳብን መለዋወጥና መወያየት አቅቷቸው አገራቸውን ከመጉዳታቸውም በተጨማሪ፣ ዛሬ ለፀፀት ወግ መቅረታቸውን በማዘን ጭምር አቶ ኃይሌ ተናግረዋል፡፡ የሞቱት ቢያርፉም እነሱ (ያሉት) ግን የፀፀት ትውልድ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን አሁንም ቢሆን ችግሮችን በመወያየትና ሐሳብ ለሐሳብ በመደማመጥ መፍታት እንዳለባቸውና በውይይት ወይም ሐሳብ በመለዋወጥ ሒደት አንዱ በሌላኛው ውስጥ ስለሚገባ እየተዋወቀ፣  እየተግባባና ችግር መስሎ የታየው ነገር በቀላሉ ሊፈታ የሚችል መሆኑን ማወቅ እንደሚያስችል የአገር ሽማግሌው አቶ ኃይሌ አስረድተዋል፡፡ በሕዝቦች መካከል የሚደረግን ውይይትና የሐሳብ ልውውጥ ለማስረፅ መገናኛ ብዙኃን ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመው፣ የኢትዮጵያን በጎ በጎ ታሪክ ትቶ ረመጥ ረመጡን በማንሳት ለሕዝብ ማስተላለፍ ምን ያህል ጉዳት እንዳለው እየደረሱ ያሉ ችግሮችን ማንሳት ብቻ በቂ ስለሚሆን ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ አሁን እንደ ችግር የሚታዩ ነገሮች ምርምር ተደርጎባቸው ጎልብተውና ታውቀው ሊከስሙ በሚችሉበት ደረጃ እንዳልተሄደባቸውም አክለዋል፡፡ በአገሪቱ ባሉ ሥራዎች ላይ ከፖለቲካ አኳያ ብቻ ውሳኔ ስለሚሰጥ፣ ከጀርባቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እንደሚያስከትሉም አቶ ኃይሌ ተናግረዋል፡፡ የፖለቲካ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት በባለሙያ ተጠንቶ፣ በሕግ ባለሙያ ታይቶ፣ በሥነ አዕምሮ ባለሙያና በታሪክ ሰዎች ታሽቶ ፈር የቀደደ ሥራ ቢሠራ ኖሮ፣ ከብዙ ችግሮች መዳን ይቻል እንደነበርም አክለዋል፡፡ ‹‹ለዚህም ነው በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አገር አቀፍ ውይይት በማድረግ ለመጪው አምስት ትውልድ የሚሆን ፈር በመቅደድ እንደበለፀጉ አገሮች እንሁን ብለን የተነሳነው፤›› ብለዋል፡፡ እንደ እነሱ ትውልድ (ያ ትውልድ) አዲሱ ትውልድ የፀፀት ትውልድ ሳይሆን፣ የደስታና የሰላም ትውልድ እንዲሆን የአደራ መልዕክታቸውን አቶ ኃይሌ አስተላልፈዋል፡፡

የኢንተርናሽናል ሪቫይቫል ሚኒስትሪ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሬቨረንድ ዳንኤል ጣሰው የውይይቱ ዓላማ ጥራዝ ነጠቅና ጽንፍ ሆነው በግራ በቀኝ የሚታዩ አስተሳሰቦችን ወደ መሀል ለማምጣት ውይይት ማስፈለጉንና ከውይይት የመፍትሔ ሐሳቦች ይመነጫሉ ብለዋል፡፡ በመሆኑም በተለይ ከምርጫ ጋር በተገናኘ ውይይቶችን በማዘጋጀትና በማወያየት የሚታወቀው ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ፣ ጠለቅ ያሉ ምርምሮችን በማድረግ ጥናታዊ ጽሑፎችን ለውይይት እንደሚያቀርብ አስረድተዋል፡፡ በጥናታዊ ጽሑፎችና በውይይቱ ተሳታፊዎች ከፍተኛ የሐሳብ ግብዓቶች ማግኘት እንደሚቻል አክለዋል፡፡

ሬቨረንድ ዳንኤል የሚመሩት ድርጅት ላለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያና በአሜሪካ ተመዝግቦ በሰላምና በፍትሕ ጉዳይ ላይ ሲሠራ የነበረ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት መሆኑን ጠቁመው፣ በቅርቡ የሚጀመረውን ሁሉን አቀፍ አገራዊ የማግባባት ውይይትን ለማድረግ፣ ከሁሉም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከአክቲቪስቶች፣ ከሃይማኖት ተቋማትና ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሰላምና ዕርቅ ኮሚሽንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ጋር ሰፊ ውይይት እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡ ውይይቱ ተራ በተራ ከሁሉም ጋር እንደሚደረግ፣ እንዲሁም ከክልል መንግሥታትና ከክልል ነዋሪዎች ጋር ውይይቱ ለ18 ወራት እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ብዙ ስለሰላም የሚናገሩ፣ የሚሰብኩና ስለሰላም የሚማልዱ መኖራቸውንና ጥሩም እንደሆነ የተናገሩት ሬቨረንድ ዳንኤል፣ አሁን ግን ከዚህ አለፍ ብሎ ሰላም ማምጣት አስፈላጊ የሆነበት ደረጃ ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን አንድ ላይ አድርጎ ሰላም ማምጣት ላይ በጋራ መሥራት በማስፈለጉ፣ እነሱም ይህንን ከግብ ለማድረስ እየሠሩ መሆኑን አክለዋል፡፡ የመወያያና የሐሳብ መለዋወጫ መድረክ እንጂ፣ ‹‹ጉልበትና ጡንቻ ማሳያ የግላዲያተርስ መድረክ አይደለም›› በማለት፣ በሚዘጋጀው መድረክ ላይ የሁሉም ሕዝብ ትርክት መደመጥ እንዳለበትም አክለዋል፡፡ ‹‹ከሐሳባችን ጋር አንላቀቅም ማለት የለብንም፡፡ ከእሱ ተላቀንና ሐሳብ ለሐሳብ ለመለዋወጥ ወደ መሀል ቀርበን መወያየት አለብን፤›› ብለዋል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሚቀጥሉት 18 ወራት ማለትም ምርጫ 2012 ተካሄደም አልተካሄደም ከዚያ በፊት፣ በዕለቱና ከምርጫ በኋላም ውይይቱ የሚቀጥል መሆኑንና እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ለማሳየት የተዘጋጀውን የፕሮጀክት ንድፈ ሐሳብ አምባዬ አጋቶ (ዶ/ር) እና የሰላምና የዕርቅ አማካሪ የሆኑት አቶ ጋረደው አሰፋ ለተሰብሳቢዎቹ በማቅረብ ስብሰባው ተጠናቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...